የሰው ዘር መገኛ ምድር የሆነው የአፋር ክልል፣ እምቅ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትም ነው። የክልሉ ሀብት ሀገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚና ፀጋ ነው። ክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ በርካታ እድሎችን ይዟል። ክልሉ ካለው የኢንቨስትመንት ሀብት በተጨማሪ አንፃራዊ ሰላም ያለበት መሆኑ፣ የአምራች ዘርፍ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ምቹ የሆነው የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መኖሩ፣ ክልሉ የወደብ ባለቤት ከሆኑ ጎረቤት ሀገራት (ኤርትራ እና ጅቡቲ) በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቱ በባለሀብቶች ዘንድ ክልሉን የተሻለ ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የክልሉ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃት አሳይቷል። 451 የሚደርሱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ።
የአፋር ክልል በ2015 በጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ማስመዝገቡን የአፋር ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች ያሳያሉ። የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ አይሻ መሐመድ አደን ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት በሥራ እድል ፈጠራም ሆነ በቴክኖሎጂ ሽግግር የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ያሳደገ እንደሆነ ይናገራሉ።
ወይዘሮ አይሻ እንደሚገልጹት፣ በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ ለ105 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ ለ118 ባለሀብቶች ፈቃድ በመስጠት ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች በእርሻ (63)፣ በኮንስትራክሽን (23)፣ በማምረቻ (15)፣ በሆቴልና ቱሪዝም (7)፣ በአስጎብኝነት (5)፣ በእንስሳት እርባታ (3)፣ በማዕድን (1) እና በትምህርት (1) ዘርፎች የሚሰማሩ ሲሆን፤ ያስመዘገቡት የካፒታል መጠንም ከሰባት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ነው። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለ12 ሺ 252 ዜጎች (3741 ቋሚ እና 8511 ጊዜያዊ) የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤ ይህም በበጀት ዓመቱ ታቅዶ ከነበረው ለስድስት ሺ 715 ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር እቅድ ጋር ሲነፃፀር ከእቅድ በላይ የሆነ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደተቻለ ያመለክታል። በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። ዳያስፖራዎች በእርሻና በሌሎች ዘርፎች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ወይዘሮ አይሻ በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወኑ ስላሉ ሥራዎች ሲያብራሩ፣ ‹‹ቅድሚያ የምንሰጠው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ነው። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን እናበረታታለን። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ሀብት ይዘው፣ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሀገራቸው ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዲሁም ራሳቸውንና ኅብረተሰባቸውን እንዲጠቅሙ በማበረታታት ቅድሚያ እንዲያገኙ እናደርጋለን›› ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ክልሉ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚመጡና አቅም ያላቸው ባለሀብቶችን እንደሚያስተናግድና በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ የሚያበረታታ እንደሆነም ኮሚሽነሯ ይናገራሉ።
በበጀት ዓመቱ የክልሉን የኢንቨስትመንት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራትም ተከናውናዋል። ክልሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ የዲጂታል የአሰራር ሥርዓትን (Digital System) ተግባራዊ አድርጓል። ይህም ፈቃድ ማውጣትና ማሳደስን ጨምሮ ቀደም ሲል ረጅም ጊዜ ይፈልጉ የነበሩ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ በማቅረብ የሀብት ብክነት እንዲቀንስና ምርታማነት እንዲጨምር አስችሏል።
በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል አንዳንዶቹ በውላቸው መሠረት ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ውልን አክብሮ የመሥራት ውስንነት ይስተዋልባቸዋል። ይህ የአፈፃፀም ልዩነት በአፋር ክልልም ይስተዋላል። ይህን በተመለከተ ወይዘሮ አይሻ ሲናገሩ ‹‹ሁሉም ፕሮጀክቶች በእኩል ፍጥነት የሚራመድ አፈፃፀም የላቸውም። አንዳንዶቹ ጥሩ አፈፃፀም ሲኖራቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የዘገየና ደካማ የሆነ አፈፃፀም ይኖራቸዋል። ጥሩ አፈፃፀም ላላቸው ፕሮጀክቶች እውቅናዎችንና ሽልማቶችን በመስጠትና ድጋፎችን በማድረግ እንዲበረታቱ እናደርጋለን። መሬት ወስደው አጥረው የሚያስቀምጡና ሥራ ጀምረው ያቆሙ ባለሀብቶችን በተመለከተ ደግሞ በቅድሚያ በውላቸው መሠረት ሥራ እንዲጀምሩ ጥሪ ይቀርብላቸዋል፤ ሥራቸው የሚገኝበት ደረጃም ይገመገማል። ሥራ ጀምረው ያቆሙት ወደ ሥራቸው ተመልሰው እንዲጨርሱ እናበረታታቸዋለን። ሥራ ያልጀመሩት ደግሞ ሥራ ለመጀመር ያላቸውን ፍላጎት በማጤን ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እናደርጋለን፤ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀርበውላቸው ሊገኙ ያልቻሉት ደግሞ የወሰዱትን መሬት እንዲነጠቁ ይደረጋል›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሥራ ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ ባለሀብቶች ለአፈፃፀም ድክመታቸው ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮች ቀዳሚ ሆነው ይጠቀሳሉ። ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ አንፃራዊ ሰላም ከሰፈነ ወዲህ ባለሀብቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ሥራ ጀምረው ያቋረጡት ባለሀብቶች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። መሬት ከወሰዱ በኋላ ለረጅም ጊዜያት ወደ ሥራ ያልገቡትና በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ከኮሚሽኑ ጋር ለመነጋርም ፍላጎት ያላሳዩት ግን የወሰዱትን መሬት የማስመለስ ሥራ ተሰርቷል። በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት 62 ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱ ተደርጓል።
በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች እንዲሟሉላቸውና ምላሽ እንዲያገኙ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች አሉ። ወይዘሮ አይሻ እንደሚያስረዱት፣ የመሠረተ ልማት፣ በተለይም የመንገድ እና የኃይል፣ አቅርቦት ጥያቄ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጥያቄ የሚያነሱባቸው መስኮች ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የእርሻ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በጎርፍ የመጎዳት ችግር ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል። ባለሀብቶች በእነዚህ ዘርፎች በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ ኮሚሽኑም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተበባር ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር፣ ከአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን እና ከአፋር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር በመቀናጀት በጎርፍ በሚጠቁ አካባቢዎች የውሃ መፋሰሻ ቦዮችንና ግድቦችን በመገንባት የጎርፉን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
መንገድን በተመለከተ ከክልሉ ትራንስፖርት ቢሮና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሆኑ መንገዶች ግንባታ በእቅድ ውስጥ እንዲካተትና አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውም ጥገና እንዲደረግላቸው ተደርጓል። በማለት ክልሉ አጠቃላይ የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን የሚጠበቅበት እንደሆነ ይናገራሉ።
የአፋር ክልል የሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ካደረሰባቸው ክልሎች መካከል አንዱ ነው። በጦርነቱ ስድስት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ማሽኖቻቸውና ሌሎች ንብረቶቻቸው ተነቃቅለው ተወስደውባቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ በከፊል ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን ቀሪዎቹም ወደ ሥራ እንዲመለሱ እየተሠራ እንደሚገኝም ወይዘሮ አይሻ ይገልፃሉ።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል ባለፈው ዓመት፣ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም፣ ይፋ የተደረገውና እየተተገበረ የሚገኘው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻልና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው። ንቅናቄው ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ጉዞው የአምራች ኢንዱስትሪው አፈፃፀም እንዲሻሻል ያደረጉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት ተገልጿል።
