የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በመጪው ዓመት በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድር ለማለፍ በማጣሪያው የሚገጥሙትን ቡድን አውቀዋል፡፡ የመጀመርያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከቡሩንዲ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደርጋሉ፡፡
በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት (እአአ 2024) በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ድልድል ይፋ ሆኗል። ባለፈው ሳምንት በሞሮኮ ራባት በተደረጋው የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓትም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ተጋጣሚያቸውን ማወቅ ችለዋል፡፡ በሁለት ዙር በሜዳና ከሜዳ ውጪ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድሮች 42 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ሞሮኮ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ ያለምንም ማጣሪያ በቀጥታ ትሳተፋለች፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያቸውን ከሚያደርጉ ሀገራት አንዷ ስትሆን፤ በሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ውድድር ደግሞ ሁለት በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የማያደርጉትን ሀገራት በማከል 20 ሀገራት ጨዋታቸውን አድርገው 11 አሸናፊ ሀገራት ለ2024ቱ የሞሮኮ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል። ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ያሸነፈችው ደቡብ አፍሪካ ግን በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያው አትሳተፍም፡፡
በወጣው ድልድል መሰረትም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጪ በመጪው ነሃሴ ወር 2015 ዓ.ም ከብሩንዲ አቻው ጋር የሚገጥም ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በእጣ አወጣጥ ሂደቱ በቋት ሁለት ተደልድላ የነበረ ሲሆን ብሩንዲ ደግሞ በቋት ሶስት ተደልድላ ነበር፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ የሚሆነው ደግሞ በሁለተኛው ዙር ከኡጋንዳ እና አልጄሪያ ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
በፊፋ የሀገራት ደረጃ አሰጣጥ መሰረት 40ዎቹን ሀገራት በሶስት ቋት በመክፈል የእጣ ድልድሉ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት 9 የመጀመሪያ ምርጥ ደረጃ ያላቸውን፣ 9 ሁለተኛ ምርጥ ደረጃ ያላቸውን እና 22 ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን ቡድኖች አካቷል፡፡ በደረጃ አንድ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቱኒዚያ፣ አልጄሪያ፣ ማሊና ሴኔጋል ሲሆኑ፤ በምድብ ሁለት ግብጽ፣ ኮንጎ፣ ቶጎ፣ ጋምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ጋቦን፣ ጊኒ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ናቸው፡፡
በመጨረሻውና ሶስተኛው ደግሞ አንጎላ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ብሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ጅቡቲ፣ ስዋቲኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኬኒያ፣ ላይቤሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ኒጂየር፣ ሩዋንዳ፣ ሳኦቶሜ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ ሊዘረዘሩ ችለዋል። በሶስቱ ቋት መሰረት ድልድሉ ተደርጎ ሁሉም ሀገራት በመጀመሪያ ዙርና በሁለተኛ ዙር የሚገጥሙትን ብሄራዊ ቡድኖች ለይተው ማወቅ ችለዋል፡፡
ሉሲዎቹ በመድረኩ ምንም እንኳን ውጤታማ ባይሆኑም የተሻለ ተሳትፎ ግን አላቸው፡፡ እአአ በ2002 የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን ኡጋንዳን በማሸነፍና ከማሊ ጋር እኩል በመሆን ከምድቡ መጨረሻ በመሆን ነበር ያጠናቀቁት። በ2004 እንዲሁ ለተሳትፎ ቢበቁም በምድባቸው ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍና ከዚምቧቡዌ ጋር ደግሞ ነጥብ በመጋራት በግማሽ ፍጻሜው በናይጄሪያ ተሸንፈው ለፍጻሜ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በመጨረሻም በጋና ብሄራዊ ቡድን በመለያ ምት ተሸንፈው የነሃስ ሜዳልያውን ሳያጠልቁ ውድድራቸውን መቋጨት ችለዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ በውድድሩ ተሳትፎ ውጤት ሳይቀናው ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በ2013 በመድረኩ ጥሩ እንቅስቃሴን በማድረግ ምርጥ የሚባል ብቃቱን ማሳየት ችሎ ነበር፡፡
ሉሲዎቹ በዓለም አቀፍ የሴቶች እግር ኳስ ደረጃ 125 ደረጃን ይዘው ይገኛሉ፡፡ ተጋጣሚያቸው የብሩንዲ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በፊፋ እውቅና የተሰጣቸውን ጨዋታዎች ማካሄድ የጀመረው ከ2016 አንስቶ ሲሆን ዋና ብሄራዊ ቡድን ባለመኖሩ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድኑ ነው በርካታ ጨዋታዎችን የሚያደርገው፡፡
ሉሲዎቹ በአሁኑ ወቅት ለ2024ቱ ኦሊምፒክ የማጠሪያ ጨዋታ በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል እየተመሩ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። አፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በመድረኩ በመንገስ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ለ11 ጊዜያት በማሸነፍ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡
ዓለማሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም