ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው በተለያየ መንገድ ከዜጎች የሚሰበሰብ ግብር ነው። ከዚህ የተነሳም መንግሥታት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብር በመሰብሰብ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ለዜጎቻቸው የምትመች ሀገር ለመፍጠር አብዝተው ይተጋሉ። በሂደቱ የተሳካላቸውም ከራሳቸው አልፈው በተጨባጭ ለሌሎች ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ሀገራትን መገንባት ችለዋል።
አሁን ላይ በዕድገታቸው ግንባር ቀደም የሆኑ ሀገራት የእድገት ምስጢርም ከዚህ የተለየ አይደለም። ዜጎቻቸው ስለ ግብር ያላቸውን አመለካከት አዎንታዊ በማድረግ ፣ በበጎ ህሊና እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፣ ከፍ ላለ ተጠያቂነት የተገዛ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት በመፍጠር፤ ይህንንም የዜግነት ቀዳሚ ግዴታ አድርገው በጠንካራ ዲሲፕሊን በማስፈጸማቸው ነው።
በእኛ ሀገር የግብር ጉዳይ ከሀገሪቱ የመንግሥት ምስረታ ታሪክ ጋር የተያያዘ የረጅም ዘመን እድሜ ቢኖረውም፤ በሕዝቡ ውስጥ ተገቢውን ግንዛቤ ባለማግኘቱ ፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ሆነ ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን ሂደት የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል። ይህም በራሱ አሁን ለምንገኝበት ድህነትና ኋላ ቀርነት አንድ ተጠቃሽ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።
በሕዝቡ ውስጥ ስለ ግብር ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆን፤ በመንግሥት ደረጃ ግብር ለመሰብሰብ ለሚደረገው ጥረት ተግዳሮት ነው፡፡ በግብር መልክ የሚሰበሰበው የሕዝብ ሀብት ለሕዝቡ አገልግሎት እንዲውል ማድረግ የመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት ቢሆንም፤ ሕዝቡ የመንግሥት ሀብት ማለት በግብር መልክ ከእርሱ የተሰበሰበና እሱን ታሳቢ ለሚያደርጉ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል፤ ሀገራዊ የሀብት ክፍፍሉን ፍትሐዊ የሚያደርግ መሳሪያ መሆኑን በአግባቡ መገንዘብ አለመቻሉ ለግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ ውጤታማነት ዋነኛው ተግዳሮት ሆኗል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱን የግብር ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፋፊ ሥራዎች ተጀምረው ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም መታየት ጀምረዋል። ይብዛም ይነስ ዜጎች ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታቸው እንደሆነ ከመረዳት አልፈው፤ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በስፋት ሲንቀሳቀሱ እየተስተዋለ ነው። ለዚህ ደግሞ በግብር መክፈያ ቢሮዎች የሚታዩ ሰልፎችን መመልከት በራሱ ከበቂ በላይ ነው።
በእርግጥ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ ከመጣበት ኋላቀር አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከወለደው አሰራር የተነሳ ፣ ግብር ለመክፈል ዜጎች ያልተገባ እንግልት እያጋጠማቸው ቢሆንም ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግብርን ለመክፈል የተፈጠረው መነቃቃት ፣ ግብር ሰብሳቢ ተቋማትን አሰራር በማዘመን ፤ አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ የግብር ሥርዓት ለማዘመን የተሻለ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል።
ግብር ሰብሳቢ ተቋማትም ቢሆኑ ራሳቸውን ከማዘመን ባለፈ ኅብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን መነቃቃት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ ተልዕኳቸውን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥርዓቶችንና አሰራሮችን በመፍጠር ፤ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍ ያለ የአገልግሎት ርካታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
ቀጣይነት ያለው ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችንና ንቅናቄዎችን በመፍጠር ዜጎች ግብር ከመክፈል ባለፈ የከፈሉት ግብር በአግባቡ የእነርሱን ሕይወት እና የሀገራቸውን እጣ ፈንታ በሚለውጡ የልማት ሥራዎች ያለስርቆትና ብክነት መዋሉን የማረጋገጥ መነቃቃት የሚፈጥሩበትን አሠራር መገንባት ይኖርባቸዋል። ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት በየትኛውም መንገድ በግብር ሰብሳቢ ተቋማት ቢሮክራሲያዊ አሰራር ለፈተና መዳረግ የለበትም።
ግብር ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስኬት ለሚያስፈልገን ከፍ ያለ ሀብት ዋንኛ አቅም ከመሆኑ አንፃር ግብር ሰብሳቢም ሆኑ መላው ሕዝብ በግብር እና ውጤታማ በሆነ የግብር አሰባሰብ ዙሪያ ከፍያለ ትኩረት ሰጥቶ በንቃት በመንቀሳቀስ የበለጸገች ሀገር የመፍጠር ሀገራዊ ራዕይን ተጨባጭ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015