ይህን መሠረት በማድረግም የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን በመጠቀም ለአፋር ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮች ፈጣን ምላሽ እየሰጡ አምራች ዘርፉ የተሻለ አቅም እና በሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ላይም ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ወይዘሮ አይሻ ይናገራሉ። ‹‹ኢንቨስተሮች የሚያቀርቧቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በንቅናቄው ስለሚሳተፉ፣ ንቅናቄው የዘርፉን ችግሮች በትብብር ለመፍታት እድል ይፈጥራል። በዚህ መሠረት በንቅናቄው ትግበራ የአምራች ዘርፉን ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት ጥረት ይደረጋል›› በማለት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በአፋር ክልል ስለሚከናወኑ ተግባራት ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። በዚህ ረገድ በአፋር ክልል የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የክልሉን ህብረተሰብ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኙ ወይዘሮ አይሻ ይገልፃሉ።
‹‹የኢንቨስትመንት ሥራዎች የኅብረተሰቡን ችግሮች ለማቃለል ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ሲሰማሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚኖረውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ከሚያደርጉባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሥራ እድል ፈጠራ ነው። የክልሉ ወጣቶች ካሉባቸው ችግሮች አንዱ ሥራ አጥነት ነው። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ባለሀብቶች አገልግሎት ሰጪ የመሠረተ ልማት ተቋማትን (መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን…) ገንብተው ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል። ኅብተረሰቡም የኢንቨስትመንት ተቋማቱን ጥበቃና እንክብካቤ ያደርግላቸዋል›› በማለት ያስረዳሉ።
የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ የፕሮሞሽን ሥራ (Promotion) ይፈልጋል። ክልሉም ሆነ ሀገሪቱ ከክልሉ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የክልሉ ሀብቶች በስፋት እንዲተዋወቁ እየተደረገ እንደሚገኝም ወይዘሮ አይሻ ይናገራሉ።
የኢንቨስትመንት የትኩረት መስኮች እንደአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና አቅም የተለያዩ መሆናቸው አይቀርም። በዚህ ረገድ የአፋር ክልል ዋና ዋና የኢንቨስትመንት የትኩረት መስኮች እርሻ፣ ማዕድን፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ማምረቻ እና እንስሳት እርባታ ስለመሆናቸው ወይዘሮ አይሻ ያብራራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ክልሉ ለም የሆነና ያልታረሰ ሰፊ መሬት እንዲሁም ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት አለው። መሬቱንና የእንስሳት ሀብቱን በቴክኖሎጂ ታግዞ በማልማት የክልሉን ሕዝብና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል። በመሆኑም የግብርና ምርቶችን በመጠቀም የማምረቻውን ዘርፍ ማነቃቃትና ማስፋፋት ከኢንቨስትመንት ዐብይ ተግባራት መካከል አንዱ ነው። በክልሉ ከጨው በተጨማሪ ወርቅ፣ ፔትሮሊየም፣ ጂብሰምና ሌሎች ማዕድናትና ሀብቶች ይገኛሉ። እነዚህን ሀብቶች ማልማትም ትኩረት የሚያገኝ ሌላው የዘርፉ ተግባር ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም ክልሉ ዳሎልና ኤርታሌን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የሚጎበኟቸው የቱሪስት መስህቦች ባለቤት በመሆኑ ባለሀብቶች በሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩና ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር እቅድ ተይዟል።
በርካታ ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉ ብዙ የኢንቨስትመንት አቅሞች ባሉት የአፋር ክልል፣ በተያዘው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ዘርፉ ዋነኛ የትኩረት መስኮች የሚሆኑት ዘርፎች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል። በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት በክልሉ በስፋት ሊሰራባቸው የተለዩት ዘርፎች እርሻ፣ ማዕድን፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ማምረቻ እና እንስሳት እርባታ ናቸው። ክልሉ በእነዚህ ዘርፎች እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ በዘርፎቹ የሚከናወኑ ኢንቨስትመንት ተግባራት ለባለሀብቶች፣ ለክልሉ ሕዝብና ለሀገር ትልቅ ውጤት ማስገኘት ይችላሉ። ለዚህም ክልሉ በዘርፎቹ ስላለው አቅምና ምን ያህል ባለሀብቶችን ማሳተፍ እንደሚቻል ከዘርፎቹ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረገባቸው እንደሚገኙ ኮሚሽነር ወይዘሮ አይሻ መሐመድ ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2015