በፈጠራ ሥራዎቿ ለሴቶች ምሳሌ የሆነችው እንስት

 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለስምንት ዓመታት በበረራ አስተናጋጅነት አገልግላለች። በዚህም የተለያዩ ሀገራት የመዘዋወር እድል ገጥሟት የውጪውን ዓለም እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል በሚገባ ለመረዳት ችላለች። ይህ ልምድና በውጭ ያየችው ተሞክሮ ወደራሷ ቢዝነስ ፊቷን እንድታዞር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎላታል። ያኔ በትንሹ የጀመረችው መሰረታዊ የኮምፒዩተር እውቀት ማስተማርና የህትመት ሥራ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ወደ ኮምፒዩተር አስመጪነት አሸጋግሯታል።

አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር ሁሌም የማይቦዝነው አዕምሮዋ በሴቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሁለት ልዩ የፈጠራ ሥራዎችን እንድታፈልቅ አስችሏታል። እነዚህ የፈጠራ ሥራዎቿ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተመዝግበው ቀጣዩን ሂደት እየተጠባበቁ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ ማህበረሰቡ ላይ ትኩረቷን በማድረግ ሞዴል ከተማ ለመገንባት ‹‹ዜሮ አንድ ግሪን ቪሌጅ›› የተሰኘና ማህበረሰቡ የተሟላና የዘመነ አገልግሎት የሚያገኝበት መንደር የመገንባት ዓላማ የያዘ ፕሮጀክት ቀርፃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች።

ይህች ሴቶች በራሳቸው ጥረት በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንደሚችሉ ምሳሌ የሆነች፣ የአዳዲስ ሥራ ፈጠራዎች ባለቤትና የተለየ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ይዛ ብቅ በማለት ህልሟን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገች የምትገኘው የዛሬው የሴቶች አምድ እንግዳችን የኖታ ኮምፒዩተር ንግድ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቃልኪዳን መሸሻ ናት።

ወይዘሮ ቃልኪዳን ውልደቷና እድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በመሰረተ እድገት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮልፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ደግሞ በቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ገብታ በሴክሬታሪያል ሳይንስ ትምህርቷን ተከታትላ በዲፕሎማ ተመርቃለች።

በመቀጠል በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥራ የሥራውን ዓለም ተቀላቅላለች። በዚህ ተቋም ለስምንት ዓመታት አገልግላለች። በዚህ የአገልግሎት ዘመኗ የውጭውን ዓለም የማየት አጋጣሚ ተፈጥሮላታል። በበርካታ ሀገራት ተዘዋውሮ የመሥራት እድልም ተፈጥሮላት ስለነበር ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴው ምን እንደሚመስል በሚገባ ለማየት ችላለች፤ ሰፊ ልምድም ቀስማበታለች። በተለይ ደግሞ እነ ቻይናና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችን የመሳሰሉ ሀገራት ከትንሽ ተነስተው እንዴት ራሳቸውን እንዳሳደጉ በቅርበት ለመረዳት ችላለች።

ቻይናና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በአጭር ጊዜ እንዳደጉት ሁሉ ኢትዮጵያን በማልማት ሂደት ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ የሚውል ከሆነ ሀገሪቷ በርካታ ሀብት ስላላት በኢኮኖሚ ራስን የማሳደግ ሰፊ እድል እንዳለ በበረራ አስተናጋጅነት ሥራዋ ተገንዝባለች። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሥነ-ምህዳር ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ቀጠና በመሆኑ ይህ ቀጠና ሀገሪቷን በኢኮኖሚ ሊለውጥ እንደሚችልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ሚስጥርም ይኸው ሀገሪቱ የምትገኝበት ወሳኝ ቀጠና መሆኑን በሚገባ አውቃለች።

ወይዘሮ ቃልኪዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ተቀጥራ የመሥራት እድል በማግኘቷ በጊዜው ጥሩ ገቢ ማግኘት ችላለች። ለስምንት ዓመታት በዚህ ተቋም ከሰራች በኋላ ሥራዋን አቋርጣ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀለች። ከሃያ ዓመት በፊት በቆጠበቻት አነስተኛ ገንዘብ አዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ የማስታወቂያ ህትመት ሥራ ጀመረች። በሂደት ሥራውን በማሳደግ የኮምፒዩተር መሰረታዊ እውቀት ማስተማር ቀጠለች። በሂደት ደግሞ የተለያዩ ኮምፒዩተሮችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት ወደ መሸጥ ተሸጋገረች።

በኋላ ደግሞ ባለቤቷ ከባንክ ገንዘብ በመበደር የግንባታ ማሽነሪዎችን እያከራየ ይደግፋት ጀመር። ባለቤቷ ብርቱ የንግድ ሰው በመሆኑና የቤተሰቡን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ወስዶ ልጆቻቸውን በማሳደግ ጭምር ትልቅ እገዛ ስላደረገላት ትኩረቷን በፈጠራ ሥራዎች ላይ አተኮረች። በአሁኑ ጊዜም ይበልጥ ውጤት አመጣበታለሁ ያለቻቸውን ሁለት የፈጠራ ሥራዎችን ሰርታለች። የፈጠራ ሥራዎቿ መነሻዎችም ያየቻቸው ችግሮች ናቸው።

አንደኛው የፈጠራ ሥራዋ የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ ሲሆን ከጊዜያቸው ቀድመው ለሚወለዱ ህፃናት ሙቀት እንዲያገኙ የሚያስችል መሣሪያ ነው። የሥራ ፈጠራው በአብዛኛው በሆስፒታሎች ጥቅም ላይ የሚውለውን የጨቅላ ህፃናት ማሞቂያ መሣሪያ የሚተካና እናቶች በአነስተኛ ወጪ በቀላሉ በራሳቸው እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ነው። የመብራት መቆራረጥ ባሉባቸውና የህፃናት ማሞቂያ እንደልብ በማይገኙባቸው የጤና ተቋማት አካባቢ የሚታየውን ችግር በመፍታት ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

የሥራ ፈጠራው ዲዛይን የተዘጋጀው የህፃናት ማቀፊያ ቦርሳዎችን በማመሳሰል ሲሆን ከማዘያው ከጀርባ ላይ ህፃናትን ሊያሞቃቸው የሚችል የተለያዩ ክፍሎች አሉት። ይህ ሙቀት ህፃናቱ የሚፈለገው የክብደት መጠን እስከሚደርሱ ድረስ በእንክብካቤ እንዲድጉ ያስችላል። ይህ ሙቀት የሚነጨውም ከማቀፊያው ቦርሳ ከሚመነጭ የጎንዮሽ ጉዳት ከማያመጣ ኬሚካል ፓውደር ነው። የማሞቂያ ማቀፊያ ቦርሳው ከመሞቁ በፊት በተገቢው የሙቀት መጠን ደረጃ ላይ በመገኘት ሙቀቱን ለህፃኑ መስጠት ሲያስፈልግ ከጀርባው ያለውን ማስጀመሪያ በመጫን ሥራ ላይ የሚውል ነው።

ወይዘሮ ቃልኪዳን ይህን የፈጠራ ሥራዋን በማበልፀግ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ የፈጠራ ሥራዋ በዋነኛነት የእናቶችንና ህፃናትን ሕይወት ሊያግዝ የሚችል ሲሆን የሥራ ፈጠራውን ከራሷ ልጆች በመነሳት አበልጽጋለች። በአሁኑ ጊዜም የፈጠራ ሥራው ወደ ገበያ እንዲገባና እናቶች እንዲጠቀሙበት የክሊኒካል ፍተሻ ሂደት ውስጥ ይገኛል። በዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ ካሉ የጤናው ዘርፍ አካላት ማበረታቻና ድጋፍ አግኝቷል። ሥራው በተለይ በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ እናቶች በነፃ ቀርቦ እንዲገለገሉበት ትልቅ ተስፋ ሰጥቷል።

ሁለተኛው የወይዘሮ ቃልኪዳን የፈጠራ ሥራ ደግሞ የዋና ላይ ደህንነት የሚያስጠብቅ መሣሪያ ሲሆን ይህም የፈጠራ ሥራ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተመዝግቦላታል። ለዚህ የፈጠራ ሥራ መነሻ የሆኑትም በአዲስ አበባ ከተማ ባለ አንድ ታዋቂ ሆቴል ውስጥ የአንድ ታዳጊ ሕይወት በዋና ገንዳ ውስጥ ገብቶ መስጠም ዜና ነበር።

ይህ የፈጠራ ሥራ የዋና ገንዳዎች ሲሰሩ ውሃ ከመሞላታቸው በፊት ከስር መረብ እንዲወጠር በማድረግ የሚሰራ ሲሆን ህፃናት ሲዋኙ ድንገት ቢሰምጡ ሕይወት አዳኝ ጠላቂዎች ሳይኖሩ ወይም ጠላቂዎቹ የሰመጠውን ሰው ገና ፈልገው እስኪያገኙ ድረስ በአውቶማቲክ ማብሪያና ማጥፊያ አማካኝነት በቅፅበት የሰጠመውን ሰው ወደላይ ማውጣት ያስችላል። በሂደት ደግሞ የፈጠራ ሥራው ይበልጥ ሲበለፅግ ሰዎች ሲሰጥሙ በዋና ገንዳው ውስጥ በተገጠመ ሴንሰር አማካኝነት በመረቡ ወደላይ ተስበው እንዲንሳፈፉ ያደርጋል።

ወይዘሮ ቃልኪዳን የፈጠራ ሥራዎቿን ከአንድም ሁለት ጊዜ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ለውድድር አቅርባዋለች። በነዚህ የሥራ ፈጠራዎቿም በተለይ ከውጭ ሀገራት የተለያዩ ድጋፎችን አግኝታለች። ሆኖም ያገኘቸው ድጋፍ(ፈንድ) በቂ ባለመሆኑ የሥራ ፈጣራዎቿን ለማጎልበት ብዙም አልጠቀማትም። ይሁንና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎቿን በአብዛኛው በራሷ ወጪ እያከናወነች ትገኛለች።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከተሞች ቢያድጉና ቢለሙ ለብዙ ሰው የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ በማሰብ ‹‹ዜሮ አንድ ግሪን ቪሌጅ›› የተሰኘና ማህበረሰቡ የተሟላና የዘመነ አገልግሎት የሚያገኝበት መንደር የመገንባት ዓላማ የያዘ ፕሮጀክት ቀርፃ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህ ፕሮጀክት በዋናነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መንደሮች በውስጣቸው አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በዘመነና በበቂ ሁኔታ ተሟልተውላቸው ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል።

በዚሁ ፕሮጀክት መነሻነት የማህበረሰብ ልማት ሥራዎችን እያከናወነች የምትገኘው ወይዘሮ ቃልኪዳን ሞዴል የሆነ ከተማ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በ23 ሄክታር መሬት ላይ ማህበረሰቡን በማስተባበር የመገንባት ህልም ይዛ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ትገኛለች። ለዚህ ሥራም የአክሲዮን ማህበር ተቋቁሟል። የዚህ ማህበር ዋነኛ ተግባርም ራሱ ከማህበረሰቡ ገቢ በማሰባሰብ ሁሉን ያሟላ ሞዴል ከተማ መገንባት ነው። ይህ ሞዴል ከተማ የገበያ ማእከል፣ የመዝናኛ ስፍራ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የህክምናና የትምህርት ተቋማት፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና ሌሎችንም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ያካትታል።

ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ በማህበረሰቡ በኩል ሰፊ ድጋፍ አግኝቷል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግበት ወረዳ በኩልም ተቀባይነት አግኝቷል። በቀጣይ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው አካላት ሲሄድ ደግሞ ጥሩ ምላሽና ድጋፍ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የተቋቋመው ማህበርም ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ለማግኘት ቀጣዩን ሂደት እየተጠባበቀ ይገኛል።

ወይዘሮ ቃልኪዳን የፈጠራ ሥራዎቿ ላይ እየተጋች፤ የኮምፒዩተር ንግዷንም እያቀላጠፈች ከትምህርቱ ዓለም ሳትወጣ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ሊድስታር ዩኒቨርሲቲ አሽላድ በተሰኘ የአዲስ አበባ ወኪሉ አማካኝነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። በኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛለች። በድጋሚ ደግሞ የሶስተኛ ዲግሪዋን በዚሁ የኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት የትምህርት ዘርፍ እየሰራች ትገኛለች።

በቀጣይ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎቿን ለፍሬ የማብቃት እቅድ አላት። የፈጠራ ሥራዎቿ ወደ ምርት ተሸጋግረው ከሀገር ውስጥ አልፈው ወደ ምስራቅ አፍሪካና ወደሌሎችም የዓለም ገበያዎች እንዲገቡ የማድረግ ውጥንም ይዛለች። የዋና ደህንነት ፈጠራ ሥራው ከአፍሪካ የመጀመሪያ ፈጠራ ስለሆነ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የማሻገር ሃሳብ ይዛለች። ከዚህ ባለፈ ሰዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ አዳብረው ራሳቸውንና ወገኖቻቸውን እንዲረዱ ማህብረሰቡ ላይ በስፋት የመሥራት ፍላጎት አላት።

ልክ እንደርሷ ሁሉ ሌሎች ሴቶችም በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉና የተለያዩ ሥራዎችን በመፈጠር ራሳቸውን እንዲለውጡ መጀመሪያ እንደሚችሉ ማመን አለባቸው ትላለች ወይዘሮ ቃልኪዳን። ሁሉም ሴቶች በተፈጥሮ የተሰጣቸው የየራሳቸው ብቃት አላቸውና ይህ ድንቅ ተፈጥሯዊ ብቃት እንዳላቸው ማመን እንደሚገባቸውም ትጠቁማለች። ከዚህ አኳያ እነርሱ በራሳቸው እንደሚችሉና ከሌሎች ጋር ሲተባበሩ ደግሞ ይበልጥ ከራሳቸው አልፈው ማህበረሰቡን ሊለውጡ እንደሚችሉ ትናገራለች። ስለዚህ ሴቶች ከዚህ እሳቤ ተነስተው ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ መልእክቷን ታስተላልፋለች።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *