ለዘመናዊ የግብይት ሥርዓት- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርሻ

 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አገልግሎቱን ለማሻሻልና የተሳለጠ ለማድረግ፤ ምርት አቅራቢውን፣ ላኪውን፣ የሕብረት ሥራ ማህበራትንና አርሶ አደሩን በአንድነት ለማገልገል እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ሀገሪቷ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን አስመልክቶ በ2015 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት እንዲሁም በቀጣይ በ2016 በጀት ዓመት ለማከናወን ያቀዳቸውን ሥራዎች የሚመለከታቸውን የሥራ ክፍል ኃላፊዎች በማነጋገር ከዚህ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ይቀርባል።

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተለዋዋጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየጊዜው አዳዲስ አካሄዶች የሚከተል እንደሆነ በመግለጽ ሃሳባቸውን ያካፈሉን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ሀገር ከዘርፉ የምታገኘውን ውጤት ማሳደግ ያስፈልጋል። ለዚህም ተከታታይ ለውጦች ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን አስመልክቶ በ2015 በጀት ዓመት የዓለም ገበያን ግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በበጀት ዓመቱ የግብርና ምርት የሆኑትን ጥራጥሬና የቅባት እህሎች፣ ቅመማ ቅመምና ከደን የሚመረቱ ምርቶች ሀብት የሚገኙ ግብዓቶችን ጨምሮ በድምሩ 22 የሚደርሱ ምርቶችን አገበያይቷል። ዕጣን፣ ግብጦ፣ ባቄላና ኮረሪማን ወደ ዘመናዊ ገበያ ማምጣት የተቻለ ሲሆን፤ ባለፈው በጀት ዓመትም እንዲሁ አብሽን ጨምሮ ጥቁር አዝሙድ፣ ቁንዶ በርበሬና ሌሎች ምርቶችን ወደ ዘመናዊ ገበያ ማስገባት ተችሏል።

የደን ምርት የሆነው ዕጣን በሀገሪቱ በከፍተኛ መጠን የሚገኝና ዕምቅ ሃብት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ግብይት የጥራት ደረጃ ያልነበረው እንደሆነም አስታውሰዋል። ይሁንና በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕጣን የጥራት ደረጃ መስፈርት ማዘጋጀት ችሏል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዕጣን የጥራት ደረጃ ሲያዘጋጅ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ እንደነበሩ በማስታወስ አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የክልል ቢሮዎች ጭምር መሳተፋቸውን አመላክተዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከዛሬ 15 ዓመት አስቀድሞ ስንዴና በቆሎን በዘመናዊ ግብይት ማገበያየት የጀመረ ቢሆንም ሊዘልቅበት ግን አልቻለም›› የሚሉት አቶ ነጻነት፤ ለዚህም ዋናው ምክንያት በቂ ምርት ያልነበረና ምርትና ምርታማነት ያላደገበት ወቅት እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት፤ በወቅቱ ስንዴና በቆሎን ከጥቂት ቀናት ውጭ ማገበያየት አልተቻለም። ነገር ግን በአሁን ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለስንዴ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የስንዴ ምርትና ምርታማነት በእጅጉ እያደገ በመምጣቱ ሀገሪቷ በስንዴ ምርት እራሷን ከመቻል አልፋ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኗ እጅግ የሚበረታታ ነው።

ከዛሬ 15 ዓመታት አስቀድሞ የነበረው የስንዴ ፍላጎት ዝርያና የገበያ ሁኔታ አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ እንዲሁም የገበያው ሁኔታውም ተለዋዋጭ በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የግብይት ኮንትራት ማሻሻል እንዳስፈለገና እንደተሻሻለ የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ይታሰብ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ግን በሀገር ውስጥ እሴት ጨምረው የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ያሉ ፋብሪካዎች በመኖራቸው የሚመጣውን የስንዴ ዝርያ ባህሪ ጭምር ግምት ውስጥ ያስገባ የምርት ኮንትራት ተዘጋጅቶ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጸደቀ መሆኑን ተናግረው፤ ይህ ኮንትራትም ለአንድ ጊዜ ሳይሆን በየጊዜው እየተከለሰ ሥራ ላይ የሚውል እንደሆነ ነው ያመላከቱት።

በቀጣይም በሀገሪቱ ምርትና ምርታማነት እያደገ ሲመጣ እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎች በምርት ገበያው በኩል መገበያየት የሚያስችላቸው ዕድል ስለመፈጠሩ ያነሱት አቶ ነጻነት፤ ምርት ገበያው ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ልምድ ያለው እንደሆነና የአኩሪ አተር ምርት ተጠቅመው ዘይት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ልዩ የግብይት መስኮት ተከፍቶላቸው ይገበያዩ እንደነበር ጠቅሰዋል። ይህ ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ተግባራዊ በመሆኑ ልምዱ አለ። ስለዚህ ስንዴውን በዚህ መንገድ ማገበያት ይቻላል። ይህም ለምርት ገበያው ትልቅ አቅም ከመፍጠር ባለፈ ተጠያቂነት ያለበት በሕግ የሚመራ አሰራር በመሆኑ ሀገርም ከዘርፉ መጠቀም የሚያስችላት እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አንድ ምርት ለገበያ የሚቀርብበት ዋጋ በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን ላኪውም ሆነ አቅራቢው በቀጥታ መረጃውን ማግኘት ይችላል። ግብይቱ በተካሄደ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥም እንዲሁ የገበያ መረጃው በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዝኛ አየር ላይ የሚውል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ይህ ከተደራሽነት አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ ያለውና አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ሲያወጣ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ በመሆን ያስችለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ዋጋ ተቀባይ ሳይሆን ዋጋ ሰጪ በመሆን ምርቱን ሸጦ የተሻለ ዋጋ ማግኘት ያስችለዋል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪም ምርት ገበያው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በክፍያና ርክክብ ሥርዓት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ተጠቃሽ እንደሆነ አቶ ነጻነት ሲገልጹ፤ የግብይት ተዋናይ የሆኑ ላኪዎች፣ ሕብረት ሥራ ማህበራት፣ አርሶ አደሩ፣ አቅራቢውና ሌሎችም ምርታቸውን በሸጡ ማግስት ገንዘባቸውን የሚያገኙበት የክፍያ ሥርዓት ተፈጥሯል። ለዚሁ ተግባርም ባንኮች ከምርት ገበያው ጋር በጋራ ይሠራሉ። እነዚህ አካላት በቴክኖሎጂ ተጣምረው የሚሠሩ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ብቻ አምስት ባንኮችን ወደ ሥርዓቱ በማስገባት በድምሩ 22 ባንኮች በአሁን ወቅት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ። በቀጣይም ይህው አጋርነት ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በተለይም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስችላል።

ሌላው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የወደፊት የግብይት ሥርዓትን ተግባራዊ የማድረግ ሥራን የጀመረ ሲሆን፤ በሥራ ላይ ካለው የወዲያው የግብይት ሥርዓት የሚለይ እንደሆነ አቶ ነጻነት አስረድተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ የወዲያው ግብይት ምርት ገበያው ምርቱን ተረክቦ በእጁ ላይ ያለውን ምርት ለገበያ ያቀርባል። ነገር ግን አሁን ላይ ዓለም አቀፍ የሆነው ገበያ የወደፊት ግብይት በመሆኑ ወደዛው መግባት አስፈላጊ ነው። የወደፊት ግብይት ሲባል ሻጭና ገዢ በምርቱ አይነት፣ መጠን፣ ጥራትና ዋጋ ላይ አስቀድመው በመነጋገር የሚደረግ ግብይት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመሀል ሆኖ የማመቻቸትና የተለያዩ አገልግሎቶችን የማቅረብ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱም የወደፊት ግብይትን ተግባራዊ ማድረግ ተችሎ 4400 ሜትሪክ ቶን ምርት በ252 ሚሊዮን ብር ማገበያየት መቻሉን አቶ ነጻነት ጠቅሰው፤ አብዛኛው ምርት አረንጓዴ ማሾና የተለያየ አይነት ያላቸው የቦሎቄ ምርቶች እንደሆኑ አስረድተዋል። በውጭው ዓለም በተለይም በእስያ ሀገራት እነዚህ ምርቶች በስፋት የሚፈልጉ ሲሆን ይህም በበጀት ዓመቱ ያሳኩት ትልቅ ስኬት እንደሆነ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአሁን ወቅት በጠቅላላው 22 የሚደርሱ ምርቶችን በግብይት መድረኩ በማገበያየት 257 ሺ ሜትሪክ ቶን ምርት ማገበያየት ችሏል። ምርቱ 24 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ናቸው። ከተገበያየው ምርት ቀዳሚዎቹ ቡና እና ሰሊጥ ሲሆኑ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች በግብይት ውስጥ ተከታዮች ናቸው።

ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ነጻነት፤ አርሶ አደሩ ገንዘብ በብድር ከባንክ የሚያገኝበት ሥርዓት የተዘረጋ እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሮች፣ አልሚዎችና የራሳቸው የእርሻ ቦታ ያላቸው የህብረት ሥራ ማህበራት ከባንክ ብድር የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ማለት ህብረት ሥራ ማህበራትና አልሚዎች ምርታቸውን ወደ ምርት ገበያ በማምጣት ከምርት ገበያው የምርት መረከቢያ ደረሰኝ ያገኛሉ። ይህን የምርት መረከቢያ ደረሰኝ በመያዝም ወደ ከባንኮች የአጭር ጊዜ ብድር ያገኛሉ። ገንዘቡን ለማዳበሪያና በቶሎ ለሚፈልጉት ወጪ በማዋል አምርተው ምርታቸው ሲደርስ ብድራቸውን ይከፍላሉ። ለዚህ ሥራ ባንኮች ፈቃደኛ በመሆን እየተሳተፉ ሲሆን፤ በቀጣይ በጀት ዓመትም ይህው የብድር አገልግሎት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ አመላክተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ወደ ዘመናዊ ግብይት የሚገቡ አዳዲስ የግብርና ምርቶች ስለመኖራቸውና እየተጠኑ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የማዕድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችንም ጭምር ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማስገባት ዝግጅት መደረጉን አንስተው ይህም የምርት ገበያው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም አቅጣጫና ፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል። ከማዕድን ሃብቶች መካከል ጌጣጌጥ ማዕድናት የሚባሉትን ወደ ግብይት ሥርዓት ለማስገባት የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ በማስታወስ ይህንኑ ሥራ በተሟላ ግብይት ሕጋዊነት ባለውና ተገቢውን ጥራት በጠበቀ መንገድ መገበያየት እንዲችል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከማዕድን በተጨማሪም የሲሚንቶ ምርትን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በማስገባት ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለኢንደስትሪ ግብዓት እና ለምግብነት የሚውል ጨውም እንዲሁ በዘመናዊ ግብይት እንዲገባ ምርቱ ወደ ሚገኝበት ቦታ በመሄድ ጥናት እየተጠና መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የጨው ሃብት በመኖሩ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ስለመኖሩ ተናግረዋል። በመሆኑም ምርቱን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በማስገባት የአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር ተጠቃሚ መሆን እንዲችል በቀጣይ ዓመት የሚሠራበት እንደሆነ ነው የገለጹት።

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን በየጊዜው እያዘመነ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጣይ 2016 በጀት ዓመት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማድረስ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ለአብነትም ማንኛውም ተገበያይ ወደ አዲስ አበባ ምርት ገበያ መምጣት ሳይጠበቅበት ባለበት ቦታ ሆኖ የእጅ ስልኩን ብቻ በመጠቀም መገበያየት የሚያስችለውን አሰራር ተግባራዊ አድርጓል። ከግብይቱ በተጨማሪ ማንኛውም ተገበያይ የአባላት ምዝገባ፣ የክፍያና የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ሲፈልግ ባለበት ሆኖ ማግኘት የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል። ይህም ለዘመናዊ ግብይት ዋነኛና ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ የተለያዩ እንቅፋቶች እንደገጠሙት ያነሱት አቶ ነጻነት፤ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ሁሉንም ተገበያይ ወደ ህጋዊ ግብይት የሚያመጣ በመሆኑ ሕጋዊ ታክሰ ከፋይ ያደርጋል። ይሁንና ይህን የሚጠሉ አካላት ምርቱን በኮንትሮባንድ የመሸጥና በሕገወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ከምርት ገበያው ባለፈ ሀገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ ትልቅ ኪሳራ በመሆኑ አንዱ ተግዳሮት ነው።

የዓለም ገበያ ሁኔታ ተለዋዋጭ መሆኑም ሌላው ትልቁ ችግር እንደሆነ በመጥቀስ፤ በተለይም የምርቶች ዋጋ በዓለም ገበያ ሲቀንስ በሀገር ውስጥ ያለው ዋጋም ይቀንሳል። ለአብነትም ቡና በዘንድሮ ዓመት ያለው ዋጋ እና የዛሬ ዓመት የነበረው ዋጋ ተመሳሳይ አልነበረም። ባለፈው ዓመት የቡና ዋጋ ከፍ በማለቱ ሀገሪቷ ተጠቃሚ ነበረች። በዘንደሮ ዓመት ግን ዋጋው በከፍተኛ መጠን የቀነሰ በመሆኑ ምርት ገበያውን ጨምሮ አምራች አርሶ አደሩ፣ ላኪው፣ አቅራቢው እንዲሁም ሀገርም እንደ ሀገር ተጎጂ ሆነዋል። አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅና ጦርነቱም ጭምር በዘንድሮ ዓመት እንቅፋት እንደነበሩ ነው አቶ ነጻነት ያስታወሱት።

የኢትየጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ምርቶችን ከማገበያየት ባለፈም አካዳሚ በመክፈት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ለማሳካት የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ ይገኛል ያሉት አቶ ነጻነት፤ ምርት ገበያ ስልጠና የመስጠት ሕጋዊ ፈቃድ ያለው በመሆኑ ስልጠናዎችን ለሀገር ውስጥና ከውጭም ፍላጎት ላላቸው አካላት የሚሰጥ ነው። በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው በርካታ ተግባራት መካከልም ይህ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ምርት ገበያ ውስጥ የተገነባው ሥርዓት በመኖሩ የልዕቀት ማዕከል ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ያለውን ልምድና ዕውቀት ቀምሮ ያሰለጥናል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ልምድ የሚቀስሙበትና የመመረቂያ ጽሑፍ ማዘጋጀት የሚችሉበት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነጻነት፤ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ሀገራት በተለይም አፍሪካ ሀገራት ማለትም ጋና፣ ማላዊ፣ ታንዛንያና ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ልምድ ወስደው በሀገራቸው የምርት ገበያን መክፈት የቻሉ መሆኑን አመላክተው፤ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በዚህ ደረጃ መሥራት መቻሉ ከፍተኛ ሚና ያለውና የሀገሪቱን የንግድ አድማስ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማስፋት አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 10/2015

Recommended For You