ሁለቱም የ21 ዓመት አፍላ ወጣት ናቸው። የተወለዱት በ1992 ዓ.ም ሲሆን፤ ወጣት ሙሉዓለም ታምሬ ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸኖ ወረዳ ቁንጌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዛው በትውልድ አካባቢው በሚገኝ ኢትሳ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ተከታትሏል።
ወጣት ደረጄ ሠቦቃ ደግሞ ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወላንሳ ወረዳ ነው። ደረጄ በሕፃንነቱ ቤተሰቦቹ በሞት ስለተለዩት የቤተሰቦቹን አደራ ተቀብሎ የሚያሳድገው እና የሚያስተምረው የቅርብ ዘመድ አልነበረውም። በዚህም ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል ለመቅሰም አልታደለም። የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ገና በልጅነቱ በሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት ግድ አለው።
ወጣቶቹ ባደጉበት ቀዬ ሕይወታቸውን ይገፉ ነበር። የሰው ልጅ ኑሮውን ከዛሬ ነገ የተሻለ ለማድረግ ያቅዳል። ያቀደውን ለማሳካት ይጥራል፣ ይወጣል፣ ይወርዳል…። በተመሳሳይ ወጣት ሙሉዓለም እና ደረጄ የተሻለ የሥራ ዕድል አግኝተው ነገ ላይ የተሻለ ሕይወት ለመኖር ያቅዳሉ። ይህንን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ሁለቱም ከየአቅጣጫው ተነስተው በ2009 ዓ.ም የ17 ዓመት አፍላ ወጣት እያሉ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።
በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚመጣውን ሰው አንተ ከየት ነህ? ማን ነህ? ብሔርህ ምንድን ነው? ሳትል ሁሉንም በፍቅር እጇን ዘርግታ የምትቀበለው ሸገር፤ ወጣቶቹንም እጇን ዘርግታ በፍቅር ተቀበለቻቸው። ተቀብላም የእለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ አላሳጣቻቸውም። ሁለቱም እንደመጡ ብሎኬት ማምረቻ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ቀን ብሎኬት በማምረት ማታ ደግሞ በዚሁ ድርጅት በጥበቃ ሠራተኝነት እያገለገሉ በሚያገኙት ገቢ ከትናንት የተሻለ በልተው፣ ለብሰው መኖር ጀመሩ። አራት ዓመታትን በዚህ ሥራ ላይ እንደዋዛ አሳለፉ።
በአራት ዓመት ቆይታቸው በሥራ ቦታቸው ሠርተው ባገኙት ገንዘብ በልተው፣ ጠጥተው፣ ተደስተው ከማደር ውጭ የገጠማቸው የከፋ ችግር አልነበረም። ወጣቶቹ እንደወትሮው ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ20 ገደማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም በተለምዶ ጉልት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የብሎኬት ማምረቻ ድርጅት በጥበቃ ሥራቸው ላይ ነበሩ። የክረምት ወራት በመሆኑ ሰማዩ ጉም አዝሎ ድቅድቅ ያለ ጨለማ ነበር። በተጠቀሰው ቦታና ሰዓት ወጣት ደረጄ የሰው ኮቲ ሰምቶ ሥራ ቦታውን ለመቆጣጣር በአጋጣሚ የእጅ ባትሪ ሲያበራ፤ ሁለት ከዚህ ቀደም በስምም ሆነ በአካል የማያውቋቸው “አቶ ያደታ ጣፋ እና አቶ ደገፋ ጣፋ” የተባሉ ግለሰቦች በብሎኬት ማምረቻ በሩ ሲያልፉ የባትሪው ብርሃን ጨለማውን ሰንጥቆ ላያቸው ላይ አረፈ።
ከግለሰቦቹ አንደኛው በአካል ፈርጠም ያለው “መንገድ እየሄድን ባትሪ የምታበሩብን ለምንድን ነው?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ወጣት ሙሉዓለም ቀበል አድርጎ “ጥበቃዎች ነን! ብርሃኑ ላያችሁ ላይ ያረፈው ድንገት ለመቆጣጠር ስናበራ ነው። ” ይላቸዋል። ግለሰቦችም በምላሹ “እኛ እኮ መንገደኛ እንጂ ሌባ አይደለንም። ጥበቃ ብትሆኑ እንዴት ታበሩብናላቹህ?” ሲሉ ይመልሳሉ። እንዲህ አንድ ሁለት ቃላት እየተለዋወጡ በአካል ተጠጋግተው መነጋገር ጀመሩ።
ከመንገደኞቹ አንደኛው የያዘውን እንጀራና ዘይት መሬት ላይ አሽቀንጥሮ ጥሎ ከሙሉዓለም ጋር ተጠጋግተው ተጨቃጨቁ፤ “እቃ ወስዳችሁብናል መልሱልን” ወደሚል የከረረ ንግግር ጭቅጭቁ ተሸጋገረ። ወጣት ሙሉዓለምና ደረጄ “የወሰድነው እቃ የለም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንሂድ” ይላሉ። መንገደኞቹ በበኩላቸው ፖሊስ ጋር አንሄድም ፖሊስ ምን ያመጣል እያሉ ይዝቱ ጀመር። ከመዛትም አልፎ በሰውነት አቋሙ ፈርጠም ያለው ግለሰብ “እንዴት ባትሪ ታበራብናለህ?” ብሎ ወደ ደረጄ ተጠግቶ አንገቱን አንቆ ያዘው። ይሄኔ ደረጄ አንገቱ ላይ ያደረገው የብር ሃብል ተቆርጦ መሬት ላይ ይወድቃል።
ደረጄም ሃብሉን ሊያነሳ ጎንበስ ሲል ባጎነበሰበት በክርኑ ጀርባው ላይ ይመታዋል። ደረጄም ቀና ብሎ ለምን ትመታኛልህ ሲለው፤ “እኔ እራሴ ፖሊስ ነኝ፤ ሽጉጥ ይዣለሁ፤ ዱላውንም ባትሪውንም አምጣ?” ብሎ ደረጄን ከእጁ ላይ ዱላውንም ባትሪውንም በኃይል መንጭቆ ይቀበለዋል። ይሄኔ ደረጄ ሁኔታው ስላላማረው ቀጥታ አንድ ቀደም ሲል ለሚያውቀው ፖሊስ ደውሎ እንዲደርስለት ይማጸናል። ይሁን እንጂ “በጭንቅ ጊዜ አይደለም ወዳጅ የራስ ልብ አይታመንም” እንደሚባለው ፖሊሱም በአካባቢው እንደሌለና የሌላ ፖሊስ ስልክ እልክልሃለሁ ብሎ ስልኩን ይዘጋበታል።
ደረጄ ከሚያውቀው ፖሊስ ጋር ተደዋውሎ ስልኩ ጆሮው ላይ እንደተዘጋበት፤ ከመንገደኞቹ አንደኛው በሰውነት አካሉ ቀጠን ያለው ባዶ እጁን ጨብጦ መሉዓለምን ለመምታት ይዘጋጃል። ሙሉዓለም ግለሰቡ እንደያዘው ቀድሞ በያዘው የእንጨት ዱላ በመሰንዘር አናቱ ላይ ይመታዋል። ግለሰቡም አናቱ ላይ ያረፈውን ዱላ ከቁብ ሳይቆጥረው ሙሉዓለምን በሁለት እጁ ብድግ አድርጎ መሬት ላይ ያፈርጠዋል። ከወደቀበትም በቦክስ ግራና ቀኝ ፊቱን እያገላበጠ ይመታዋል። ይባስ ብሎ በሰውነት አቋሙ ወፈር ያለው ግለሰብም ደረጄን ቀምቶ በያዘው የእንጨት ዱላ ሙሉዓለምን በወደቀበት ለሁለት እያገላበጡ ይቀጠቅጠው ጀመር።
ይሄኔ ጓደኛውን ለሁለት እያገላበጡ ሲቀጠቅጡት ደረጄ የድረሱልኝ ጩኸቱን ኡ! ኡ! ብሎ ቢያሰማም በዚያ ውድቅት ሌሊት ማንም ሰው ደርሶ ሊያስጥላቸው አልቻለም። ደረጄም “ጓደኛዬንማ ሲገሉት ቆሜ አላይም እሱን ከጨረሱት በኋላ ወደኔ መዞራቸው አይቀርም” ብሎ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጦ ተነሳ። ሙሉዓለምን አጋድመው እየቀጠቀጡት እያለ ደረጄ ወደ ግለሰቦቹ ተጠግቶ በያዘው እጀታው ባለፕላስቲክ መልኩ ጥቁር ጩቤ መጀመሪያ በሰውነት አቋሙ ወፈር ያለውን ግለሰብ ሠንዝሮ ወገቡ ላይ እና ጀርባው ላይ ሲወጋው መሬት ላይ ይወድቃል።
በተመሳሳይ በተክለ ሰውነቱ ደቀቅ ያለውን ግለሰብም ጀርባው ላይ ደጋግሞ በጩቤ ሲወጋው መሬት ላይ ወደቀ። ሁለቱም መሬት ላይ እንደወደቁ ሙሉዓለም ተራውን ከወደቀበት ተነስቶ አንደኛው ግለሰብ የያዘውን ዱላ ከወደቀበት እጁ ላይ ቀምቶ ሁለቱንም አንዳንድ ጊዜ አናታቸውን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደረታቸውን በዱላ ይመታቸዋል።
ሙሉዓለም ግለሰቦቹን በወደቁበት ይህን ያህል ዱላ ሲያሳርፍባቸው አይደለም አጸፋ መመለስ ይቅርና ከወደቁበት እንኳን አይንቀሳቀሱም ነበር። ይሄኔ ሙሉዓለም ደንግጦ ዘወር ሲል ከአጠገቡ ማንም የለም። ጓደኛው ደረጄ ተሰውሯል። እሱም እግሩን መትትወት ስለነበረ ለመራመድ በጣም ተቸግሮ ነበር። በእጁ የያዘውን በደም የተጨማለቀ ዱላ እየተመረኮዘ እንደምንም ወደ ቤቱ አምርቶ ሀገር ሰላም ብሎ ይተኛል። ፖሊስም እግር በእግር ተከታትሎ ሙሉዓለምን በቤቱ ከተኛበት ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ ይዞት ሲሄድ፤ አንደኛው ግለሰብ በሥፍራው ሞቶ ይመለከታል። ሌላኛው ግለሰብ ደግሞ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ሆስፒታል ላይ ሕይወቱ እንዳለፈ በማግስቱ ለፖሊስ ቃል ሲሰጥ እንደተነገረው ሙሉዓለም ለፖሊስ በሰጠው ቃል ላይ ተናግሯል።
በጥቅሉ ወንጀሉ በተፈጸመበት ጊዜና ቦታ በወቅቱ የነበረው ጭቅጭቅ፣ ክርክር፣ ድብድብ፣ የጸቡ መንስኤ … ወዘተ ምን ይመስል እንደነበር ከላይ በተገለጸው መሰረት ተጠርጣሪዎቹ ሙሉዓለም ታምሬ እና ደረጄ ሠቦቃ ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነው ለፖሊስ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ገልጸዋል።
የምስክሮች ቃል
ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 ገደማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ቦሌ አራብሳ ኮንደሚኒየም ፖሊስ ጣቢያ ጀርባ በተለምዶ ጉልት እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ ወንጀሉ መፈጸሙን ከምስክሮች አንዱ የሆነው አቶ ኤሊያስ ሊቺሳ ጠቅሶ፤ እሱም በወቅቱ ጉልቱን በመጠበቅ ሥራ ላይ ነበር። የእጅ ስልኩ ባትሪ ዘግቶበት በአካባቢው በሚገኘው አናኒያ ግሮሰሪ አጠገብ ከሚገኘው አሳምቡሳ ቤት ቻርጅ ለማድረግ ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 ገደማ ያቀናል። ቻርጅ ለማድረግ በሄደበት ወቅት ተጠርጣሪዎች ከሞቱት ከሁለቱ ግለሰቦች ጋር በምን እንደተጣሉ ባያውቅም በወቅቱ ሲጨቃጨቁ እንደነበር ያወሳል።
ሟቾቹ በንግግራቸው ወቅት ንብረታችን መልሱልን፤ ንብረታችን ካልመለሳችሁ ከዚህ ንቅንቅ አንልም በማለት ሲናገሩ እንደነበር አቶ ኤሊያስ ጠቁሞ፤ እሱም ምን ሆናቹህ ነው? በማለት ቢጠይቃቸውም ምንም ምላሽ ስላልሰጡት ተመልሶ ወደ መጣበት ሥራ ቦታው ያመራል። ወደ ሥራ ቦታው አምርቶ ተኝቶ በግምት አንድ ሰዓት ያህል እንደቆየ ፖሊሶች መጥተው ከተኛበት አስነስተው መጀመሪያ ሲጨቃጨቁበት ወይም ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ ይዘውት ይሄዳሉ።
በቦታውም ከነሙሉዓለምና ደረጄ ጋር መጀመሪያ ሲጨቃጨቁ ወደ ነበሩበት አንዱ ከፐብሊክ ሰርቪስ መታወቂያው ላይ ስሙ ሲነበብ የሰማው ያደታ ጣፋ የተባለው ሆድና ፊቱ በደም ተጨማልቆ ፊቱ ላይ ተመትቶ ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዳለፈ ማየቱን ይናገራል። እንዲሁም በጀርባው በኩል ሁለት ቦታ ላይ በስለት የተወጋ መሆኑንም ማየቱን ይገልፃል።
በወቅቱ ከሟቾቹ ጋር ሲጨቃጨቁ ከነበሩት አንደኛው ደረጄ ሠቦቃ የተባለው በቦታው ያልተገኘ ሲሆን፤ ሙሉዓለም ታምሬ የተባለው ተጠርጣሪ ከተኛበት ቤት ፖሊሶች ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ ይዘውት መጥተው በቦታው የሞተውን ግለሰብ እንዲያይ አድርገዋል። እንዲሁም ሙሉዓለም ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ የተከሳሽነት ቃሉን ሲሰጥ ሟቾችን በያዘው ዱላ መምታቱን አምኖ፤ ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ ሕይወቱ አልፎ የተገኘውን ፊቱ ላይ በዱላ እንደመታው እና ሆስፒታል ተወስዶ በዚያው ሕይወቱ ያለፈውን ደገፋ ጣፋ የተባለውን ግለሰብ ደግሞ ጭንቅላቱ ላይ አንድ ጊዜ እንደመታው ለመርማሪ ፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ መስማቱን አቶ ኤሊያስ ይናገራል።
እንዲሁም ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ለመርማሪ ፖሊስ ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነው ቃላቸውን ሲሰጡ መስማቱን ሌሎች ምስክሮችም አክለው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ከነሐሴ 03 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪዎችን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟቾችን የአስከሬን የምርመራ ሕክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰርትባቸው መረጃውን አቅርቧል።
ዐቃቢ ሕግ
በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና 540 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች ሰውን ለመግደል በማሳብ ከላይ ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታና ጊዜ ከሟቾች ጋር “ለምን መብራት ታበሩብናላቹሁ” በሚል የጸብ መነሻ 1ኛ ሟች ያደታ ጣፋን 1ኛ ተከሳሽ ደረጄ ሠቦቃ በጩቤ ደረቱን እና ጀርባውን በመውጋት መሬት ላይ ሲጥለው 2ኛ ተከሳሽ ሙሉዓለም ታምሬ በዱላ ጭንቅላቱን እና ፊቱን በመምታት በራስ ቅሉና በግራ ደረቱ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሰው ግድያ ወንጀል ተከሰዋል።
እንዲሁም 2ኛ ሟች ደገፋ ጣፋን በተመሳሳይ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ባደረሱበት ጉዳት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሰው ግድያ ወንጀል 2ኛ ክስ ተመስርቶባቸዋል። በጥቅሉ ተከሳሾች በፈፀሙት ተራ የሰው ግድያ ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል። ዐቃቤ ሕግም 11 የሰው ማስረጃ፤ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በቁጥር ጳሀ8/684 በቀን 10/12/2013 ዓ.ም ስር የተሰጠ የሟቾች የሞት ምክንያት የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከነመሸኛው እና ማብራሪያ ከነትርጉሙ 12ገጽ ቅጂ፤ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፍ በደብዳቤ ቁጥር ፌፎ/ባ-03 /515/2014 በቀን 06/12/2014 ዓ.ም የተላከ የደም ምርመራ ውጤት ከነመሸኛው 02 ገጽ ቅጂ፤ የሟቾችን የአማሟት ሁኔታና ጉዳት፣ ተከሳሾች የድርጊቱን አፈጻጸም ሲመሩ የሚያሳይ እንዲሁም የወንጀል ስፍራውን የሚያሳዩ አጠቃላይ 23 ገላጭ ፎቶግራፎችን እንዲሁም ተከሳሾች በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 27(2) መሰረት ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነው ቃል ሲሰጡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልን የያዘ 02 ሲዲ በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በፍጥነት እንዲታይ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቢ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።
ውሳኔ
ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ 1ኛ ምድብ ችሎት በተከሳሾች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ20 (ሀያ) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015