በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከቀደምት ጋዜጦች ለትውስታ ያህል ከሁለት የተለያዩ ሰፊ ዓምዶች ግርምትን የሚፈጥሩ ታሪኮችን መርጠናል። ገንዘብና ዝና ለማግኘት መስተዋት እበላለሁ፣ የዳቦ ነጋዴዎች እየቆመሩብን ነው.. የመረጥናቸው ሃሳቦች ሲሆኑ ከሳምንቱ አጋጣሚዎች ሁለቱን ለቅምሻ ያህል አክለን እንደሚከተለው ልናስታውሳችሁ ወደናል።
“…ገንዘብና ዝና ለማግኘት መስታወት እበላለሁ”
በዓለማችን ለትውልድ የሚተርፍ አኩሪ ተግባር የፈጸሙ ልዩ ተሰጥዖና ተደናቂነትን ያተረፉ ከሞቱ በኋላ እንኳን ስማቸው ዛሬም ገኖ የምንሰማው ተሰምቷል። እናም ባልተጠና መልኩ ወደ አደባባይ ብቅ የሚሉ እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች በጀብደኝነት የሚከተሏቸው ወጣቶች እንደማይጠፉ ሊታወቅ ይገባል።
………….
በሀገራችን እራሳቸውን ከሞትና ከአደጋ ጋር አፋጠው መጨረሻቸው ያላማረ ሆኖ የተገኙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ለዚህም በአንድ ወቅት በየነ የተባለ ግለሰብ ብረታ ብረትን እየቆረጣጠመ “ታዋቂነትን “ ለማትረፍ ሲል እድሜው አጥሯል። በሌላ ወቅት በአፉ እሳት ሲጎርስ፣ ምላጭ ሲውጥ የነበረ ሰውም እንዲሁ ሕይወቱ አልፏል።
……….
ሰሞኑን በአደባባይ ብቅ ብሎ “ድንቅ” ተግባሩን በማሳየት ላይ የሚገኘውን የኢሊባቦር ተወላጅ የሆነው ሐሰን መሐመድ ሐሰን የፍሎረሰንት መብራት፣ የመስታወትና የአምፖል ስብርባሪዎችን ከያዘው ፌስታል ውስጥ እያወጣ በጥርሶቹ እየከሸከሸና በውሃ እያወራረደ ሲበላ አይተናል።
በቤተሰብ ምክንያት ሰላም በማጣቱ ወደ ዓረብ ሀገር ከእህት ወንድሞቹ ጋር መሰደዱን እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃድ ባለማግኘቱ ሳይሳካለት ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ሀገሩ ለመመለስ መገደዱን ይናገራል። ይሁንና እናቱ በማረፋቸውና ሀብታም ነጋዴ ናቸው የሚላቸው አባቱ ተገቢውን ድጋፍ ስላላደረጉለት ቤተሰቡን ተቀይሞ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ይናገራል። ከሀገር ተመልሶ ወደ ውጪ ለመውጣት አማራጭ አድርጎ የወሰደው መስታወት መብላትን ነው።
……..
ከዚያስ….ከሐሰን ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ ይህን ይመስላል፡-
በአሁኑ ወቅት መስታወት ለመብላት ምን አነሳሳህ?
“መስታወት መብላት መቻሌን ለሕዝብ ለማሳየት ነው”
እኮ ለምን?
“በቃ…ኑሮን ማሸነፍ እፈልጋለሁ፤ ገንዘብ ዝና ማግኘት ይኖርብኛል።”
ታዲያ ሌሎች ዘዴዎች ለመሞከር ለምን አላሰብክም… ለምሳሌ በሩጫ በእግር ኳስ ተጫዋችነት፤ ሕዝብንና እራስህን በሚጠቅም በልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራ ታዋቂ መሆን ይቻላል?
“ለነገሩ በልጅነቴ ኳስ ጨዋታ እሞክር ነበር፤ የሚያበረታታኝ ጠፋ እንጂ በዚያ ዝነኛ መሆን እችል ነበር። አሁን ግን ለጊዜው ያገኘሁት መፍተሔ መስታወት መብላት ነው።”
……….
የወደፊት አዓላማህ ምንድነው?
“የኮብራ መስታወት ለመብላት ነው። ጠንካራውን የኮብራ መኪና መስታወት በዚህም ዝና፣ ገንዘብ ለማግኘት እሻለሁ።”
( አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 ቀን 1986 ዓ.ም)
የዳቦ ነጋዴዎች እየቆመሩብን ነው
ዳቦ-ድሮ ቀረ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ ነው። ዳቦ መጠኑ በሚያሳዝን ሁኔታ እየቀነሰ ጥራቱም እያሽቆለቆለ፣ ዋጋው ደግሞ እየተተኮሰ ይታያል።
…………..
የድሮ ዳቦ ዳቦ መልኩ ብቻ ይበቃ ነበር ብል የምን ማግነን ነው እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
………..
ወዝ የሌለው ዳቦ በየቦታው ሞልቷል። ዳቦ ከተባለ ማለቴ ነው። እንቡጥ አይገኝበትም። ያሳስራል፣ ያስቀጣል፣ ተብለው ይሆን ውሃ አጥቶ እንደደረቀ ቅጠል የሚያቆረፍዱት; በእዚህ ላይ መጠኑ በጣም እጅግ ያስገርማል። ኪኒን እያከለ መጥቷል። በእዚህ ላይ ተፈርፍሮ የሚያልቀውና ቤት የሚያበላሸው አይነሳም። የሀምሳ ሳንቲም ዳቦ ስትገዛ የሁለት ብር መጥረጊያ መግዛትህን እንዳትረሳ እየተባለ የሚነገረውም ለዚሁ አይደል፡ የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች አይነት መሆኑ ነው።
……
ዛሬ ሕጻናት ሁለት ዳቦ በልተው አይጠግቡም። እረ ይጨመርልን በሚል እያጉተመተሙ ነው ወደ ትምህርት ቤት የሚጓዙት። ገና አንድ ክፍለ ጊዜ ሳይጨርሱ ሆዳቸው ምግብ ይጠይቃቸዋል። አዋቂዎች አፋቸው ባዶ ባዶ እንዳይል ካልሆነ በስተቀር የዘመኑ ዳቦ አላረካቸውም። ግማሹ ለአፈር የተቀረው ለከንፈር በመሆኑ ከሆድ አይደርስም።
……..
የምንበላው ሳይሆን የምንስመው ዳቦ መጥቷል።
…..
የዳቦ ነጋዴዎች እስከመቼ ነው የሚቆምሩብን፡ ነዳጅ ጨመረ ሲባል በዚያው ልክ ዋጋ ይጨምሩብናል። በ20 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ዛሬ እየቀረ ነው። አንዳንዶቹ የ20 ሳንቲሙን 50 ይቀበሉበታል። ግፍ የፈሩ ደግሞ የ50 ሳንቲሙን 60 ይቀበሉበታል።
………
የዳቦ ነጋዴዎች በእኛ ስቃይ እንዴት ይከብራሉ። ባንገዛቸውስ; ሌላ መላ መፈለግ አቅቶን ነው፣ እንደኔ እምነት ግን በአንድ ሰሞን ዘመቻ ዳቦ ቤቶችን ልክ ማግባት የሚቻል ይመስለኛል። ዘንድሮስ እየቆመሩብን አይኖሩም የእስካሁኑ ይበቃል ባዮች በዝተዋል። እባካችሁ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሁሉ የዳቦ ቤቶችን አሠራር የሚያስተካክል አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ ?
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 1989ዓ.ም)
የሳምንቱ አጋጣሚዎች
ውስኪ በመወደዱ ምክንያት ብዙ ሰዎች አረቄ እየተለማመዱ ናቸው። ብዙዎች ውስኪ በመጥፋቱ ተናደዋል። እኔ ግን ሜታ ቢራን እወድ ስለነበረ በአካባቢዬ በመጥፋቱ የጎንደርን ጠጅ በግድ እየተለማመድኩ በዚህ ሳምንት አራት ብርሌ ጠጥቻለሁ።
እንዳለ ቶለሳ
ከብርድ ልብስ ተራ
ከባልንጀራዬ ጋር መጠጥ ጠጥተን በጣም ሰክረን ነበር። ታዲያ ከማስታውሰው ጨዋታ አንዱ ባልንጀራዬ ወደ ውጪ ሊወጣ ሲል ስለተንገዳገደ “አንተ ጠርሙስና ብርጭቆውን እንዳትሰብር “ ብለው “ዶሮ እንቁላልዋን አትሰብርም“ አለኝ።
ማናዬ
ከበዴሳ
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8 ቀን 1988ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም