ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነው። የተወለደው ደግሞ በ1992 ዓ.ም ኅዳር ላይ። ወላጅ አባቱ የጥበብ ሰው ናቸው፤ እናቱ ደግሞ የቤት እመቤት። መጠሪያ ስሙ ትንሽ ለየት ይላል ”አጃዬ” በምን አጋጣሚ ይህ ስም እንደወጣለት ሲናገር እርሱ በተወለደ ማግስት ወላጅ አባቱ የህንድ ፊልም በሚከታተሉበት ወቅት ከፊልሙ ተዋናይ ስም እንደሰጡት ይናገራል። ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነው። ወጣት አጃዬ ማጆሬ ይባላል። ውልደቱ እና እድገቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወላይታ ዞን አረካ ከተማ ነው።
ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ብሎም ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ዕርከን በትውልድ ከተማው አረካ ተከታትሏል። በአሁኑ ሰዓት የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል። በትምህርቱ መካከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች ውስጥ የሚመደብ እንደነበር ወጣት አጃዬ ይናገራል።
ከልጅነቱ ጀምሮ የፈጠራ ሥራዎችን ይሰራ እንደነበር የሚነገረው ወጣት አጃዬ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ማለትም የሰባት እና የስምንት አመት ህፃን ሆኖ ሳለ በሽቦ መልክ የተሰሩ መኪኖችን በራሱ ሰርቶ ለጨዋታ ይገለገልባቸው እንደነበር እና ይህ ነገር ለምን በእጅ ይገፋል ብሎ በማሰብ ዕድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ ባለአራት እግር ተሽከርካሪ መኪና ለመስራት እንደሞከረ የፈጠራ ባለሙያው ወጣት አጃዬ ይናገራል። የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ትራክተር፣ ድሮን እና ሌሎች መሳል የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ይሞክር እንደነበርም ይገልፃል። በወቅቱ ቤተሰቦቹ በገንዘብ የመደገፍ አቅም ባይኖራቸውም በሀሳብ እና በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከጎኑ ይቆሙ እንደነበር እና እስከ አሁንም ድረስ በተቻላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ እያደረጉለት ስለመሆኑ የፈጠራ ባለሙያ ይገልፃል።
ከሶስት ዓመት በፊት ማለትም 11ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በሊትር እስከ 40 ኪሎ ሜትር መጓዝ የምትችል እና (ከበቡሽ) የሚል ስያሜ የተሰጣት ተሽከርካሪ መሰራት መቻሉን የሚነገረው ወጣት አጃዬ ማጆር ይህንንም የወዳደቀ ብረታ ብረትን በመጠቀም ተሽከርካሪዋን መሥራት እንደቻለ ይናገራል፡፡ በወቅቱ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ባደረገለት ድጋፍ የተሰራችው ተሽከርካሪዋ የባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ ሞተርን በመጠቀም የተሰራች ሲሆን ወደ ኋላ መሄድ እንድትችል (reverse gear) አድርጎ በማሻሻል መሥራቱን ይገልፃል።
ይህን የፈጠራ ሥራውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚሠራበት ቦታ ድረስ በመሄድ እንደጎበኙት እና እንደበረታቱት ወጣት አጃዬ ተነግሯል። በወቅቱ ተሽከርካሪዋ አራት ኩንታል ክብደት ያላት እና እስከ 4 ሰዎች የመጫን አቅም ያላት እና በአንድ ሊትር እስከ 40 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደምትችልም ይነገራል። በዚህ የፈጠራ ሥራውም ከቀድሞ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ እጅ ሽልማት ተቀብሏል።
የመኪና ፈጠራ ሥራውን ባበረከተበት ወቅት ወጣት አጃዬ ማጆሬ ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች በግል ጥረቱ የሰራውን የመኪና ሂደት እንዲሁም ተሞክሮውን አካፍሎ እንደነበር እና በቴክኖሎጂ ሽግግርና ስርጸት መስክ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠልና ልምድና ተሞክሮን ለማስፋፋት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ልምዱን ለማካፈል ዕድሉን አግኝቶ እንደነበር ያስታውሳል።
በዩኒቨርሲቲው ልምድ እና ዕውቀቱን ለማጋራት በተገኘበት ወቅት ከልጅነቱ ጀምሮ የሽቦ መኪና በመስራት ዝንባሌውን እያሳደገ መምጣቱን እና ምንም እንኳ ሥራውን ሲጀምር የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውት የነበረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን ህልሙን በማሳካት ደስተኛ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡ በትጋት እስከ መጨረሻው ከለፉ ሰዎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ መልዕክት ለማስተላለፍ ዕድል ያገኘበት መሆኑንም ይገልጻል፡፡
ወጣት አጃዬ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለሙያው ማበረታቻ እና ሥራውንም አጠናክሮ እንዲያስቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንዳደረገለት ከምስጋና ጭምር ይገልጻል፡፡ ብሎም ልምድ እና ተሞክሮውን እንዲያካፍልም ከተማሪዎች ጋር አብሮ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡
ወጣት አጃዬ ሲናገር ማንኛውም ሰው ህልሙን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን ቢሰራ አሸናፊ መሆን ይችላል የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ተማሪዎች ህልማቸውን ለመኖር ሁሌም ተግተው መሥራት እንዳለባቸው እና ‹‹እንደማይችሉ›› ለሚነግራቸውም ሰውም ሆነ ሁኔታ እጅ መስጠት እንደሌለባቸው የፈጠራ ባለሙያው ወጣት አጃዬ ይናገራል።
በቅርቡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሞተር ሳይክል ሰርቶ ከ2 መቶ ሺህ ብር በታች ለገበያ እየቀረበ ያለው የአረካ ከተማው ወጣት አጃዬ ያረጁ እና አነስተኛ ሲሲ ያላቸውን ሞተር ሳይክሎች ጠፍጥፎ ቅርጽ እና መጠናቸውን በማሳደግ ከፍተኛ ጉልበት እንዲኖራቸው አድርጎ በተለያየ መጠን ይሰራል። የወላይታ የቀድሞ ንጉሥ ስያሜ የተሰጣት (‘ኬቲኤም’ ማለትም ካዎ ጦና ሞተርስ) የተባለ መጠሪያ ያላት ሞተር ሳይክል በራሱ ሰርቶ ለገበያ አቅርቧል። ተመሳሳይ ሞተር ከውጭ ተገዝቶ ሲገባ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣል የሚለው ወጣቱ እርሱ ግን ይህን ሞተር ሰርቶ ከ2 መቶ ሺህ ብር በታች ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ይናገራል።
ሞተር ሳይክሉ ረዥም ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም ያለው ብቻ ሳይሆን በጣም አስቸጋሪ በሆነ መልክዓ ምድር ለመዝናናት፣ ለጤና ጣቢያዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት፣ ለመከላከያ ሰራዊት እና መሰል አገልግሎቶችን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በማለፍ በቀላሉ አገልግሎት ለመስጠት እና ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ወጣት አጃዬ ይናገራል። የሞተሩ አገልግሎት ለሀገር አቋራጭ ተጓዥ ቱሪስቶች እና ለረዥም ኪሎ ሜትር ጉዞ አመቺ ተደርጎ የተሰራ ባለራይዳተር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ወጣት አጃዬ ይገልፃል።
ይህንን የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ምን እንዳነሳሳው ወጣት አጃዬ ሲነገር ‹‹ትልቅ ሲሲ ያለው ሞተር ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የለም›› እርሱ ለግል አገልግሎት ፈልጎ ለመግዛት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ያገለገለ ሞተር እንኳ አምስት መቶ እና ስድስት መቶ ሺህ ብር ዋጋቸው መሆኑን ሲያውቅ ”እንዲህ ውድ ከሆነ ባገኛውት ዕቃ እራሱን መሥራት አለብኝ ፤የእኔንም ህልም መሳካት አለብኝ፤ ለወጣቱም ደግሞ አርአያ ለመሆን ሲል ሥራውን በትጋት ለመስራት እንደተነሳሳ ይናገራል፡፡ ‹‹ሞተር ሳይክል ይህን ያህል መወደድ እንደሌለበት ማሳየት አለብኝ” በማለት ከሌላ ሞተር ባገኘው ኢንጂን ፈይበር ሻንሲውን በብረት በማድረግ እራሱን መሥራት እንደቻለ ተናግሯል።
ይህን የፈጠራ ሥራውን የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ እንደጎበኙት እና በዞን እና በከተማ ደረጃ ለእርሱ የፈጠራ ሥራ የሚያግዙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አንፃር ልዩ ትኩረት በመስጠት በሁለም ዘርፍ ለማገዝ ቃል እንደገቡላት የሚነገረው ወጣቱ፤ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች እስከ ሥራ ቦታ ድረስ መጥተው መጎብኘታቸው ለፈጠራ ሥራው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርለት እና በቀጣይ ለሥራው ማስፋፋት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርለት እንደሚሆን ይናገራል።
ይህ የፈጠራ ሥራው የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር እና የሀገር በቀል ዕውቀትን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት በር የሚከፍት መሆኑንም የ23 ዓመቱ ወጣት አጃዬ ይነገራል። የፈጠራ ሥራ እንደ ግኝት ለሀገር የሚጠቅም ሀብት ነው የሚለው ወጣት አጃዬ ፈጠራው ዋጋ የሚያጣው ሥራው ወደ መሬት መውረድ ሳይችል ሲቀር ነው ይላል። ይህንን በመለወጥ ወደ መሬት መውረድ ከተቻለ እና ወደ ምርት የሚገባበት ዕድል ከተፈጠረ ”እራሳችንን መለወጥ የማንችልበት ምክንያት እንደሌለ” ይገልፃል።
የልጅነት ህልሜን ለመኖር ጥረት ሳደርግ ከሚገጥሙኝ ተግዳሮቶች አንዱ አንዳድ ግለሰቦች ነቀፋዊ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጡም ነበር ብሏል ወጣት አጃዬ፤ በተለይም “ቻይና መኪና ይሰራል፣ አንተ መኪና ግፋ “የሚሉት ሰዎች አሁንም ድረስ የሚገርሙት እንደሆነ እሱ ግን ያንን ለመስማት ጆሮ እንዳልሰጠ ይናገራል።
ዘመኑ ሁሉንም ነገር በቀላሉ በእጃችን መገኘት የምንችልበት የቴክኖሎጂ ዘመን ነው የሚለው ወጣት አጃዬ የማይቻል ነገር የለም ይላል፤ ‹‹ገንዘብ የለኝም››፤ ‹‹የሚያግዘኝ ሰው የለኝም›› በማለት የተቀመጡ ወጣቶች አሉ፡፡ሆኖም ዕውቀት ካለ ባለን ግብዓት ብቻ ከቀላል ነገር በመጀመር አስደማሚ ፈጠራዎችን ለሀገገር ብሎም ለዓለም ማቅረብ እንደሚቻል ያስረዳል፡፡ ‹‹ወጣቶች ለመሥራት ለፈጠራ ስራ ዝግጁ መሆን አለባቸው›› ወጣቶች በያሉበት መንቃትና እራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን ለመለወጥ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው ምልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ወጣቶች ለዓላማቸው መሳካት መክፈል ያለባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል አለባቸው፤ የነገው ራዕያቸውን ከግብ ለመድረስ ቀን እና ሌሊት ሳይሉ እና ተስፋ ሳይቆርጡ መትጋት እንደሚገባቸው እና ብዙ ጠልፈው ለመጣል ከፊት የሚቀድሙ መሰናክሎች ቢኖሩም ነገን አሻግሮ መመልከት እንዳለባቸው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
መንግስት በየአካባቢው እንደ እርሱ አይነት የፈጠራ ተስጥኦ ያላቸው ህፃናት እና ወጣቶች ማበረታታትና ሥራቸውን ማጎልበት የሚችሉባቸው ማዕከላትን ቢያስፋፋ ኢትዮጵያ በቀላሉ በፈጠራ በተካኑ ወጣቶች እንደምትሞላ ያለውን ተስፋ አካፍሏል፡፡
የወደፊት ህልሙን ሲናገርም የገንዘብ አቅሙን አደራጅቶ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት በስፋት ለመሥራት ውጥን እንዳለው እና በፈጠራ ሥራ ብዙ ችግር ፈቺ የሆኑ ነገሮችን መሥራት እንደሚፈለግ ይገልፃል፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራአጥነት ለመቀነስ እንደሚሰራ እና ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ተክቶ ለመሥራት ከፍ ሲልም ደግሞ ወደ ውጭ በመላክ እራሱንም ሀገሩንም መጥቀም እንደሚፈልግ ተነግሯል። በመኪና እና ሞተር እቃዎች ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች አብረውት እንዲሰሩም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ወጣት አጃዬ ከልጅነቱ ጀምሮ በሥራው ሁሉ ከጎኑ ሆነው ያበረታቱትን ቤተሰቦቹን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ጓደኞቹን አመስግኗል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015