መንግሥት በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ያለውን እና ለሀገር ደህንነትም ስጋት እየሆነ የመጣውን ሕገወጥ የማዕድን ፍለጋ፣ ማምረትና ግብይትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥናት በማካሄድ ርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህም በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር ላይ የተሰማሩ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችን፣ ተባባሪዎቻቸው ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ከማዋል አንስቶ የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው፡፡
በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው በወርቅ ማምረትና ማዘዋወር ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ማህበራት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መረጃዎቹ አመልክተዋል፡፡ ርምጃዎቹን ተከትሎም ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት በሕገወጦች ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ የማዕድን ሀብቱን ከዘረፋ ከመታደግ አንጻር የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው ስንል ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህርና ተማራማሪ ዶክተር ሞላ ዓለማየሁ፤ በማዕድን ዘርፉ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ ወጥ ድርጊት ፈርጀ ብዙ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ በሀገሪቱ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያስከትል ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ የማዕድን ሀብቷን ተጠቅማ እንዳታድግ እንደሚያደርጋት ነው ያስገነዘቡት፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውሩ በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ከባድ አሉታዊ ተጽእኖ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይገባል፤ አንደኛ ሀገሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንዳትጠቀም ( ሀብቷ በሕገወጥ መልኩ እንዲበዘበዝ) ያደርጋል፤ የምታገኘውን ጥቅምም ያሳጣል፡፡ ያላትን ሀብት በአግባቡ ካልተጠቀመችበት የሀብት ብክነት ይከተላል፡፡ ሁለተኛ የማዕድን ሀብቱ በቀጥታ ለሀገሪቱ ጥቅም ሳይውል ሕገወጥ አካላት ለሕገወጥ አላማ መጠቀሚያ እንዲያውሉት ያደርጋል፤ ይህ ሲሆን የሀገሪቱን ደህንነት የሚፈታተን አደጋ ሊያመጣ ይችላል፡፡
በማዕድን ዘርፉ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥነት ከኢትዮጵያ እስከ ውጭ ሀገር ድረስ የሚዘልቅ ሰንሰለት እንዳለው ጠቅሰው፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ በድርጊቱ ተሳታፊ ከሆኑት አካላት አብዛኛዎቹ የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውም ይህንኑ እንደሚጠቁም ይገልጻሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የችግሩን ጥልቀት ያመለክታል ነው ዶክተር ሞላ የሚሉት፡፡
ዶክተር ሞላ መንግሥት በእነዚህ ሕገወጦች ላይ እርምጃ በመውሰድ በኩል መዘግየቱንም ነው ያመለከቱት፤ መንግሥት አፋጣኝ ርምጃ ባለመውሰዱ የተነሳ ሕገወጦቹ ውጭ ሀገር ድረስ መስመር ዘርግተው የሀገሪቱን የማዕድን ሀብት እንደፈለጉት መዝረፋቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህን ድርጊት ፈጥኖ ማስቆም አለመቻሉ ብዝበዛውን የከፋ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ ህገወጥ ድርጊቱ ሀገሪቱ በርካታ የማይተካ የማዕድን ሀብቷን እንዲታጣ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት በማዕድን ላይ የሚደረገውን ሕገወጥ ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ዶክተር ሞላ ይጠቅሳሉ፤ ከአራት ወር በፊት የባንግላድሽ፣ የፓኪሲታን እና የሕንድ ዜጎች በሕገወጥ የማዕድን ዝውውሩ ላይ ተሰማርተው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ያስታውሳሉ፤ በእነዚህ አካላት ላይ ስለተወሰደው ርምጃ በወቅቱ በግልጽ ይፋ የተደረገ መረጃ እንዳልነበረ የሚጠቅሱት ዶክተር ሞላ፣ ህገወጥ የማዕድን ዝውውሩ ተስፋፍቶ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ኃይለመስቀል ገአዙም ይህን የዶክተር ሞላን ሃሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ ያነሳሉ፤ በየትኛውም ዘርፍ ላይ የሚፈጸም ሕገወጥነት በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል ጠቅሰው፣ ሀገር ማግኘት ያለባትን ገቢ እንዳታገኝ ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚታየው ሕገወጥነት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እንደሚያስከትልም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ኃይለመስቀል ገለጻ፤ ሕገወጥነት የሀገር ኢኮኖሚን በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑ ባሻገር በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ ይጎዳል፤ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ በሕገወጦች ወደ ውጭ የሚወጣ የማዕድን ሀብት የውጭ ምንዛሪ ከማሳጣቱ በተጨማሪ ሌላ አሉታዊ ተፅእኖም ያሳድራል፤ ማዕድኑ እሴት ከተጨመረበት በኋላ እንደገና ወደ ሀገር ውስጥ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባበት ሁኔታ ሊኖርም ይችላል፡፡
ዶክተር ሞላ ስለ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀጠመጥ አስፈላጊነትም ይጠቁማሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥት የማዕድን ዝርፊያውን ለማስቆም የማዕድን ዘርፉ የሚመራበትን ግልጽ የሆነ ሕግ ማውጣትና ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ሥራ መግባት ይኖርበታል፤ ይህ ሕግ በማዕድን ዘርፉ ላይ የሚሳተፉ አካላት በግልጽ እንዲታወቁ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ሕጉ በዘርፉ የሚሳተፉ ወይም የሚሰማሩ አካላት ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት፣ ከማዕድን ሀብቱ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ ተቆጣጣሪው አካል ማን መሆን እንዳለበት፤ የክትትልና የግምገማ ሥርዓቱ ምን መምሰል አንዳለበት የሚያመለክት መሆን ይኖርበታል፡፡
በማዕድን ዘርፉ ላይ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋትም ይኖርበታል፡፡ የሚመለከተው አካል ማን እንደሆነ በትክክል ተቀምጦ ወደ ሥራ መግባት ይኖርበታል፤ በእያንዳንዱ ሥራ ላይ ቁጥጥርና ክትትል ቢካሄድ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሕገወጥነቱ መልሶ እየተሰፋፋ ሊቀጥል እንደሚችል ነው ስጋታቸውን የጠቆሙት፡፡ በማዕድን ላይ የተዘረጋው ሕገወጥ ሰንሰለት እንዲቋረጥ የሚያደርግ ርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ለእዚህም መንግሥት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግልጽ አሠራር መዘርጋት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
በማዕድን ፍቃድ አሰጣጥም ሆነ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግልጽ የሆነ አሠራር የለም፤ በተለይ በማዕድን ሀብት ላይ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ያላቸው መብትና ግዴታ በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ አሁን አንዳንዶች በሕጋዊ ሽፋን ሀገር ውስጥ ገብተው ሕገወጥ ድርጊት ላይ ተሳትፈው መገኘታቸው የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል የላለና ግልጽ የሆነ አሠራር እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በማዕድን ላይ እየታየ ያለውን ሕገወጥነት የተንሰራፋበት አሠራር በማስተካከል ወደ ሥራ መግባት እስካልተቻለ ድረስ ሀገሪቱ ያላትንና መተካት የማትችለውን የማዕድን ሀብቷን ለብሔራዊ ጥቅሟ ለማዋል ሳትችል እንደምትቀር ይጠቁማሉ፡፡
ከዛሬ አመት ጀምሮ በማዕድን ሀብት ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ብልጭ ድርግም ሲሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ መንግሥት ስትራቴጂ ነድፎ ይህንን ሕገወጥ ተግባር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወደ ሥራ እስካልገባ ድረስ አሁን በሕገወጥ ማዕድን ዝውውር ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ እሳት የማጥፋት አይነት ሊሆን ይቻላል ይላሉ፡፡ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ ያስችላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው ዶክተር ሞላ የሚናገሩት፡፡ ይህ ጉዳይ የሆነ ወቅት ላይ የሚነሳ ተመልሶ ደግሞ የሚረሳ መሆን እንደሌለበትም ዶክተር ሞላ አስታውቀዋል፡፡
ዶክተር ሞላ ሕገወጦቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል ብቻውን ለሌላውን የሚያስተምር ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው፡፡ የፍርድ ሂደቱና በሕገወጦቹ ላይ የሚተላለፍባቸው የቅጣት ውሳኔም ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበትና ከዚህም ትምህርት ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ማዕድናት በዓለም ላይ እንደፈለገነው የምናገኛቸው አይደሉም የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚውን ወደሌላ መቀየር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ይመክራሉ። አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ኃይለመስቀል፤ አሁን መንግሥት ሕገወጥ የማዕድን ዝውውሩን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው ርምጃ ሊበረታታ ይገባዋል ነው የሚሉት፡፡ መንግሥት በሕገወጥነቱ ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር እና እየተወሰደ ያለው ርምጃ ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል ባሻገር ጠንከር ያለና አስተማሪ መሆን ሲሉ የገለጹትም የዶክተር ሞላን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የተሰጣቸው እንደ የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ፣ የክልል ፖሊሶችና የፀጥታ አካላት ያሉት ተቋማት ከሙስና የፀዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ አካላት ሕግን በተከተለ መልኩ የሚያደርጉት ሕገወጥነትን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ ወሳኝና ለውጥ ማምጣት የሚያስችልም ነው፡፡
‹‹በሀገሪቱ በማዕድን ሀብት ላይ ሕገወጥ ድርጊቱ እንዲስፋፋና እንዲባባስ ያደረገው አንዱ ምክንያት ሙስናና ሌብነት ነው›› ሲሉ ገልጸው፣ ሌብነትና እስካልቆመ ድረስ ሕገወጥነቱን ማስቆም እንደሚያስቸግር ያስገነዝባሉ፡፡ በማዕድን ዘርፉ ላይ እየታየ ያለው ሕገወጥነት ከሙስና ጋር ተያያዥነት እንዳለው ጠቅሰው፤ መንግሥት በሙስና ላይ እየወሰደ ያለውን ርምጃ በደንብ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ኃይለመስቀል ሕገወጥነትን መቆጠጣር ካልተቻለ ሀገሪቱ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያሳጣታል ይላሉ፡፡ የማዕድን ዘርፉ ግልጽ በሆነ ሕግ መመራት አለበት በማለትም ዶክተር ሞላ ያነሱቱን ተመሳሳይ ሃሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ አቶ ኃይለመስቀል አንስተዋል፡፡ ዘርፉ ግልጽ በሆነ ሕግ ካልተመራ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት እንደሚስፋፋም ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ የሀገርን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚጎዳ ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ሕገወጥ ተግባሩን መንግሥት ብቻውን ሊቆጣጠረውና ሊያስቆመው አይችልም›› የሚሉት አቶ ኃይለመስቀል፣ የኅብረተሰቡም ተሳትፎ በእጅጉ ወሳኝነት እንዳለው ይመክራሉ፡፡ ሕገወጥነት እንዲህ በተስፋፋበት ወቅት ኅብረተሰቡ በስፋትና በእኔነት ስሜት ተነስቶ ተስፋ ሳይቀርጥ ሀብት እንዳይባክን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል፡፡ ይህን አይነት ማህበረሰብ መፍጠር ከተቻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ነው አቶ ኃይለመስቀል ያስገነዘቡት፡፡
አቶ ኃይለመስቀል፤ መንግሥት በማዕድን ዘርፉ ላይ የተንሰራፋውን ሕገወጥነት በደንብ መቆጣጠር ከቻለ የሀገር ገቢ በእጅጉ ይጨምራል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን በሌሎች ላይ የሚጨምረው የታክስ ጫናም ይቀንሳል፤ የመሥራት አቅምም እንዲሁ ይጨምራል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ተግባር ተከትሎ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን መቀነሱ በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወቃል። መንግሥት በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ግብይትና ሌሎች የኮንትሮባንድ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ርምጃዎችን እንደሚወሰድ ሲያስታውቅ ቆይቷል፤ መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ይህን ሕገወጥ ተግባር መከላከልና መቆጣጠር ቀጣይ ተግባራቸው መሆኑን መጠቆሙም ይታወሳል፡፡
መንግሥት ይህን ሕገወጥ ተግባር የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ርምጃ ገብቷል፤ በዚህም በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን ተባባሪዎቻቸው በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከእነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባለፈው መጋቢት ወር መግለጹ ይታወሳል፡፡
የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎችንና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በመያዝ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጿል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም እንዲሁ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በዚህ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ማስታወቁም ይታወሳል። በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው 32 የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አመራሮችና አምራቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በዚህ ወር አጋማሽ አካባቢ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ማስታወቁም ይታወሳል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በወጣ መረጃ በክልሉ በሕገወጥ የወርቅ ግብይት ላይ የተወሰደውን ርምጃ ተከትሎ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡ የክልሉ ማዕድን ቢሮም ይህንኑ አረጋግጧል። ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ለውጥ እያሳየ መምጣቱን ቢሮው ጠቅሶ፣ ርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015