ወላጆች ለልጆቻቸው እኩል ዕድል እየሰጡ ማሳደጋቸው ልጆች የየራሳቸው የወደፊት ህልም እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለው ያስባሉ። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኢቢሲ) የማህበራዊ ጉዳዮች አርታኢ ዙቤይዳ አወልም እናቷ ያሳደጓት በዚህ መንገድ ነው።
ዙቤይዳ አወል ‹‹ብዙ ልጆች የየራሳቸው የወደፊት ህልም አላቸው። ዶክተር ፣መምህር፣ፓይለት፣ፖሊስ እያሉ ወደፊት የሚሆኑትን ከወዲሁ የሚናገሩት ለዚህ ነው›› ትላለች። እርሷም ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች ጀምሮ ልጆች የራሳቸው ህልም ኖሯቸው እንዲያድጉ ለማስቻል እናቶቻቸውን ለመደገፍ በግሏ ስትጥር ቆይታለች።
በተለይ በኢቢሲ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ መሥራት ከጀመረች አንስቶ በሥራ ላይ የሚገጥሟት ከእናቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራ አድርጓታል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚገጥማትን ሁሉ በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በማጋራትና ሌሎችን በማሳተፍ ጭምር ይህን በጎ ተግባር ለሁለት ዓመታት ስትከውን ቆይታለች። የእርሷ በእናቷ መልካም ስብእና መቀረፅ በዘር፤ ቀለምና ሃይማኖት ሳይለዩ የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት የበጎ ተግባር ተምሳሌት የሆኑትን ማዘር ትሬዛን እንድትወድ አድርጓታል።
ዙቤይዳ ጋዜጠና ብቻ ሳትሆን የማህበራዊ ሚዲያ አንቂም ናት። በዚህ ዓመትም ቢያንስ ኢትዮጵያዊት ማዘር ትሬዛ በመሆን በጎ ተግባሩን በተቋም ደረጃ ማስጀመር አለብኝ ብላ በማሰብ ‹‹እናት ዙበይዳ›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁማለች። በዚህ ድርጅት በርካታ ልጆች የራሳቸው ህልም እንዲኖራቸው፣ በርካታ እናቶችም ልጆቻቸው የራሳቸው ህልም ኖሯቸው እንዲያድጉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። ለእናቶች በሚደረገው ድጋፍ ውስጥ ልጆችም ተጠቃሚ ሆነዋል። ስማቸው ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የተቀየረው የአስር ዓመት ታዳጊ ህፃን ዮናስ አበበና እናቱ ወይዘሮ አስምረት ጋሻው ደግሞ የዚህ ድጋፍ ተቋዳሽ ናቸው።
ወይዘሮ አስመረት ሁለት መንታ ልጆች እንዳሏት ትናገራለች። ልጆቿ በቤት ውስጥ ያለባትን ችግር እንደሚያዩና በተለይ ልጇ ዮናስ ‹‹እኛ ልጆችሽ ቶሎ አድገንና ተምረን ሥራ በመያዝ እናሳልፍልሻለን ፤ቆንጆ ቤትም እንገዛልሻለን›› እያለ ተስፋ እንደሚሰጣት ነው የምትገልፀው። የአስር ዓመቱ ልጇ ዮናስ በጣም ጎበዝ ተማሪ እንደነበር ሆኖም በሚኖሩበት አዲስ አበባ አሜሪካ ጊቢ አካባቢ በድንገት ተገዶ እንደተደፈረባት በሃዘን ትገልፃለች። በወቅቱ ሕክምና ቢያገኝም የአካል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የስነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰበትም ታስረዳለች። በዚህም ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል። ይህንንም ተከትሎ ወደ ጎዳና መውጣቱን ወይዘሮ መሰረት ታስታውሳለች።
“ከብዙ ፍለጋ በኋላ ሜክሲኮ አየነው ብለው ሰዎች ነገሩኝ። ኃይለኛ ዝናብ እየዘነበ በእኩለ ሌሊት ጎዳና ላይ የተኙ ልጆችን በሙሉ እየገለጥኩ ስፈልግ ቆይቼ በመጨረሻ አገኘሁት›› ትላለች ወይዘሮ መሰረት በሃዘን ስሜት ውስጥ ገብታ። በዚያ ሌሊት እሱን ፍለጋ ወጥቼ ሳገኘው ደንግጦ ጭለማውን ለምን እንዳልፈራሁ ጠይቆኝ ተስፋ በመቁረጥ በቀላሉ እሽ ብሎ አብሯት ወደ ቤት ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳልነበረም። በኋላ ላይ ግን ብዙ አባብላና ለምና ወደ ቤት እንዳስገባችው ትናገራለች።
‹‹እንቢ ሲለኝ ምርር ብዬ ሳለቅስና ወደቤት የማይመለስ ከሆነ እራሴን እንደማጠፋ ስነግረው ነው አብሮኝ የተመለሰው›› ትላለች ወይዘሮ መሰረት። ይሄን ያልኩት ለጊዜው ወደ ቤቱ እንዲመለስልኝ ለማባበል ብቻ ሳይሆን በርግጥም ጉዳቱ ተሰምቶኝም ጭምር ነው ስትል ትገልፃለች።
ወይዘሮ መሰረት እንደምትናገረው፣ ልጇ ዮናስ ከመደፈሩ በፊት ሻይ በመሸጥ ነበር እሱንና መንትያ እህቱን የምታሳድጋቸው። ልጇ ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ግን ሥራውን አቁማ እሱን ፍለጋ መባዘን ሆነ ሥራዋ። በዚህ ወቅት ሻይ የምታፈላበትና የምትሸጥበት ማንቆርቆሪያና ብርጭቆዎች እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችም ተዘርፈውባት ነበር። አሁን ግን የዮናስ እናት የ‹‹እናት ዙቤይዳ›› በጎ አድራጎት ድርጅት ባደረገላት የፔርሙስ፣ የሌሎች ቁሳቁሶችና የመነሻ ካፒታል ድጋፍ አሜሪካን ጊቢ አካባቢ ሻይ እያፈላች በመሸጥ ልጆቿን እያሳደገች ትገኛለች።
“ቀበሌ የሰጠኝና የምኖርበት ቤት እጅግ ከመጥበቡም በላይ አይመችም” የምትለው ወይዘሮ መሰረት፤ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ዙቤይዳ ‹‹ቤታችን ከጎዳና አይሻልም፤ ጎዳናም ኖርኩ እቤት ውስጥ ልዩነት የለውም›› የሚለውን ልጇን እናትህን ትተህ የትም መሄድ የለብህም ስለዚህ በቤት ውስጥ ከእናትህና ከእህትህ ጋር መኖር ይሻልሃል›› ብላ እንደመከረችው ታስረዳለች። ይሁንና ልጇ ዮናስ ከደረሰበት የስነ ልቦና ጉዳት በቶሎ አገግሞ ትምህርቱን መቀጠል እንዳልፈለገ ትገልፃለች። ካልሲ በመሸጥ እናቱን መርዳት እንደሚፈልግ ተናግሮ እንደነበርም ታስታውሳለች። በዚህም ይህን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለው የገንዘብ ድጋፍ በድርጅቱ በኩል ተደርጎለት ወደ ሥራ መግባቱን ትናገራለች።
ልክ እንደ ወይዘሮ መሰረት ሁሉ ወይዘሮ ብርቱካን ከበደም /ለዚህ ፅሁፍ ስሟ የተቀየረ/ በድርጅቱ በኩል ድጋፍ የተደረገላት ናት። እርሷ እንደምትለው ቀደም ሲል ሦስት ልጆቿን ታሳድግ የነበረው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጎዳና ላይ በመሸጥ ነበር። ሆኖም በተደጋጋሚ ደንብ አስከባሪዎች እቃዎቿን ስለወሰዱባት ለኪሳራ ተዳርጋ ስራውን ትታለች። ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ዓይኗን ታማ እይታዋ ተጋርዶ በህመም ስትሰቃይ ቆይታለች።
‹‹በህመሜ ከኔ ይልቅ ልጄ የበለጠ ይሳቀቅ ነበር። ብዙ ጊዜ አዝኖ አጠገቤ ኩርምት ብሎ ይቀመጥና ሲያድግ ዓይኔን እንደሚያሳክመኝና ዳግም እንደማልታመም ይልፅልኝ ነበር›› ትላለች ወይዘሮ ብርቱካን። እንኳን ለዓይኗ መታከሚያ ይቅርና ለልጆቿ የምታበላው የዕለት ጉርስ እስከማጣት ደርሳ እንደነበርም ትጠቁማለች።
አሁን ላይ ግን ያ ጊዜ አልፎ ወይዘሮ ብርቱካን በልጇ አማካኝነት ያገኘቻት ዙባይዳ ዓይኗን እንድትታከም አድርጋላታለች። የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሐኪሞች በየአይኗ ውስጥ በቅሎ የነበረውን ፀጉር ለቅመው ስላወጡላት ከህመሟም ተፈውሳለች። ደንብ አስከባሪዎች ከዚህ በፊት ወስደውባት የነበሩትን አይነት ‹‹ኤርገንዶ›› ጫማዎች ዙበይዳ መርካቶ ወስዳ ገዝታላት እየሸጠች ትገኛለች። ልጇም ደስ ብሎት ትምህርቱን እየተማረ ነው።
ዙበይዳ ስለ ወይዘሮ ብርቱካን እንደምትናገረው ክፍል ውስጥ ሲማር አንድ መምህር ‹‹ስታድጉ ለወላጆቻችሁ የምታደርጉላቸውን ነገር ንገሩኝ›› ብሎ በጠየቀው ጥያቄ ምክንያት አግኝታዋለች። ‹‹እናቴን ዓይኗን አሳክማታለሁ›› የሚል መልስ ለመምህሩ እንደመለሰም ተረድታለች። ቃለ መጠየቅ ስታደርግ ‹‹ሳድግ ለእናቴም፤ ለእኔም ጫማ እገዛለሁ›› ያላት ሌላም ልጅ ገጥሟታል።
ነገር ግን የእነዚህ ልጆች ህልም እናትን ከማሳከምና ጫማ ከመግዛት አልፎ አውሮፕላን አብራሪ ሆነው እያንሸራሸሩ ሀገር እስከ ማስጎብኘት፣ ቪላ ቤት እስከ መግዛትና የሀገር መሪ እስከመሆን መዝለቅ እንዳለበት ትጠቁማለች። በድህነት ምክንያት በተለይም በቤት ውስጥ ባለ ችግር ሃሳብ ስለሚይዛቸው አብዛኞቹ ልጆች በትምህርታቸው ጎበዝና ውጤታማ እንዳልሆኑና ጎበዝ የነበሩ ልጆች ውጤታቸው ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንደሚሄድም ትጠቅሳለች።
የድርጅቱ ዓላማም በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ እናቶች ቢያንስ በልቶ ማደር የሚያስችልና ትንሽም ቢሆን ገቢ እንዲኖራቸው፤ ልጆቻቸውም የየዕለት ችግር ከማሰብ እንዲወጡ የሚያደርግ አነስተኛ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ታስረዳለች። በዚህ ድጋፍም ልጆቹ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚታሰብም ትጠቅሳለች።ባሎቻቸው ሞተው ወይ ተለይተዋቸው ብቻቸውን ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ልጅ ኖሯቸው ለልጆቻቸው ሲሉ ሥራቸውን ትተው ቤት ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር ለመቀመጥ የተገደዱ እናቶች በድጋፉ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ትገልፃለች። ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚቸገሩ እናቶች በተለይ አካል ጉዳተኛ ልጆች የያዙ ከመሆናቸውም በላይ ተደራራቢ ጉዳት እንደሚደርስባቸውም ዙቤይዳ ታስረዳለች።
አብዛኞቹ ልጆቻቸው የፓንፐርስ ድጋፍ የሚፈልጉና ራሳቸውን ችለው የማይንቀሳቀሱ ናቸው። ቢያንስ የልጆቻቸው ተፈጥሯዊ ጉዳት እንዳለ ሆኖ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው እናቶቻቸው ልጆቻቸውን የሚንከባከቡበት እነሱ የማይበሳጩበት፤ ልጆቻቸው ተስፋ የማይቆርጡበት እንዲሁም የራሳቸው ህልም እንዲኖራቸው ማድረግ የድርጅቱ ዓላማ ነው።
ዙበይዳ እንምትገልፀው በዚህ ዓመት መጨረሻም ድጋፍ የሚደረግላቸው ሃያ እናቶች ተመርጠዋል። የተወሰኑት በሥራ አጋጣሚ የተገኙ ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ ደግሞ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ገብተው የሚማሩ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አካል ጉዳተኞችም ይገኙበታል። በአብዛኛውም መምህራኖቻቸው ችግራቸውን በሚገባ የሚያውቁላቸው ወላጆች ናቸው ለእርዳታ የተሰባሰቡት። ለነዚህ ሃያ እናቶች መሥራት የሚችሉትን ሥራ እንዲሰሩ መነሻ ካፒታል በመስጠት ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያሳድጉና ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሻሽሉ ይደረጋል።
‹‹የእኛ ልጆች ህልም አላቸው፤ የእነዚህ እናቶች ልጆች ከእኛ ልጆች ጋር እንደማደጋቸውና የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናቸው ለልጆቻችን የምናስረክባት ኢትዮጵያ የነዛም ልጆች ኢትዮጵያ ናት ብለን ማሰብ አለብን›› የምትለው ዙበይዳ፤ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው እናቶች ልጆች ሀገር ኢትዮጵያ እንጂ ሌላ ሀገር ባለመሆኗ ሀገሪቱ ለእነሱ ዕድል እየሰጠች፤ ኃላፊነት እንዳለባት እያሳየች ያሳደገቻቸው ሀገር እንዲመስላቸው ተደርጎ እንዲያድጉ እንደምትፈልግ ትገልፃለች። ህብረተሰቡ ደግፎኛል፤ አግዞኛል እንዲሉ እንደምትፈልግም ትናገራለች።እነዚህ ልጆች ነገ ሲያድጉ የተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጣቸው አይቀሬ መሆኑንም ትጠቁማለች።
‹‹ትናንት ያልደገፋቸውንና ያላገዛቸውን ማህበረሰብ እንዴት አድርገው ያግዛሉ?›› ስትል የምትጠይቀው ዙበይዳ፤ ይሄ ችግር የግድ መቀረፍ እንዳለበትና ህብረተሰቡ በሰጣቸው ልክ እነርሱም መልሰው ስለሚሰጡ ዛሬ ላይ ለነዚህ ልጆች እየሰጠን ማሳየት አለብን ትላለች። ኢትዮጵያ ለእነዚህም ልጆች ሀገራቸው ስለሆነች ሌሎች ልጆቻችን ብቻ የሚረከቧት ሀገር አትኖርም ብለን ለራሳችን ዕውነቱን መንገር ይኖርብናል ስትል ትገልፃለች።
‹‹ልጆቻችን ሰላማዊና ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ ከፈለግን እኛ የእነሱን አቻ ጓደኞቻቸውን ማገዝ ነው ያለብንም›› ትላለች። ቂም ያልያዙና እኔን ትናንት የገፋኝ ማህበረሰብ ነው የማይሉ ሰላማዊ ልጆችን መፍጠር ከፈለግን የግድ እነሱም ሰላም መሆን አለባቸው ስትል ታስረዳለች። ‹‹በተደረገላቸው ልክ ሀገራቸውን ፣ወገናቸውን፣ሕዝባቸውን ማገልገገል የሚፈልጉ፤ እነሱም ኃላፊነት የሚሰማቸው፤ እኔ ተደርጎልኛ እዚህ ደርሻለሁ፤ በመሆኑም የተቸገሩትን እረዳለሁ እንዲሉ ማድረግ ደግሞ የእኔ አላማ ነው ››ትላለች ዙቤይዳ።
ዙቤይዳ እንደምትለው እነዚህ የችግረኛ እናት ልጆች ትንሽ ሲደረግላቸው የሚረዱና ምንድነው የምታደርጉት ሲሏቸው እኔም የተቸገሩትን እረዳለሁ፤የራበውን አበላለሁ የሚሉ ናቸው። በመሆኑም ልጆቹ ያልሰጠናቸውን ስለማይሰጡን ዛሬ እየሰጠናቸው ማሳየት አለብን። ማህበረሰቡም የተቸገሩ ሰዎችን ሲያይ አንድ ብርና ሁለት ብር ከመስጠት ባሻገር ጎረቤቱ የሆኑትንና እሷ የምትደግፋቸውን ዓይነት እናቶችን መደገፍ አለበት። ‹‹ምንድነው ችግርሽ ፤ምንድነው ያጣሽው፤ እስቲ ምን ባደርግልሽ ነው የተሻለ የምትሆኚው›› በማለት ቀረብ ብለው ይህችን እናት ቢዋይዋት የተሻለ ትሆናለች።
እርሷ በማህበራዊ ሚዲያ ዛሬ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባት እናት አገኘሁ በምትልበት ሰዓት የማያውቋቸው ሰዎች ከአንድ ሺህ ብር ጀምሮ እስከ አስር ሺ ብር የሚልኩበት ሁኔታ መኖሩን ለማሳያ በመጥቀስ፤ እነዚህ ሰዎች የሚያውቋቸው ጎረቤቶች አጠገባቸው እንደነበሯቸው፤ ሆኖም እንዳላይዋቸው ታወሳለች። ‹‹እኔ ስናገር ግን እዛ ማዶ ላለውና ለማያውቁት ድጋፍ አደረጉ›› ስትልም በጎረቤትና በአካባቢያችን፤ በዘመዶቻችን፤ የሞተ ዘመድ ካለን ባለቤቱ እንዴት ነው ልጆቿን እያሳደገች ያለችው ብለን ልንጠይቅ ይገባል ስትል ትመክራለች።
ሕብረተሰቡ ስለ አኗኗራቸው ማወቅ እንዳለበትም ጠቁማ፤ በተለይ ፣ወላጆቻችን የጎረቤቶቻቸውን ኑሮ ስለሚያውቁ ‹‹እስኪ ይቺን ቅመሺ ብለው በርበሬ የሚልኩት ካላት ትቀምሳለች ከሌላት እንድትጠቀምበት ብለው እንደሆነም ታነሳለች። ይሄ ልጅ ሲያጠፋ ጎረቤት ያገባኛል ብሎ ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን ሲራብም እናቱን በመደገፍ በኃላፊነት ጭምር ለመርዳት እንደሚበጅም ታነሳለች። አንድን ልጅ ጎረቤቱ ሁሉ ያሳድገዋል የሚባለው ለዚህ እንደሆነም ትጠቅሳለች። ይሄን አባባል በመረዳት ችግርን በጋራ መመከት እንዳለብን ታሳስባለች። ለኢትዮጵያዊያን ይሄ የኖርንበት ባህል በመሆኑ ሥራዬ ብለን ከያዝነው አይከብደንም ስትል ዙቤይዳ ትገልፃለች። ሰው ተቸገረ ሲባል ተረባርበን መደገፍ አለብንም ትላለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015