አንበሳ አውቶብስ ውስጥ ቁጭ ብየ ወደ ሥራ እየሄድኩ ነው። እንደእኔ በአንበሳ አውቶብስ የተመላለሰ ሰው በአዲስ አበባ ምድር አለ አልልም። እንዴትም ብኖር የዚህን አውቶብስ ውለታ እንደማልከፍለው አውቃለሁ።
ቅዳሜም አላርፍም። እረፍቴ አንድ እሁድ ናት እሷንም ለብዙ ነገር ነው የማብቃቃት። እንደዛም ሆኖ በቅታኝ አታውቅም። ከዛኛው እሁድ ወደዚኛው እሁድ የተሸጋገሩ በርካታ ጉዳዮች አሉኝ። ከነገ ወደሚመጣው እሁድም የማሻግራቸው አሉ። ባስ ውስጥ ሆኜ አስባለሁ። ስለትናንት ስለዛሬ ስለነገ።
አውቶብሱ ውስጥ ብዙ አይነት ድምጾች ይሰማሉ። የማለዳ ድባብ ለሁሉም አንድ አይነት አይደለም። ደልቶት የነቃ አለ፣ ግድ ሆኖበት የተነሳ፣ የጣመ በልቶ የሚያዛጋ፣ ባዶ ሆዱን የሚያቅራራ የማለዳ መልክ ብዙ አይነት ነው። ፊቱን እሬት እንደጠጣ ሰው አጎምዝዞ፣ ውሃ ባልነካው እዳሪ ፊት አጠገብህ መጥቶ የሚሰነፍጥ ትንፋሹን የሚያጋራህ አለ። ምን የመሰለ ቀን ሙሉ የሚታወስ ውብ ጠረኗን ይዛ፣ መንገጭላዋ ስር ከሚላመጥ ማስቲካዋ ጋር ጎንህ ቆማ የምትታከክህ ውብ አይናማ አትጠፋም። መቆሚያ ያጣ እግሩን እግርህ ላይ አነባብሮ ፍቅረኛህን ልታገኝበት በሌለ ኑሮ ውድነት ሰላሳ ብር አውጥተህ ያስጠረከውን የክት ጫማህን አቆሽሾ ቀን ሙሉ እንድትነጫነጭ የሚያደርግህም አለ። በሰበቡ ልትወዳጅህ አስባ መላወሻ ያጣች በመምሰል አንገትህ ውስጥ ሰምጣ በውብ ትንፋሿ የምታሞቅህ የአዲስ አበባ ልጃገረድ አትጠፋም። መንገድህን የሎጥ የምታደርግልህ ሳዱላ። በዛው ልክ ‹ምን ያጋፋሃል፣ ኧረ እግሬን ረገጥከኝ፣ ኪሴ ሊገባ ነው እንዴ? የሚሉ አዛውንትና ወጣት የቁጣና የእርግማን ድምጾች የአውቶብስ ውስጥ ትዝታዎቼ ናቸው።
አውቶብስ ውስጥ በልጋግ ያጌጠ እድፋም ፊት ማየት አዲስ ነገር አይደለም። አይኖቹን በቢጫ በአይናር ቀልሞ፣ የአፉን ግራና ቀኝ በለሀጭ አትሞ፣ አምስት መቶ ሜትር የሚሰነፍጥ የአፍ ሽታውን አውቶብሱ ውስጥ ላሉ ሁሉ የሚያዳርስ አይጠፋም። ያን ፊት እና ያን ጠዋት የሚያስረሳ የቆንጆ ሴት ውብ ፈገግታም እጣ ፈንታህ ነው። የሆነው ሆኖ.. አንበሳ አውቶብስ በኑሮ ውድነት ብቻውን ለሚያወራው ለአዲስ አበቤ ህዝብ ባለውለታው ነው።
የታደለ አጠገቡ ካለ ሰው ጋር ያወራል። ያልታደለ ከራሱ ጋር እያወጋ እስከሚሄድበት ይሄዳል። አንደበቱን ለጉሞ ከራሱም ከሌላውም ጋር የተኳረፈ ፊት ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ኢትዮጵያን ነፍስ አበጅታ የምታያት አንበሳ አውቶብስ ውስጥ ነው። ሀብታሙ፣ ድሃው፣ የጎዳና ተዳዳሪው፣ የቸገረው ያልቸገረው የአንበሳ አውቶብስ ታሪክ አለው። የትም ያላገኘውን የቆንጆ ሴት ዳሌና አጎጤ ለመታከክ ከቤት መኪናው ይልቅ ግፊያ የበዛበትን አውቶብስ የሚመርጥ ሰው እንዳለ በልምዴ ያረጋገጥኩት እውነት ነው። መቆሚያ ጠፍቶ፣ አንዱ በአንዱ ላይ ተደርቦ ሥራ የሄድኩባቸው ቀኖች ብዙ ናቸው። አፍ ለአፍ ገጥመው አውቶብሱ ወዲያና ወዲህ ብሎ እስኪያሳስማቸው ድረስ የሚሆነውን በጸጋ የሚቀበሉ መንገደኞች ቤት ይቁጠራቸው። እኔን እንኳን ከስንቱ አሳስሞኛል። ብዙዎችን አስተዋውቆ ጎጆ እንዳላስወጣ ብዙዎቹንም አጋራቸው ፊት ከሌላ ሰው ጋር አሳስሞ ያፋታቸው አሉ። በዘመኔ ከሳምኩት ከንፈር ሁሉ ዛሬም ድረስ ጣዕሙ ከአፌ ያልተለየው የአንዲት ቆንጆ ልጅ ከንፈር ነው። የሆነ እለት በሞላ አውቶብስ ወደሥራ ስሄድ መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ተጫኑ። አንዲት እድሜዋ ሃያዎቹ ግድም የሚንቀዋለል መልከኛ ሴት ካለሁበት መጥታ ጉያዬ ውስጥ ውድቅ አለች። እጆቼን ዘርግቼ የአውቶብሱን ብረት ግራና ቀኝ ጨብጫለው። ደረቴ ለማቀፍ እንዲመች ሆኖ ተንጣሏል። እዛ ደረት ላይ አንዲት ቆንጆ ሴት ወደቀችበት። እጆቼ ስለተዘረጉ እንዲያቅፏት ሆነው ነበር። ጉያዬ ውስጥ ሆና እስኪበቃን ተሳሳምን። አለማፈሯ ዛሬም ድረስ ያስደንቀኛል። ሆን ብላ ለመሳም ጠዋት ነቅታ አውቶብስ የምትጠብቅ ነው የመሰለችኝ። በሌላ ቀን ደግሜ ልስማት ብጠብቃት ሳላገኛት ይሄው ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ። ያ ከንፈር፣ ያ አጋጣሚ ትናንቴን ስገልጥ፣ አንበሳ አውቶብስን ሳስብ ፊቴ የሚደቀኑ የጉዞ ማስታወሻዎቼ ናቸው።
በተቀመጥኩበት ሆኜ ተሳፋሪውን አስተው ላለሁ። ሁሉም በራሱ ዓለም ላይ በሃሳብ ተሳፍሯል። ይሄ የኑሮ ውድነት ያላሳበደው ሰው የለም አልኩ። እንደዛሬ ትክክል የሆነ ነገር አስቤ አላውቅም። እንደወረርሽኝ ያልገባበት የለም። ሰፈራችን ውስጥ ገብቶ አራት ጎረቤቶቼን ጨምሮ ሁለት ቡና አጣጪዎቼን ለብቻቸው እንዲያወሩ አድርጓል። እኔጋ መች እንደሚመጣ አላውቅም። የጎረቤቴን በር አንኳኩቶ እኔን እንደማይዘለኝ አውቃለው። እስኪመጣ መሳቅ ነው.. ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደር..
አውቶብሱ ውስጥ አብዛኛው ወሬ ስለኑሮ ውድነት ነው። ለብቻቸውም ሆነ አብሯቸው ከተቀመጠ ሰው ጋር ለወሬ የተከፈቱ አፎች የሚያወሩት አንድ አይነት ወሬ ነው። ‹እንጀራ 20 ብር ገባ›። ‹እሱን ትያለሽ! ዳቦ ባቅሙ ጨምሮ የለ? ሌላው ይቀጥላል። በተለያየ ፊት ላይ አንድ አይነት ሃሳብ ያረምማል። በሃሳብ መውረጃውን እየረሳ ያለቦታው የሚወርድ ብዙ ነበር። ሃሳቤን ከገራልኝ ብዬ ራሴን ወደሌላ ሃሳብ ልወስደው ታገልኩ። ከፊት ለፊቴ በቆሙት ሰዎች ላይ በተከፈተች ትንሽዬ ቀዳዳ አንድ አሮጊት ታዩኝ። አውቶብሱ ወዲያ ወዲህ ሲል ሰዎቹም አብረው ወዲያ ወዲህ ስለሚሉ ቀዳዳዋን እያሰፉና እያጠበቡ እየደፈኑም ከአሮጊቷ ሴት ጋር የነበረኝንት ቁርኝት ስጋት ላይ ጣሉብኝ። ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ሴትዮዋን አያታለሁ። እድሜያቸውን ገመትኩት.. ከሰባ ስምንት እስከ ሰማንያ ሶስት አደረስኩት። አውቶብሱ መናኛ መንገድ አገኘው መሰለኝ ወዲያ ብሎ ወዲህ ባለበት ቅጽበት ሰፍታ በጠበበችው ቀዳዳ የሴትዮዋን እጅ አየሁት። ውሽማ ፈላጊ ጌጥ የሚያስርበት መሀል ጣታቸው ላይ ቀለበት አየሁ። ሰፍቷቸው ይሆናል እንጂ መቼም በዚህ እድሜአቸው ባል እየደፈለጉ አይሆንም ስል ሌላ ሃሳብ አሰብኩ።
አጠገባቸው መሆን አማረኝ። አጠገባቸው ብሆን የምጠይቃቸው የመጀመሪያ ጥያቄዬ ‹ጣትሽ ላይ ቀለበት አየሁ። ባል እየፈለግሽ ነው ወይስ? ብዬ ማቆም። ከወይስ በኋላ ያለውን ከእሳቸው የምሰማው ይሆን ነበር። እገምታለሁ የሆነ ነገር.. ጥያቄዬን ተከትሎ አዛውንት ፊታቸው የማን ደፋር ነው ብሎ ሲቀየመኝ። እገምታለሁ የሆነ ነገር.. አዛውንት ፊታቸው አይ የልጅ ነገር ብሎ ሳቅ ሲል። እገምታለው የሆነ ነገር በኑሮ ውድነቱ ሃሳብ ገብቷቸው ዝም ሲሉኝ። እገምታለሁ የሆነ ነገር..
መውረጃቸው ደርሶ ቀድመውኝ ወረዱ.. ከግምቴ ሌላ ሆነ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015