የትኛውም ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል

ማምሻ ግሮሰሪ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ጨለምለም ብላለች። መቼም ልማድ ከዕውቀት ይበልጣልና ዝናብ ቢዘንብም፤ ጨለማው ቢበረታም ማምሻ ቤቱን እንደ ቤተክርስቲያን መሳለም ልማድ የሆነባቸው ተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ጎራ ሳይሉ ወደ ቤታቸው አይገቡም። ማምሸታቸው ቤተሰባቸውን ቢያስከፋም፤ በዝናብ እና በብርድ እንዲንከራተቱ ቢያደርጋቸውም እነሱ ግን ጎራ ከማለት ወደኋላ አይሉም።

እንደለመዱት ተሰማ፣ ዘውዴ እና ገብረየስ አንድ ጠረጴዛ ታቅፈው የዕለቱ አጀንዳቸውን በትንሹ ከፍ አድርገው በዓለም ደረጃ ያለውን ችግር እየተወያዩ ጀመሩ። አንዴ እየተስማሙ መልሰው እየተጨቃጨቁ ውይይታቸውን ቀጠሉ።

ተሰማ ‹‹አልገባችሁም፤ የአፍሪካ መሪዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ያለ እርዳታ እና ብድር መላወሻ የላቸውም። ወደ ውጪ የሚልኩት ምርትም ሆነ ጥሬ ዕቃ ወጪያቸውን የሚሸፍን አይደለም። ስለዚህ ምንም እሴት ያልተጨመረበት ጥሬ ሃብት ልከው ትንሽ ገንዘብ ይሰበስባሉ። ብዙውን በጀታቸውን የሚሸፍኑት ደግሞ በእርዳታ እና በብድር ነው።

እርዳታ እና ብድሩን የሚሰጡ አገራትም ሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ደግሞ የሚሰጡት በቅድመ ሁኔታ ነው። ምናልባትም ቅድመ ሁኔታዎቹ ሕዝባቸውን እንዲያስቀይሙ፤ አገራቸውን እንዲጎዱ የሚያስገድድ ይሆንና ማድረግ ይከብዳቸዋል። ይህም ሆኖ ግን እነ እርሱ አገር እና ሕዝብን ለመጉዳት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው፤ ብድር እና እርዳታ ለማጣት ቢወስኑም ሕዝብን ለማስተዳደር ተስኗቸው፤ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ቢሆን እንኳን እነ እርሱ እምቢ ያሉትን በእግራቸው የሚተካው ቀጣዩ መንግስት እሺ ሊል ይችላል። በዚህ ላይ እርግጠኛ አይደሉም። ስለዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ። ብዙሃኑ ሕዝብ ደግሞ ይህንን አይረዳም። ›› አለ።

ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ተሴ አንተ ትክክል ነህ። ነገር ግን መካድ የማይቻለው ከምንም በላይ ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ወሰን የለሽ የመበዝበዝ እና በእጅ አዙር የመግዛት ፍላጎት ነው። በሕዝብ ታምነው የተመረጡ መንግስታት የአገርን ሃብት ይዘርፋሉ፤ በሌላ በኩል ሌላኛው ዓለም (ያደጉት አገራት) እኛን ድሆቹን በተለይም አፍሪካውያንን ይመዘብራሉ። የድሃ አገራት መንግስታት ምንም ተፈጠረ ምን፤ ከስልጣናቸው መነሳት አይፈልጉም። እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ እየገዙ መኖርን ይሻሉ። ይህ ደግሞ አፍሪካ ላይ ይበረታል።

የአፍሪካ አገራት ጉዳይ እጅግ በጣም የሚያሳዝነው መሪዎቹ ምንም ተፈጠረ ምን ስልጣን አለመልቀቃቸው ብቻ ሳይሆን፤ ብዝበዛው እና የግፍ አገዛዙ ከውስጥም ከውጪም መሆኑ ነው። በውስጥ አንዴ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትም ሌላ ጊዜ በሌሎች አጋጣሚዎች፤ የመንግስትን ስልጣን የተቆናጠጡ ሰዎች ባለማወቅ ጥፋት ያጠፋሉ፤ ነገር ግን ጥፋታቸውን ተከትሎ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይሆኑም። ለዚህ በአፍሪካ ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ያልሆኑ የአገር መሪዎች ብለን ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ብዙ አሉ። ስልጣን ካለመልቀቃቸው ባሻገር በተለያየ መልኩ ሕዝብን የሚወዱ እና ለሕዝብ የሚሠሩ መስለው በመታየት ይዘርፋሉ።

በሌላ በኩል እርዳታ እና ብድር ሰጪዎቻችን ስግብግብነታቸው አይካድም። ነገር ግን ክፋታቸውና ተግባራቸው የሚታየው በግልፅ አይደለም። የሚሾሙ መስለው የሚሽሩ፤ የሚያድኑ መስለው የሚገሉ ናቸው። ‹‹በጠላት መመታት እና መጠላት ጥሩ ነው። ›› ይባላል። ለእዚህ አባባል ዋነኛው ምክንያት ጠላት ጠላትነቱ የሚታወቀው ሲመታ ነው ከሚል መነሻ ነው። ከመታ ጠላት መሆኑ ታወቀ ማለት ነው። ካልመታ እና ከሌላው ጋር ከተቀላቀለ ካለው መካከል ለመለየትም ሆነ፤ የጠራ መሥመር ለመዘርጋት ያዳግታል።

ጠላት ሲመታ እና ሲተናኮል የበለጠ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ጠላት ጫናው እየጨመረ ሲመጣ፤ ሥራዎች በትኩረት በሚገባ በከፍተኛ ጥንቃቄ ይከናወናሉ። ዋነኛው ችግር ግን ሁላችንም የምናየው በጠመንጃ የመጣ ጠላትን ብቻ መሆኑ ነው። በጠመንጃ የመጣን ጠላት ለመቋቋም አያዳግትም። ችግሩን በትክክል ነቅቶ በማወቅ በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ ይሰጣል። ነገር ግን በጠመንጃ ሳይሆን በሴራ አገር ለማፍረስ የሚሰራ የውጪ ጠላት አካሄዱ ጭድ ውስጥ እንደሚርመሰመስ እባብ በመሆኑ ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል።›› ብሎ የውስጡን ተነፈሰ።

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ኢትዮጵያ ክፉ የውጪ ጠላቶች አሉባት። የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን በማረጋገጫ ያሳየች ኢትዮጵያ፤ ስሟ ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ አጥብቀው የሚሠሩ አሉ። የህዝብ ብዛቷ የሚያሳስባቸው፤ የተፈጥሮ ሃብቷ የሚያጓጓቸው፤ ማደጓ የሚያንገበ ግባቸው ብዙ ስለመሆናቸው መካድ አይቻልም። ምክንያታቸው ደግሞ በዓለም ላይ ለዘላለም ነጭ የበላይ ሆኖ፣ ዓለምን ገዝቶ እንደኖረ እንዲታሰብ ብሎም ዓለምን እየገዛ እንዲኖር ስለሚሹ ነው። ኢትዮጵያ የምትባል አገር እስካለች ድረስ ደግሞ፤ ይህ ሊሆን አይችልም።

በእርግጥም ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ እንዳሉ ካልተረዳን በጣም የሚያስቆጭ ስህተት እንፈፅማለን። ስህተት የሚፈፅመው ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕዝብም ጭምር ነው። ነገር ግን ሕዝብ ይህንን በተመለከተ እንዲያውቅ በደንብ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። አገር አገር ሆና እንድትቆም፤ ኢትዮጵያ በልማቱም እንዲሳካላት፤ መንግስት የራሱን ሃሳብ እና ፍላጎቱን መፈፀም ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ ጋር መመካከር፤ በደንብ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያለውን እንቅፋት በተጨባጭ ማስረዳት፤ የተሳሳቱትን ማረም እና እውቅና ሊሰጠው ሊበረታታ የሚገባውን ማበረታታት፤ መቀጣት ያለበትን መቅጣት አለበት።

በመለማመጥ እና በመልመጥመጥ ትልቅ ውጤት ማምጣት ቀርቶ አገር ማቆም ያዳግታል። ስለዚህ መፍትሔው ሁሉንም በእኩል ደረጃ ሕግ እንዲያከብር ማስገደድ ነው። ሕግ አላከብር ያለው ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይገባል። እርምጃ ከተወሰደ ስርዓት ይያዛል። ሰላም ይሰፍናል። በአገር ውስጥ ሰላም እና ሥርዓት ከሰፈነ በኋላ አሻጥር ለመሥራት መሯሯጥ ቢኖርም መክሸፉ አይቀርም። ስለዚህ አሁን የሚያሳስበን አሻጥር ሳይሆን ሕግ የማስከበር፤ ስርዓት የማስፈን እና ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ሊሆን ይገባል።

ሕግ ማስከበር ጥቅሙ ለተወሰነ ቡድን ብቻ ሳይሆን፤ ለአጠቃላይ ለሕዝብና ለመንግስትም ጭምር ነው። ሕግ ማስከበር በብዙ መልኩ መድሃኒት ነው። ሕዝብ ሕግን ተከትሎ ሲሔድ፤ የአገር ሕመም መድሃኒት ያገኛል። በአገር ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል። ሕግ ሳይከበር ለውጥ እና ዕድገትን ማሰብ ተራ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ነው።

ሕግ ለማስከበር ሕግ በሚጥሰው ላይ የኃይል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የኃይል እርምጃ ሳይወስዱ መዘግየት የበለጠ ሕግ የሚጥሰውን ቡድን ማፈርጠም በዚህም አገር የማፍረስ፤ ሕዝብን የመበዝበዝ እንዲሁም ለስርዓት አልበኞች አሳልፎ መስጠት ነው።›› ብሎ ሃሳቡን ቋጨ።

ተሰማ በዘውዴና በገብረየስ ሃሳብ ተስማምቷል። ነገር ግን የኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶች ጠንክረው እንደሚሠሩ ለማመልከት አንዳንዶች ደግሞ ባለማወቅ የጠላቶችን ሃሳብ በመደገፍ እና በማራገብ የሚሳተፉ መሆኑን ለመጠቆም አስቦ፤ ‹‹በተራ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በማጋነን እንደብሔር ግጭት እንዲወሰድ እና ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲጣላ፤ አንዱ የሌላው ጠላት እንዲመስል የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ይህንን የጠላትን ሃሳብ ገዝተው ሳያውቁ ደግፈው ጉዳዩን ያራግባሉ።

የውጪ ጠላቶች ኢትዮጵያ ነጻነቷን የምታስቀድም አገር መሆኗ፤ ሌሎች አገሮችም የእርሷን ፈለግ እየተከተሉ ለነጭ ትዕዛዝ ተገዢ አንሆንም ይላሉ፤ የሚል ስጋት እንዳለባቸው ባለመረዳት፤ ልክ የውጪው ዓለም በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብት እንደሚቆረቆር ሲገልጽ እርሱን ተከትለው የሚያስተጋቡ ብዙ ናቸው።

የውጪ ጠላቶች ዋናው ዓላማቸው እንደፈለጉ እያጭበረበሩ ለመዝረፍ፣ የባህል ወረራ ለማካሔድ ተፅዕኖ ለመፍጠር፤ በዴሞክራሲ ሳይሆን በማስገደድ በተዘዋዋሪ ብድር በመከልከል ኢትዮጵያ ዘለዓለም ከተረጂነት እንዳትላቀቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። የሚሠሩት ሥራ ለሕዝብ የሚደግፉ መስለው ሕዝብን ችግር፤ ቅራኔ ውስጥ የሚከቱ፤ አንዱ ከሌላው ጋር ያለውን ልዩነት በማጉላት የጠላትነት ስሜት እንዲሰማ የሚያደርጉ ናቸው። በዚህ በኩል የሕዝቡም ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ እየተሳካላቸው ነው። ›› ሲል ተናገረ።

ዘውዴ ደግሞ፤ ‹‹ሕዝብ የሚፈልገው በሰላም በአንድነት ኖሮ የአገሩን ሰላም እና ልማት ስኬታማ ማድረግ ነው። ከጥቂት ስግብግብ ቡድን በስተቀር የትኛውም ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል። ሰላምን የማይፈልገው የተወሰነ ቡድን ነው። በአብዛኛው የቡድን ዓላማ ደግሞ ስግብግብነት ነው። በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ሲስገበገቡ በአገር ውስጥ ዘላቂ ጦርነት እንዲኖር ወይም ዜጎች ተወልደው አድገው የመሞቻ ቀናቸው እስኪደርስ በስጋት ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጉ አሉ። ያለፈ ታሪክን እንደምክንያት እያነሱ መባላት አስፈላጊ ካለመሆኑም ባሻገር ካለመሰልጠንም በላይ ከኋላቀርነት ወለል ትንሽ እንኳ ከፍ አለማለትን የሚያሳይ ነው። ›› አለ።

በመጨረሻም ተሰማ፡ ‹‹በተናጠል መልካም ነገር ማሰብ ጥሩ ቢሆንም በጋራ ማሰብ የተሻለ ነው። የአገር ስኬት እንዲረጋገጥ እና ጠላት እንዲያፍር በጋራ መቆም ይበጃል። በእርግጥ የአገር የሃብት ምንጮችን የግለሰብ እስከ ማድረግ የዘለቀ ስግብግብነት ሊኖር ይችላል። የለም ብሎ መከራከር ያዳግታል። ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ እስከመስጠት የዘለቀ ስግብግብነት አለ። የተለያዩ ግለሰቦች ጉዳዩን እንደስህተት ባለመቁጠር በተለያየ መልኩ የአገር እንቅፋት የሚሆኑበት ሁኔታም ያጋጥማል። ነገር ግን ይህንን በመረዳት ግለሰቡ ስህተት ላይ እየወደቀ መሆኑን ከመግለፅ ባሻገር በጋራ አገርን ጉዳት ላይ የሚጥል ተግባር እንዳይፈፀም እስከመጨረሻው መፍጨርጨር ያስፈልጋል።

መፍጨርጨሩ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ለብቻ ሆኖ ሳይሆን እንደአገር ሁላችንም የምንስማማበትን ግብ በማስቀመጥ ሊሆን ይግባል። በእርግጥም ማንም የበላይ ማንም የበታች መሆን የለበትም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ነው። ነገር ግን መታወቅ ያለበት፤ የኢትዮጵያን እጅግ ለመጠምዘዝ የሚሹ ትልልቅ ጠላቶች አሉን። ጠላቶቻችንን ማሸነፍ የምንችለው በግልፅ በመወያየት እና በመደጋገፍ ብቻ ነው›› አለ።

ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ከፈቀዳችሁልኝ በግልፅ ካወራን እና ከግልፅ ውይይቱ በኋላ በእውነት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማግኘት ከተጀመረ የምንለው ብዙ አለን። በእውነትም ምንም ያህል ትልልቅ ቢሆኑም የውጪ ጠላቶችን ማሸነፍ አያዳግተንም። ነገር ግን ለእዚህ መሠረቱ ስግብግብነት ሳይሆን አስተዋይነት እና ተነጋግሮ መተማመን ነው። አብሮ ለመዝለቅ በአንድነት ለማደግ መፍትሔው በብልሃት ህዝብን መምራት እና ለሁሉም እኩል መሆን ሕግን ማስከበር መቻል ነው። ›› ብሎ ወደ ቤቱ ለመሔድ ተነሳ።

 ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *