የዲጅታል ዘመን አመራር

አሁን ያለንበት ዲጅታላይዜሽን ዓለም በየዕለቱ ተለዋዋጭ ክስተቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። በየጊዜው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተፈጠሩና ትግበራ ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህን ቴክኖሎጂዎች አውቆና ተረድቶ ወደ ተግባር ለመተርጎም ዘመኑን የዋጀ ክህሎት እና እውቀት ባለቤት መሆንና ራስን ማብቃት ያስፈልጋል።

ለዚህም ደግሞ አንድን ተቋም ከሚመራው መሪ ጀምሮ እስከታች ያለ ሠራተኛ ድረስ ቴክኖሎጂውን በሚገባ ሊያውቅና በተግባር እንዲያውለው ማድረግን የሚጠይቅ ነው። አመራሩ ቴክኖሎጂን በሚገባ ተረድቶ ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል አሠራርን በመከተል ተቋሙን በማዘመን ሊመራው ይገባል።

በቅርቡም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ‹‹የአመራር ልሕቀት በሳይበር ዘመን›› በሚል ርዕስ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎችን ያሳተፈ ሴክተር-አቀፍ ሀገራዊ የአመራር ሴሚናር አካሂዶ ነበር። በሴሚናሩም የዲጅታል ዘመን አመራር በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የተሰጠበት ነበር።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፤ ለአንድ ተቋም ስኬታማነት የአመራሩ ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። የትኛውም የሙያ ዘርፍ በመሪዎች ክትትል የሚመራ ነው። በሳይበር ዘመን ራሳቸውን ለአመራርነት ብቁ የሚያደርጉ መሪዎች ተቋምን ውጤታማ ያደርጋሉ።

ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ሴሚናሩ ያስፈለገበትን ዋና ዓላማ ሲናገሩ፣ በሳይበር ዘመን ቁልፍ የአመራር ክህሎቶች ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የየዘርፉን በጎ የአመራር ተሞክሮ በማስፋት የተናበበ የጋራ የአመራር እሴት በመፍጠር በሀገር ግንባታ ሂደት የሀገርን ገጽታ እና የአመራር ጥበብን ለማጎልበት ያለመ ነው። በየዘርፉ በጥናት የተገኙ ውጤት ያስገኙ ሀገር በቀል የአመራር አስተሳሰቦችን እንዲሁም አርአያ የሆኑ አመራሮች ተሞክሮዎችን በመቀመር ለመመሪያነት ለመጠቀም ነው። በሀገር አቀፍ የአመራር ፍላጎት ግብዓት የሆኑ ሃሳቦችን ለማመንጨት ታስቦ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አሁን ባለንበት ዘመን በብዙ ዘርፎች የመሪዎች እጥረት ያለ ሲሆን፤ እያደገ ካለው ምጣኔ ሀብትና ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ እና የዲጅታላይዜሽን እንቅስቃሴ አንጻር በርካታ ብቁ መሪዎች ያስፈልጋሉ። መሪነት ከሌሎች ተከታዮችም ሆነ ከብዙኃኑ ህዝብ የተሻለ የሚንቀሳቀስበት የገሀዱን ዓለም በሚገባ መረዳት መቻል አለበት ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዓለም ላይ በርካታ መሪዎች የሚያሰለጥኑ በርካታ ተቋማት ቢኖሩም በተግባራት ግን ሌሎች ባለሙያዎች ማሰልጠን እንደሚቻለው ሁሉ መሪዎችን በስልጠና ብቻ ማብቃት አይቻልም። መሪዎች ጥበብን ከተግባር ማግኘት ይችላሉ። መሪዎች የሚመሯቸውን ሠራተኞች ለማነሳሳት፣ ለመምራትና ኃላፊነት ለመውሰድ አቅምን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ከሠራተኞቻቸው ጋር ከሚፈጥሩት መስተጋብር ባሻገር የአሁናዊ የዓለም ሁኔታን ከግንዛቤ በማስገባት መረዳት፣ ማዳበርና ማጎልበት ያስፈልጋቸዋል።

‹‹የዲጅታል ወይም የሳይበር ዘመን በየትኛው የአመራር ደረጃ ያለን አካል ችሎታውንና እውቀቱን በየጊዜው ማዘመንንና ከጊዜው ጋር አብሮ መሄድን የሚጠይቅ ነው። በትምህርት ቤት በተማርነው አልያም ቀድመን የምናወቀውን ጉዳይ አኩራርቶ የሚያስቀምጠን ወቅት ላይ አይደለንም። የሳይበር ዘመን መሪ ለማወቅ ክፍት እእምሮ ያለውና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንዲሁም አመለካከቶች ለመማር ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ይጠይቃል። ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት በማቅለል ረገድ ዓለም አቀፋዊ ቅርርብና ትስስር በመፍጠር የሚጫወተው ሚና መኖሩ አጠያያቂ አይደለም። የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ተከትሎ የመጡ የጎንዮሽ ስጋቶችም የዚሁን ያህል አሳሳቢ ሆነዋል። ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ መሪዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ›› በማለት ተናግረዋል።

እንደ ዲጅታል ዘመን መሪ መንግሥታዊ ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ቴክኖሎጂ ባመጣው ለውጥ ውስጥ ማለፍ ግዴታቸው መሆኑን ተገንዘበው ዘመኑ ከፈጠራቸው ቴክኖሎጂዎች ጋር ራሳቸውን ማለማመድ የግድ ይላቸዋል። በዚያው ልክ ያሉ ተግዳሮቶች ማለትም የሳይበር ጥቃቶችም መቋቋምና መከላከልን ታሳቢ ያደረገ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ከሆኑት ስጋቶች አንዱ የሀገራት ብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት ስጋት የሆነውን የሳይበር ጥቃት በመረዳት ልብ ሊባል ይገባል። የሀገራችንን ደህንነት በማረጋገጥ መሪው የሚመራው ዘርፍ ሊያገኝ የሚገባንን ብሔራዊ ጥቅሞች መጠቀም የሚያስችል አካሄድ በመከተል በየዘርፎቹ ሰፊ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ነው አቶ ሰለሞን የሚናገሩት።

እንደ ሀገር በአመራነት ያለን ልምድና እውቀት የሚጠበቀውን ያህል ርቀት ተጉዟል ብሎ መናገር አያስደፍርም ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከዚህም በላይ በየቦታው ተበታትነው የሚገኙ በአመራርነት ዙሪያ የተሻለ ልምድና እውቀት ያላቸው አመራሮችን እርስ በርስ የሚገናኙበትና የሚማማሩበት መድረክ አለመኖሩ በሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ መሪ ሊሆኑ የሚችሉ አመራሮችን ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።

በይበልጥ ዘመኑን በውል የተረዳና እኩል የሚራመድ መሪ ከማግኘት አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እንደ አንድ የመንግሥት ተቋም በሕዝብና በመንግሥት ከተሰጠው ዋና ተልዕኮ ጎን ለጎን እንደሀገር ያለውን የአመራር ጥበብ ዙሪያ ክፍተት ለመሙላት የራሱን ተቋማዊ ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹እንደዚህ አይነት መድረኮች መዘጋጀታቸው የሳይበር ዘመን አመራር ጥበብ ምን መምሰል እንዳለበትና ልምድ የምንለዋወጥበት የተሻለ ሃሳብ የሚመነጭበት ነው›› ብለዋል።

አሁን ላይ በአንድ በኩል ዲጅታል ዘመን ምን እንደሚመስል መረዳት የሚያስፈልግ ሲሆን በሌላ በኩል ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድና ዘመኑን የሚመጥን የአመራር እውቀትና ክህሎት በቀጣይነት ባለው መልኩ ማዳበርና ማስፋት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ባለንበት የዲጅታል ዘመን በተቋማት መሪዎች መካከል የትብብርና የመመካከሪያ ጊዜ ሊኖር ይገባል። የመሪነት አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ ተግባቦት ሲሆን ትብብርና ቅንጅት የሚፈጥሩ ግንዛቤዎችንና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የተቋማት ኃላፊዎች ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር አጋርነትና ትብብር በመፍጠር መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ይህም ለሙያው እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክትና ከሌሎች የተቋማት አመራሮች ጋር ያለን ግንኙነት የሚያሰፋ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ወደፊት የተቋሙ የአመራርነት ሚና ለመወጣት አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችና እውቀቶች የሚገኝበት እንደሆነ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በቀጣይም እንዲህ አይነቱ የምክክር መድረክ ሁሉን አቀፍ የአመራር አቅም የመፍጠር ተሞክሮ በመለዋወጥ ለሀገር እድገት መደላድል በሆነ መልኩ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው የሳይበር ወይም የዲጅታል ዘመነ አመራር ምን መመሰል እንዳለበት ማብራሪያ ሰጥተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አመራሮች ማለት የተቋማት መሪዎች ናቸው። ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ እንደመሆናቸው መጠን ራሳቸው ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ መጓዝ የሚያስችላቸው ብቃት ሊኖራቸው ይገባል። እንደ ሀገር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በቅንጅትና በትብብር መስራት የሚሻ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂው ጋር አብሮ መጓዝ የሚችል መሪ ያስፈልጋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትና አስተዳዳር ኤጀንሲ (ኢንሳ) በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነትና ስልጣን ቁልፍ የኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማቶች ከጥቃት መከላከል ነው። በዚህም የአሰራር ሥርዓትን፣ የሰው ኃይልንና ቴክኖሎጂን በተመለከተ ሥራዎችን የሚሰራ ሲሆን፤ የአመራርነት ጉዳይ የሰው ኃይል የሚመለከት ነው። አመራሮች በማብቃት ተቋምን የሚመሩ መሆን ያለባቸው ሲሆን፤ ተቋምን ሊመሩ ከሆነ ደግሞ ቴክኖሎጂ በሚገባ ሊያውቁ ይገባል በሚል እሳቤ ግንዛቤ መፍጠር ይሠራል። በየተቋማቱ የማማከር እና በየስልጠናም የመስጠት ሥራ እየተሠራ ነው።

በተቋሙ የሚዘጋጅ የሳይበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ያለው ሲሆን፤ በሚዲያ የሚተላለፍ ‹ሳይበረኛ› በሚል ፕሮግራም እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ ነው። ለተቋማትም ከመሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ጀምሮ ስልጠና ይሰጣል። በአስገዳጅነትም የሚሰጣቸው ተቋም እንዳሉ ሆኖ በተለይ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማት የንቃተ ህሊና ስልጠናዎች ይሰጣል። ይህ በተቋሙ በኩል የሚያከናወኑ ተግባራት ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ግን ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመጓዝ ሁሉም አመራሮች ቴክኖሎጂውን ተጠቅመ እራሳቸው በማብቃት፣ ሁልጊዜ ማንበብ ብዙ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።

በተመሳሳይ በተቋማት ላይ የስጋት ጊዜ ትንተና የሚሰራ ሲሆን፤ በተለየ ስጋት ተጋላጭነት (Risk Threat) ያሏቸው ተቋማት ጋር የአሠራር ሥርዓት፣ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ስንመለከት የሰው ኃይል ክፍተት ይታያል። የቴክኒካል ባለሙያዎች እጥረት ፣ አንድን ነገር ጨርሶ አጠናቅቅ የማወቅ ክፍተት እና ቴክኖሎጂውን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አምጥቶ ከመትከል በዘለለ አውቶሜት አድርጎ ጥቅም ላይ የማዋል ክፍተቶች እንዳሉ መረዳት የቻሉ እንደሆነ ነው ምክትል ዳይሬክተሯ የሚገናገሩት።

‹‹ብዙ ተቋማት ስንመለከት ያላቸው የቴክኖሎጂ እውቀትና አጠቃቀም ውስንነት ያለው ነው። ያላቸው እውቀት ቴክኖሎጂውን እንዴት እየተጠቀምኩበት ነው? ምን አይነት ዳታ እየሰበሰብኩ ነው? የሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች በጥልቀት ከማየት ይልቅ ይህንን አይነት ‹ሲስተም ገዝቻለሁ፤ አለኝ› ከሚል የዘለለ አይደለም›› ይላሉ። ‹‹ለዚህ በዚህ ዓመት ግን በተለየ መልኩ የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ጉዳዮች እና የኦዲት ሥራ አጠናክሮ መሥራት ይገባል። ይህ ሲሆን ንቃተ ህሊናን ይጨምራል፤ አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ ለማውጣት ያስችላል። ያንን ተግባራዊ የማያደርግ አካል ሲኖር ደግሞ እስከመቅጣት ድረስ የሚያስችል አሠራርን ይዘረጋል። ግንዛቤ ካለን የሚጠበቅብንን መወጣት እንችላለን። ያወቀ መሪ ካለ መስራት የምችለውን በሚገባ ተረድቶ ይሰራል›› በማለት ተናግረዋል።

እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሁን ላይ ቁልፍ መሠረተ ልማትና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የሚናገሩት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ ሁሉንም ነገር በተቋሙ ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ተቋማትም በራሳቸው መስራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ይናገራሉ። ለዚህም ተቋማትን ማብቃት ያስፈልጋል። ተቋሙ እንዳለው አይነት በቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራ ቡድን እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ሳይበር ደህንነትን በሚመለከት የተቋማት አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የስልጠና ሙጅሎችን በማዘጋጀት ከመሠረታዊ የኮምፒውተር ስልጠና ጀምሮ የሳይበር ባለሙያ እስከ መሆን የሚያስችሉ ጥልቀት ያላቸው ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ያስረዳሉ።

ሳይበር በንድፈ ሃሳብ የሚሰጥ ትምህርት አይነት አይደለም፤ በተግባራዊ እውቀት የሚፈልግ ነው የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ ቀደም ሲል እንደነበረው ሳይበርን የሚመለከት ትምህርት ለመማር አብዛኛው ሰው ውጭ ሀገር በመሄድ የሚማር እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ላይ ይህንን ክፍተት ከመድፈን አንጻር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይበር ደህንነት የተመለከቱ የትምህርት ዘርፎችን በመክፈት የማስተርስና የፒኤች ዲ (PhD) ፕሮግራም ቀርጸን ወደ 60 ለሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም ከሌሎች ተቋማትም ሁለት ሁለት ባለሙያዎችን በመወሰድ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።

‹‹አመራር የሁሉ ነገር ቁልፍ ነው፤ አመራሩ ከተጣመመ ተቋም ይጣመማል›› የሚል እምነት እንዳላቸው የሚገልጹት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ አመራሩ ከሰነፈ ሠራተኛው ይሰንፋል ይላሉ። በዚያው ልክ ደግሞ ጎበዝ አመራር ካለ ግን እንደሀገር ተሰናስሎ ጥሩ ሀገር መፍጠር ይቻላል። ታች ያለውን አበረታትቶ ሥራ ለመሥራት የአመራሩ ኃላፊነት ትልቅ ስለሆነ መበርታት ይፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 16/2015

Recommended For You