ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የቱንም ያህል በጥቃቱ ቢጎዱ ችግራቸው በአደባባይ እንዲወጣ አይፈቅዱም። ሌላው ቀርቶ በቤተሰባቸው እንዲሰማባቸው እንኳን አይሹም። ብዙ ጊዜ በደላቸውን የግል ምስጢር አድርገው መውሰድ ይቀናቸዋል። ምክንያቱም ማኅበረሰቡ መልሶ እነሱን እንደ ጥፋተኛ የሚቆጥርበት፤ መጠቋቆሚያ የሚያደርግበት ሁኔታ ሰፊ ነው።
ጋዜጠኞች ጥቃትን የሚዘግቡበት ሂደትም በራሱ ክፍተት አለው። የተጠቂዋን ችግር በማጉላት የበለጠ መጠቋቆሚያ እንድትሆን የሚያደርግ ልክ ያልሆነ አካሄድ ይንፀባረቅበታል። ሚዛናዊም አይመስልም። ነገር ግን የጥቃት ዘገባ መፍትሄ አመላካች እንጂ ችግር አጉሊ ብቻ መሆን የለበትም። ይሄ ሀሳብ የተንሸራሸረው በቅርቡ በኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር እና በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ የጥቃት ሰለባ ሴቶች ታሪክ ተቀንጭቦ ቀርቧል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ታሪክ እንዴት መዘገብ እንዳለበትም ተነስቷል። እኛም በመድረኩ ያገኘናቸውን ጋዜጠኞች፤ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችንና ባለሙያዎችን በማነጋገር ትንሽ ልንላችሁ ወደናል። ወጣት ሕይወት በለጠ በአንድ ፍርድ ቤት የችሎት ፀሐፊና ፋይል አቅራቢ ሆና ትሠራ ነበር። ሥራዋ ለሦስት ዳኞች ሲሆን፤ አንደኛው በማታውቀው ምክንያት ለእሷ ጥሩ አመለካከት አልነበረውም። ሁልጊዜም በሁለቱ ዳኞችና ተገልጋዮች ፊት ብቃት እንደሌላትና ለቦታው እንደማትመጥን በመጥቀስ ሥራዋን አጣጥሎ ይሰድባታል።
«በየዕለቱ የማስበው ስለሥራዬ ሳይሆን ዳኛው ምን ብሎ ሊሰድበኝ እንደሚችል ነበር» ትላለች በስድቡ ስትሸማቀቅ መኖሯንና ሥነ ልቦናዋ በብርቱ መጎዳቱን ስታስታውስ። አንድ ቀን ሰው በሌለበት ጠብቃ ለምን እንደሚሰድባት ብትጠይቀውም እርሱ ግን እንደ ልማዱ አጣጥሎና ሰድቦ እንደመለሳት ትናገራለች። ሆኖም ተገልጋዩ ሥራ የማይችለውና የማይረባው እሱ መሆኑን ስለሚነግራት ሳትደብቅ ስለማንነቱ ትነግረዋለች። የዚህን ጊዜ በመካከላቸው ጸብ ይፈጠራል። ሰዎች ተሰብስበውም ገላገሏቸው። ይሁንና የችግሩ ፈጣሪ እርሷ ተደርጋ በዘገባውም ሆነ በዳኝነቱ ለእርሱ እንዲታይ ሆኗል። ይህ ደግሞ የፈጠረባት ጫና ቀላል እንዳልነበር ታስታውሳለች።
ወጣት ሕይወት እንደምትናገረው፤ ተገዶ መደፈር ጎልቶ ቢወጣም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችም ቀላል አይደሉም። ፈርጀ ብዙ ናቸው። አንዱ በሰው ፊት መስደብና ማዋረድ፤ ዝቅ አድርጎ መመልከት፤ ላለችበት ደረጃና ብቃት እውቅና አለመስጠት ነው። በሰው ፊት መሰደብና ዝቅ ተደርጎ መታየት ደግሞ ሞራል ይነካና ቅስም ይሰብራል። የሥራ ተነሳሽነትን ይቀንሳል። ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ይዳርጋል። ስለሆነም ሰዎች ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብተው ብዙ ሴቶችን ከጥቃቶች መከላከል አለባቸው።
«ጥቃቱን ያደረሰብኝ ለቤተሰቦቼ እንደ ዘመድ የሚታይና አዘውትሮ ቤታችን የሚመጣ ሰው ነው» ስትል የነገረችን ሌላዋ የጥቃት ሰለባ ስሟም ለደህንነቷ ሲባል እንዲቀየር ያደረግናት ኤምራኬብ ተስፋዬ ናት። ቤተሰቦቿ በሰው ቢያውቁትም ለእሷና ለእነሱ ቅርበቱ ካስተዋወቀው ሰው በላይ ሆኗል። እሷ ሳቂታና ቀልደኛ፤ እሱም እንዲሁ በመሆናቸው ጥሩ ተግባቦት እንደነበራቸው ትናገራለች።
ያስተዋወቃቸው ሰው በመካከላቸው ሲኖርም ተግባቦታቸው ወጣ ብሎ ሻይ ቡና እስከ ማለት ይደርሳል። ይሄን የወንድ ጓደኛዋም አሳምሮ ያውቃል። ሆኖም በተለየ ሁኔታ አይቶም ሆነ ተቃውሞ አያውቅም። አንዳንዴ እንዲያውም እሱም አብሯቸው ሻይ ቡና ይላል። በመሐል አስቸኳይ ስልክ ተደውሎለት ሄደ እንጂ ጥቃቱ የደረሰባት ዕለት እንኳን አብሯቸው ሲበላና ሲጠጣ ነበር።
«የዐብይ ፆም መያዣ ዕለት ከወትሮው ያለፈ ነገር ይኖራል ብዬ አልገመትኩም» የምትለው ኤምራኬብ፤ በወቅቱ ያስተዋወቃቸው አብሯቸው በመኖሩ ምንም አልተጠራጠረችም ነበር። ሆኖም ውስጠ ዝርዝሩን ባታስረዳንም በስተመጨረሻ ሰውዬው በመጠጥ አስክሮ እንደደፈራት አልሸሸገችንም።
ኤምራኬብ አሁን ይሄን ምስጢር ማንም እንዲሰማባት፤ አውቆም የጣት መጠቋቆሚያ እንዲያደርጋት አትፈልግም። ለቤተሰቦቿ አልነገረቻቸውም። ሌላው ቀርቶ ምስጢረኛዬ ለምትላት ጓደኛዋ እንኳን ትንፍሽ አላለችም። ጓደኛዋንም ቢሆን ከእርሷ የሚፈልገው ነገር እንዳለ ስለምታውቅና በጥቃቱ ምክንያት ያንን ማድረግ ባለመቻሏም ዓይኑን ማየት እንኳን ስላልቻለች ሸሽታዋለች።
ከቤተሰቦቿና ከሰዎች ጋር የነበራት ግንኙነት ተቀዛቅዟል። እንደ በፊቱ ብዙ ጓደኛ የሏትም። ምስጢረኛዬ የምትላትንና እስካሁን ልትርቃት ያልቻለችውን ጓደኛዋን ትታ ብቻዋን መሆን እንደምትፈልግ ሁሉ ነግራናለች። ኤምራኬብ በደረሰባት ጥቃት ራሷን የማግለል ስሜት ውስጥ ገብታለች። ድብርት ውስጥ ነች ማለት ይቻላል።
ጥቃት ከሴትነት ጋር እጅግ ከባድና ፈታኝ ነው። ጥንቃቄ የጎደለው ዘገባ ደግሞ ጥቃቱን የበለጠ ያባብሰዋል የሚል ዕምነት ያላቸው ደግሞ ወይዘሮ ማርታ በረሄ ናቸው። ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በመገናኛ ብዙኃን የሚሰጣቸውን ሽፋን አዘውትረው የሚከታተሉ መሆኑን ይገልፃሉ። በቅርብ በነበረው ጦርነት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ራሳቸውን እንዲገልፁ ይደረግ የነበረበት አግባብ የድርጊቱን አፈፃፀም እንዲያሳዩ እስከ ማስገደድ የደረሰ ስለሚመስል ልክ አልነበረም ባይ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ዘገባ የተጠቂዋን ጉዳት የሚያባብስና ለጣት መጠቋቆሚያነት አጋልጦ የሚሰጥ ነው። ሴቷ የወደፊት ሕይወቷን ተገልላ እንድትኖር ያስገድዳታል ይላሉ።
‹‹ጥቃት በደረሰባቸው ሴቶች ዙሪያ የምንሠራውን ዘገባ ቀለል አድርገን ማየት የለብንም›› ስትል አስተያየቷን የሰጠችን ደግሞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅና ኤዲተር ጫልቱ ጎለልቻ ነች። ጫልቱ እንደምትለው፤ ሁሌ ጥቃት ስንዘግብ ከራሳችን፤ ከሴትነታችን አንፃር እያየን መሆን አለበት። ጥቃቱ እኔ ላይስ ቢሆን የደረሰው መታየትና ቤተሰቦቼ እንዲሰሙብኝ እፈልጋለሁ የሚለውን ማጤን ይኖርብናል። እኛ መታየትና ቤተሰቦቻችን እንዲሰሙብን እንደማንፈልግ ሁሉ የጥቃቱ ሰለባዎችም እንደማይፈልጉ መገንዘብ ግድ ነው።
ጫልቱ፤ ሴቷ የደረሰባት አካላዊ ጉዳት ወይም ሥነልቦናዊ ጥቃት ሊሆን ይችላል። ጥቃቱ ራሱ የሚያደርስባት ተፅዕኖ አለ። በጉዳቱ የምትሸማቀቅ መሆኗን ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በጥቃቱ ሕይወቷ የመጨረሻ ደረጃ የደረሰ ሊመስላት ይችላል። እዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ የገቡ ሴቶችም ገጥመዋት ያውቃሉ። ስለዚህ የእሷን ችግር አጉልተን ማሳየት አለብን የሚል ዕምነት የላትም። ይልቁንም ሕክምና የምታገኝበትን መንገድ፤ የሕግ ባለሙያ ሴቶች እንዴት ነው የሕግ ከለላ ሊያደርጉላት የሚችሉት፤ ሌሎች አካላትና ቤተሰቦቿ እንዴት ይጠብቋታል የሚለውን ማንሳት አለብን ትላለች።
ለደህንነቷና ለወደፊት ሕይወቷ ስንል ስሟን፤ ድምጿንና አካባቢዋን መቀየር፤ ፊቷን መሸፈን እንደሚያስፈልግ የምትገልጸው ጫልቱ፤ ጉዳቱ ዘላቂነት ያለው ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። እነርሱም ላይ አስከፊ የሥነ ልቦና ጫና ሊፈጥር ይችላልና ዘገባ ሁሉንም ማዕከል ያደረገ መሆን ይገባዋል። ዘገባችን ጥቃት ደርሶባት፤ ተገዳ ተደፍራ ማኅበረሰቡ እንዴት ነው የሚያያት ብሎ መጠየቅና የማኅበረሰቡን አሉታዊ አመለካከት መስበርም ይገባዋል ስትል ትመክራለች።
‹‹እሷ ጥቃት የደረሰባት፤ የተጎዳችው እያለች እኛ ጋዜጠኞች ነን ብለን እንዴት ነበር የተደፈርሽው፤ አንቺ እዚያ ቦታ ምን ልታደርጊ ሄድሽ ስንል ቁስሏን መቀስቀስና ህመሟን ማባባስ የለብንም ›› የምትለው ጫልቱ፤ ጥቃት የደረሰባትን ሴት ችግር መቅረፍ የምንችለው በዚህ መልኩ ስንዘግብ እንደሆነ ታስረዳለች። ቁስሏን ለሚቆሰቁስ ዘገባ ትኩረት መስጠቱ መፍትሄ እንደማያመጣም ትጠቁማለች።
አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙትና ለረጅም ጊዜ በዳኝነትና በሕግ ጉዳዮች ላይ የሠሩት አቶ ተሾመ እሸቱ በበኩላቸው ወንጀሉ ምን ያህል እንደሚያስቀጣና በአካሏና በሥነ ልቦናዋ ላይ ስለደረሰው ጉዳት በባለሙያ እንደበት እንዲገለጽ በመደረጉ ይስማማሉ። በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በተለይም አስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚያሳፍርና የሚያፀይፍ በከባድ ወንጀልም የሚያስጠይቅ የዓለም ሀገራት በሙሉ ያወገዙት ጥፋት ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ድሮም ስታወግዘው የኖረችና አሁንም በወንጀለኛ መቅጫና በተለያዩ ሕጎች እያወገዘችው ያለ እኩይ ተግባር ነው። ስለዚህም መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱ ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ያለባቸው በዚህ ቅኝት ውስጥ ሆነው ነው ይላሉ።
አቶ ተሾመ፤ የጥቃቶች መንስኤ አብዛኛው ኅብረተሰብ ለሴቶች ከሚሰጠው ዝቅተኛ ሥፍራ የሚነሳ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለሴቶች በሰውነታቸው ልክ ክብር አለመስጠት እንደሆነም ያስረዳሉ። ጉልበተኞች ጉልበት በሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉልበታቸውን የሚያሳዩበት ወንጀል በመሆኑ እየተባባሰ መጥቷል። ተግባሩን እንደበቀል መውጫ አድርጎ ወደ መውሰድም ተገብቶበታል። ለዚህም ማሳያው ባለፈው በሀገራችን በነበረው ጦርነት በሴቶች ላይ ይፈፀም የነበረው ጥቃት እንደነበር ያነሳሉ።
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፤ ወንጀሉ ተረጋግጦ ሲመጣ ፈፃሚው እንደጥፋቱ በእስርና ገንዘብ ይቀጣል። በተለይ በጦርነት ወቅት የሚፈፀመው ከዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ጋር ተያይዞ ወንጀለኛውን የሚያስጠይቅበትና የሚያስቀጣበት አግባብ አለ። ወንጀልነቱን የከፋ የሚያደርገው በተጠቂዋ ቀጣይ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው የሥነ ልቦና እና ሥነ አዕምሮ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መኖሩ ሲረጋገጥ ነው። እናም የመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ተጠቂዋ ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር መጋለጧን በሕግ እና በሥነ ልቦና ባለሙያ፤ በቤተሰቦቿና በሌሎች አካላት አማካኝነት በማስነገር ማጉላትና መፍትሄ እንድታገኝ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ሕክምና ክፍል የክሊኒካል ሳይኮሎጂስት አማረ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ለሥነ ልቦና እና ለአዕምሮ ጤና ችግሮች ተጋላጭ ናቸው። በተለይም ብዙ ጊዜ ጥቃቱ የሚደርስባቸው በጎረቤት፤ በቤተሰብ አባልና በቅርብ ሰው መሆኑ የሥነልቦና ጫናውን ይበልጥ ያጎለዋል። ለሁሉም ሰው ደስ የማይሉ ስሜቶች እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል። ከዚያም በላይ ብዙ ጊዜ የመገለል፤ የመፍራት፤ ብቻ የመሆን ስሜትን እንዲያንጸባርቁ ይሆናሉ።
ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ዝቅተኛ በራስ መተማመን ስሜትን ያዳብራሉ። የጥቃቱ ሰለባ ሴቶች አንዳንድ ጊዜም ጥቃቱ የደረሰባቸው በራሳቸው ጥፋት እንደሆነ አድርገው ይወስዳሉ። ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ማውራትም አይፈልጉም። ይህንን ደግሞ እሳቸው በሚሠሩበት በዲላ ዩኒቨርሲቲና ሆስፒታል በተደጋጋሚ እንደሚያዩት ያስረዳሉ።
አቶ አማረ፤ ጋዜጠኞች እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት የሚዘግቡበትን አስመልክተው ትዝብታቸውንም ሲያጋሩም እንዲህ ይላሉ። በወንጀለኛውና ወንጀሉ ላይ አስገድዶ መድፈርም ሆነ ሌላው ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ዘገባ የጥቃቱን ሰለባዎች ስሜት የበለጠ የሚያባብስ ነው። በእነሱ ላይ የሚደርሰውን ጫናም ታሳቢ አያደርጉም። ምክንያቱም ትኩረት ሲያደርጉ የሚታየው የደረሰባቸው ጥቃት ላይ ብቻ ነው።
ጥቃቱ እንዴት እንደደረሰባቸው መጠየቅ አግባብ ቢሆንም በተለይ ተገድደው የተደፈሩ ሴቶች የሚጠይቁበት አግባብ ዳግመኛ ስቃዩን የሚያባብስ ሊሆን አይገባም። ምስላቸውና ድምፃቸው እንዲሁም አካባቢያቸው የማይደበቅበት ሁኔታም አለ። ይሄ ደግሞ ጥቃቱን ያልሰሙት ሁሉ እንዲሰሙና ጣት መጠቋቆሚያ እንዲያደርጓቸው ያስገድዳል።
በተለይ ገና ከጥቃቱ ባላገገሙበት ሁኔታ ስለ ሁኔታው እንዲተርኩ ማድረግ በአዕምሯቸውና በሥነ ልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ሙሉ በሙሉ ካገገሙና ጥቃቱ ካደረሰባቸው ስሜት ከወጡም በኋላ ወደ ጥቃቱ ትውስታ መመለሱ ጤናቸውን ያቃውሳል። ስለሆነም ጋዜጠኞች ዘገባቸውን ሲሠሩ ከተጠቂዎቹ ይልቅ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ጥቃት በማንም ሊደርስ የሚችል መሆኑን ተገንዝቦ እንዳያገል፤ መጠቋቆሚያ እንዳያደርጋቸው፤ ማኅበረሰቡን ማስተማር ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ያጋራሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2015