በአህጉር አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ክለቦች ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮምፌዴሬሽን ካፕ የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህርዳር ከተማ ከፊታቸው ለተደቀነባቸው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ክለቦቹ ቀደም ብለው ወደ ዝግጅት ከመግባት ባለፈ በዝውውርም ራሳቸውን በማጠናከር ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያን በመድረኩ የሚወክሉት ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው በአህጉር አቀፎቹ ውድድሮች ተሳታፊ እንዳደረጋቸው ይታወሳል። በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ከሜዳ ውጪ የሚያደርገው ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዝግጅቱን ከጀመረ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኖታል። ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም በታንዛኒያ ዳሬሰላም አዛም ኮምፕሌክስ ስቴዲየም ከዛንዚባሩ ኬመኬመ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን፤ ለዚህም እንዲረዳው ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ጠንክር ያለ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ፈረሰኞቹ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለ16ኛ ጊዜ በማሸነፍ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳታፊ በመሆን ቀዳሚ ነው። በሀገር ውስጥ ውድድሮች በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ታላቅ ክለብ መሆኑን ማስመስክር ቢችልም በአፍሪካ መድረክ ግን ውጤታማ መሆን አልቻለም። በቻምፒዮንስ ሊጉ ከአስር ያላነሱ ተሳትፎዎችን ማድረግ ሲችል በአንድ አጋጣሚ ብቻ የጥሎ ማለፍ ዙርን ተቀላቅሏል። የዘንድሮውን የቻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ የተሻለ ለማድረግም ዝግጅቱን አስቀድሞ ጀምሯል። በአንጻሩ ተጋጣሚውም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ረጅም የዝግጅት ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፍ የሚችል ከሆነም ከግብጹ ኃያል ክለብ አል አህሊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል። ጨዋታው ጠንከር ያለ በመሆኑን ተከትሎም ረዘም ያለ ዝግጅቱን የቀጠለም ነው የሚመስለው። በተጨማሪም የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚጀመርበት ወቅት በመቃረቡ እና የኢትዮጵያ ዋንጫም በአዲስ መልክ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ውድድር ስለሚመለስ ሀገር እና አህጉር አቀፍ ውድድሮቹን ታሳቢ በማድረግ በሰፊው እየተዘጋጀም ይገኛል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ፈረሰኞቹ በክለቡ ያሉትን ነባር ተጫዋቾች ውል በማደስ እና አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣት ክለቡን የማጠናከር ስራዎችንም እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል። ክለቡን ከተቀላቀሉት ተጫዋቾች ውስጥም ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ናቸው። በግብ ጠባቂነት አምና በባህር ዳር ከተማ ቆይታ የነበረውን ፋሲል ገብረሚካኤልን በሁለት ዓመት ኮንትራት ማስፈራማቸው ይታወሳል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በክለቡ አጥቂ ስፍራ ተሰልፎ በፕሪሚየር ሊጉ ኮኮብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ከክለቡ ጋር በተለያየው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ምትክ ደግሞ አማኑኤል ኤርቦን አስፈርሟል። ፈረሰኞቹ በክለቡ ረጅም ዓመታትን የቆዩትን፣ እንደ ናትናኤል ዘለቀ የመሳሰሉትን ተጫዋቾች ኮንትራት አድሷል። ያስፈረሟቸውን አዳዲስ ተጫዋቾችን በማካተትም ልምምዳቸውን ቀጥለው ጨዋታቸውን የሚያደርጉበትን ቀን ብቻ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድራቸውን በሁለተኝነት የጨረሱት ባህር ዳር ከተማዎችም በአፍሪካ ኮምፌዴሬሽን ካፕ ይሳተፋሉ። የጣና ሞገዶቹ በመድረኩ ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ ለቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸው የሚያግዛቸውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በነሐሴ ወር አጋማሽ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከታንዛኒያው አዛም ክለብ ጋር የሚያካሂዱም ይሆናል። በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አስደናቂ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉት የጣና ሞገዶቹ ለመድረኩ አዲስ መሆናቸው ውድድሩን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ይገመታል። ነገር ግን የአምናውን ብቃታቸውን መድገም ከቻሉ በመድረኩ ረጅም ጉዞን ማድረግ ይችላሉ። ለዚህም እንደ ፈረሰኞቹ ሁሉ ቀደም ብለው ዝግጅታቸውን መጀመር ችለዋል።

ዝግጅታቸውን ቀደም ብለው ከመጀመራቸው አንጻር የተሻለ የመዘጋጃ እና ቡድኑን የማዋሃጃ ጊዜ እንዲኖረው የሚያደርግ ስለሆነ የተሻለና ተፎካካሪ ቡድን ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። በአህጉር አቀፍ ውድድር እንደመሳተፉ በዝውውር መስኮቱ የነቃ ተሳትፎን እያደረገም ነው። ክለቡ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛል። ውላቸው የተጠናቀቀ ተጫዋቾችንም ውላቸውን በማደስ በክለቡ እንዲቆዩ ማድረግም ችሏል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *