ከፈነዳው ቦምብ በስተጀርባ …

በኢትዮጵያ ባህል ቡና አፍልቶ ጎረቤትን ቡና ጠጡ ብሎ መጥራት የተለመደ ነው። ጎረቤታማቾችም ሰብሰብ ብለው ቡና እየጠጡ እየተጨዋወቱ ልምዳቸውን፣ ሀሳባቸውን፣ መረጃዎችን ከመለዋወጥ ባለፈ ለችግሮቻቸው የመፍትሔ ትልሞችን የሚያስቀምጡበት የማህበራዊ መስተጋብር ማንጸባረቂያ መድረክ ነው። በዚህ ኢትዮጵያዊያን ባህልና ወግ መሠረት ወይዘሮ ይፍቱሥራ ታደሰ ከጎረቤቶቿ ጋር ቡና እየተጠራሩ ይጠጣሉ፣ ይጨዋወታሉ፣ ይወያያሉ … ወዘተ።

እንደወትሮው ሁሉ ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ወይዘሮ ይፍቱሥራ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ወረገሩ ዋፈደ መንደር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ ቡና አፍልተው ጎረቤቶቿን (ወይዘሮ ስንዱ ቀቻ፣ ወርቂቱ ደምሴ) ቡና ጠጡ ብለው ይጠራሉ።

ቡናው ተቆልቶ፣ ጭሱ ተጫጭሶ፣ በቡናው ጡዑም ማዕዛ የወይዘሮ ይፍቱሥራ ቤት ምሽቱን ደምቋል። ጎረቤቶቿ ወይዘሮ ስንዱ ቀቻና ወርቂቱ ደምሴ ቡና ሊጠጡ በእርሳቸው ቤት ተሰይመዋል። ጎረቤታማቾቹ እንዲህ ሰብሰብ ብለው ቡና እየጠጡ፣ ቡና ቁርሳቸውን እየበሉ እየተጫወቱ እያለ የቤቱ በር ይንኳኳል። የቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ይፍቱሥራ ቡና ሲካድሙበት ከነበረው መቀመጫቸው ተነስተው በሩን ከፈቱት። የተከራያቸው የአዲስዓለም በቀለ ባለቤት አቶ በነበር ተሰማ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ በሩ ላይ እንደጅብራ ተገትሮ ቆሟል። እሳቸውም “ግባ ቡና እየጠጣን ነው፣ ቡና ጠጣ” ይሉታል። እሱም በምላሹ “እሺ” ብሎ ወደ ቤት የሚገባ መስሎ በእጁ የያዘውን ነገር ቡና ከሚጠጡበት መሀል ወርውሮ በሩን ላያቸው ላይ ጥርቅም አድርጎ ይዘጋባቸዋል። በሩን በዘጋው ቅጽበት አንዳች ነገር “ዷ” ብሎ ፈነዳ። የፍንዳታው ድምጽ ከወይዘሮ ይፍቱሥራ ቤት አልፎ በአካባቢው ያሉ የጎረቤቶቿን ቤት ሁሉ አንቀጠቀጠ።

ቡና ሲጠጡ የነበሩ ሦስቱም ጎረቤታማቾች ቤት ውስጥ እንዳሉ በያሉበት ወደቁ። አቶ በነበር ወደ ቤት ወርውሮ ቤቱን በላያቸው ላይ ዘግቶ ያፈነዳው ቦምብ ሆኖ ቆይቶ፤ ወይዘሮ ወርቂቱ ደምሴ በወደቀችበት ዳግም ላትነሳ በዚያው ወድቃ ቀረች። ወይዘሮ ይፍቱሥራና ስንዱ የቦምቡ ፍንጣሪ የተለያየ የአካላቸው ክፍል ላይ ጉዳት አድርሶባቸው ደም በደም ሆነዋል። መላ አካላቸው ቆስሏል። የቤቱ ግድግዳ በቦንቡ ፍንጥርጣሪ ተበሳስቷል። ሳሎን የነበሩ እቃዎች (ቡፌ፣ ፍሪጅ ወዘተ) ከጥቅም ውጭ ሆነው ደቀዋል።

ከፍንዳታው በኋላ የቤቱ ባለቤት እንደምንም ከወደቀችበት እየተንገዳገደች ተነስታ የቤቱን በር ከፍታ ወደውጭ ስትወጣ፤ አቶ በነበር ይባስ ብሎ ወደ ቤት ዘልቆ በመግባት በያዘው ዱላ ወይዘሮ ስንዱን ከወደቀችበት ሶስት ጊዜ ደጋግሞ ጀርባዋን መትቷት ከቤት ወጣ። እሱም ይህንን ወንጀል ፈጽሞ ወደ መኖሪያ ቤቱ አቅንቶ የቤቱን በር በኃይል ከፍቶ ወደ ውስጥ ገብቶ የእንጨት አጣና ዱላ ካስቀመጠበት አንስቶ እየተጣደፈ ከግቢ ወጥቶ ይሄዳል። ይሄኔ ባለቤቱ ወይዘሮ አዲስዓለም (ቀደም ብሎ የፍንዳታ ድምጽ ሰምታ ስለነበር) ተጠራጥራ ተከታትላው ከቤት ወጥታ የግቢው በር ላይ ቆማ “ኡ! ኡ! ድረሱልኝ! ሰው ገሎ እየሄደ ነው” እያለች ጩኸት አሰማች።

በፍንዳታው ድምጽ ተሸብሮ ግራ ገብቶት የነበረው የመንደሩ ማህበረሰብ የድረሱልኝ ጩኸቱን ሲሰማ በየአቅጣጫው ግልብጥ ብሎ ወጣ። ቀድመው የደረሱት አቶ ግርማ ዋኬኔ እና ልጃቸው ጫላ ግርማ ነበሩ። እነርሱም አቶ በነበርን ቁም እያሉ ከኋላ ከኋላ እየተከተሉ ሲጠጉት በእጁ በያዘው ቢላዋ ይሁን ጩቤ ባልታወቀ ስለታማ ነገር መጀመሪያ ሰንዝሮ ጫላ ግርማን ሊወጋው ሲል ጫላ እንዳይወጋው ሲከላከል ግራ እጁን በስለት ይወጋዋል። አባት “ለምን ልጄን ትወጋዋለህ” ብሎ ሲጠጋ እርሳቸውንም በስለት ሰንዝሮ የግራ ጆሯቸው አካባቢ ጨረፍ አድርጎ ጉዳት ያደርስባቸዋል። እንዲህ ተጠርጣሪው ከአባትና ከልጅ ጋር እየተፋጠጠ እያለ የአካባቢው ማህበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ይዞ ለፖሊስ ያስረክበዋል። አባትና ልጅ ለፖሊስ በሰጡት የምስክርነት ቃል ተጠርጣሪው ጉዳት እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም ከላይ በተገለጸው መሠረት ጎረቤታማቾቹ ቡና እየጠጡ እያለ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ ከቤት መሰወሩን የቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ይፍቱሥራ እንዲሁም ቤት ውስጥ ቡና እየጠጣች የነበረችው ወይዘሮ ስንዱ ለፖሊስ በሰጡት የምስክርነት ቃል ገልጸዋል። ወይዘሮ ይፍቱሥራ አክለውም፤ ተጠርጣሪው ይህን ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ከእርሳቸው ጋርም ሆነ ከጎረቤቶቿ ከሟች ወርቂቱ እና ስንዱ ጋር ምንም አይነት ፀብ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

ነገር ግን ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም ወይም ወንጀሉ ከመፈጸሙ ከሦስት ቀን በፊት የከተራ እለት ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ ተጠርጣሪው አቶ በነበርና ባለቤቱ አዲስዓለም “አምሽተሽ መጣሽ፣ ስልክ ስደውልልሽ አላነሳሽልኝም፤ የዋልሽበትን አይቼዋለሁ፤ መሥሪያ ቤትሽ አካባቢ ነው የዋልሁት” ብሎ ተጣልተው ሊደበድባት ነበር። በወቅቱም ሊደበድባት ሲል ባለቤቱ አምልጣ ወይዘሮ ሀና ከተባለችው ሌላኛዋ ተከራያቸው ቤት ዘላ ገብታ ቤቱን ከወደ ውስጥ ቀረቀረችበት። ተጠርጣሪው ዱላ ይዞ ባለቤቱን ሊደበድባት ስለነበር እንዳይደበድባት በማለት እሳቸው፣ ሟች ወይዘሮ ወርቂቱ እና ተጎጂ ስንዱ ሆነው ወገቡን ጥምጥም አድርገው ይዘው እንዲተው በመለመን ዱላውን ተቀብለው ወደቤቱ ያስገቡታል። እነሱም “አንተም ተው፣ አንቺም ተው” ብለው ገስጸው ባልና ሚስቱን ያስማሟቸዋል። ባልና ሚስቱም ወንጀሉ እስኪፈጸም ድረስ ሰላም እንደነበሩ ይናገራሉ።

ተጠርጣሪው “ለምን ይህን የወንጀል ድርጊት እኔና ጎረቤቶቼ ላይ ሊፈጽምብን ቻለ” ብዬ ቁጭ ብዬ ሳወጣ ሳወጣሳወርድ ባልና ሚስት የተጣሉ ጊዜ “ሴት ናት፣ ብትመታት ትጎዳብሃለች፣ አትምታት” የሚል ምክር አዘል ንግግር ተናግረውት እንደነበር ወይዘሮ ይፍቱሥራ ጠቅሰው፤ “ይህን ሁኔታ ለሚስቱ ተደርቤ እንደተናገርሁ ቆጥሮት ቂም ይዞ ሊሆን ይችላል። ቤት ባከራየውም በቤት ኪራይ ጉዳይ ተነጋግረን አናውቅም። የቤት ኪራይ የምትከፍለኝ ባለቤቱ ናት” ሲሉ በተጨማሪ ለፖሊስ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የሚስት የምስክርነት ቃል

ወይዘሮ አዲስዓለም በቀለ ከተጠርጣሪ ባለቤቷ አቶ በነበር ጋር በመሆን የወይዘሮ ይፍቱሥራን ቤት ተከራይተው በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ጠቁማ፤ በቀን 10/05/2014 ዓ.ም ባለቤቷ “ስልክ ስደውልልሽ ለምን አታነሽም” በሚል ምክንያት ተጣልተው ነበር። በወቅቱም ባለቤቷ ሊመታት ሲል በግቢው ውስጥ ተከራይታ ከምትኖር ወይዘሮ ሀና ከምትባል ጎረቤቷ ቤት ገብታ ታመልጣለች። በዕለቱም ባልና ሚስቱን “በዓል ነው፣ ተው አትጣሉ” ብለው አከራያቸው ወይዘሮ ይፍቱሥራ፣ ሟች ወይዘሮ ወርቂቱ፣ ተጎጂ ስንዱ እና ሀና ሆነው ያስታርቋቸዋል። ከታረቁም በኋላም ወንጀሉ እስከተፈጸመበት ቀን ድረስ እንዳልተጣሉ ትናገራለች።

ወንጀሉ በተፈጸመበት ቀን (13/05/14 ዓ.ም) ምሽት አካባቢ ላይ ሥራ ውላ ወደ ቤቷ ስትመለስ የመኖሪያ ሰፈር አካባቢያቸው ስትደርስ ባለቤቷ አቶ በነበርን አግኝታው ተያይዘው ወደ ቤታቸው ያመራሉ። ቤታቸው ገብተው እያለ አከራያቸው ወይዘሮ ይፍቱሥራ ቤታቸው ድረስ መጥታ “ሀና ጋር ለምንድነው የምትኮራረፉት” ብላ ባልና ሚስቱን ታናግራቸዋለች። እሷም በምላሹ “አላኮረፍናትም ደግሞም አልተገናኘንም” ብላ መልስ ትሰጣለች። ባለቤቷ ግን “ለምንድነው ከፍለን በምንኖረው ቤት የምትጨቀጭቁን” በማለት በኃይልና በቁጣ ድምጹን ከፍ በማድረግ ለአከራያቸው መልስ ሰጥቶ በሩን ገፍትሮ ይዘጋዋል። “እንደውም ቤቱን እለቅልሻለሁ” ብሎ ይናገራል።

አከራያቸውም በምላሹ “ከለቀቅህ በሰላም ልቀቅ” ብላ ስትመልስለት ወይዘሮ አዲስዓለም በንግግራቸው መሃል ገብታ “ግቢ ወደ ቤትሽ” ብላ አከራያቸውን ወደ ቤቷ ታስገባታለች። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ባለቤቷ የለበሰውን ነጠላ ጫማ አውልቆ ሽፍን ጫማ አጥልቆ፣ ከላይ ኮቱን ጣል አድርጎ ቁምሳጥኑንና ቡፌውን ፈተሽ አድርጎ ከቤት ይወጣል። ከቤት ሲወጣ እሷ የእንጀራ ሊጥ እያቦካች ስለነበር ምን ይዞ እንደወጣ አላስተዋለችም። ከቤት ወጥቶም ሀና ከተባለችው ጎረቤታቸው ቤት በሩ አካባቢ ቁሞ በስሟ ሲጠራት ለተወሰነ ደቂቃ አቤት አላለችውም ነበር። “ሀና ውጭ፣ ምን አስፈራሽ፣ አናግሪኝ” ብሎ ደጋግሞ በስሟ ሲጠራት ወጥታ “ፈርቼ ነው” ብላ ይቺን ቃል ብቻ እንደመለሰችለት ትናገራለች። ምክንያቱም አዲስዓለም ቤት ውስጥ ስለነበረች ምን እንደተነጋገሩ በደንብ አልተሰማትም።

አቶ በነበር ከሀና ጋር ተነጋግሮ ከጨረሰ በኋላ ወደ ራሱ መኖሪያ ቤቱ በሩ አካባቢ መጥቶ ከውስጥ ባለቤቱና ልጁን ጨምሮ በድምሩ ሦስት ሰው እያለ የቤቱን በር ከወደ ውጭ በኃይል ዘግቶባቸው ይሄዳል። ቤቱን ከወደ ውጭ ዘግቶባቸው ከሄደ ከሁለት ደቂቃ በኋላ “ዷ” የሚል የፍንዳታ ድምጽ ተሰማ፤ የቤቱ ግድግዳም በኃይል ተነቃነቀ። የፍንዳታው ድምጽ ከተሰማ በኋላ ባለቤቷ ወደ ቤቱ መጥቶ በሩን በኃይል ከፍቶ ወደ ውስጥ ገብቶ ቤት ውስጥ ያስቀመጠውን የእንጨት አጣና ዱላ ይዞ በፍጥነት ከግቢ ውጭ ወጥቶ እየሮጠ ይሄዳል። እሷም “አንድ የሆነ ያደረገው ነገር አለ” ብላ ተጠራጥራ ተከታትለው ከቤት ወጥታ የግቢው በር አካባቢ ቆማ “ኡ! ኡ! ድረሱልኝ፣ ሰው ገሎ እየሄደ ነው” እያለች ጩኸት አሰማች። ከዚያም የመንደሩ ሰው ጩኸቷን ሲሰማ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ተጠርጣሪውን ይይዘዋል።

በወቅቱም ፖሊሶች መጥተው ቃሏን እየተቀበሏት ስለነበር ሁለቱ (ይፍቱሥራና ስንዱ) ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ሐኪም ቤት ተወስደው ስለነበር የደረሰባቸውን ጉዳት አላየችም። ይሁን እንጁ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ከመጡ በኋላ ጉዳት እንደደረሰባቸው አይታለች። በተጨማሪም ሟች ወርቂቱ ከይፍቱሥራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ወድቃ ከፍተኛ ደም ፈሷት ሕይወቷ እንዳለፈ ማየቷን ለፖሊስ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ወይዘሮ አዲስዓለም ገልጻለች።

የተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል

በኦሮሚያ ክልል ተወልዶ እንዳደገ ተጠርጣሪው አቶ በነበር ጠቁሞ፣ ትምህርቱንም እስከ 4ኛ ክፍል ተወልዶ በአደገበት ቀየ ተከታትሏል። ተወልዶበት ባደገው አካባቢ በቤተሰብ ቂም በቀል የተነሳ ከአንድ አቶ በልግነህ ከተባለ ግለሰብ ጋር ታኅሳስ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ተጣልቶ፤ ግለሰቡን በእንጨት ዱላ ጭንቅላቱን ደጋግሞ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደርጋል። ይህንን ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎ መረጃ አጠናቅሮ ለአቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርትበት ያቀርባል። አቃቤ ሕግ በተጠርጣሪ ላይ ክስ መስርቶበት ፍርድ ቤት በ18 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ውስኖበት ይታሰራል። ኋላም አምስት ዓመት ከመንፈቅ ታስሮ በአሞክሮ ከእስር መለቀቁን ይናገራል።

ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የቀን ሥራ እየሠራ ሕይወቱን እየመራ እያለ ከወይዘሮ አዲስዓለም ጋር ተዋውቀው በ2009 ዓ.ም ትዳር መሰረቱ። አንድ ወንድ ልጅም አፍርተዋል። እንዲህ አንድ ላይ ከላይ በተጠቀሰው አካባቢ ቤት ተከራይተው በሰላም እየኖሩ እያለ በቀን 10/05/2014 ዓ.ም ለባለቤቱ አዲስዓለም በተደጋጋሚ ስልክ ሲደውል አታነሳም። ሥራ እንደ ሄደች በዛው አድራ በነገታው ወደ ቤቷ ትመለሳለች። እሱም “ምን ሆነሽ ነው? ስልክሽ የማይሠራው” ሲላት ባለቤቱ በአግባቡ መልስ እንዳልሰጠችው ያስረዳል።

በአግባቡ ሳትመልስለት ስትቀር ተበሳጭቶ ዱላ አንስቶ ሊመታት ሲል ዘላ ሀና ከተባለችው ጎረቤታቸው ቤት ትገባለች። ከሀና ቤት በሩ አካባቢ ቁሞ ባለቤቱ ውስጥ እንዳለች “አንቺ … እንትን” እያለ ይሰድባታል። በዚህ ምክንያት ተጣልተው እያለ በእለቱ “ተው” ብለው ሟች ወርቂቱ፣ ስንዱና አከራያቸው ይፍቱሥራ ሆነው እንዳስታረቋቸው ይገልጻል።

በ13/05/2014 ዓ.ም ሀና የተባለችውን ጎረቤታቸውን “ሰላም ስላት” ዝም አለችኝ የሚለው ተጠርጣሪው፤ ሀናን “ምንሆነሽ ነው? ዝም ያልሽኝ” ብሎ ሲያናግራት “ከባለቤትህ ጋር እያለሁኝ ሰድበኽኛል” ትለዋለች። እሱም ከሀና ጋር እንዲህ እየተነጋገረ እያለ ከሀና ቤት ውስጥ የነበረ አንድ ከዚህ ቀደም በአካል አይቶት የማያውቀው ግለሰብ ውጥቶ “አፍህን አትክፈት፣ ዞር በል ከሰው በር” እንዳለው ይናገራል።

ይሄኔ እሱም ንግግሩን ትቶ ወደ አከራያቸው ወይዘሮ ይፍቱሥራ ቤት አምርቶ አከራዩን “ሀና አኩርፋኛለች ምክንያቷን ጠይቁልኝ” ይላቸዋል። አከራያቸውም “እሁድ አስታርቃችኋለሁ” እያሉት በራቸው ላይ ቁመው እያወሩ እያለ፤ ከሀና ቤት ውስጥ የነበረው ግለሰብ ወደነሱ መጥቶ ሟችና ተጎጆች ወዳሉበት የሆነ ነገር ወርውሮ አፈንድቶ ሲሮጥ ለመያዝ ሲከተለው እንዳመለጠው አቶ በነበር ያስረዳል።

ከዚያም የማያውቃቸው የሰፈሩ ሰዎች “አንተ እራስህ ነህ ቦምብ ያፈነዳኸው” ብለው ይዘው ለፖሊስ እንዳስረከቡት ጠቅሶ፤ “እኔ ቤቴ ውስጥ ቦምብ የለኝም፤ ሟችና ተጎጆች ላይ ቦምብ ወርውሬ የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ አላደረስሁም፤ ወንጀሉን አልፈጸምሁም፤ ወንጀሉን የፈጸመው ሌላ ሰው ነው” ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን ለፖሊስ ሰጥቷል።

ፖሊስም የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ ሟች በቦንብ ፍንዳታ ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ የሕክምና ውጤት፣ የአማሟት ሁኔታ፣ የደረሰባትን ጉዳት … ወዘተ የሚያስረዳ እንዲሁም ተጎጂዎች የደረሰባቸውን ጉዳት የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ ክስ እንዲመሰርትበት መረጃውን አቅርቧል።

ዐቃቤ ሕግ

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና 539፣ 27/1 ሥር ተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ ከላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ቦታ እና ጊዜ Y3PLM-Y-80 583 የሆነ አሜሪካ ሠራሽ ቦንብ በመወርወር ሟች ወርቂቱ ደምሴ ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል፤ እንዲሁም በወይዘሮ ይፍቱሥራና ስንዱ ላይ ደግሞ ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግ በፈጸመው የግድያ ሙከራ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ በተከሳሽ ላይ ክስ መስርቶበታል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።

 ውሳኔ

 ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሽ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

 ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *