የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዓመታዊ ገቢ አድጓል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአክሲዮን ማህበር መመራት ከጀመረ ጥቂት የሚባሉ ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያትም በብዙ ፈተናዎች አልፎ እነሆ የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመንን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ ከገጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተጨማሪ ተስፋን የሚያጭሩና ደረጃውን የሚያሳድጉ ሥራዎችንም ሰርቷል፡፡ ከነዛም መካከል ሊጉ እንዲሸጥና የቴሌቪዥን ስርጭትን እንዲያገኝ እንዲሁም ተፈላጊነቱ እንዲጨምር መንገድ መክፈት ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሥራ ስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፤ ሊጉ ከፋይናንስ አኳያ ተሽጦ ገንዘብን ማምጣት በመጀመሩ ገቢው ማሳደግ በመቻሉ ተፈላጊነቱና ተወዳጅነቱ እየጨመረ መምጣት መቻሉን ለአዲስ ዘመን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም በዓመቱ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢን እስከማግኘት ደርሷል፡፡ የአገር ውስጥ ድርጅቶች የኢትዮጵያን እግር ኳስ እየፈለጉት ስለሆነ ብዙዎቹ ከሊጉ ጋር መስራት እንደሚፈልጉም ለመረዳት ተችሏል፡፡ በርካታ የማህበረሰብ ክፍል ስለሚከታተለው ምርትን ለማስተዋወቅ አመቺ በመሆኑ ሊጉ ገንዘብ ማምጣት እንደሚችል አሳይቷል፡፡ በዚህም ዓመታዊ የሊጉ ገቢ ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል። በዚህ መጠን የውጭ ምንዛሬን በማምጣት ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተፎካካሪ እየሆነም ይገኛል፡፡ ከተሰራ ደግሞ ተጫዋቾችን ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይችላል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ ስራ ውድድሩን በበላይነት መምራት፣ ማስተዳደር እና ሀብትን ማመንጨት እንደመሆኑ አብሮ መሥራት የሚፈልጉ አካላት ጋር ይሰራል፡፡ በቀጣይም የስያሜ ለውጥ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ሲሆን አዲሱ ለሁለት ዓመት ሚቆይ ስምምነትም በቅርቡ ይታወቃል፡፡

ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱ የኢትዮጵያን እግር ኳስ መስመር እንዲይዝ አድርጓል የሚሉት አቶ ክፍሌ ሰዓት ከማክበር፣ የተጫዋቾች የዳኞችን እና የአመራሩን ዲሲፒሊን እና እግር ኳሱን በሕግና ሥርዓት እንዲመራ ከማድረግ ጀምሮ ከገንዘብም በላይ በርካታ ጥቅሞችን እንዲያገኝ አስችሏል፡፡ በሶስት ዓመቱ ጉዞ ጥቂት ጨዋታዎች ደቂቃዎችን ከመዘግየት ውጪ በሰዓትና በሥነ ሥርዓት ተካሂደው ተጠናቀዋል፡፡ ዋናው ዓላማ ሊጉ የመሸጥ ደረጃ እንዲኖረው መሥራት በመሆኑ በዚህ ሊግ ቢዝነስ መሥራት የሚል የብሮድካስቲንግ ድርጅት እንዲመጣም ይሰራል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ ወደ ፊት ገቢውን ይበልጥ ለማሳደግ ከስያሜ መብትና ከቴሌቪዥን መብት ካሉት ሥራዎች ውጭ የማርኬቲንግ ሥራ ለመስራትም አቅዷል። በዚህም መሠረት ሶስት የሚደርሱ እቅዶችን ይዟል፡፡ በ2016 ዓ.ም የትኬት ሽያጭ ሥርዓቱን በኤሌክትሮኒክስ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ በመሆኑም ለሚቀጥለው ትውልድ መስመር የያዘ ተቋም ለማስረከብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሠረታዊ ችግር ስቴድየም በመሆኑ እንጂ ውድድሩን መምራት በጣም ቀላል ነው። በመሆኑም ስፖርቱን የሚመራው አካል ስቴድየም ላይ ብዙ መሥራት ይኖርበታል የሚሉት አቶ ክፍሌ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጠንካራ እና ተወዳጅ ነው፤ ስለሆነም እግር ኳስ ሀብት እንደመሆኑ እንደሌላው ኢንዱስትሪ መንግሥት አስቦ ስታዲየሞች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ማድረግ ያስፈልጋል›› ሲሉ አክለዋል፡፡

እንደ ሊግ ከባዱ ነገር የሜዳው ደረጃውን የጠበቀ አለመሆን ነው፤ ይህ ከተቀረፈ ሊጉን በተሻለ ደረጃ መምራት እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ስታዲየሞቹ ቀድመው ቢሰሩ ኖሮ ማጫወት እና ሕግና ሥርዓቱን መስፈጸም ብቻ ነው የሚጠበቅብን፡፡ በፊት መሠራት ያለበትን አሁን እየሰራን ነው፡፡ ስታዲየም መሥራት በዚህ ዘመን ብዙ ሀብት ያስፈልገዋል፡፡ እግር ኳስን የሚመሩ አካላት ተወያይተው መሥራት የሁላችንም የቤት ሥራ ነው›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ክለቦች የክለብ ስታንዳርድ ስለሌላቸው ከደሞዝና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር መቸገራቸውን ያነሱት አቶ ክፍሌ በዚህ ዓመት ትልቁ እቅድ ክለቦቹን መደገፍ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹መጀመርያ ክለቦች ተቋማዊ እንዲሆኑ ከዛም ቢዝነስ እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው፡፡ ከደመወዝና ተያያዥ ነገሮች ጋር ችግር ውስጥ የሚገቡትም እግር ኳሳዊ የሆነ ተቋማዊ አሰራር ስለሌላቸው በመሆኑ ሰነዳዊ እንዲሆኑ እየደገፍን ነው›› ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም መሠረት አስራ አምስት መስፈርቶችን አሟልቶ በመመዝገብ ሰነዱ በቀጣይ ኦዲት እንደሚደረግና የባለሙያ ቅጥርና ድጋፍ የማድረግ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ በቀጣይም አንድ አይነት ተቋማዊ አሰራር ሥርዓት እንዲኖራቸው ለመስራትም ታቅዷል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *