ኢትዮጵያ ላለፉት አራት አመታት በተከታታይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብርን ተግብራለች። በዚህም 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል።
ሀገሪቱ ሁለተኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ደግሞ ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ሀሳብ በዚህ አመት ማካሄድ ጀምራለች፤ በዚህም ዘንድሮ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመተከል ታቅዶ የችግኝ ተከላው እየተካሄደ ይገኛል።
ሀገሪቱ በመጀመሪያው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በዓለም በአንድ ጀንበር የተተከሉ ችግኞችን ክብረወሰን መስበርም ችላለች። በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ብቻ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን የተለያዩ የዛፍ ችግኞች ለመትከል አቅዳለች።
የአረንጓዴ አሻራው በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ፋይዳዎች እንዳለው እየተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን በዘርፉ ላይ እየሠሩ ያሉ አካላት ይገልጻሉ።
በአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የአፍሪካ የደንና የተፈጥሮ መፍትሄዎች አስተባባሪ ዶክተር ገመዶ ዳሌ ለተከታታይ አመታት እየተከናወነ ያለው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግብርናው ሥራ ላይ ያለውን አዎንታዊ ጎን ይጠቁማሉ።
‹‹የደን ልማት በአግባቡ በተሠራባቸው፣ የተፋሰስ ልማት ሥራም እንዲሁ በአግባቡ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የእርጥበት መጠን ይጨምራል። የእርጥበት መጠን ጨመረ ማለት ደግሞ ለግብርና ምርታማነት ቀጥታ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል የሚሉት ዶክተር ገመዶ፣ ዝናብ እንኳን ባይጥልና ድርቅም ቢከሰት በአግባቡ በተያዘ ሥነምህዳር ላይ የሚዘሩ ሰብሎችም ሆኑ ተክሎች ለውጤት ይበቃሉ። ምርትም ይሰጣሉ›› ሲሉ ይገልጻሉ።
በሁለተኛ ደረጃ ባነሱት ሀሳብ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ለአፈር ለምነት የሚጠቅሙ ንጥረነገሮች በአፈር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የአፈር ለምነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ገመዶ፣ በዚህ ሁኔታ የሥርዓተምህዳር መስተጋብር ሲሻሻል ምርታማነትም ያድጋል ወይንም ይጨምራል ይላሉ። የደን ልማት ባለባቸውና የአፈር መከላት ባጋጠመባቸው አካባቢዎች ያለው የእጽዋት እድገት ልዩነትንም በግልጽ መለየት እንደሚቻል ነው የጠቆሙት።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የዛፍ ችግኝ ተከላው የአየር መዛባትንም በማስተካከል ለእጽዋት እድገት ተስማሚ ሁኔታ ይፈጥራል፤ ምርታማነት ጨመረ የምንለው እጽዋቱ በአግባቡ በቅለውና አድገው ፍሬያማ ሲሆኑ ነው። በአጠቃላይ የደን ልማቱ ከዘር እስከ ብቅለት ያለውን ሂደት የተስተካከለ ስለሚያደርገው የደንና የደን የሥርዓተ ምህዳር መስተጋብር ምርታማነት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አለው፤ በመሆኑም የደን ልማቱ ወይንም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብሩ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ አለው።
ዶክተር ገመዶ፤ የደን ልማት መጠናከር አስፈላጊነትንም አስመልክተው እንዳብራሩት፤ የደን አፈር በጣም ለም በመሆኑ ያለማዳበሪያ በተፈጥሮ ምርት ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ ነበር። ለደን የሚደረገው እንክብካቤ በመቀነሱና በተለያየ ምክንያት የተመናመነውን ደን ለመተካት ያለው እንቅስቃሴም የተጠናከረ ባለመሆኑ ምርታማነትን ለመጨመር ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ወደ መጠቀም ግዴታ ተገብቷል።
ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ለመጠቀም ግዴታ ውስጥ የተገባውም በአፈር ውስጥ ያለው ንጥረነገር እየተሟጠጠ በመምጣቱ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህን ሁኔታም አንዳንድ አርሶ አደሮች መሬት ጉበኛ ሆነች በሚል በቅሬታ ሲገልጹ እንደሚሰማም ይጠቅሳሉ።
የደን መመናመኑ ከፍተኛ መሆኑንና በዚህም ቀደም ባሉት ወቅቶች በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደነበር የጠቀሱት ዶክተር ገመዶ፤ ለደን ልማቱ ትኩረት ባልተሰጠባቸው ወቅቶችም ብዙ ነገሮች እንደታጡ ነው ያመለከቱት።
ያለፉትን ክፍተቶች መሠረት በማድረግ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ የደን ሽፋን እንዲጨምር እየተደረገ ያለው ርብርብ አበረታች እንደሆነም ዶክተር ገመዶ አስታውቀዋል። በልማት እንቅስቃሴው ላይ መታረም ያለባቸው ነገሮች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ለውጤት የሚያበቁ ሥራዎች እየታዩ መምጣታቸው አንድ ለውጥ እንደሆነና ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ዶክተር ገመዶ የደን ልማቱ ሥራ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም ዓይነት የዛፍ ችግኝ ለግብርናው ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ መወሰድ የለበትም ሲሉም ሙያዊ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የግብርና ሥራ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች መተከል የሌለባቸውን ዛፎች መለየት ያስፈልጋል። ለአብነትም አንዱ ባህር ዛፍ ነው። ይህን ተክል በእርሻ ቦታ መትከል ማለት ውስን የሆነውን የውሃ መጠን በመውሰድ ወይንም በመሻማት በምርቱ ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር መፍቀድ ይሆናል። በእርሻ ቦታዎች የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ እንደ ግራር (አኬሺያ) ያሉ ተክሎችን ለይቶ መትከል ይመከራል።
እንዲህ ያሉ ተክሎች ከደቂቅ አካላት ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር የአፈር ለምነት እንዲጨምር ከማድረጋቸው በተጨማሪ ጥላ በመስጠትና የተለያዩ ግልጋሎቶች እንደሚያበረክቱም ይናገራሉ። ተክሎቹ በተከላ ወቅትም በጥምር ግብርና ሳይንሳዊ አሠራር ተለይተው መተከል ይኖርባቸዋል ይላሉ። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብሩ ችግኞች በሚተከሉበት ወቅት እንዲህ ያሉ ጥንቃቄዎች ካልተደረጉ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ሊያሳድሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብርን ከግብርናው ሥራ ጋር በተያያዘ ከተለያየ አቅጣጫ ማየት እንደሚቻል የገለጹት በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ታደሰ፣ በተፈጥሮና በተለያየ መንገድ የተመናመነ ደንን በሰው ሠራሽ መመለስ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ታዬ ማብራሪያ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ዓይነት ተግባሮች መጠናከር የአካባቢ ሥነምህዳርን ለማስተካከል ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው በሳይንስም የተረጋገጠ ነው። በአሁኑ ጊዜ በተፈጥሮ ሀብት መመናመን ሳቢያ የሚከሰት የበረሃማነት መስፋፋት አንዱ ተግዳሮት ነው። የካርቦን ልቀት መጠን መጨመር (ግሎባል ዎርሚንግ) ከፍተኛ የሆነ ሙቀት የሚጨምር በመሆኑ የሰብል ልማት ምርታማነትን በመቀነስና በተለያየ መንገድ ተጽእኖ ያሳድራል። ድርቅንም በማስከተል ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።
የዛፍ ችግኞችን በመትከል የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ወይንም ግሪን አግሪካልቸር (አረንጓዴ ግብርና) መፈጠር አለበት የሚለው ሀሳብ ዓለምአቀፋዊ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ታዬ፤ በኢትዮጵያ ለተከታታይ አመታት ተጠናክሮ የቀጠለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በትክክለኛው ጊዜ እየተፈጸመ ያለ እንደሆነ አመልክተዋል።
ዶክተር ታዬ ከደን ልማቱ ጋር ተጣምረው የሚሄዱ የልማት ሥራዎችንም በጥንካሬ ጠቅሰዋል። በተለይም በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ መንግሥት እንደ አቅጣጫ ይዞ ወደ ትግበራ የገባበት ደንን ከማልማት ወይንም የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ከመሥራት ባለፈ ከምግብ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ከመፍታት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሰብሎችን በተለይም አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከዛፍ ችግኝ ተከላው ጋር አካቶ መርሃግብሩ እንዲተገበር መደረጉ በመልካም ጎን እንደሚታይ ገልጸዋል።
ሌላው መርሃግብሩ ለግብርናው ዘርፍ ያለው ጠቀሜታ ብለው ዶክተር ታዬ የጠቀሱት፤ ከእንስሳት መኖ ጋር ተያይዞ ያለውን ነው። በእንስሳት መኖ አቅርቦት መሻሻልም ሆነ በምርትና ምርታማነት መጨመር በአጠቃላይ ዘላቂ የሆነ የግብርና ልማት ሥራዎችን ለመሥራት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስታውቀዋል። በአጠቃላይ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ከሰብል ልማቱ ጋር ተሳስሮ መከናወኑ ጠቀሜታው ሀገራዊ እንደሆነ በመጠቆም፣ በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ ነው ያመለከቱት።
ዘርፉ ላይ እንዳለ እንደ አንድ ተመራማሪ ለደን መመናመን ምክንያት የሆኑና እያስከተለ ያለውንም ችግር መጥቀስ ይቻላል ያሉት ዶክተር ታዬ፤ ለእዚህም በዝናብ አገባብና አወጣጥ ላይ ያለውን ክፍተት እና የሙቀት መጠን መጨመርን ለአብነት ጠቅሰዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በምርምር ሥራ ላይ በተደጋጋሚ ከሚነሱት መካከልም በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ምርትና ምርታማነት ላይ የራሱን ጫና ስለሚያሳድር ለውጥን መቋቋም የሚችል የአመራረት ዓይነት (ክላይሜንት ሪዚላን)፣ የወቅቱን የአየር ንብረት በመቋቋም የምርት መቀነስ ችግር እንዳያጋጥም ማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች መኖራቸውን ነው።
አሁን እየታየ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ቀደም ሲል በአካባቢ ላይ በተፈጸመው ውድመት ምክንያት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ታዬ፣ ችግሩ በቀጠለ ቁጥር ጫናው አሁን ካጋጠመው በላይም ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ጫናውን መቀነስ የሚቻለው ተፈጥሮን በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ ከተቻለ ብቻ እንደሆነም አመልክተዋል።
እየቀነሰ ለመጣው የመሬት ለምነት፣ እየታየ ላለው የዝናብ እጥረት መፍትሄ ማስቀመጥ፤ የሙቀት መጨመርን መቀነስ ካልተቻለ የሰብል ምርትም ሆነ የተለያዩ ልማቶችን ማከናወን አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም አስገንዝበዋል። ምርምር ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሠራና ቴክኖሎጂንም ማምጣት ቢቻል ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከጠፋ በኋላ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቀርቶ ባለው ሁኔታም ለመቀጠል የማያስችልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ፤ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ለግብርናው ዘርፍ የሚኖረው አስተዋጽኦ ዘርፈብዙ መሆኑን ያመለክታሉ። የደን ሽፋንን ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት የውሃ ሽፋን እንዲጨምር እንዲሁም የከረሰምድር የውሃ ስርገት ወይንም ማቆር መጠን ከፍ እንዲል ለማስቻል መሠረት መሆኑን ይገልጸሉ። ዶክተር ይፍሩ፣ መርሀ ግብሩ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ በአጠቃላይ ለሕይወት ወሳኝ እንደሆነም ነው የገለጹት።
‹‹ለዝናብ ምንጭ የሆነው ደን ሲኖር ዝናብ አለ ማለት ነው። ዝናብ ካለ ደግሞ እርሻ አለ ማለት ነው። በቂ ዝናብና ሥነምህዳሩ የተስተካከለ መሬት ሲኖር ጥሩ ምርትም መሰብሰብ ይቻላል። የዝናብ መቆራረጥ ሳይኖር በመኸር፣ በበልግና በበጋ ለሚከናወነው ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ወንዞች ከአመት አመት ውሃ መያዝ ሲችሉ በመስኖ የሚከናወነውን የግብርና ሥራ ከማገዙ በተጨማሪ የግብርና ሥራውን ለማዘመንም ፋይዳው ላቅ ያለ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር ይፍሩ ማብራሪያ፤ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ያላቸው ሀገራት በፈጠሩት የአየር ንብረት ለውጥ ወይንም ወደ አየር በሚለቁት በካይ ጋዝ (የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት) የተነሳ ኢትዮጵያም ተጎጂ እየሆነች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በተከታታይ አመታት እያከናወነች ያለው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ይህ ትልቅ ቀውስ እየፈጠረ ያለውን የአየር ንብረት መዛባት ለመከላከል ከፍ ያለ ፋይዳ አለው።
ኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ መርሃግብሩን በመተግበር በረሃማነትን ለመከላከል እያደረገች ያለችው ጥረት ከራሷ አልፎ ለክፍለ አህጉሩ በአጠቃላይ ለዓለም ጭምር ይጠቅማል። ይህ ሁሉንም ለመታደግ እያደረገች ያለችው በጎ ተግባር ያስመሰግናታል።
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን አስመልክቶ ዶክተር ይፍሩ እንደገለጹት፤ በደን ውጤቶች ላይ የሚሳተፉ ባለሀብቶችን ለመሳብ ይረዳል። የደን ሽፋኑ በጣውላ ምርት የተለያዩ መገልገያዎችን በመሥራት ለገበያው ለሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎችም ግብአት በመሆን፣ እንደሀገርም ከውጭ በግዥ የሚገባውን በመተካት በሀገር ምጣኔ እድገት ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በየተፋሰሱ እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ይፍሩ፤ የዓባይ ግድብን ጨምሮ ሐይቆች በደለል እንዳይሞሉ ያስችላል ብለዋል።
ለተከታታይ አመታት እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ መርሃግብር የግብርና ሥራውን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ያለው አበርክቶ በተለይም የአፈር መከላትን በምን ይህል እንደቀነሰ፣ ጎርፍን በመቀነስ ምን ያህል እንደተከላከለ፣ ከተተከሉት ችግኞች ምን ያህሎቹ እንደጸደቁና ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ ጥናት ለማካሄድ የያዘውን እቅድ ለመተግበር የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት ሁኔታ እየጠበቀ እንደሆነ ዶክተር ይፍሩ ጠቁመዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2015