አዲስ አበባ፡- አምስት የውጭ አገር ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡ አገር በቀል ባንኮች ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እና ቀድሞ የነበራቸውን ስትራቴጂ መከለስ እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎንም የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡
‹‹ሥራውን አሁን እያጠናቀቅን ነው፡፡ አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው:: ከለጋሾች አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው:: በወራት ዕድሜ ለህዝብ እንደራሴዎች ይቀርባል:: ስለዚህ ስራው እየተፋጠነ ነው” ብለዋል አቶ ሠለሞን::
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሠለሞን ገልጸዋል:: እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ፤ የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን ከገበያ እንዳያስወጧቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሰሩ ይገባል፤ለዚህም የተቀመጠ አሰራር መኖሩን አመልክተዋል::
ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉትና ይህም ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በዚሁ አግባብ ክትትል እንደሚደረግ አቶ ሠለሞን አስረድተዋል:: አሁን ቀድሞ እንደተለመደው መሄድ አይቻልም ያሉት አቶ ሠለሞን፣ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ፤ በጀት ተመድቦም በሰፊው መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል::
“በተለይም ማን ከማን ጋር መሥራት አለበት፤ ማን ከማን ጋር ቢዋሃድ ያዋጣል የሚለውን ከአሁኑ ማሰብ ይገባል:: ከውጭ ከሚመጡ ተቋማትም ጋር እንዴት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ከወዲሁ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፤ ካፒታል፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ እንዴት መጋራት እንደሚቻልም ባንኮቹ ከወዲሁ ሊያጤኑት ይገባል:: በተጨማሪም ሌሎች ባንኮችን ሄደው መጎብኘት አለባቸው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
በተለይም የቦርዱ አመራርና አሰራር፣ ማኔጅመንቱ የሚያስተዳድርበትን መንገድና ሥርዓት፣ የህግ ማዕቀፎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የሰው ኃይል አስተዳደር ጭምር ማወቅ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል::
ወደዚህ ሥራ ለመግባትም የፋይናንስ ተቋማት ካፒታላቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የገለፁት ምክትል ገዥው፤ ቀደም ሲል የነደፉትን ስትራቴጂ ብቻ መጠቀም ሳይሆን መልሰው ማየትና መከለስ አለባቸው፤ ከሚመጣው ሁኔታ አኳያ እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን ታሳቢ የሚያደርጉ ጉዳዮችን በሙሉ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ መሥራት ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል::
በአጠቃላይ ባንኮች መጪውን ጊዜ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ያደረገ ሥራ እና አቅም መገንባት ብሎም በሴክተሩ ላይ የተሻለ ልምድና እውቀት አካብተው መገኘት እንዳለባቸው አቶ ሠለሞን አሳስበዋል::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015
Very interesting details you have remarked, thanks for posting.
Euro travel guide