በ1967 ዓ.ም የተቋቋመ አንጋፋ ተቋም ነው። የዛሬን አያድርገውና በዘርፉ የሀገሪቱ መተንፈሻ ሳንባ ነበር ማለት ይቻላል። ያለሱ የሚሆን ነገር አለ ለማለት በሚያስቸግር መልኩ በመላ ሀገሪቱ በብቸኝነት ኃላፊነቱን በትጋትና በጥራት ሲወጣ ኖሯል፡፡ ይህንንም በዚህ ሙያ የተሰማሩ በሙሉ ይናገሩለታል። በተለይ በየመማሪያ መጻሕፍቱ ላይ ባለውና የትምህርት ሚኒስቴር የቁልምጫ ስሙ ይታወቃል፡፡ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት፡፡ ዛሬስ?
ዶ/ር ተመስገን ጋሮማ ከግንቦት 2014 ዓ/ም ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 1263 በደንብ ቁጥር 487/35 በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር የተደራጀው የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የድርጅቱ ራእይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና ጥራታቸውን የጠበቁ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማቅረብ በ2022 ዓ.ም በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ሆኖ መገኘት ነው፡፡
በብቁ፣ ታማኝነት፣ በተነቃቃ ሠራተኛና ጥበብ በተሞላ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ የትምህርቱን ዘርፍ መደገፍ፤ ብሎም የባለ ድርሻ አካላትን ፍላጎት ማሟላት ደግሞ የድርጅቱ ተልእኮው ሲሆን ከድርጅቱ ስልጣንና ተግባራቱ መካከል አንዱና የመጀመሪያው የትምህርት መሳሪያዎችን ማምረት፣ ማስመረት፣ መጠገን፣ መትከል፣ ማከፋፈል፤ እንዲሁም፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ገዝቶ ማከፋፈል ነው፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ሥራ እየሰራ አይደለም፡፡ እንደውም ድርጅቱ ምንም ሥራ የማይሰራበትና ቁጭ ከማለት በሚል አዋጭ ያልሆነና ማሽኖቹና የሰው ኃይሉ ሥራ ከሚፈቱ የተማሪዎችን ደብተር ወደ ማተም ሥራ ገብቷል፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመበት ዐቢይ አላማ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ማምረትና ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የትምህርት ተቋማት በሙሉ ወደዚህ ድርጅት በመምጣት የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እንዲመረትላቸው ያዙ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ይህንን እንድንሰራላቸው ወደ እኛ የሚመጡ የትምህርት ተቋማት ቁጥር ውስን ናቸው፡፡ የሚመጡትም ቢሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሰሩላቸው የሚፈልጓቸው መሳሪያዎች ውስን ናቸው፡፡
ሥራ አስፈፃሚው እንደሚናገሩት በአሁኑ ጊዜ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው ማለት አይቻልም። አሁን ባለው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ድርጅቱ ሥራውን በሁለት መንገድ ያከናውናል። አንደኛው በድርድር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጨረታዎችን በማሸነፍ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ እድል የለም። በግል ከደራሲያን ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶችና አጋዥ መጻሕፍትን በመሸጥ ካልሆነ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
ክልሎችም አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕትመት እንኳን አያዙም፡፡ የሚያዙትም ምናልባት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ነው፡፡ ለምሳሌ ሱማሌ ክልል 592 ሺህ፣ ሀረሪ 230 ሺህ፣ አዲስ አበባ ከ1ሚሊዮን በታች፣ አማራ 800 አካባቢ ነው ያዘዙት። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ያለውን አቅም ተጠቅሞ በ10 ሚሊዮኖች እንኳን ማምረት አልቻለም። ምናልባት አንዳንዴ ክልሎች አንዴ ስለሚልኩ የመደራረብ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከአቅሙ በላይ የሆነ ሥራ መጥቶበት አያውቅም።
የአቅርቦትና ፍላጎት ጉዳይን በተመለከተም፣ የክልሎች ትእዛዝ ራሱ በመቶ ሚሊዮን ከሚቆጠሩ ተማሪዎች ፍላጎት ጋር የሚሄድ አይደለም። በመሆኑም እጥረት መኖሩ የሚገርም አይደለም፡፡
ከፍተኛ ደረጃ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ፍላጎት አለ፡፡ የትምህርት ተቋማትና ራሳቸው ትምህርት ቤቶች እየመጡ ድርጅቱን ይጠይቃሉ፤ እንዲሸጥላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ይህን ማድረግ እንደማይችልና የሚችለው የመዋዕለ ሕፃናትንና አጋዥ መጻሕፍትን ማምረት ብቻ ነው።
ድርጅቱ መሥራት የሚችላቸው ምርቶች ውጭ ሀገር ተመርተው ወደሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እዚሁ መሥራት እየተቻለ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ የሕትመት ሥራዎች በመኖራቸው ሊቀሩ ይገባል፡፡ ወደ ውጭ መላኩ ከወጪ፣ ጊዜና ጥራት አኳያ አዋጭ አይደለም። ከዚህ አንፃር እዚሁ ሀገር ውስጥ ባሉ የሕትመት ተቋማት ቢሰራ ድርጅቱም፤ ሀገርም ይጠቀማሉ። ከገቢ፣ ከሥራ እድል፣ ከውጪ ምንዛሪ፣ ከማድረሻ ጊዜ፣ ከመጓጓዣ ወዘተርፈ አንፃር በማየት እዚህ ማሳተሙ የተሻለ ነው፡፡
የሕትመት ሥራው ወደ ውጭ ሀገር ይውጣ ከተባለ ሀገር ውስጥ ያለውን አቅም በሚገባ በመፈተሽ ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ድርጅቱ መሥራት በሚችለው ልክ እየሰራ አይደለም፡፡ አመቱን ሙሉም እየሰራና እያመረተ አይገኝም፡፡ ሥራዎች ቢመጡም የመጀመሪያና አራተኛው ሩብ አመት ላይ ነው እንጂ በመሀል ምንም የሚመጣ ሥራ የለም፡፡
የኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ምሁር ዶክተር ተመስገን በበኩላቸው ድርጅቱ ለውጭ ድርጅት ተሰጥቷል ስለሚባለው ጉዳይ አያምኑበትም። እንደውም ጉዳዩ ወደ ውይይት መጥቶ ክርክር ሊደረግበት ይገባል ይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው አባባል የውጭ ድርጅት አንዱን በ50 ብር አትማለሁ ቢልና የእሳቸው ድርጅት 100 ብር ቢል፣ እናንተ 100 ብላችኋል፤ እሱ 50 በማለቱ አሸንፏል ይባላሉ። ይህ ስህተት ነው። የውጭው 50 ብር ቢል ከዛ እዚህ የሚጓጓዝበት የትራንስፖርት ወጪ አለ። እዚህ ሀገር ውስጥ የሚሰራጭበት ወጪ አለ፤ ብዙ ወጪ አለ። እሱ ያንን ሁሉ ስለማያወጣ 50 ብር ሊል ይችላል። የእሳቸው ድርጅት ደግሞ 100 ብር ቢል በየተቋማቱና ትምህርት ቤቶች በራሱ ትራንስፖርት ነው የሚያደርሰው። ስንትና ስንት ገደል አልፎ፤ ጭቃ ውስጥ እየገባና እየወጣ ያደርሳል። በየትኛውም መስፈርት የውጪው 50 ብር (የማምረቻ ዋጋ) ካለው እሳቸው የሚመሩት ድርጅት 100 ብር ያለው ነው አዋጪው። ከጊዜ አንፃርም ቢሆን ቶሎ ሊያደርስና ችግሩን ሊፈታ የሚችለው የሀገር ውስጥ ድርጅት እንጂ የውጭው አይደለም።
ከቴክኖሎጂ አኳያም የውጭ የሚባሉት የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ የድሮ ነው፡፡ ከእኛ ምንም የተለየ አይደለም የሚሉት ዶክተሩ፤ አስፈላጊ ከሆነ ቁጭ ብለን መነጋገር እንችላለን ሲሉም በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። የማምረቻ ዋጋ እንጂ ሌላውን አይነግሩንም፤ እስኪ የጉምሩኩን፣ የትራንስፖርቱን ይንገሩን፤ ሀገሪቱ ለዛ የምታወጣውን ዶላር ማንም አይነግረንም። ዝም ተብሎ በ50 ብር አሸንፏል ነው የሚባለው ሲሉም የአሰራር ዝንፈት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ “እዚህ የሀገርን ማሽን ሥራ ፈት አድርጎ፣ የሰው ኃይልን አባክኖ … ዶላሩን ወደ ሌላ ሀገር መላክ ምንድነው ጥቅሙ?” ሲሉም ነው የሚጠይቁት። “በጉዳዩ ላይ ቁጭ ብለን እንከራከርበት” ሲሉም ነው የሚመለከታቸውን ወደ መድረክ የሚጋብዙት።
ሥራ አስፈፃሚው እንደሚገልፁት ድርጅቱ የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችን የሚያመርት ሲሆን ለአብነትም የማስተማሪያ እና አጋዥ መጻሕፍት ሕትመት ፤ የቁሳቁስ (ፈርኒቸር) – ለምሳሌ ለትምህርት ቤቶች መቀመጫ ወንበር፣ ለሆስፒታሎች፣ ለላቦራቶሪዎች ወዘተ ያመርታል፡፡ የተለያዩ ትእዛዞችንም በመቀበል ይሰራል፡፡ ለትምህርት መርጃ የሚውሉ፣ ላፕቶፕ፣ ታብሌትና ሌሎችን የሚያካትቱ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችለውን ጥናት አከናውኗል፡፡
ድርጅቱ ለትምህርት ዘርፉ መጻሕፍትን፣ ለላብራቶሪ የሚውሉ የሳይንስ ኪቶችን፣ ለመማሪያ የሚያገለግሉ ወንበሮችን፣ ጠመኔና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማምረት ለመጀመሪያና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያቀረበ እንደሚገኝ፤ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በዋናነት ለአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማቅረብ እቅድ ይዟል፡፡ ድርጅቱ ያለበትን ችግር ለመፈታትም በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ ከባለ ድርሻ አካላት ጋርም ተነጋግሯል፡፡
በተለይም ከትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር ንግግሮችን አካሂዷል፡፡ በገበያ ጥናትና ምርምር ዘርፉም ለችግሮች መፍትሔ አፈላልጓል፡፡ የተለያዩ ቡድኖችን እያዋቀረ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በመላክ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ ከክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሳይቀር በጉዳዩ ላይ ሲመክር መቆየቱንና አሁንም ይህንኑ እንደሚቀጥሉና ከድርጅቱ ጋር መነጋገር ለፈለገ ሁሌም በሩ ክፍት ነው፡፡
የተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ዋነኛ ምክንያት የካሪኩለም መቀየር፣ የሕትመት ቁጥር ውስንነት፣ የአሰራር ውስብስብነት፣ የግልፅነት መጓደል፣ ችግሩን ለመፍታት የሚኬድበት ርቀት ውስን መሆን ናቸው፡፡ የሕትመት ፍላጎትን ለማሟላት ድርጅቱ ፍላጎት ቢኖረውም የክልሎች ትእዛዝ ውስንነት በመኖሩና ጨረታዎችን አለማሸነፉ ይህን የፍላጎት ክፍተት መሙላት አላስቻለውም፡፡
የመማሪያ መጻሕፍት በፒዲኤፍ ተሰራጭተዋል የሚለው የአንዳንድ ክልሎች አስተያየት ለዶክተሩ ብዙም የሚጥም አይደለም። ከ80 በመቶ በላይ አርሶ አደርና የገጠር ነዋሪ ባለበት ሀገር “ፒዲኤፍ …” የሚለው ነገር ብዙም አያስኬድም ባይ ናቸው። በመሆኑም የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን እስኪዳብር ድረስ መጻሕፍትን አሳትሞ ማሰራጨት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለ። አሳትሞ ማሰራጨቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ ነው የሚበጀው፤ ቢያንስ እስከ አስር አመት ድረስ ሊቀጥል እንደሚገባው ነው የኛ ጥናት የሚያሳየው። የክልሎችን የበጀት እጥረት መፍታት ይገባል። መጻሕፍትን ከፍ ባለ ቁጥር ማሳተም ችግሩን ይቀርፈዋል።
የደንበኞች ፍላጎትን ከማርካት አኳያ ሁሌም በትጋት እንደሚሰሩ የሚናገሩት ዶ/ር ተመስገን አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተወሰነ ሰጥቷቸው በጥሩ ሁኔታ ሰርተው እንዳስረከቡና አሁንም ሁለት መጻሕፍት በመሥራት ላይ መሆናቸውንም ይገልፃሉ።
ቀድሞ በነበረው አሰራር በተከታታይ ትእዛዛት ይመጣሉ፣ በተከታታይ ሥራዎች ይሰራሉ፣ ሥርጭትና አቅርቦቱም በዛው ልክ ይካሄዳል። በመሆኑም እጥረት የሚባለው ነገር አይኖርም።
ጥያቄዎች፣ በተለይ ከግሎች ከሐምሌ ጀምሮ እስከ ጥቅምት በተከታታይ ስሩልን እያሉ ይመጣሉ፤ እሱ አይነቱ አሰራር ቢፈቀድ ጥሩ ነው። ምናልባትም ቁጥጥር ካስፈለገ የቁጥጥር መንገዱን መዘርጋት ይገባል። አብረን ስለምንሰራ አቅም ያላቸው የግል ድርጅቶች እንዳሉ እናውቃለን። በመሆኑም የሀገር ውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። ለማተሚያ ቤቶች ረዘም ያለ ጊዜ ሰጥቶ ሰርተው እንዲያቀርቡ ማድረግም ለችግሩ መቀረፍ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።
ሌላው ከአሰራር አኳያ መሻሻል አለበት የሚሉት ጉዳይ ያላቸው ሲሆን፣ እሱም የጊዜ ጉዳይ ነው። ይህንንም፣ “ያሸነፈው ከታወቀ ወርና ሁለት ወር በኋላ በ30 ቀን አድርሱ በሚል የሚመጡ ትእዛዛት አሉ። ይህ ተገቢ አይደለም። ለምን እንዲህ ሊባል ቻለ የሚል ነገርም ያስነሳል። እውነት ለትምህርቱና ለተማሪዎች በማሰብ ነው ወይ ያስብላል። በ30 ቀን ማንም፣ ውጪም ቢሆን የሚያደርስ የለም። እንዴት ሆኖ ነው የሚደርሰው፤ የማይሆን ነገር። ይህ ችግር እንዲፈታ ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ በግልፅ እየተነጋገርን ነው።” ሲሉም ይገልፁታል። እነዚህና ሌሎች ሥራዎች ከተሰሩ ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣም ይችላል እንጂ ክልሎች እና ትምህርት ሚኒስቴር ብቻ አሳትሞ የሚያሰራጨው ችግሩን ይቀርፈዋል ለማለት ያስቸግራል” የሚለው የዶክተሩ የችግሩ መፍቻ ይሆን የተሰነዘረ የመፍትሄ ሀሳብ ነው።
ሥራን በተመለከተም እኛ ክልሎች እኛ ጋ ብቻ ይምጡ አንልም። በትክክለኛው አካሄድ ብቻ ይስሩ ነው የምንለው። የሀገር ውስጥ ማተሚያ ድርጅቶች (ለምሳሌ ብርሃንና ሰላም፣ ዓባይ፣ መልባ …) ይሁኑ እኛ በትክክል እንጠቀም ነው የምንለው። ለምሳሌ እኔ ዓባይ ሄጄ እጅግ ሶፈስትኬትድ (ዘመናዊ) የሆነ ማሽን ድንኳን ለብሶ አይቼ አዝኛለሁ። ያለ ሥራ ተቀምጦ። ባለቤቱ እየዞረ ይለምናል። ሥራ የሚሰጠው የለም። እኛስ ልምድም ምንም ስላለን ያንን ተጠቅመን እንቀሳቀሳለን።
እኔ የሕትመት ድርጅቱ በሚገባ እየሰራ ነው ማለት አይቻልም። በሚገባ እንነጋገር። የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ መድረክ ይምጡ። እናንተም በሚገባ ፍሬም አድርጋችሁ ስሩበትና ለለውጥ እንስራ። ስለ እውነት ለመናገር እኛ እየተንቀሳቀስንና ወደፊት እየሄድን ያለነው በፈርኒቸርና በኬሚካል ነው እንጂ በሕትመት ሥራ ነው ማለት አይቻልም ሲሉም የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ።
“ለግለሰብ ደራሲያንስ ውድ ናችሁ?” የሚለውንም አስመልክተው እነሱ ከማንም በተሻለ እንደሚሰሩና ውድ ነው የሚልም ካለ ከወረቀትና የውጭ ምንዛሪ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ ቢያጤነው ጥሩ ነው። ምን ያልጨመረ ነገር አለና ነው እኛ ጨመራችሁ የምንባለው? በድሮው ዋጋ ሥራ እንድንሰራ ይጠበቃል? ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ር ተመስገን በቶን መቶ ምናምን የነበረው ወረቀት አሁን ሁለት መቶ ምንምን ሺህ ገብቷል ሲሉም ልዩነቱን ይገልፃሉ።
በማጠቃለያም፣ የመማሪያ መጻሕፍት እጥረትን በተመለከተ በመቶ ሚሊዮኖች እየተፈለገ በመቶ ሺዎች እያሳተሙ ችግር ሊፈታ አይችልም። አንድ ክልል እንኳን ከሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ቢኖሩት እያንዳንዱን ተማሪ የእያንዳንዱ ትምህርት የመማሪያ መጻሕፍት እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ሥራን ይፈልጋልና እነዛን ሥራዎች መሥራት ይገባል የሚሉት ዶክተር ተመስገን፣ ነገሮችን ኤቲካልና ስትራተጂክ በሆነ መንገድ መመልከት እንደሚያስፈልግ፤ ለዚህም ድርጅታቸው በርካታ ጥናታዊ ሥራዎች፣ መረጃዎች ያሉት በመሆኑ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ ሊያደርግ እንደሚችል ይናገራሉ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2015