ክረምት እና የጸጉር ውበት

ጸጉር አንዱ የውበት መገለጫ ነው፡፡ ስለ ውበት ስናስብ የጸጉር ውበት ዘንፋላነቱን፣ ልስላሴውንና መሰል ነገሮቹን በመገለጫነት ማንሳታችን አይቀርም። ቆንጆ የምንላቸውን ሰዎች እንኳን ጸጉር ከሌላቸው ከውበታቸው አንዳች ነገር የጎደለ ያህል ይሰማናል፡፡ ጸጉር የውበት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ማጌጫም ነው። በተለየ መልኩ ለሴቶች የተለየ ውበትን ይሰጣል፡፡ የውበት መመዘኛ መስፈርትም ነው፡፡

በተለምዶ ‹‹የሴት ልጅ ውበቷ ጸጉሯ ነው›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ምንም እንኳን ውበት እንደተመልካቹ ነው ቢባል በተለይ የሴቶችን ውበት መመልከትም ሆነ ማድነቅ ስንጀምር ቅድሚያ የምንሰጠው የጸጉሯን ውበትን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት ረጅም ጸጉር ያላትን ሴት የተመለከተ ሰው የጸጉሯ ውበት በአግራሞት ከመመልከት ባሻገር አድናቆት ሳይችሯት አያልፉም፡፡

ሴቶቹ በዚያው ልክ ለጸጉር ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ በመታጠብ፣ በመስራት እና በመንከባከብ የጸጉራቸውን ውበት ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሴቶች ከሌሎች ውበት መጠበቂያዎች ይልቅ ለጸጉራቸው የሚሰጡት ክብደትም ከፍ ያለ ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ዘመኑ እየዘመነ ሲመጣ ለጸጉር የሚሰጠው ቦታና አመለካከት እንደዘመኑ ተለውጧልና ያንን ሁሉ ያደርጋሉ።

አሁን ላይ በአንዳንድ ምክንያቶች ‹‹የሴት ልጅ ውበቷ ጸጉሯ ነው›› የሚለው አባባል ያስቀረ ይመስላል። ምክንያቱ ደግሞ ዘመን አመጣሽ በሆነው ጸጉር ሴቶቹ መዋብ ስለሚችሉ ነው፡፡ ጸጉራቸውን በሚመቻቸው እና ውበት ይሰጠኛል ባሉት መልኩ ያስጌጡታል። እናም ጸጉር አያስፈልገኝም ያሉ ልክ እንደ ወንድ ሙሉ ለሙሉ የሚቆረጡበት፤ ላዘናፍለው ካሉም በዘመን አመጣሹ ሰው ሠራሽ ጸጉር (human hair) ድምቅ የሚሉበት፤ ካሻቸው ደግሞ በዊግ የተለያየ የሹሩባ አይነቶችን በመሰራት የሚዘንጡበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል።

በዘመን አመጣሹ ሰው ሠራሽ ጸጉር (human hair) በአብዛኛው ዘንድ ተመራጭ መዋቢያና ማጌጫ የሆነበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ አንዱ ጸጉር ለመታጠብ ለመስራት እንዲሁም ከተሰራ በኋላ ስሪቱን ለመፍታት ሆነ ለመንከባከብ ረጅም ጊዜ መውሰዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ያዘንጣል ተብሎ መታሰቡ ነው፡፡ ስለዚህም አሁን ሰው ሠራሽ ጸጉር ከመበራከቱ የተነሳ የተፈጥሮ ጸጉር እና ሰው ሰራሽ ጸጉርን መለየት እስከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ሁሉም እያጌጠ ነው እንዲባል ሆኗል።ህም ሆኖ ግን የጸጉር ሥራ እንደወቅቱና እንደሰው ፍላጎት የተለያየ ነው። በተለይን ክርምትን ስናስብ አብዛኛው ሰው የሚያዘወትረውና ተመራጭ የሚያደርገው ምን አይነት ነው ካልን ምላሹን የጸጉር ባለሙያዎች እንዲህ ያብራሩታል፡፡

አሁን ወቅቱ ክረምት በመሆኑ አብዛኛውን ሴቶች ሹሩባ እና ስፌት መስራትን ይመርጣሉ የጸጉር ባለሙያዋ ብርቱካን አሰግድ ሀሳብ ነው፡፡ እርሷ እንደምትለው፤ የጸጉር ሙያ ጸጉር ከማጠብ ጀምሮ መጠቅለል፣ የሽሩባ መስራትና ስፌት፣ ካውያ፣ ፖዬስትራ ፣ የቁርጥ ቀለም እና የመሳሳሉ በርከት ያሉ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ነው፡፡ በተለይ በእንደዚህ አይነት የክረምት ወቅት በጸጉር ሙያ የሹሩባ እና የስፌት ሥራዎች ከሁሉም በላይ ተመራጭ ናቸው ፡፡

የጸጉር ሥራ ህጻናት፣ ወጣቶች እና በሁሉም እድሜ ክልል ላይ ያሉ ሁሉም የሚሰሩት ሥራ ነው። የሚለየው የሚፈልጉት ዲዛይን እና ምርጫቸው ነው። ሁሉም ሰው ጸጉሩን ተሰርቶ መዋብ ይፈልጋል፡፡ አብዛኛውን የጸጉር ባለሙያ የጸጉር ሙያ ወዶትና ፈቅዶት የሚሰራው ሥራ ስለሆነ አንድን ሰው ጸጉር ከፊቱ ቅርጹ ጋር በሚሰማማ መልኩ የሚፈልገው አይነት ሥራ በመስራት ውበቱን ጠብቆ እንዲያምርበት ያደርጋል ትላላች፡፡

ቀደም ሲል አብዛኛው ሰው ያለውን ጸጉር በጥንቃቄ ይዞ በመስራት ውበቱን ይጠብቅ ነበር የምትለው ብርቱካን፤ አሁን ግን በራሱ ጸጉር ከሚያጌጠው ሰው ይልቅ በሰው ሠራሽ ጸጉር( ሂውማን ሄር) ወይም ጸጉርን በዊግ በመስራት የማጌጡት ይበልጣል፡፡ በጣም ጥሩ የሚባል ጸጉር ያላቸው እንኳን ከራሳቸው ይልቅ በሰው ሠራሽ ወይንም በዊግ በመስራት በመዋብን ይፈልጋሉ። በክረምቱም የአብዛኞዎቹ ምርጫ እነዚህ ላይ ያርፋል ስትል የወቅቱን ምርጫ ታነሳለች፡፡

አብዛኛዎቹ ሴቶች በሰው ሠራሽ ጸጉር ለመዋቢያነት የሚመርጡበት ዋንኛ ምክንያት ሰው ሠራሹን ጸጉርም ሆነ ዊግ እንደፈለጉት አድርገው በፈለጉት አይነት(ስታየል) መጠቀም ስለሚችሉ ነው፡፡ በጸጉሩን ረጅም ማድረግ የፈለገ ረጀሙን ሰው ሠራሽ ጸጉር መጠቀም የሚችል ሲሆን፤ አጭር እንዲሆንለት ከፈለገም አጭሩን በመግዛት ይጠቀማል፡፡ ሲፈልጉ ደግሞ እንደየፈላጎታቸው እያቀያየሩ መጠቀም ይችላሉ። በቀለም በኩልም የፈለጉትን አይነት ያገኛሉና እንደየምርጫቸው ይጠቀሙበታል፡፡ የተፈጥሮ ጸጉራቸው ከሆነ ግን እንዲህ ሊሆንላቸው አይችልም ትላለች፡፡

ቀደም ሲል የጸጉር ሥራ እንደሙያ አይታይም ነበር የምትለው ብርቱካን፤ አንዲት ሴት አጊጣ፤ ተውባ ስትታይ እንኳን ማነው እንዲህ ያሳመረሽ እየተባለ ውበቷ እየተደነቀ እንኳን እንደሙያ እውቅና አይሰጠውም ነበር። አሁን ግን ሙያው የሰው እራሱን ጠብቆ ሆኖ ውብ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርግ መሆኑን አብዛኛው ሰው እየተረዳው አመለካከቱ እየተቀየረ ነው፡፡ ለሰዎች ጸጉራቸውን እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው እና ከእነሱ ጋር የሚሄዱ የጸጉር ሥራዎች ምን አይነት መሆን እንዳለባቸው በመንገር ምክረ ሀሳብ የሚሰጥበትም እድል አለ፤ ተጠቃሚዎችም ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ለባለሙያው እውቅና መስጠት እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ሌላኛዋ የጸጉር ባለሙያዋ አልሚ ብርሃኑ በበኩሏ እንደምትለው፤ ቀደም ሲል ከነበረው አሁን ላይ ሰዎች ለውበታቸው ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ ለውበታቸው መጨነቅም ጀምረዋል፡፡ ሰዎች እንደ የወቅቱ ሁኔታና እንዳለባቸው ፕሮግራም አይነት የሚሰሩት የጸጉር ሥራም እየተለያየ መጥቷል፡፡ ነገር ግን በክረምት ወቅት አብዛኛዎቹ ሹሩባና ስፌትን ይመርጣሉ፡፡ በእርግጥ ሰው ሠራሽ ጸጉርንም መጠቀም የሚፈልጉ አሉ፡፡ ወቅቱ ክረምትም ቢሆን ካውያ ፣ፖዬስትራ የሚሰሩ እንዲሁ ሞልተዋል፡፡ ስለዚህም ሰው የፍላጎቱን የተመቸውን በዚህ የክረምት ወቅትም ቢሆን ይሰራል፡፡

ጸጉር በጥንቃቄ መያዝና አስፈላጊውን እንክብካቤ ይፈልጋል የምትለው አልሚ፤ አንዳንዶች ለጸጉራቸው ግድ አይሰጣቸውም፤ ፕሮግራም ወይም በዓላት ሲሆን ብቻ በመስራት መዋብ እንዳለባቸው ያስባሉ ትላለች፡፡

ሴቶች ጸጉራቸውን ሊሰሩ ሲፈልጉ በራሳቸው ምርጫው አለያም ባለሙያውን እንደሚያማክሩ የምትናገረው አልሚ፤ ሴቶች በተለየ መልኩ ጸጉራቸውን በመሥራት መንከባከብ እና ውበታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ትመክራለች፡፡ አብዛኞቹ ጸጉራቸው ከተጎዳ በኋላ ለመሥራትና ለመንከባከብ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ምንም ሳይሆን በፊት በየጊዜው በሚገባ ቢይዙትና ቢንከባከቡ ጥሩ ይሆን እንደነበርም ታስረዳለች። በሰው ሠራሽ ጸጉር ማጌጡ የሚጠላ ነገር ባይሆንም ካለው የዋጋ ውድነት እና ሌሎችም ነገሮች አንጻር የራስን ጸጉር ከሥር መሰረቱ መንከባከብ ይገባል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋልች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *