በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ልዑክ ዛሬ ወደ ሃንጋሪዋ ቡዳፔስት ያመራል። በተለያዩ ዙሮች ተከፋፍሎ ወደ ስፍራው የሚጓዘው የአትሌቲክስ ቡድን የአሸኛኘት መርሃግብርም ተደርጎለታል።
በዓለም ቻምፒዮና መድረክ ከ800 ሜትር (በሴቶች ብቻ) እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች የምትፎካከረው ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን ይሰበስባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ኦሪጎን በተካሄደው ቻምፒዮና 10 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛውን ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ከቀናት በኋላ በሚጀመረው ቻምፒዮናም ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን በውጤታማነት ለመመለስ የሚያስችለውን ዝግጅት ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ ሲያከናውን ቆይቷል። ዝግጅቱን አጠናቆ የውድድሩን መካሄድ ብቻ በመጠባበቅ ላይ የሚገኝም ሲሆን፣ አስቀድሞ ወደ ስፍራው ይጓዛል። የመጀመሪያው ልዑክም ዛሬ ወደ ቡዳፔስት የሚያመራ ይሆናል።
በቻምፒዮናው በተለይም በረጅም ርቀት ውድድሮች ስኬታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ታሪክ ከአንዱ በቀር በሁሉም ተሳትፋለች። በዚህ ቻምፒዮና ላይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ6 ርቀቶች 19 ሴት እና 16 ወንድ በጥቅሉ በ35 አትሌቶች የምታሳተፍ ይሆናል። ቡድኑ ጉዞውን የሚያደርገው በ7 ዙር ሲሆን፤ እንደየርቀቱና የውድድር መርሃ ግብሩ የሚከፋፈልም ይሆናል። ይህንን ተከትሎም ለቡድኑ ከትናንት በስቲያ የሽኝት መርሃ ግብርና የባንዲራ ርክክብም ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩም ላይ ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ተገኝተዋል።
ቡድኑ እንደቀደመው በውጤታማነት እንደሚመለስ በመድረኩ የተጠቆመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት እና የቡድኑ መሪ አትሌት ገዛኽኝ አበራ ስለ አትሌት አመራርጥ እና ዝግጅት አጠቃላይ ማብራሪያ ሰጥቷል። መልካም ውጤት እንደሚመጣም እምነቱን ገልጿል። አትሌቶች እና አሰልጣኞችም የነበራቸውን የዝግጅት ቆይታ አስረድተዋል። በዚህም በቻምፒዮናው ተሳታፊ የሆኑ አትሌቶች ከሌላው ጊዜ የተሻለ ፈጣን ሰዓት ያላቸውና በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ በመሆኑ በነበራቸው ዝግጅት ታግዘው ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ለቻምፒዮናው ዝግጅት አስተዋጽኦ የነበራቸውን አካላት አመስግና፤ ለቡድኑ መልካም ምኞቷን አስተላልፋለች። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር
አሸብር ወልደጊዮርጊስም የመልካም ምኞት ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ ከአሸናፊ አትሌቶች ጋር በመተባበር ለሚሮጡ አትሌቶች ሽልማቱ ዳጎስ ያለና ተመሳሳይ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ የመዝጊያና የመልካም ምኞት የሽኝት ንግግር ካደረጉ በኋላም የሀገር አደራ ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ለአትሌቶቹ አስረክበዋል።
ከሽኝት መርሃ ግብሩ አስቀድሞ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን በሚያደርግበት ወቅት የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እንዲሁም በዓለም ቻምፒዮና መድረክ በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ከሆኑ ታሪካዊ አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተገኝቶ አትሌቶችን አበረታትቷል። በንግግሩም ‹‹ኢትዮጵያዊ አትሌት ብልጥ ነው፤ በብልጠትም ማንንም ማሸነፍ ትችላላችሁ። እዚህ አካዳሚ ብቻችሁን እሮጣችሁ፤ እዚያ በብዙ ሰው ፊት እና በካሜራ ፊት ትሮጣላችሁ። ሌላ ምንም ልዩነት የለውም ሁልጊዜ ውድድር ሲደርስ መጨነቅ የለባችሁም። ምንም እንዳትፈሩ አሁን ያላችሁበት ሁኔታ በጣም ጥሩ ነው። ሁላችሁም ያላችሁን የሩጫ ታሪክ ተከታትያለሁ። በጣም ጥሩ ላይ ናችሁ። ለኢትዮጵያ ሀገራችሁ ታሪክ ስሩ። ሩጫ ትጥቅ አይደለም፣ ምቾት አይደለም፣ ሩጫ ቁርጠኝነት ነው። ቆራጥ ከሆናችሁ በብልጠት ከሮጣችሁ አትጠራጠሩ ታሸንፋላችሁ። ድሉ የእኛ ነው። በርቱ! አንበሳ በ24 ሰዓት ውስጥ 22 ሰዓት ይተኛል፤ ሁለት ሰዓት በሚገባ ያድናል። እናንተም አሁን ውድድሩ ስለደረሰ ሁለት ሰዓት በሚገባ ተለማመዱ። 22 ሰዓት እረፍት አድርጉ፤ አትጠራጠሩ ታሸንፋላችሁ›› በማለት ልምዱን አካፍሏል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2015