ሕመም ያልበገራት የፅናት ተምሳሌት

በተከታታይ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክ በ10ሺ ሜትር የሴቶች ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ብቸኛዋና ታሪካዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ናት።በመድረኩ በነበሯት ተሳትፎዎች በጠቅላላው 5የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ቀዳሚ የሆነችው ጥሩነሽ እአአ በ2005 እና 2007 ተከታታይ ድሎችን አስመዝግባለች።ከእነዚህ ድሎች መካከል ግን በኦሳካው ቻምፒዮና ያገኘችው ሜዳሊያ የአትሌቷን ጥንካሬ የሚያስመሰክር፣ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ አልፋ ያገኘችው በመሆኑ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ምንጊዜም የማይዘነጋ ነው።

እአአ በ2003 በፓሪስ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ የሆነችው ጥሩነሽ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያን ለሀገሯ በማስገኘት ነበር ከቻምፒዮናው ጋር ያላትን ቁርኝት የጀመረችው።በቀጣዩ የሄልሲንኪ ቻምፒዮና ላይ ደግሞ አትሌቷ በታወቀችበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ አድናቆትን ልታተርፍ ችላለች።ቀጣዩን ቻምፒዮና የጃፓኗ ኦሳካ አዘጋጅ ስትሆን ጥሩነሽ እንደተለመደው ሀገሯን በ10ሺ ሜትር ለሶስተኛ ጊዜ ለመወከል ከውድድሩ ስፍራ ተገኝታለች።የስፖርት ቤተሰቡም ይህቺን ተዓምረኛ ወጣት የምታደርገውን የአሸናፊነት ትግል ለመመልከት በጉጉት ተሞልቶ ከስታዲየም ተገኝቷል።

የውድድር ሰዓቱ ደርሶም ሩጫው ተጀመረ።የሩጫው ዙሮች ከመክረራቸው በፊትም ተጠባቂዋ አትሌት ሩጫዋ ከኋላ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊያን በማርሽ ቀያሪነታቸው የታወቁ በመሆናቸው በርቀቱ አጋማሽ ወደፊት ትወጣ ይሆናል የሚል ነበር የስፖርት ቤተሰቡ ግምት።በሂደት ግን አትሌቷ አንዳች ችግር እንደገጠማት በተደጋጋሚ ሆዷን በመያዝ ከምታደርገው ጥረት ለመረዳት ተቻለ።ውድድሩን በድምጽ እያስተላለፉ የነበሩት ኮሜንታተሮችም በአትሌቷ ላይ ምን እንደተፈጠረ ጥያቄ ሆኖባቸው በተደጋጋሚ ስሟን ያነሱ ነበር።

በእርግጥ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በመሰል የጤና ችግሮች ውስጥ ሆነው ሀገራቸውን ሲወክሉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። እንደ እሳት በሚያቃጥል ንዳድ አስፓልት ላይ ባዶ እግራቸው እየደማ፣ የቀዶ ህክምና አድርገው በቀናት ልዩነት የተወዳደሩ፣ ከወሊድና ከጉዳት ሳያገግሙ፣ ወድቀው እየተነሱ ሀገራቸውን ለድል ያበቁ በርካታ አትሌቶችን ያፈራች ሀገር ናት።በስፖርታዊ ውድድሮች ህግ ብልጫ ያለው ሊያሸንፍ፤ ያልተቻለውም ሊረታ የግድ ነው።በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ይህንኑ ተቀብለው አቅማቸውን አውጥተው በመሮጥ ለማሸነፍ ይጥራሉ፤ ሽንፈታቸውንም ቢሆን በጸጋ ተቀብለው ለቀጣይ ይተጋሉ።ነገር ግን በገጠማቸው ችግር ምክንያት ውድድር ማቋረጥ የሚለው ከባድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እጅግ ሩቅ ናቸው፡፡

የያኔዋ ወጣት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ጤናዋ መታወኩ በግልጽ ቢታይም ውድድሩን አቋርጣ ህመሟን ማዳመጥን አልመረጠችም።ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው ለመፋለም የትኛውም ምድራዊ ኃይል የማይበግራቸው ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተተኪ ናትና ሀገሯን አስቀድማ ህመሟን ልትጋፈጠው ወሰነች።ርቀቱ እየገፋ ሲመጣም በእሷና በሌሎች አትሌቶች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ቻለች።በመጨረሻም በጎን በኩል በመውጣት ወደፊት ተጠጋች።የመጨረሻዎቹ የርቀቱን ሜትሮችም አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ቀድማ ወጥታ ከነበረችው ለቱርክ የምትሮጠውን ትውልደ ኢትዮጵያዊት አትሌት አቢይ ለገሰን በመከተልና አሳማኝ በሆነ ብቃት በመጨረሻው ዙር ተስፈንጥራ በመውጣት በሰፊ ልዩነት የወርቅ ሜዳሊያውን ለሁለተኛ ጊዜ ከእጇ ማስገባት ችላለች።

31:55.41 በሆነ ሰዓት በመግባትም ምንጊዜም የማይረሳ አስደናቂ ገድል ልታስመዘግብም ችላለች።ይህንን ተከትሎም አትሌቷ በሰጠችው አስተያየት ‹‹በህይወቴ አስቸጋሪው ውድድር ነው።ከባድ የሆድ ህመም ገጥሞኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ወደፊት ለመምጣት የምችል እስከማይመስል ድረስ ከኋላ ቀርቼ ነበር።ነገር ግን ውድድሩን ለሀገሬ የማደርገውና ኢትዮጵያዊያንም የሚጠብቁት ውጤት በመሆኑ ህመሜን ውጬ ለመታገል ወሰንኩ፤ እናም አሸነፍኩ።ይህም በህይወቴ ትልቁ ውድድር ነው›› ስትል ነበር የገለጸችው።

 ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *