
ቡናችን በዓለም ገበያ ተገቢውን ዋጋ እያጣ ነው። ባለፉት ዓመታት የግብርና ምርቶች የዓለም ገበያ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ምንጫችን የሆኑት የግብርና ምርቶች በተለይ የቡና ምርታችን ዋጋ ቀንሷል። የቡና ዋጋ ዘንድሮም በተመሳሳይ መቀነሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ፍተሐዊ ባልሆነው ዓለም አቀፉ የቡና ገበያ ጥቂት ሞኖፖሊስቶች አንድ ኪሎ ቡናን ከአንድ ሲኒ ቡና ባነሰ ዋጋ እየገዙም ይገኛሉ።
ዘንድሮ ለቡናችን የተሰጠው ዋጋ ከ13 ዓመት በፊት የነበረው ወይም ከዚያ የቀነሰ ነው። ዓለም አቀፉ የቡና ዋጋም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት በአሜሪካ ሳንቲም 20 በመቶ ቀንሷል። አገራችን ወደ ውጭ የምትልከው የቡና መጠንም እንዲሁ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ወደ አምስት በመቶ የመጠን ቅናሽ አሳይቷል። በገቢም 10 ነጥብ 9 በመቶ ቀንሷል።
ለዋጋው መቀነስ ሁለት አበይት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። አንዱ ውጫዊ ምክንያት ነው። ይህም በዓለም ገበያ ከፍላጎቱ በላይ የሆነ የቡና ምርት መቅረቡ ነው። ዓለም አቀፍ የቡና ግብይቱ በጥቂት ከፍተኛ ቡና ቆዪዎችና ቡና ነጋዴዎች ተጽእኖ ውስጥ መውደቁም ሌላው ውጫዊ ምክንያት ነው።
ሀገሪቱ ከፍተኛ ውድድር እንደሚጠብቃት የሚያመለክቱ ናቸውና እነዚህ ችግሮች ከኛ ውጪ ናቸው ብለን የምንተዋቸው አይደሉም። ገጽታችንን በመገንባት፣ የቡናችንን ጥራት እንደ ቀድሞው በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅ ሥራ ላይ በትኩረት በመሥራት ፈቀቅ ማድረግ ይቻላልና ከዚህ አኳያ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።
ሌሎቹ በአፋጣኝ ልንፈታቸው የሚገባ ውስጣዊ ችግሮችም አሉ። በቡና ግብይት ውስጥ የሚገኙት አካላት ሽኩቻ ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስ እያደረገው ነው። ሁሉም ባይባሉም ቡና በቅናሽ ዋጋ ገዝተው እየሸጡ ከዚያ ባገኙትም የውጭ ምንዛሪ ሌሎች ሸቀጦችን እያስገቡ በቡና ያጡትን ትርፍ በሸቀጦች የሚያካክሱ ላኪዎች የዘርፉ ዋና ተግዳሮት ሆነዋል። እነዚህ አካላት ሌሎች ላኪዎች በስርዓቱ ለመገበያየት የሚያደርጉትን ጥረት ከንቱ በማስቀረት ላኪዎቹንም፣ ሀገሪቱንም ለጉዳት እየዳረጉ ይገኛሉ።
የተሻለ ዋጋ በመጠበቅ ቡና ማከማቸት ሌላው የቡና ግብይቱ ተግዳሮት ነው። በዚህ የተነሳም አለስፈላጊ የቡና ክምችት እየተፈጠረ ነው። ከባለፈው ዓመት የዞረ 30 ሺ ቶን ቡና መኖሩም ይህንን ያመለክታል። ቡና ከሚፈለገው በላይ መከማቸቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳረፉ በተጨማሪ የጥራት ጉድለት እንዲከሰት ያደርጋል። እዚህ ላይ እንደ ሀገር እየታሰበም አይደለም።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ቡና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሀገራችን የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን እየተገበረች ብትገኝም እያደገ የመጣውን ልማቷን ለማሳለጥ አሁንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚኖርባት ከቡና የወጪ ንግድ ነው። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በምታደርገው ጥረትም የውጭ ምንዛሬ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የቅርብ ጊዜ መረጃ ባይገኝም ቡና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 25 ሚሊዮን ከሚጠጋ የኢትዮጵያ ህዝብ ሕይወት ጋር የተሳሳረ ነው። ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ሲባል በሀገሪቱ በባለሀብቶች ጭምር በቡና ልማት ላይ ሰፊ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህም ምርትና ምርታማነት እያደገ ነው። ይህም ሰፊ ገበያ ይፈልጋል።
ሀገራችን የልዩ ቡና ባለቤትም ናት። በዚህም ከሌሎች አገሮች ቡና የተሻለ ዋጋ እንድታገኝ የሚያስችላት መሆኑ ይታወቃል። አሁን ባለው መረጃ መሰረት ግን ከቡናዋ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አይደለችም።
እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የቡና ግብይቱ ሳንካዎች ናቸው። በቡና ግብይት ላይ በትኩረት መሥራትን የግድ ይላሉ። ሀገሪቱ ከቡና ማግኝት ያለባትን ጥቅም ያስቀራሉ። በመሆኑም በቡና የዓለም ገበያ በህገወጥ መንገድ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላትን አደብ ማስገዛት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር መሆን ይኖርበታል። ይህ ዓይነቱ ህገወጥ አሠራር በማያዳግም መልኩ መታረምም ይኖርበታል።
የሚታረመው ደግሞ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላትም የጋራ ጥረት ነው። ከዚህ አንጻር የቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን ዝቅተኛ የቡና መሸጫ ዋጋ ለማስቀመጥ የሀገሮች ተሞክሮ መሰረት አድርጎ ለመሥራት ለመንግሥት ሃሳብ ማቅረቡን ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። መንግሥት ይህን ሃሳብ ዓይቶ ወደሥራ ማስገባት ያስፈልጋል።
በቡና ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር ምርት ገበያ መጋዘን ውስጥ የነበረውን የጥራት ችግር ቡናው ከመኪና ሳይወርድ ግብይት የሚፈጸምበትን ሁኔታ በመፍጠር ለመፍታት እየሠራ መሆኑ አንድ ጥሩ ነገር መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ በስፔሻሊቲ ቡናችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ ግድ ይላል። ገጽታችንን በመገንባት፣ ቀደም ሲል ቡናው ከሚታወቅባቸው ሀገሮች በተጨማሪ አዳዲስ ፍላጎቶችን በማጥናት እና በማነፍነፍ ተጠቃሚነትን ማስቀጠል ይገባል።
ቡና የውጭ ምንዛሬ ምንጫችን ነው። ከቡና የወጪ ንግድ የምንጠብቀውን ዋጋ ለማግኘት ብዙ መሥራት ያለብን እንዳለ ሆኖ ገበያውን እያየን ቡናውን ከእጃችን ማውጣቱን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም። ባቀረብነው ቡና የምንጠብቀውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደማንችል ስንረዳም የቡና ዋጋ ሲወድቅ እንደሚደረገው ሁሉ ቡና በብዛት በመላክ ከቡና የወጪ ንግድ ለማግኘት የታቀደውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳካት መሥራት ይገባል።
የቡና ዋጋ ገና ለገና ይጨምራል በሚል ቡናውን ይዞ መቆየት አይገባም፤ የማምረቻና የመሳሳሉትን ዋጋ መሸፈኑን በማረጋገጥ በብዛት ለዓለም ገበያ ማቅረብም ያስፈልጋል።
በመሆኑም የግብይቱን ሳንካዎች በማስወገድ በላኪዎችና በአገር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ማስቀረት እንዲሁም የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ግኝት እቅድ ማሳካት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011