ዓርብ የገድ ቀኔ ነው። ዓርብ መጥቶ ሳይቀናኝ ቀርቶ አያውቅም። በረከቶቼ ሁሉ ዓርብ እለት የተዋወኳቸው ናቸው። አያቴ ታዲያ ዓርብን አትወደውም። ዓርብ ምን እንዳደረጋት እንጃ ምንም ይሁን ዛሬ ዓርብ ነው የምትለው ፈሊጥ አላት። እኔን እንኳን ብዙ ጊዜ ዛሬ ዓርብ ነው ደማቅ ልብስ አትልበስ። ዛሬ ዓርብ ነው ወደወንዝ እንዳትወርድ። ዛሬ ዓርብ ነው ከቤት እንዳትወጣ ብላኝ ታውቃለች። ዓርብና አያቴ ለምን በዛ ልክ እንደተጠማመዱ ሳላውቅ አደኩ። አድጌ እንኳን የዓርብ በረከት አልተወኝም።
አንድ ከሰዓት..ጀምበር ወደቤቷ ስታዘግም ያው እንደነገርኳችሁ ዓርብ እለት ነው ከቤት ወጣሁ። ከቤት ወጥቼ ግን አልቀናኝም ገዴ ባልኩት ዓርብ ላይ ወዴትም የማያንቀሳቅስ አንድ አደገኛ የሴት ልጅ ውበት ገጠመኝ። ከቁጥጥሬ ውጪ የሆነ ‹ዋው› የሚል የአድናቆት ድምጽ ከአፌ ሲወጣ ማስቆም አልቻልኩም። ዓርብ ብዙ ዕድሎችን አሳይቶኝ ያውቃል እንደዛሬ አድርጎኝ ግን አያውቅም። አስፓልቱን ስትሻገር ቆሜ ሳያት አስታውሳለሁ። አስፓልቱን ጨርሳ ከፊት ለፊት ካለ ዘመናዊ ካፌ ስትገባ ቆሜ ሳያት ነበር።
ወደገባችበት ካፌ አቀናሁ። ‹ሴት ኃጢያት ናት። እንደ ሴት ልጅ ዓለም ኃጢያት የላትም። ሁሉም ኃጢያት ግን የሚሰረዩት በኃጢያተኛዋ ሴት ነው የሚል ከየት እንደመጣ የማላውቀው ሀሳብ ያቋረጠችውን አስፓልት ሳቋርጥ ተዋሓደኝ። ሀሳብ አለቀቀኝም ‹ሁሉም የወንድ ልጅ ኃጢያት በሴት ልጅ የሚሰረይ ነው። ሴት የወንድ ንስሐው ናት› አለኝ ያው ሀሳብ። አስፓልቱን ጨርሼ የገባችበት ሆቴል ገባሁ። ትንሽ አልፍታኝ ማንም እንዳያያትና እንዳያገኛት በሚመስል ሁናቴ አንድ ሰው ብቻ በምታስቀምጥ ብቸኛ ወንበር ላይ በብቸኝነት ተቀምጣ አገኘኋት። አቀማመጧን ታክኬ በብዙ ነገር እርግጠኛ ሆንኩ። የመጀመሪያው ሰው እንዳልቀጠረች እና እንዳልቀጠራት። ሰው ብትቀጥር ማንም ፈልጎ በማያገኛት ሰዋራ ቦታ ላይ ራሷን አትሰይምም ነበር አልኩ። ቀጥሎ..የሆነ ሩህሩህ እጅ የምትፈልግ መሰለችኝ። አቀማመጧ..አይዞሽ ባይ ክንድ የሚፈልግ መስሎ አዕምሮዬ ውስጥ መጣ። ቀጥሎ..ቀጥሎ ብዙ አሰብኩ። ያሰብኩት ሁሉ እውነት ከሆነ ሀሁ ላጠና እንደገና ትምህርት ቤት መግባት እንዳለብኝ አመንኩ። ይቺን ቆንጆ ሴት በገመትኩት ግምት ውስጥ እውነት ሆና ካገኘኋት እስካሁን ድረስ ቆንጆ ሴቶችን በሚመለከት የማውቀው ነገር ሁሉ ውሸት ነው ስል ደመደምኩ። የሆነው ሆኖ ፊት ለፊቷ ተቀመጥኩ። እንድታየኝ ሆኜ።
የዛሬ ትልቁ ጉዳዬ ይቺን ሴት መተዋወቅ እንደሚሆን አላጣሁትም። መተዋወቅ ብቻ አይደለም በቀሪ ዘመኔ ሙሉ የምደነቅበትን አጋጣሚ መፍጠር እንዳለብኝ ሲሰማኝ ነበር። የሴት መልክ አይቼ ቃላት ያጣሁበት የመጀመሪያው ቀን በወንድነቴ ውስጥ ተፈጠረ። ከራሴ አልፌ ለብዙ የሰፈር ልጆች የሴትን ልብ የሚቆፍር በውብ ቃላት ደብዳቤ እንዳልጻፍኩ እና በምናገራቸው ውበታም ቃላት ሴቶች በፍቅር እንዳልወደቁልኝ ዛሬ ለዚች ሴት አቅመ ቢስ ሆንኩ። ፍጹምናዋን የምገልጽበት አንደበት አጠረኝ።
ዓርብን ዛሬ ገና ፈራኋት። በልጅነቴ የተዋወኳትን ቅዱስ ዕለት ሰጋኋት። ስትቸረኝ የኖረችውን ዕድል አሳይታ ልትነሳኝ፣ በዚች ሴት ልትቀጣኝ አመሻሽ ላይ ከቤት ያስወጣችኝ መሰለኝ። በመደነቅ አፌን የከፈትኩባቸው፣ በተመስጌን ባዶዬን የሞላሁባቸው ያለፉ ዕድሎቼ ይቺን ሴት የራስ ከማድረግ ጋር አይደለም ከመተዋወቅ ጋር ሲነጻጸሩ እንኳን ኮሰሱብኝ። ፊት ለፊት በደንብ አየኋት። ሞባይሏ ላይ አቀርቅራለች። ቀይ ናት..ምሥራቅ አድማስ ላይ እንዳቅላላች አራስ ጀምበር። ፀሐይን የሚመስል የዓለም አይኖችን ሁሉ የሚያጥበረብር ውበት አላት። ሰማይን የሚያክል ለብዙ ነፍሶች የሚበቃ ሰፊ ሴትነትም። አልተኳኳለችም..ከንፈሯ ላይ ብቻ ቀይዳማ ቀለም ይታየኛል። ሳታየኝ ባቀረቀረችበት ስልኬን ድምፁን አጥፍቼ ፎቶ አነሳኋት። ዝቅ ያለች እንስት፣ ብርሀን የረጨ ስክሪን ላይ አቀርቅራ ስልኬ ላይ ተፈጠረች።
ላወራትና ላናግራት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ራሴን አሰናዳሁ። በዛ ዝምታና በዛ ብቸኝነት ውስጥ እንዴት ብዬ መግባት እንዳለብኝ ያሰላሁትን ስሌት ከአንድ እስከ ዩኒቨርስቲ እስክማር ድረስ አልሞከርኩትም። ሊተወኝ ያልቻለ መጥፎ ባሕሪዬ ሴት ስቀርብ መጀመሪያ የሚመጣልኝ ውሸት ነው። ወደሕይወቴ የመጡ ሁሉም ሴቶች በውሸት ጀምሬ በእውነት የቋጨኋቸው ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ይቺን ሴት በእውነት ልቀርባት ልቤ አስገደደኝ። እውነት መልኩን አላውቀውም..። ፊቷ ስቀርብ ምን እንደምላት እንኳን እርግጠኛ አልነበርኩም። እርግጠኛ የሆንኩበት አንድ ነገር ልዋሻት እንደማይገባኝ ነው።
ከሁነኛ ውሸት ወደሁነኛ እውነት መሸጋገር ኪሎማንጃሮን የመውጣት ያክል አንገዳግዶኝ ነበር። ለዚች ሴት የሚሆን ሁነኛ እውነት በዓለም አጣሁ። በውሸትና በእውነት መካከል የሆነ ነገር ትውስ አለኝ። ትውስታዬ እንዳይሰወርብኝ ሰግቼ ወንበሬን ይዤ ወደተቀመጠችበት ሄድኩ። ስታየኝ በትንሹ ደንገጥ ብላ ተረጋጋች።
እንደደረስኩ ‹ጠባቂዎችሽ የሉም? አልኩ ዙሪያዬን እየቃኘሁ።
‹የምን ጠባቂ? ስትል ግራ ለመጋባት ሞከረች። አካሏ ላይ ብቻ አይደለም ድምጽዋም ላይ ብቸኝነት የወደቀባት ሆና አገኘኋት።
‹መቼም ይሄ ውበት ያለጠባቂ ነው የሚንቀሳቀሰው ትይኝና ዓመት እንዳልስቅ› አልኳት።
ሳቀች..የትም ያልተሰማ ውበታም ሳቅ። የቪክቶሪያን ፏፏቴ የሚያስንቅ ደስ የሚል ሳቅ አደመጥኩ። ሳቋ ሌላ ውበቷ ሆኖ አደነዘዘኝ። ማደንዘዣ እንደወጉት ሰው ደነዘዝኩ። በሴት ሳቅ ስደነዝዝ ያ የመጀመሪያዬ ሆነ። ሀይ ስኩል እያለን በሳቋ ብቻ ያፈቀርኳት ወጋታ በዚች ሴት ሳቅ ደበዘዘችብኝ።
‹እስከዛሬ ውበቴን በተመለከተ ከወንድ አፍ ሰምቼው ያሳቀኝ ወሬ አልነበረም› አለች።
‹ለምን? አልኩ ተቻኩዬ። ተቻኩዬ ብቻ አይደለም በችኮላዬ ውስጥ ግራ መጋባትም ነበረበት።
‹ሁሉም ወንዶች የሴትን ልጅ ውበት በተመለከተ አንድ ዕውቀት ብቻ ነው ያላችሁ። እንዲህ እንዳንተ ቆንጆ ነሽ፣ ታምሪያለሽ ብቻ። እኔ ቆንጆ ነሽ ብቻ የሚለኝን ወንድ አልፈልግም። ወደሕይወቴ የሚመጣው ወንድ ሌሎች ወንዶች ያላዩትን የሚያይ እንዲሆን እፈልጋለሁ። አዲስ ነገር ናፋቂ ነኝ› ካለችኝ በኋላ አሳዘንኳት መሰለኝ እንጃ ‹ዛሬ ግን አስቀህኛል እንኳን ደስ አለህ› አለችኝ።
እንደዛሬ የኮራሁበት አጋጣሚ የለም። ስንት ጀብድ የሠራ ወንድነቴ ይቺን ሴት ማሳቅ በመቻሉ የተሰማውን ኩራት የትም አላስተናገደም። እንዴትም ባስብ ወደሕይወቷ መግቢያ ቀዳዳ አጣሁ። ቀላል ሆና የማትቻል ሆነችብኝ። ቀላል ሆኖ አለመቻል ይቻላል?
ቀጥዬ ምን ማለት እንዳለብኝ ያሰብኩትን ማሰብ፣ የተከዝኩትን ትካዜ የትም፣ መቼም፣ ለማንም እንደማልደግመው ባለሙሉ ተስፋ ነበርኩ። ወደልቧ መግቢያ ቀዳዳ አጣሁ። ትንሽዬ የማርያም መንገድ ሻትኩ። በመጨረሻም በሳቋ መግባት እንዳለብኝ አሰብኩ። ዘፍጥረት ታወሰኝ በሔዋን ሳቅ ሞት እንደመጣ። ጊዜ አላጠፋሁም ‹ከዛሬ ጀምሮ ያለምንም ክፍያ ለውበትሽ ዘብ ልቆም ራሴን አዘጋጃለሁ› አልኳት ከተውኩት ውሸት ጋር እየተገናኘሁ።
ከቅድሙ የተለየ መልከ ልውጥ ሳቅ አስተናገድኩ። በአንድ ጉሮሮ የተለያየ ሳቅ? አጄብ አልኩ። አንድ አይነት ሳቅ የላትም። ቅድም የተደነኩበት፣ ልጅነቴን ያስረሳኝ ሳቋ በሌላ ኃይለኛና መልከኛ ሳቅ ተቀይሮ ለሁለተኛ ጊዜ ደነዘዝኩ። ከሳቋ ሌላ ወደዚች ሴት ልብ መግቢያ መንገድ እንደሌለኝ ለብዙኛ ጊዜ እርግጠኛ ሆንኩ።
ጆሮዬ የማይታመን ነገር ሰማ። ‹ደስ ይለኛል› ስትል ሰማሁ። ዓርብ መጥቶ አፍሬ አላውቅም።
ቀጥዬ የተሞላቀቅኩ ይመስለኛል። ዘና ለማለት እየሞከርኩ (በዛ ውበት ፊት ዘና ማለት የማይቻል ከተቻለም በሚሊዮን ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ እንደሆነ የገባኝ እኔ ብቻ ነኝ) ታዲያ ምን አሞላቀቀኝ? እኔጃ! ብቻ ያልገመትኩትን የእሺታ መልስ በመስማቴ እንደሚሆን አታጡትም።
‹ጥበቃዬን ከዛሬ መጀመር እፈልጋለሁ። እናም ዛሬ ማታ ራት ልጋብዝሽ ምኞቴ ነው› ስል ቅደም ተከተሉን ስለመጠበቁ እርግጠኛ ያልሆንኩትን፣ ቀጥሎ ምን እንደምትለኝ ማወቅ አይደለም ለመገመት የማልደፍርበትን ጥያቄ ጠየኳት።
ከአፏ መቼም የማይታመን አንድ እውነት ሰማሁ ‹እንደምኞትህ ይሁን› የሚል። ያን አይነት ምላሽ ስለመስማቴ ለማመን ስንት ደቂቃ ዝም እንዳልኩ አላስታውስም።
ስልክ ተቀያየርን እንደምኞቴ አሪፍ ራት በላን። በነጋታው ‹አዲስ ነገር ያለህ ትመስላለህ። ነፍሴ አዲስ ነገር ላለው ወንድ ቅድሚያ ትሰጣለች..እናም እስከወዲያኛው አብረኸኝ ብትሆን ምኞቴ ነው› አለችኝ።
የሆንኩትን አላስታውስም። የማስታውሰው ነፍሴ በልቤ ውስጥ በደስታ ስትሰቃይ ብቻ ነው። በሕይወቴ ጣይ ያልወጣችበት ወንድነት አልነበረኝም..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015