በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ በስኬታማነቱ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ሀገሩን ለሶስተኛ ጊዜ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ሴካፋ) ውድድር ላይ እንደሚወክል ይታወቃል። ለስድስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው ክለቡ ትናንት ከሰዓት በኋላ የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር ወደ ሆነችው ኡጋንዳ አምርቷል። በመጀመሪያው ምድብ የደለደለው ክለቡ በውድድሩ መክፈቻ ዕለት ከብሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ ጋር የሚጫወትም ይሆናል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ ካስጀመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ነው። እአአ በ2021 ግብጽ ካይሮ ላይ የተጀመረው ይህ ውድድር፤ በሊጎቻቸው ቻምፒዮን የሆኑ ክለቦች በየዞኖቻቸው በሚያደርጉት የማጣሪያ ውድድር አሸናፊ ሲሆኑ የሚካፈሉበት ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሩን በመወከል በሴካፋ ዞን ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ በቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳታፊ ለመሆን ከጫፍ ደርሶ ሳይሳካለት መመለሱ ይታወሳል። ነገ በሚጀመረው ውድድር ላይም ከእስካሁኖቹ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመወከልም ወጥኗል።
በተጫዋቾች የዝውውር መድረክ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየው ክለቡ ለማጣሪያ ውድድሩ የሚረዳውን ዝግጅት ከሐምሌ ወር አጋማሽ አንስቶ በሀዋሳ ከተማ ሲያደርግ ቆይቷል። በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው ቡድኑ የሀዋሳ ቆይታውን አጠናቆ ከትናንት በስቲያ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ሲሆን፤ ምሽት ላይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ አመራሮች፤ እንዲሁም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በተገኙበት የሽኝት መርሃ ግብር ተከናውኗል።
ሽኝቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፤ ክለቡ በሚያስመዘግበው ድል የባንኩን ስም ከማስጠራት በዘለለ በዓለም አቀፍ መድረክም የሀገር ኩራት መሆናቸውን እያስመሰከሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዚህ ቻምፒዮና ላይም በሁለቱ ተሳትፏቸው ያጡትን ውጤት ከአምናው ተሞክሮ በመውሰድና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የነበራቸውን የበላይነት በመተግበር እንደሚያሳኩ ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው፤ ክለቡ ለኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል። በመድረኩ ተከታታይ ተሳትፎ ያደረገው ክለቡ ከዚህ በኋላ በኬንያ እና ታንዛኒያ የነበሩትን ክፍተቶች በማረም ወደ ቻምፒዮንስ ሊጉ በማለፍ ሀገራቸውን እንዲያስጠሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከክለቡ ጋር ለሶስተኛ ጊዜ ለሴካፋ የበቃው አሰልጣኝ ብርሃኑ ገዛኸኝ፤ በሁለቱ የሴካፋ ተሳትፎ ዋንጫ ባይመጣም ተጫዋቾቻቸው ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። በዚህ ቻምፒዮናም በውጤት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንና የኢትዮጵያን ጥንካሬ ለማሳየት ወደ ኡጋንዳ የሚያመሩም መሆኑንም ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ያነሳችው አምበሏ ሎዛ አበራ በበኩሏ፤ ቡድኑ በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ ጠቁማለች። በውድድሩም ላይ የተሻለ ብቃት በተግባር በማሳየት ታሪካዊ የሆነ ውጤት ይዞ ለመመለስ መዘጋጀታቸውንም አብራርታለች።
በውድድሩ ዘጠኝ ቡድኖች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በሁለት ምድብ ተደልድለውም ውድድራቸውን ያከናውናሉ። በዚህም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ 5 ክለቦች በሚገኙበት የመጀመሪያው ምድብ ከኡጋንዳው ካምፓላ ክዊንስ፣ ከጅቡቲው ኤፍኤዲ፣ ከቡሩንዲው ቡጃ ኩዊንስ እና ከደቡብ ሱዳኑ ዬይ ጆይንት ስታርስ ጋር ተመድቧል። በሁለተኛው ምድብ ደግሞ የታንዛኒያው ጄኬቲ ኩዊንስ፣ የኬንያው ቪጋ ኩዊንስ፣ የሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ እንዲሁም የዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን የሴት እግር ኳስ ክለቦች ተደልድለዋል።
የማጣሪያው ውድድሩ በካምፓላ ከነሐሴ 6-18/2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ 30 አባላት ያሉት ልዑክ ትናንት ከሰዓት በኋላ ወደ ስፍራው አምርቷል። ከሁለት ዓመት በፊት በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ውድድር እስከ ፍጻሜ የተጓዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ፤ ከኬንያው ቪጋ ኩዊንስ ጋር በነበረው ጨዋታ በመደበኛ ሰዓት አንድ እኩል ቢለያይም በተጨማሪ ሰዓት ግብ ተቆጥሮበት ነበር የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እድሉ የተጨናገፈው። ባለፈው ዓመትም ታንዛኒያ ላይ በተመሳሳይ ምድቡን በመምራት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ቢችልም በኡጋንዳው ሺ ኮርፖሬት 2ለ1 በሆነ ጠባብ ውጤት በመረታቱ የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞው ሊገታ ችሏል። ለደረጃ ባደረገው ጨዋታም የሩዋንዳውን ኤኤስ ኪጋሊን 3 ለ1 አሸንፎ ሶስተኛ በመሆን ነበር ውድድሩን የፈጸመው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2015