የወቅቱ ፍቱን ህክምና – ወይባ

የሴት ልጅ ውበት ውስጣዊና ውጫዊ በማለት በሁለት ተከፍሎ ሊገለጽ ይችላል። ውስጣዊ የሚባለው የሴት ልጅ ውበት አመለካከቷን፣ መልካምነቷን፣ ፀባይዋን እንዲሁም እራሷን የምታከብር ሴት መሆንዋን የሚገልጽ ሲሆን ፤ የሴትን ልጅ ውጫዊ ገፅታዋ ደግሞ አይኗ፣ አፍንጫዋ፣ ጥርሷ፣ ፀጉሯና በአጠቃላይ ተክለ ሰውነቷን በመመልከት መግለጽ ይቻላል።

ሴት ልጅ የውበቷን ዘውድ ከምታሳይበት መካከል ፀጉሯ አይኗ ጥርሷ በጠቅላላው ተክለ ሰውነቷ መሆኑ አያጠያይቅም። ለምሳሌ የተዘናፈለ ዞማ ፀጉር በማንም ዓይን ውስጥ ገብቶ አድናቆትን ያሰጣል።

ይህን የተረዱ ብዛት ያላቸው ሴቶች የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ከፀጉራቸው ጀምሮ መላ ሰውነታቸውን ውብና ሳቢ እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ያስውባሉ። በሰዎችም ዘንድ ማራኪና ውብ እንደሚያደርጋቸው ያመኑትን የውበት መጠበቂያ በሙሉ ይጠቀማሉ።

በድሮ ጊዜ ሴቶች ቅቤና አደስ እየተቀቡ በባህላዊ መንገድ የራሳቸውን ውበት ይንከባከቡ ነበር። እንደ ሴቶቹ ዕድሜ ክልል መሠረት የተለያዩ ሽሩባዎችን በመሰራት ጌጣጎጦችንም በማድረግ ያገቡና ያላገቡ እንደሆኑ የሚለዩበት ባህላዊ መንገድም ነበራቸው። በተጨማሪ እነዚህን አጋጣሚዎች በመጠቀምም ውብ ሆኖ ለመታየት ብዙ ጥረቶች ያደርጉም ነበር።

በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ፀጉራቸውን ቅቤ እየተቀቡ የተለያዩ ባህላዊ ውበት መጠበቂያዎችን እየተጠቀሙ ራሳቸውን የሚንከባከቡ ሴቶች ቢኖሩም፣ በከተሞች ውስጥ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ባህላዊውን የውበት መጠበቂያ ተግባራዊ የሚያደርጉት ዝቅተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው ሴቶች ናቸው። አሁን ባለንበት ዘመን ሴቶች የተለያዩ ባህላዊውን በተሻለ መልኩ አሳድገው ብልሃቶችን በመጠቀም ራሳቸውን ማስዋብ ጀምረዋል።

ዘመን የወለዳቸውን ሰው ሠራሽ ቅባቶችና የመዋቢያ ምርቶችን በመጠቀም ጸጉርን ማሳመር ፊትን ማስዋብ እግርና እጅን በተለያዩ መንገዶች አሰርቶ መታየት የተለማመደ ድርጊት ከሆነ ሰነባብቷል። ሴቶች እነዚህን ሰው ሰራሽ መዋቢያዎችን መጠቀማቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ለማስዋቢያዎቹ የሚያወጡት ገንዘብ ጊዜ እንዲሁም መዋቢያዊቹ ከቆይታ ብዛት የሚያደርሱት የጎንዮሽ ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።

ዘመናዊ በሆነ መንገድ ራስን መንከባከብና ማስዋብ ችግር ያለው ባይሆንም፤ ነገር ግን ወጪው ከዛም ደግሞ በመዋቢያዎቹ ቁጥጥር ስር በመውደቅ በራስ የመተማመን ስሜትን መቀነሱ ደግሞ ከዘመናዊዎቹ የውበት መጠበቂያ ግብዓቶች ላይ ያለ የጎንዮሽ ጉዳት ስለመሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ።

በተቃራኒው በተፈጥሯዊው መንገድ ፀጉራቸውንም ሆነ መላ ሰውነታቸውን የሚንከባከቡ ሰዎች ያን ያህል ለዘመናዊው ማስዋቢያ ጥገኛ የማይሆኑ ከመሆኑም በላይ በኢኮኖሚም በሥነ ልቦና ረገድም ጠንከር ያሉ ሆነው ይታያሉ። ተፈጥሮ በሰጣቸው ኮርተው በራሳቸው ተማምነው ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ደግሞ ተፈጥሯዊ በሆነው መንገድ ያስውባሉ ፤ በተለያየ መንገድም ተፈጥሯዊ ውህዶችን ይጠቀማሉ።

ከሁሉም በላይ ግን ሰው ሠራሽ የመዋቢያ ምርቶችን አዘውትሮ መጠቀም ተጓዳኝ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል ሴቶች በተቻላቸው አቅም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ውበት በተፈጥሯዊ መንገዱ በእንክብካቤ በመያዝ ቢጠብቁት ተመራጭ ነው።

ነገር ግን የግድ ዘመን የወለዳቸውን ማስዋቢያዎች መጠቀም እንዳለባቸው የሚያምኑ ሴቶች በሚጠቀሙበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ከመሆኑም በላይ የሚገዟቸው መዋቢያዎች ይዘት፣ ምርቱ የመጠቀሚያ ጊዜው የሚያበቃበትን በደንብ መመልከት አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል፣ ሴቶች ለውበት መጠበቂያነት የሚያወጡት ወጪ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባዋል።

ወይዘሮ ፋና ኤጀሬ የፋና ወይባ ጢስና ስፓ ባለቤት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ውብ ሆኖ መታየትን የማይፈልግ የለም። ነገር ግን ውበት ከጤና ጋር ሲሆን ደግሞ ጥቅሙ የጎላ ይሆናል። በተለይ እርሳቸው የሚሰሩት የወይባ ጢስ ሴቶች ላይ ለሚከሰቱ በርካታ ተፈጥሯዊና ዘመን አመጣሽ ህመሞች ፍቱን ነው።

በፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ ገና በ16 ዓመት ታዳጊነታቸው በሙዚቀኝነት ሥራን የጀመሩት ወይዘሮ ፋና፤ ለጥቂት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ ሲኒማ ራስ በመሄድ በተወዛዋዥነት ሥራቸውን ቀጠሉ። በሥራቸው ትጉህ በመሆናቸው በዛም ሳይወሰኑ ለውጥን አብዝተው የሚፈልጉ ስለነበሩ፤ ቀን በከፈቱት ጸጉር ቤት እየሰሩ ማታ ማታ ደግሞ በምሽት ጭፈራ ቤቶች ውስጥ በሙያቸው ሲያገለግሉ ቆዩ። በኋላም የተሻለ የሥራ እድል በማግኘታቸው በዳንሰኝነት ሙያ ተቀጥረው ወደ አረብ አገር መሄዳቸውን ወይዘሮ ፋና ይናገራሉ።

“ውብ ሆኖ መገኘት አንዳንዶች እንደሚሉት ሴትነትን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን በራስ መተማመንን የሚያጎለብት ነው። አስፈላጊነቱ ላይ ከባህል ባህል የተለያየ አመለካከት ቢኖርም፣ ውብ መሆንን የሚጠላ፣ እንዲሁም የሚያምርን መመልከት የማይወድ የለም” ይላሉ ወይዘሮ ፋና የጅሬ።

ወይባ ከጥንት ጀምሮ በተለይም በወሎ አካባቢ እናቶች አራስነታቸውን ሲጨርሱ ከዛም በኋላ ውበታቸውን ጠብቆ ለማቆየት በቤታቸው አዘጋጅተው የሚሞቁት ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው የውበትና የጤና መጠበቂያ ነው የሚሉት ወይዘሮ ፋና፤ እርሳቸውም ይህንን ባህላዊ የውበት መጠበቂያ ጥራቱንና ተፈጥሯዊነቱን በጠበቀ መልኩ እየሰሩበት ለብዙዎችም ከውበት ባሻገር ብዙ ጤናዊ ጥቅሞችን እየሰጠ ስለመሆኑ ያብራራሉ።

ወይባ በተለያዩ ቦታዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል አስታውሰው፤ እርሳቸው ግን በተቻለ መጠን ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንዳይለቅ ከፍ ያለ ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን ይናገራሉ። እንደወይዘሮ ፋና ገለፃ፤ ወይባ ለሴት ልጅ ለማህጸን ህመም፣ ለዲስክ መንሸራተት፣ አላስፈላጊ የማህጸን ፈሳሾችን ለማስቀረት ፣ ለወገብ ቁርጥማት ለጉንፋን በጠቅላላው ለተለያዩ የጤና ችግሮች መፍትሔ ነው። ይህ በሚያስጠቅሟቸው ሰዎች ላይ ያዩት እውነታ ነው።

ወይባ ይህንን ሁሉ የጤና በረከት ለማስገኘቱ አንዱና ትልቁ ምክንያት ጥቅም ላይ የሚውሉት ስራስሮች በርካታ መሆናቸው ነው የሚሉት ወይዘሮ ፋና፤ ለምሳሌ ክትክታ ፣ ግዛዋ፣ ምስር እጅ፣ የወይባ እንጨት ፣ ደደሆ ፣ የሬት ስር ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ስራስሮች በተጨማሪ ለማህጸን ጤና ሲባል ሸብ ፣ ከርቤ እና ሌሎችም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ወይባ ለጤና ጠቀሜታ አለው ሲባል ማህጸኗን የታመመች አልያም ዲስኳ የተንሸራተተ ሴት ብቻ ትጠቀመዋለች ማለት አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ፋና፤ ህመም የሌለባቸው ሴቶች ሲጠቀሙት አስቀድሞ በሽታውን ይከላከልላቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የደከሙ የማህጸን ሴሎችን በማነቃቃት ጤነኝነታቸውን የሚጨምር መሆኑን ተናግረዋል።

እንደወይዘሮ ፋና ገለፃ፤ ወይባ መሞቅ ለጤና ያለው በረከት ከፍ ያለ ነው፤ በተጨማሪ ውበትም አብሮ መጠበቅ ስላላበት ወይባ የተጠቀመችን ሴት ሰውነት ማርና ቅቤ በመቀባት ሙቀት ውስጥ (ቦዲ ስቲም) እንድትቆይ ይደረጋል። በፋና ወይባ የተለያዩ ጥራጥሬዎችን በማዘጋጀት ከሙቀቱ ወጥታ ሰውነቷ ይታሻል፤ ከዛም ሰውነትን በመታጠብ ማርና የቡና ዱቄት በመቀባት እየታሸ በላስቲክ ተጠቅልላ ለተወሰነ ሰዓት እንድታርፍ ይሆናል። ይህ ምንም ዓይነት ዘመን አመጣሽ መዋቢያን ሳይፈልጉ ለመዋብ የሚያስችል ነው።

ወይባን መጠቀም ውስጥንም ውጪንም ለማጽዳትና ለማስዋብ አይነተኛ መንገድ ነው። ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው ከመሆኑ አንጻር ደግሞ ማንኛዋም ሴት በሳምንት ፣ በ15 ቀን አልያም በወር መጠቀሙ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ስለመሆኑን ያብራራሉ።

“በወር አበባ ፣ በግንኙነት ምክንያት በማህጸን ውስጥ የሚደክሙ ሴሎች አሉ ፤ በዚህም በአንዳንድ ሴቶች ላይ የማሳከክና የህመም ስሜት ይኖራል። በህክምናው የሚሰጡ መድሃኒቶችም አሉ። ነገር ግን እነዚህ መድሃኒቶች ውጫዊውን ክፍል ያጸዱ ይሆናል እንጂ፤ እንደወይባ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የማጽዳት አቅማቸው በጣም ውስን ነው። በመሆኑም ወይባ ለሴት ልጅ ወሳኝና በጣም አስፈላጊ ነው ብል ማጋነን አይሆንም” ይላሉ።

ፋና ወይባ ጢስና ስፓ ለሶስት ሠራተኞች የሥራ እድልን የፈጠረ ሲሆን፤ ወይዘሮ ፋናም አብረዋቸው እየሠሩ ሲሆን፤ በተጨማሪ የሚያሳድጓቸውን ሁለት ልጆች ጨምረው ሥራውን በጥራት እያከናወኑ ነው። ‹‹ከዚህ በላይ ሠራተኛ እንደሚያስፈልገኝ አውቃለሁ።›› የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ነገር ግን ቤቱ ጠባብ በመሆኑ ወይባ ደግሞ መጨናነቅ እና የሰው ብዛት የማይፈልግና የተረጋጋ አየር በአግባቡ የሚንቀሳቀስበት ሊሆን ስለሚገባ፤ የሠራተኞቻቸውን ቁጥር ያሳነሱት ከዚህ አንጻር መሆኑን ያብራራሉ።

ወይባ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው፤ ለብዙ ሴቶች የጤናና የውበት በረከትን እያመጣ ያለ ስለመሆኑ ይነገራል። ወይዘሮ ፋናም ወደፊት ከዚህ በተሻለ መልኩ ወሎ ላይ እንደሚሰራው ሁሉ ሴቶች ወይባውን እየተጠቀሙ ሶስትና ከዛ በላይ ቀናትን ሳይወጡ በሚገባ ጥቅሙን ወስደው ከህመማቸው ተፈውሰው እንዲወጡ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ።

“….ማንኛዋም ሴት እድሜ ሳይገድባት ወይባን መጠቀም ትችላለች ፤ አለባትም። ከላይ እንዳልነው ወይባ ለማህጸን፣ ለወገብ ህመምና ለጭንቀት ፍቱን ነው። ለምሳሌ የድሮ እናቶች 12 ልጅ አምጠው ወልደው ያለ አጋዥ አሳድገው ወገቤን የሚል ቃል አያወጡም። ምክንያቱም ጤናና ውበታቸውን የሚንከባከቡት በተፈጥሯዊ ግብዓቶችና መንገድ በመሆኑ ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ ዘመን አመጣሽ መዋቢያዎች እንዲሁም ምግቦች ያመጡብንና እያማጡብን ያለውን ጣጣ እያየን ነው። በመሆኑም እንደ ድሮ እናቶቻችንን ተፈጥሯዊውን መንገድ ተጠቅመን ጤናችንን እንጠብቅ” በማለት ወይዘሮ ፋና መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ወይዘሮ ሄለን ጌታቸው የሶሰት ልጆች እናት ናቸው። በተለይም ሁለተኛ ልጃቸውን ከወለዱ በኋላ ከፍ ያለ የወገብ ህመም ሲያሰቃያቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ብዙ ህክምናዎችን ቢያደርጉም ከጊዜያዊ ህመም ማስታገሻነት በላይ ግን መፍትሔ ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋል።

እንደወይዘሮ ሄለን ገለጻ፤ ሰዎች ለምን ወይባ አትጠቀሚም? ሲሏቸው ያን ያህል ትኩረት ሳይሰጡት ቢቆዩም የህመሙ ሁኔታ በጣም እየጨመረ ሲመጣና መንቀሳቀስ ሲከለክላቸው የተመከሩትን የወይባ ጢስ በተደጋጋሚ በመግባት አሁን ላይ ከህመማቸው ስለመዳናቸው ያብራራሉ።

“ሴቶች ከልጅነታችን ጀምሮ በብዙ ጫና ውስጥ የማለፍ ግዴታ አለብን። ከዛም ከፍ ካልን በኋላ የወር አበባ ያደክመናል። ማርገዝ፣ መውለድ፣ ማጥባት፣ የቤተሰብ ሃላፊነት፣ ልጆች መንከባከብ ብቻ አብዛኛው ነገር የእኛ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ ሰውነት ይዝላል፤ ሴሎች ይሞታሉ ፤ አቅም ይጠፋል ጤና ይዛባል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በተለይም እንደ ወይባ ጢስ ያሉ ተፈጥሯዊ የጤና በረከቶችን ማግኘት ያለእድሜ ከመሰናከል ያድናል” በማለት ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።

እኛም ቦሌ መንገድ ራማዳ ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ፋና የወይባ ጢስና ስፓ የተመለከትነው ይህንኑ ነው። ሴቶች ከተለያዩ ችግሮቻቸው ለመፈወስ እግረ መንገዳቸውንም ውበታቸውን ለመጠበቅ በብዛት ይመጣሉ። በዚህም ጥቅሙ ላቅ ያለ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። እናም በዘመን አመጣሽ የውበት መጠበቂያዎች ራሳችንን ከማበላሸት በኢኮኖሚም ከፍ ያለ ጉዳት ውስጥ ከመግባታችንና የሰው ሰራሽ መዋቢያዎች ጥገኛ ሆነን በራስ መተማመናችንን ከማጣታችን በፊት፤ አገርኛ ባህሎቻችንን እያሳደግን እየተጠቀምንባቸው ተተኪ ባለሙያዎችንም እያፈራን መሄዱ ለእኛነታችን የሚኖረው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *