የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልቂጤ ከተማን ይገጥማል። በደርቢ ጨዋታዎችና ብዙ ደጋፊዎች በሚያስተናግዱ ጨዋታዎች ላይ የጊዜና የቦታ ማሻሻያ እንደሚደረግም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በውድድር መርሃ ግብር እጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መስከረም 20/2016 ዓ.ም እንደሚጀመር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው። የውድድር መርሃ ግብሩም ከትላንት በስቲያ በተካሄደ የእጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት በአክስዮን ማህበሩ ጽህፈት ቤት ተከናውኗል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የሊግ ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት፤ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ሁሉም ሳምንታት የሚገጥሟቸውን ክለቦች ማወቅ ችለዋል። በዚህም የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፎ ከመውረድ ለጥቂት የተረፈውን ወልቂጤ ከተማን ይገጥማል።
በወጣው መርሃ ግብር መሠረት የመጀመሪያ ዙር የሊጉ ጨዋታዎች በ15 ሳምንታት ተካሂደው የሚጠናቀቁ ይሆናል። በመጀመሪያው ሳምንት አዲስ አዳጊዎቹ ሀምበርቾ ዱራሜ ከተማ፣ ሻሸመኔ ከተማና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ድሬዳዋ ከተማን፣ ወላይታ ድቻን እና አዳማ ከተማን ይገጥማሉ። ኢትዮጵያ መድን ከባህር ዳር ከተማ፣ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ መድን፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከመቻል እና ሀዋሳ ከተማ ከፋሲል ከተማ በመጀመሪያው ሳምንት የሚገናኙ ክለቦች ናቸው።
በእጣ ማውጣት መርሃ ግብሩ ላይ የደርቢ ጨዋታዎችና ከፍተኛ ተመልካች እንደሚያስተናግዱ በሚጠበቁ ጨዋታዎች ላይ የቦታና የጊዜ ለውጦች እንደሚኖሩም ለማወቅ ተችሏል። በመርሃ ግብሩ የተለየው የትኛው ክለብ ከየትኛው ጋር ይጫወታል የሚለው ሲሆን፤ ጨዋታዎቹ የሚከናወኑበት ሰዓትና ቦታ በቀጣይ ይፋ የሚደረግ መሆኑን አክስዮን ማህበሩ አስታውቋል። በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረትም ጨዋታዎቹ እንደተለመደው በተመረጡ ከተሞች ይካሄዳሉ። ከፍተኛ ደጋፊ እና የደርቢ ስሜት ያላቸው ጨዋታዎች ደግሞ ክለቦቹ መሠረት ባላቸው ቦታ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል። ጨዋታዎቹ ክለቦቹ በተመሰረቱበት አካባቢና በሚገኙበት ስፍራ የሚካሄዱት የተሻለ የደጋፊ ቁጥር ለማግኘትና የሜዳ ገቢን ለማሳደግ እንደሆነም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈም ይሄንኑ የሚያጠናክር አስታያየታቸውን ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ‹‹የእጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት አክስዮን ማህበሩ ከሚያካሄዳቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። በውላችን መሠረት አብሮን ለሚሰራው ሱፐር ስፖርት የውድድር ዓመቱን መርሃ ግብር ከአንድ ወር በፊት መስጠት አለብን። የዘንድሮውን የእጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ለየት የሚያደርገው ደግሞ በእጣ ማውጣቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሳተፉ ነው። እስከ ዛሬ ተጫዋቾች ተጋብዘው ነበር እጣውን የሚያወጡት›› ብለዋል።
እንደ አቶ ክፍሌ አስተያየት፣ በቀጣይ የካፍና የፊፋን የጊዜ ሰሌዳ በመከተል ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት ጊዜያት ይለያሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዋንጫ እንደ አዲስ ወደ ውድደር የሚመለስ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊጉ እረፍት በሚሆንበት ጊዜ እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል። ለዚህም አመቺ የሆነ ጨዋታ ፕሮግራም ለማውጣትም ከኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ጋራ በመነጋገር ላይ ይገኛሉ። አስገዳጅ ነገሮች ካልተፈጠሩ በቀር በሚወጣው መርሃ ግብር መሠረት ጨዋታዎቹ የሚካሄዱም ይሆናል።
‹‹ከትልልቅ ተቋማት ጋር እንደመስራታችን ለሊጉ ጨዋታዎችን ማቆራረጥ የጥራት ደረጃውን ይቀንሳል›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ አክስዮን ማህበሩ በ2015 ዓ.ም የውድድር ዘመን የተሻለ የተመልካች ቁጥርን ማግኘት እንደቻለ አስረድተዋል። ይሄንንም ለማሳደግ የደርቢ ጨዋታዎች ክለቦቹ በሚገኙበት አካባቢ እንደሚካሄዱ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከተማ ከባህር ዳር እና የደቡብ ክለቦች ጨዋታዎችን የሰዓትና ቦታ ማሻሻያ በማድረግ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳርና ሀዋሳ ለማድረግ እንደታሰበም ጠቁመዋል። አምና ይህንን በሀዋሳና ባህርዳር ከተማ በመተግበርም የተሻለ ደጋፊ ተገኝቷል። የስቴድየም እድሳት የሚጠናቀቅ ከሆነ ደግሞ የአዲስ አበባ ደርቢ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015