ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒና በወንዶች የማራቶን ውድድር በርካታ ሜዳሊያዎችን መቀዳጀት ችላለች፡፡ እአአ በ1983 በፊላንዷ ሄልሲንኪ በአትሌት ከበደ ባልቻ የብር ሜዳለያ የጀመረው የድል ጉዞዋ በኦሪገኑ ቻምፒዮና በአትሌት ታምራት ቶላና ሞስነት ገረመው የተመዘገቡትን 1 የወርቅ እና የብር ሜዳለያዎችን ጨምሮ፤ በመድረኩ 12 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች፡፡ በዚህም በደረጃ ሰንጠረዡ በኬንያ እና ስፔን ብቻ ተበልጣ ሶስተኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በፈር ቀዳጁ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ ሌሊሳ ዴሲሳ እና ታምራት ቶላ የተመዘገቡትን ሶስት የወርቅ ጨምሮ ስድስት የብር እና ሶስት የነሃስ ሜዳሊያዎችን በወንዶች ማሳካት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በመድረኩ የለመደችውን ድል ለማስቀጠል ከተፎካካሪ ሀገራት ቀላል የሚባል ፈተና አይጠብቃትም፡፡ በ19ኛው የቡዳፔስት ዓለም ቻምፒዮናም ፈታኝ በሆነው ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያውን ላለማስነጠቅ የምትካፈል ይሆናል ፡፡
ተሰባስቦ ዝግጅቱን ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ የሆነው ቡድኑ በተለያዩ ቦታዎች ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ወቅት በቡዳፔስት ያለው አየር ሞቀታማ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ክረምት በመሆኑ ተጽዕኖ ቢፈጥርም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በአቃቂ፣ በእንጦጦ እና ሰንዳፋ ከፍታ ቦታዎች ዝግጅቱ እየተከናወነ ነው፡፡ አትሌቶች በርቀቱ ተደጋግመው የተመዘገቡትን ድሎች ለማስቀጠል ሁኔታዎች ምቹ ባይሆኑም ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ በብርቱ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ርቀቱን በበላይነት ያጠናቅቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሀገራት ግንባር ቀደም ተገማች ሃገር ናት፡፡ ለአሸናፊነት የቅድመ ግምት እንድታገኝ ያደረጓት ደግሞ በቡድኗ ውስጥ ያካተተቻቸው እጅግ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ ላይ የሚገኙ አትሌቶቿ ናቸው፡፡ የቡድኑ ስብስብ አስፈሪ ከመሆኑ ባለፈ ከፍተኛ ልምድ ባላቸውና ስኬታማ በሆኑ የማራቶን አሰልጣኞች ታክቲክ ታግዞ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ አምና ኦሪገን ላይ በአትሌት ታምራት ቶላ የተመዘገበው የወርቅ እንዲሁም በአትሌት ሞስነት ገረመው የተመዘገበው የብር ሜዳሊያ በቡዳፔስትም እንደሚደገም አያጠራጥርም፡፡ ፈጣን ሰዓት ያዝመዘገቡትን አትሌቶች ያካተተው ብሄራዊ ቡድኑ እአአ የ2018ቱ የዱባይ ማራቶን አሸናፊና የፈጣን ሰዓት ባለቤቱን ልዑል ገብረስላሴ፣ ጸጋዬ ጌታቸው፣ ጫሉ ዴሶ፣ ሰይፉ ቱራ መሃመድ ኢሳ እንዲሁም ቻምፒዮኑ ታምራት ቶላ ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች ሰዓት ያላቸው በመሆኑ ኢትዮጵያ በመድረኩ ውጤታማ ከሚሆኑ ሀገራት ቅድመ ግምቱን እንድታገኝ አድርጓታል፡፡
እአአ በ2020 የቫሌንሺያ ማራቶን የፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው አትሌት ጫሉ ዴሶም ካለው ጠንካራ የቡድን ስብስብና ዝግጅት በመነሳት ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየቱን አንጸባርቋል፡፡ አትሌቱ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበረው ቆይታ ለዓለም ቻምፒዮናው በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጁ እንደሚገኙም ያስረዳል፡፡ በቡድን ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ አትሌቶቹ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙና ሙሉ ጤንነት ላይ በመሆናቸው የተሻለ ውጤት ይመዘገባል፡፡ የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን በፍቅርና በቡድን መንፈስ ከማድረግ ባለፈ፤ በአጠቃላይ ዝግጅቱ በአሰልጣኝ ቡድኑና በአትሌቶች መካከል በሞራልና በከፍተኛ ተነሳሽነት በመታገዝ በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠል ችሏል፡፡ አምና የመጣው ውጤት አስደሳች ሲሆን ዘንድሮም ካለው ጠንካራ ስብስብና እየተደረገ ካለው ዝግጅት አንጻር ቻምፒዮናነቱን ማስጠበቅ ይቻላል፡፡ ለዚህም አሰልጣኞች ተስማሚውን የአየር ሁኔታን በመከተል ጠንካራ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የውድድር ስፍራ ከፍተኛ ሙቀትን እያስተናገደ ቢሆንም ተቋቁሞ ለድል እንደሚበቁ እምነቱንም አያይዞ ገልጿል፡፡
በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒና በማራቶን ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ ያስገኘው እና የ2021 የአምስተርዳም ማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው አትሌት ታምራት ቶላ በማራቶኑ በቀጥታ ተሳታፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዓለም ቻምፒዮናው በኋላ በበርካታ ውድድሮች የተካፈለው አትሌቱ፤ በቫሌንሺያ ማራቶን 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ እንዲሁም በለንደን 2 ሰዓት ከ04 መሮጡን ይጠቅሳል፡፡ ለቡዳፔስቱ ቻምፒዮናም በጥሩ ዝግጅት ላይ እንደሆነና ሰውነቱም ለውድድሩ ብቁና ጤነኛ በመሆኑ ጥሩ ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን ጥረቱን እንደሚቀጥልም ተናግሯል፡፡
የማራቶን ቡድን አሰልጣኙ ሃጂ አዴሎ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተፎካካሪ ኬንያ መሆኗን ጠቅሰው፤ ብሄራዊ ቡድኑ አሉ የተባሉትን አትሌቶች በማካተቱ በውድድሩ ላይ በቡድን እርስ በእርስ በመነጋገርና በመግባባት ከአምናው የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015