አካል ጉዳተኝነት ያልበገራት በጎ አድራጊዋ ወጣት

ከዓመታት በፊት በወጣው የተባበሩት መንግ ሥታት የአካል ጉዳተኞች ሪፖርት መሠረት፤ በዓለም ላይ ካሉት 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል 15 በመቶዎቹ በታዳጊ ሀገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ካላት ሕዝብ መካከል 17.5 በመቶ የሚሆኑት ወይም 15 ሚሊዮን ሰዎች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው 15 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በ 2.5 በመቶ ከፍ ያለ ነው።

እንደሀገር በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ የግንዛቤ እጥረት፣ የአካል ጉዳተኞች መብት ያለመከበር፣ አብዛኛዎቹ መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ያገናዘቡ ያለመሆናችውና ሌሎች መሰል ጉዳዮች የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት ፈታኝ አድርገውታል።

ትምህርት ካለማግኘት አንስቶ፤ በሥራው ዓለም ለአካል ጉዳተኞች ብዙ የሚከብዱ ነገሮችን እንዳሉ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፤ በትምህርቱ ዘርፍ እንኳን በቂ የትምህርት እድል አለማግኘትን ጨምሮ፤ እነሱን ታሳቢ ያደረጉ የትምህርት ማሟያ መጻሕፍት አለመኖር በትምህርታቸው ገፍተው እንዳይሄዱ ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።

በማኅበረሰቡ ዘንድ ካለው የግንዛቤ እጥረት ጋር በተያያዘም ፤ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከልጅነታቸው ጀምሮ ማግለልና መድሎ ይደርስባቸዋል። ከዚህ የተነሳም በየቤቱ ተደብቀው የሚያድጉና ሕይወታቸውን የሚገፉ ናቸው። ከጊዜ በኋላም ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ መድሎና መገለሉ እጣ ፈንታቸው ይሆናል።

እነዚህ ችግሮች ሁሉንም አካል ጉዳተኞችን የሚያጋጥሙ ቢሆኑም፤ በሴቶች ላይ ግን፤ ሁኔታዎች የከፉ እንደሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ከቤት መውጣት ሳይፈቀድላቸው፤ ይልቁን እርባና ቢስ እና ጥቅም አልባ ተደርገው ቤት የሚቀሩ ሴት አካለ ጉዳተኞች ብዙ ናቸው።

ኅብረተሰቡ ውስጥ ካለው ጫና በተጨማሪ አካል ጉዳተኞች ለራሳቸው ያላቸው ዝቅተኛ አመለካከትም ችግሩን የበለጠ ከሚያወሳስቡ ምክንያቶች ተጠቃሽ እንደሆነም ይታመናል። እነዚህ ውጪያዊና ውስጣዊ ችግሮች አካል ጉዳተኞች “አቅማቸውን እንዲጠራጠሩ እና አንችልም ብለው እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል” ።

ይህም ሆኖ ግን አካል ጉዳተኝነት ህልምን ከማሳካት እንደማያግድ ብርሃናቸውን በሰፊው አብ ርተው ለትውልዱ በተምሳሌትነት የተገለጡ የይቻላል አርማዎች የሆኑ አካል ጉዳተኞች የመኖራቸው እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከእነዚህ መካከል እንደ አንዷ ልትቆጠር የምትችለው ወጣት ሄለን ናት።

ወጣት ሄለን ጥላሁን ተወልዳ ያደገችው በምስራቅ ሐረርጌ ውስጥ በምትገኝ ሀሮማያ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ ነው። ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ወላጅ እናቷ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ስለነበሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ልጆች በሚማሩበት ሞዴል ትምህርት ቤት ተቀላቅላ እስከ ስምንተኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል ደግሞ በአቅራቢያ ያለው የሐረር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለነበር በዚህ ትምህርት ቤት ደግሞ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቷን ለመጨረስ ችላለች። በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ ውጤት በመምጣት በብዙ ምክንያት መማር ትፈልግ የነበረውን የሕግ ትምህርት አንጋፋውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቅላ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን መያዝ ችላለች።

ወጣት ሄለን ስለ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ስትናገር፤ የሕግ ትምህርት ብዙ ማንበብ የሚጠይቅ ነው። አላማዋ ጥሩ ውጤት ይዞ መውጣት ስለነበር ወላጅ እናቷ እሷና እህት ወንድሞቿን ሲያሳድጉ “ሴት ልጅ መማር አለባት፤ እራሷን መቻል አለባት”ይሏት ነበር፡፡ ይህንኑ በልቧ ውስጥ በማሳደር ትምህርቷን በትልቅ ትኩረት ትከታተል እንደነበር ትናገራለች። የመጀመሪያው ዓመት ለሁሉም ነገር መሰረት የሚጣልበት ስለሆነ በትኩረት በመማር በጥሩ ውጤት ወደ ሁለተኛ ዓመት ስለመሸጋጋሯ ታስረዳለች።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ እንደመሆኑ ብዙ ክበቦች ነበሩ የምትለው ሄለን ከሁለተኛ ዓመት በኋላ በስፋት በክበቦች ውስጥ ተሳትፎ ታደርግ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት በሕግ ትምህርት ክፍል በተቋቋመ የአካል ጉዳተኞች ክበብ ላይም ሰፊ ተሳትፎ እንደነበራት ትገልፃለች። ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ሰዎች ከተለያየ ቦታ መጥተው በአንድ ላይ የሚኖሩበት ቦታ ነው የምትለው ወጣት ሄለን የግቢ ቆይታዋ ብዙ ነገሮችን መረዳት የቻለችበት እንደነበር ትገልፃለች።

በዩኒቨርሲቲው በነበረበት የተጎዳኝ ትምህርት እንቅስቃሴ የሕግ ትምህርቷን ባጠናቀቀች የመጀመሪያ ዓመት ማለትም 2004 ዓ.ም ላይ የሁለተኛ ዲግሪ ስኮላርሽፕ አግኝታ በማኅበረሰቡ ላይ የመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራት በሶሻል ወርክ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪዋን በ2005 ዓ.ም ማግኘት ችላለች።

“ሀገራችን ለሴቶች የምትሰጠው ቦታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” የምትለው ወጣት ሄለን፤ አካል ጉዳተኝነት ወይም ዓይነስውርነት ሲጨመርበት ደግሞ ተጨማሪ ጉዳት እንደሚያስከትል ታስረዳለች፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ “ለእኔ እዚህ መድረስ አቅም ሆኖኛል ብዬ ነው የማስበው” የምትለው ሄለን ቤተሰቦቿ ደግሞ ሁልጊዜ ምንም ነገር ማድረግ እንደምችል እንጂ ከሌላው ያነሰ አቅም እንደሌለኝ ይነግሩኝ ነበር፡፡ በትምህርት ፈተና ወቅት እንኳ አንድ ስህተት ለምን ኖረብሽ? ወንድ ልጅ ሲበልጣትም እንዴት በለጠሽ? ብለው ይቆጫሉ እንጂ አለመቻሌን አልነበረም እየነገሩ ያሳደጉኝ ትላለች፡፡ ስለዚህ አሁን ለደረሰችበት ውጤት እነዚህ ሶስት ነገሮች አቅም ሆኖውኛል ብላ እንደምታስብ ትናገራለች።

ማህበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት በአብዛኛው የተዛባ ቢሆንም አቅም የሚሆኑ ሰዎችም ነበሩ የምትለው ወጣቷ ጎረቤቶቿ፣ በሁለተኛ ደረጃም ሆነ ዩኒቨርሲቲ ላይ አጋዥ የትምህርት መሳሪያዎች ለማግኘት አስቸጋሪ በነበረበት ሁኔታ የረዱኝ እና ያስተማሩኝ መምህራን በተቻላቸው ሁሉ እያገዙ አቅም ሆነውኛል ትላለች፡፡ ሌላው እራሷን ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ የምታደርገው ጥረት አቅም እንደሆናት እና “ምንም ነገር አያቆመኝም ለችግር አልንበረከክም፣ የሰው አመለካከት አያቆመኝም መድረስ እና ማድረግ የሚፈልገውን ነገር አደርጋለሁ ብዬ የማስብ ሴት ሆኜ ማደጌ” ለዛሬ ስኬቴ አስተዋጽኦ አድርጓል ትላለች።

ወጣት ሄለን አሁን በሥራ አስኪያጅነት New Life (አዲስ ሕይወት) የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማስተዳደር ላይ ትገኛለች፡፡ ሥራ አስኪያጅ ከመሆኗ በፊት በፕሮግራም ማኔጀርነት ነበር ድርጅቱን የተቀላቀለችው፡፡ ኢትዮጵያ ባላት የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ምክንያት መስራቾቹ ድርጅቱን ማስቀጠል ባለመቻላቸው የድርጅቱ ቦርድ እሷን በሥራ አስኪያጅነት በመመደቡ የተሰጣትን ኃላፊነት እየተወጣች እንዳለች ትገልፃለች፤ ድርጅቱ ምንም ፋይናንስ ያልነበረው እና ለስድስት ወራት ያለ ደመወዝ በመሥራት መስዋትነት በመክፈል ስለመቆየቷ ተናግራለች።

“ከምንም የትም መድረስ ይቻላል” የምትለው ወጣት ሄለን 12 ሠራተኞች በስሩ አቅፎ ይዟል፡፡ ድርጅቱ ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና በስደት ላይ ሰዎችን ብሎም ልጆችን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። “ችግሮች ከምንጫቸው ነው መድረቅ ያለባቸው ብለን እናስባለን” የምትለው ሄለን ድርጅቱም ሲቋቋም ዓላማው “ጎዳና የልጆች ማደሪያ አይደለም መረማመጃ እንጂ” በማለት ከጎዳና ልጆችን በመንሳት ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ የተቋቋመ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ ድርጅቱ በሠራቸው ሥራዎችም አሁን ላይ ብዙ ልጆችን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ አድርገናል ትላለች።

ወደ ቤተሰቦቻቸው በተለያየ ምክንያት መቀላቀል ያልቻሉትን ደግሞ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ትምህርታቸውን እንዲማሩ ማድረግ መቻሉን ታስረዳለች፡፡ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉትን ደግሞ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የማብቃት ሥራ እየሠሩ እንዳሉ ተናግራለች።

“በዚህም በጣም ደስተኛ ነን የምትለው በጎ አድራጊዋ” ጎዳና ያለ ሰው አይረባም፤ አይጠቅምም ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ነገር ግን ድርጅታቸው ከጎዳና ልጆችን አንስቶ አስተምሮ ዶክተሮችን፣ ኢንጂነሮችን መምህራንን ብሎም የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ደግሞ ለራሳቸው እና ለሀገር የሚጠቅሙ ዜጎችን ስለማፍራቱ ትናገራለች፡፡ በዚህም “ትልቅ እርካታ ይሰማኛል በገንዘብ ደረጃ በዚህ ድርጅት በዓመት የማገኘውን ገቢ በሕግ ሙያ ሥራዬን ቀጥዬ ቢሆን ኖሮ በጥቂት ጊዜያት ማግኘት እችል ነበር።ነገር ግን ከገንዘብ ባለፈ ሕዝብን ሰውን መገልገል በመቻሌ፤ ሰው ሰውን ሲሸት መየት መቻሌ፤ የተሻለ ቦታ ደርሶ ማየት እና ሰዎች ሲስቁ ማየቴ እና ህፃናት ትምህርት ሲማሩ መመልከቴ ለእኔ ከምንም በላይ ደስታ የሚሰጠኝ ነገር ነው” ትላለች።

ከመንግሥት ጋር አንድ ላይ እንሰራለን የምትለው ሄለን በቅርቡም በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ባሉበት እውቅና ማግኘታቸውን ትናገራለች፡፡ ነገር ግን ድርጅታችን ከሠራው ሥራ አንፃር የሚገባውን እውቅና አግኝቷል ብላ እንደማታስብ ትገልፃለች፡፡ በዚህ ረገድ ድርጅታቸውም የሚሰራውን ሥራ ለማኅበረሰብና ለመንግሥት ማሳወቅ ግዴታ ነው በዚህ በኩል ክፍተት እንዳለ አክላለች።

“የቢሮ ኪራይ እንኳ መክፈል የምንቸገርበት ጊዜ አለ የዓመት የቢሮ ኪራይ ለመክፈል እየተቸገርን ነው፤ ሀብት ፈልገን እያመጣን ማህበረሰቡን እያገለገልን ስለቢሮ ኪራይ እንኳ እንዳናስብ የሚያደርግ ድጋፍ አልተደረገልንም፤ ስለዚህ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ሊረዱን ቢፈልጉ በራችን ክፍት ነው፡፡ ከእኛ ጋር እንዲቆሙ እና እንዲረዱንም ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብላለች።

“ልቤ ህፃናት ላይ አለ” የምትለው ወጣት ሄለን “ይህንን ሀገር የሚረከቡት ወጣቶች እና ህፃናት ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ትውልድ ላይ በሰፊው መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያላት ሀብት እየተጠቀመች ነው ብዬ አላስብም፡፡ ሀገሪቱን አምራች የሰው ኃይሏን አቅም እንድትጠቀም ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቼ መስራት እፈልጋለሁ፤ የማገገሚያ ማዕከል ኖሮኝ ህፃናትን ከጎዳና በመንሳት ከሱስ በመላቀቅ አምራች ማድረግ እና ጎን ለጎን ደግሞ የእናቶች ማሰልጠኛ ማዕከል ማቋቋም እፈልጋለሁ፤ የነገ የሀገር ተረካቢ ትውልድ ላይ መስራት እፈልጋለሁ” ብላለች።

“የማይቻል ነገር የለም የምትለው” ሄለን ተግዳሮቶች ቢኖሩም “እጅ መስጠት አለብኝ ብዬ አላስብም፤ የመፍትሔ ሰው ነኝ ብዬ ነው እራሴን የሚወስደው፤ ችግር ባጋጠመኝ ቁጥር መፍትሔ በመፈለግ ችግሩ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የመፍትሔ ትውልድ እንሁን የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ትላለች።

“ሰው አንድ ወይም ሁለት አካሉን ሊያጣ ይችላል ቀሪውን በሥነ ሥርዓት መጠቀም መቻል ነው፡፡ ትልቁ ነገር አሁን ቴክኖሎጂው ጥሩ ነው፡፡ በተለያየ መንገድ ማየት የሚችለው ሰው ሁሉ መሥራት የሚችለውን ነገር መሥራት የሚችልበት ዕድል አለ፤ ማኅበረሰቡ ቅን አመለካከት አለው፤ አካል ጉዳት ያለበት የቤተሰብ አባል ያላቸው ሰዎች ለልጆቻቸው አቅም እንዲሆኗቸው ወደፊት እንዲያመጧቸው አደራ ማለት እፈልጋለሁ›› ብላለች።

ዕድሉን ከሰጠነው አካል ጉዳተኛ ተደጋፊ ወይም ተረጂ አይደለም የምትለው ሄለን የሚገባውን ነገር ከሰጠነው እንደእኔ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ የሚችል ነው ስትል ሃሳቧን ታጠናክራለች፡፡

ወጣት ሄለን ለደረሰችበት ስኬት ሁሉ በመጀመሪያ ከምንም በላይ የረዳኝን ፈጣሪ ማመስገን እፈልጋለሁ ትላለች፡፡ በመቀጠል “ወላጅ እናቴ እዚህ ለመድረሴ ትልቅ አስተዋጽኦ አላት፤ ለእሷ ትልቅ ምስጋና አለኝ፤ ጓደኞቼ፣ መምህራኖቼ እንዲሁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ዕድል ከማመቻቸት አንፃር ላደረገልኝ ትብብር ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻም የሥራ ባልደረቦቼ የሥራ ዕድሉን ከፍተው የእኔን አቅም ተማምነው ለሀገር የሚጠቅም ሥራ እንድሰራ ዕድሉን ስለሰጡኝ በአክብሮት ማመስገን እፈልጋለሁ” ብላለች።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *