የነፍሴ ሁለት ሴት

ልባም ሴት ሁለት ቦታ ትፈጠራለች ‹ምድር ላይ እና በባሏ ልብ ውስጥ› የሚል ከማን እንዳገኘሁት የማላውቀው የልጅነት እውቀት አለኝ። ልክ እንደ ርብቃ አንዳንድ ሴቶች ብዙ ናቸው.. እልፍ መዓት። በወንድ ነፍስ ውስጥ የትም የሚገኙ..። ርብቃ በእኔ ውስጥ የሌለችበት የለም። እንደዚህ አንሼ እንደዛ መብዛቷ፣ በማይመጥናት ወንድነቴ ውስጥ ተርፋ መኖሯ የምንግዜም መደነቂያዬ ነው። አንዳንድ እለቶች እስከሕይወት ፍጻሜ የሚዘልቁ ናቸው። ስንሞት የሚሞቱ..። ከርብቃ ጋር የነበረኝ ታሪክ እንዲህ ነው። እስካለሁ ኖሮ ስሞት አብሮኝ የሚሞት።

አንዳንድ መጀመሪያዎች እጣፈንታዎቻችን ናቸው.. መጨረሻችንን የሚወስኑ። ከርብቃ ጋር ስንተያይ መጨረሻችን እንዲህ ይሆናል ብለን ሁለታችንም አላሰብንም ነበር። መጀመሪያ ሳያት ቁንጅናዋን ከማድነቅ የዘለለ አተያይ አልነበረም። ግን እንደሀሳቤ የሆነ ምንም አልነበረም። ከዓይኗ ማሕጸን ውስጥ የሚወጣ የሆነ ጨረር አለ። የምታየውን ሁሉ በፍቅር የሚመታ። ነገር በዓይን ይገባል እንደሚባለው በፍቅሯ እንደምወድቅ ከእኔ ቀድማ እሷ ነበር ያወቀችው። አይታው በፍቅሯ ያልወደቀ ወንድ እንደሌለ ያወኩት በራሴ ነው..ምንም የማይጥለውን ወንድነቴን ስትጥለው።

ርብቃ የሕይወቴ ሁለት ነፍስ ናት።

የእየሱስን ስም ጠርቼ የምምልበት ብዙ ነገር አላት.. ርብቃ ስታይ ታምራለች። ስትናገር፣ ስትስቅ ታምራለች። ዓይን አፍንጫዋ ያምራል። ከንፈር ጥርሷ ሌላ ነው። ሰውነቷ ያምራል። አለባበሷ ያስደንቃል። ዘመነኛ ሴት ናት። ዝምታዋ ግን ያስጨንቃል። ዝም ስትል ልትፈርስ የምትንገዳገድ ነው የሚመስለኝ። ከዝምታ ሌላ ሁሉ የሚያምርባት ሴት ናት። ዓይኖቿ ቡዝዝ ብለው ዓይን ላይ ሲያርፉ መከራ ይንዳሉ። ላያትም ሆነ ለሚያያት ሰው ተንቀሳቃሽ ገነት ናት።

አንዳንድ መተያየቶች አሉ..ከዛሬ ወደነገ የሚሄዱ። በነፍስ ሰሌዳ ላይ ታትመው ትላንትን፣ ድሮን፣ አምናም የሚመልሱ። አንዳንድ ግጥምጥሞሾች አሉ..በትንሽ ዓለም ውስጥ ትልቅ ትዝታ ሆነው የሚቀመጡ። በምንም የማይደበዝዙ የሰውነት

 ድምቀትና ውበት። አንዳንድ መተያየቶች በምንም የማይሽር የትዝታ ቁስልን ነፍስ ላይ ይጥላሉ። ልክ እንደዚህ ከአፍታ ረቀው ዘላለም የሚመስሉ አንዳንድ ዝምታዎች አሉ። ነፍስን እንዳልነበረች የሚያደርጉ። ርብቃም እንዲህ ናት.. ታወራ..ታወራ እና ዝም የምትለው የሆነ ዝምታ አላት። እኔን ወደአለመኖር የሚወስድ፣ ለድባቴ የሚጥል ዝምታ። የእሷን ዝምታ እንደሰጋሁት ምንም ነገር ሰግቼ አላውም። ዝምታዋ ያሰጋኛል። ዝም ስትል እፈራለሁ። እናም እንዲህ እላታለሁ ‹የአንቺ የአንድ ሰከንድ ዝምታ የእኔ የእድሜ ልክ ስቃይ ነው እናም እባክሽ ዝም አትበይ›። በዚህ ጊዜ ትስቃለች። ከዝምታዋ ውስጥ የሚወጣ የሆነ እልልታ አለ። በፈገግታ ጀምሮ በሳቅ የሚያበቃ እልልታ።

በልቤ ብራና ላይ በወርቅ ቀለም የተጻፉ አንድ ሴትና አንድ ስም አለ። ርብቃና ርብቃ የሚል። በሕይወቴ ሆነልኝ ብዬ በኩራት የምናገረው እሷ ያለችበትን ማንነቴን ነው። በመተያየት ጀምሮ በምንም የማያበቃ አልፋና ኦሜጋ ፍቅር አለን። ወንድ እንደ ሰው የሚቆጠረው ሚስቴ የሚላት ሴት ስትኖረው እንደሆነ በቅርብ ነው የገባኝ። ሴት ወንድን ትሠራለች።

ወንድነት የሚያልቀው ሴትነት ውስጥ ነው። ትዳር ለወንዶች መጠናቀቂያ ነው፣ ለሴቶች ደግሞ የፍጹምና መጀመሪያ። ትዳርን የሚፈሩ ወንዶች ሁሌም፣ መቼም ጡጦ እንደሚጠባ ሕጻን ጨቅላ ናቸው። እናቶቻችን ይጀምሩናል ሚስቶቻችን ይጨርሱናል። ወንድነት መጀመሪያውም መጨረሻውም ሴትነት ውስጥ ነው። ሴትነት የወንድነት ማብቂያ ነው። እንዲህ የሚል መጽሐፍ ልጽፍ እየተሰናዳሁ ነው።

ምድር የማትረሳኝ በሚስቴ በኩል ባደረገችልኝ ውለታ ነው። ሚስቴ የመልካም ነገር ሁሉ መጀመሪያ ናት። የማረባው ሰው በእሷ ፊት ነው የምደምቀው። በእሷ ዓይኖች ውስጥ ብቻ ነው ራሴ ባለሞገስ ሆኖ የሚታየኝ። ርብቃ ሚስት ለመሆን ብቻ እንደተፈጠረች የምናውቅ እኔ እና የፈጠራት ብቻ ነን።

ዓይን የፍቅር ማሕጸን ነው..ፍቅር አድጎ የሚጎለምስበት። እንደ ዓይን ፍቅር ቦታ የለውም። እናም አይታ ፍቅር ላይ ከጣለችኝ ከዛ በኋላም ባለው ንግግራችን እንደ ርብቃ የተረዳኋት ሴት የለችም። አንድ ቀን የእኔ የአንተ መባባል

 በጀመርንበት ማግስት ጠዋት ላይ ለአራሷ ጀምበር ጀርባዬን ሰጥቼ ፊቷ ቆምኩ። በነዛ ሲያዩ በሚያምሩት ዓይኖቿ ፊት። እንደእስከዛሬዬ አፈቅርሻለሁ ሊለኝ ነው ብላ ስትጠብቅ ‹እናትና ሚስት ነው የምፈልገው፣ እናትና ሚስት መሆን ትችያለሽ? አልኳት።

‹አንተ አባትና ባል ለመሆን ዝግጁ ነህ? ስትል ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰችልኝ።

‹ከዛም አልፎ የሚሄድ አቅም አለኝ። የምኖረው ለራሴና ከእኔ በእኔ ለእኔ ለመጡ ነፍሶች ነው። ጊዜዬ እንዲያልፍ የምፈልገው ሚስቴ ከምትሆን ሴት ጋር ብቻ ነው። እንደዚህ አይነት ሴት ካልሆንሽ አሁኑኑ መወሰን እችላለሁ› እንዲህ ስላት ያስቆጣኋት ይመስለኛል። ስትቆጣ እኔ ብቻ ነው የማውቅላት። ስትቆጣ ካስቆጣት ሰው ፊት ላይ አይኖቿን ታሸሻለች። ዓይኖቿን ከዓይኖቼ ላይ አሽሽታ በትከሻዬ በኩል ሰቀለቻቸው። እሷ ፊት እንዲህ በድፍረት ተናግሬ አላውቅም። በትክክልም ለእሷ አይነት ሴት ንግግሬ የሚያስቆጣ ነበር።

ዝም አለች..የሚያሰጋ ዝምታዋን።

ሆን ብዬ ነበር እንዲያ የተናገርኳት። የፍቅሯን እንጂ የትዕግስቷን ልኬት አላውቀውም። ስትቆጣ ምን እንደምትመስል ላያት እፈልጋለሁ። ቁጣዋን ዝምታዋ ውስጥ ደብቃ ዝም አለችኝ።

‹ሳታውቀኝ ነበር የቀረብከኝ? ሳታወቀኝ ነበር እንደምታፈቅረኝ ስትነግረኝ የነበረው? ሳታውቀኝ ነበር እንደምታውቀኝ ስታስመስል የከረምከው? ሳትረዳኝ ነበር ለሚስትነት ያዘጋጀኸኝ? ስትል በል ንገረኝ በሚመስል እቴጌያዊ ኩስተራ ዓይኖቿን ከሄዱበት መልሳ አፈጠጠችብኝ።

እጄን ሰድጄ እጆቿን ጨበጥኳቸው። ትመነጭቀኛለች ብዬ ስፈራ ዝም አለችኝ። ‹አንቺ ከሚስትነት ውጪ ለምንም አልተፈጠርሽም። እንዳንቺ የገባችኝና የተረዳኋት ሴት የለችም› አልኳት የእውነቴን።

‹ታዲያ..!

ምን ልትለኝ እንደሆነ ስለገባኝ ‹ፍቅርሽን ብቻ እኮ ነው የማውቀው። ከፍቅር ውጪ ያለችውን ርብቃ አላውቃትም። ላውቅሽ ስል እንደማላውቅሽ ሆንኩ› አልኩኝ።

በዝምታዋ ውስጥ ጥርሷን አየሁት። ፈገግታና ሳቅ የቀላቀለ ዘምቶ የፈካ ስሜቷን።

‹እና እስካሁን የተናገርከው ውሸትህን ነው ማለት ነው?

‹አዎ ውሸቴን ነው። አንቺ ከሚስትነት ውጪ ለምንም አልተፈጠርሽም አልኩሽ እኮ› ስል አቀፍኳት።

‹እኔ ደግሞ አላገባሽም ልትለኝ መስሎኝ ራሴን ከፎቅ ላይ ልፈጠፍጥ እያሰብኩ ነበር› አለችኝ እቅፌ ውስጥ ሆና።

‹አንቺ በብዙ ፍለጋ የተገኘሽ የሕልሜ ፍጻሜ ነሽ። ከእኔ ስትለይ ሊቀበሉሽ የተዘረጉ ብዙ እጆች አሉ። እናም አጥብቄ ነው የያዝኩሽ›

‹ያልከኝን አይነት ወንድ ከሆንክ እዚሁ እንድንጋባ እፈልጋለሁ። የታገባኛለህ ጥያቄ ላቅርብልህ..ልንበርከክ ወይስ?

‹እንድትንበረከኪ አልሻም። ያንቺ የእኔ መሆን ብዙ ትርጉም አለው። ከተንበረከኩም ከተንደባለልኩም እኔ አለሁ። ከሴትነት አልፈው ሚስት መሆን የማይችሉ ሴቶች ናቸው ትዳርን በእንብርክክ የሚሹት። በልብና በአእምሮሽ ካፈቀርሽኝ ይበቃኛል..›።

‹በልብና በአእምሮ ይፈቀራል እንዴ?

‹እሱን ራስሽን ጠይቂ። የምናገረው ሁሉ ካንቺ ያገኘሁትን ነው። እናትና ሚስት፣ አባትና ባል አእምሮና ልብ ውስጥ ነው ያሉት። ከአንዱ ከጎደልን በሁሉም እንጎድላለን። እናትና ሚስት የምትሆኚው በልብና በአእምሮ ስታፈቅሪና ስትፈቀሪ ነው። በልብሽ ሚስት ነሽ በአዕምሮሽ እናት ነሽ።

የምትፈልገው ወንድ ይሄን ነበር። የምታምነውን እንደሚያምን ያልገባት መስላ አረጋግጣለች። እናትና ሚስት ለመሆን በጀመረችው መንገድ ላይ አባትና ባል ሆኖ በመንገዷ መቆሙ ያለጥርጥር እንድትመርጠው አድርጓታል። ያልገባት መስላ ፊቱ መቆሟ እውነቱን ከእምነቱ ጋር ለመውሰድ ነበር። በስተመጨረሻም በመንገዷ ላይ አገኘችው።

‹እኔ ገብቶኝ አንቺ ያልገባሽ ምንም የለም። የነገርኩሽና የምነገርሽ ሁሉ ካንቺ የሰማሁትን እና የተማርኩትን ነው።

ፈገግ አለችለት…

ጀምበር በጀርባው ላይ አልፋ አናቱ ላይ ስትቆም ብዙ ሰዓት እንደቆሙ ገባሁ።

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *