በንግዱ ዘርፍ እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን በተለይም ነጋዴ ሴቶችን ለማበረታታት ያለመው የመጀመሪያው የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹ችግሮቻችንን እንስበር፤ ድልድይ እንገንባ›› በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡ ነጋዴ ሴቶችን ለማበረታታት ባለመው በዚህ የንግድ ኤክስፖ ነጋዴ ሴቶች፣ አምራቾች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የንግድ መሪዎችና የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በኤክስፖው ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ከቀረቡት መካከል የመዋቢያ ዕቃዎች፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የጽዳት ዕቃ አምራቾች፣ የአገር ባህል አልባሳት አምራቾች፣ የልጆች መማሪያና መጫወቻ ቁሳቁስን እንዲሁም የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ይዘው የቀረቡ ነጋዴ ሴቶች፣ ሴት አምራቾችና ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ይገኙበታል፡፡ ተሳታፊዎቹ ኤክስፖው የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የልምድ ልውውጥ ለማግኘት እንዲሁም ችግሮቻቸውን በመወያየት መፍታት የሚያስችላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወጣት ሶሊያና ጎሹ የግሩም ሌዘር የሽያጭ ባለሙያ ናት፡፡ ግሩም ሌዘር የእጅ ቦርሳዎችን፤ ቀበቶ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው የወንድና የሴት ቦርሳዎች፣ ለጉዞ የሚያገለግሉ ቦርሳዎች እንዲሁም የቆዳ ጃኬቶች ለሴትም ለወንድም እንደሚያመርት ጠቁማለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ ምርቶቹንም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ ምርቶቹንም በአገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም የውጭ አገር ጎብኚዎች በሚያዘወትሩበት ቦሌ አካባቢ በሚገኙ የገበያ አዳራሾች፣ ጊዮን ሆቴልና ሌሎችም ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ያቀርባል። ከአገር ውስጥ በተጨማሪም እያንዳንዱን የቆዳ ውጤት በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያዎችም ያቀርባል፡፡
ግሩም ሌዘር የቆዳ ውጤት ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን የጠቀሰችው ወጣት ሶሊያና፤ በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ ለሴቶች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ ነው የተናገረችው፡፡ በዚህም ሴቶችን እንደሚያበረታታና ወደ ሥራ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ትገልጻለች፡፡
ኤክስፖው የነጋዴ ሴቶች መሆኑ በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች መለየት የሚችሉበትና ለችግሮቻቸው መፍትሔ የሚያፈላልጉበት፣ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ነው ትላለች፡፡ ለዚህም ግሩም ሌዘር ያለውን ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም የገበያ ዕድል ለሌሎች ለማካፈልና ከሌሎች ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ተናግራለች፡፡
ሌላው አምራች ዚ የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ ዘለቃሽ ሽፈራው አካል ጉዳተኛ ናት፡፡ ሴት አካል ጉዳተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው መሥራት እንደሚችሉ ትገልጻለች፡፡ ዊዴፕ ከተባለ ሴቶችን የሚደግፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በቆዳ ምርት ስራ የተለያዩ ስልጠናዎችን ማግኘቷን የምትናገረው ወይዘሮ ዘለቃሽ፣ ስልጠናውን ወደ ተግባር በመቀየርም ቦርሳዎችን፣ ቀበቶና ሌሎች ምርቶችን አምርታ ለገበያ እያቀረበች መሆኗን ትገልጻለች።
ቦርሳዎች፣ ቀበቶና የተለያዩ ቁሳቁስን እንዴት ማምረት እንደሚቻል ባገኘችው ስልጠና በቤቷ ውስጥ የቆዳ ውጤቶችን እያመረተች ለገበያ የምታቀርበው ወይዘሮ ዘለቃሽ፤ የገበያ መዳረሻዬ የአገር ውስጥ ውስን ቦታዎች ናቸው ትላለች፡፡ በመኖሪያ ቤቷ የምታመርታቸውን የቆዳ ውጤቶች ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች በሚያዘጋጇቸው ባዛሮች ላይ በማውጣት ለገበያ ታቀርባለች፡፡ ወደ ተለያዩ ቢሮዎች በመውሰድ ለሠራተኞች በብድር እንደምታቀርብም ገልጻ፤ በእንዲህ አይነት የንግድ ኤክስፖዎች ላይ መሳተፍ መቻሏ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው የገለጸችው፡፡ ኤክስፖው ምርቶችን ከመሸጥ ባለፈ ችግሮቻችንን ለመንግሥት አካላት ተሰባስበን ማቅረብ ያስችለናል ብላለች፡፡
ሌላው በኤክስፖው የተሳተፈው ድርጅት ልጆች እየተጫወቱ መማር የሚችሉባቸውን የመማሪያ ቁሳቁስ ያቀረበው ‹‹ኪንደር ኢዱኬሽናል ቶይስና ጌም›› ነው። የድርጅቱ የማርኬቲንግ ባለሙያ ጽጌረዳ ተስፋዬ እንዳለችው፤ ድርጅቱ ከውጭ አገር የሚመጡ የልጆች መጫወቻና መማሪያ ቁሳቁስን በአገር ውስጥ ያመርታል፤ በኤክስፖው ምርቶቹን ይዞ የቀረበው ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ነው፡፡ ቁሳቁሱን በአገር ውስጥ ለማምረት የወሰኑትም ከውጭ የሚገቡትን ለማስቀረት ነው፡፡ ወደ ማምረቱ ሥራ ለመግባት ባሰቡ ጊዜም በከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡ የጥናቱ ውጤት የሚያሳየውም መጫወቻና መማሪያ ቁሳቁስ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ አገር የሚገቡና በፕላስቲክ የተሠሩ መሆናቸውን ነው፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ ቁሳቁሱን በአገር ውስጥ ማምረት እንደተቻለ የገለጸችው ጽጌረዳ፤ ቁሳቁሱ የሚሠሩትም በአገር ውስጥ ግብዓት /በእንጨት/ እንደሆነ ነው የተናገረችው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ወደ ገበያው እየገባ ሲሆን፣ ስዊድሽ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በከተማ ውስጥ ለሚገኙ አምስት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች መማሪያና መጫወቻ ቁሳቁሱን እያቀረበ ይገኛል ብላለች፡፡
ምርቱ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሳ፣ ለውጭ ገበያም መቅረብ እንደሚችል ተናግራለች፡፡ መማሪያና መጫወቻ ቁሳቁሱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ጀርመን አገር ከሚገኙ ደንበኞች ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ ጠቁማለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የልጆች መማሪያና መጫወቻን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተለይም ምርቱን በአገር ውስጥ ግብዓት በሆነው በእንጨት መሥራት መቻሉ ልጆች አገራቸውን ይበልጥ እንዲረዱ ከማድረግ ባለፈ ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ለማስረዳት ያስችላል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውሮ የተመለከታቸው የህጻናት መጫወቻና መማሪያ ቁሳቁስ በሙሉ ከውጭ የሚገቡ ነገር ግን በአገር ውስጥ በቀላሉ መሠራት የሚችሉ ስለመሆናቸው ያስረዳችው ጽጌረዳ፤ እንደዚህ ያሉ ኤክስፖዎች ምርቱን ለማስተዋወቅና የገበያ ዕድል ለመፍጠር እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑም ተናግራለች።
በኢፌዴሪ ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙና ጀማል፤ ‹‹በብሔራዊ የልማት ዕቅድ የተለየ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ነው›› ይላሉ፡፡ ዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ በተለይም የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑ ሴቶችን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ማድረግ ለኢኮኖሚው ዕድገት ከሚኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለማህበረሰብ ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለው ይላሉ፡፡
ዋና ስራ አስፈሚዋ እንዳሉት፤ በእንደዚህ አይነት ኤክስፖዎች የአገር ውስጥ ምርቶችን ማህበረሰቡ እንዲያውቃቸውና በአገሩ ምርት በኩራት እንዲጠቀም እንዲሁም ለሌሎች አምራች ድርጅቶች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱ አምራቾችን በማስተዋወቅ ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋት ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ እንዲያድጉና ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምሩ በሚደረገው ድጋፍ ሴት ባለሃብቶች በቀጣይ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊደረስበት ከታለመው የዕድገት ደረጃ ለመድረስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና በአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው አካታችነትና የእኩል ተጠቃሚነትን በማስፈን የግሉን ዘርፍ ሚና ከፍ ማድረግ ትልቅ ስትራቴጂ ተደርጎ መወሰዱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸው፤ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም የነጋዴ ሴቶች፣ ሥራ ፈጣሪዎችንና ቢዝነስ መሪዎችን ለማበረታታት የተለያዩ የማበረታቻ ስልቶችን እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች፣ ሴት አምራቾችና ሴት የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና መሪዎች ብድር ማግኘት የሚችሉበትን፣ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትን ለሥራ አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ መደረጉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ኤክስፖው ፈር ቀዳጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ኤክስፖው በአይነቱ ለየት ያለና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሥራ ፈጠራ፣ በአምራችነት፣ በኢንዱስትሪ፣ በገበያ ትስስር፣ በመሰረተ ልማትና በተወዳደሪነት ሴቶች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችና ፓኬጆችንና ማስፈጸሚያ ስልቶችን በመቅረጽ ወደ ተግባር እንዲገቡ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ሴቶችን ለማብቃት እየተሰሩ ባሉ ሰፋፊ ሥራዎች የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች፣ የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና መሪዎች ከብድር አቅርቦት፣ ከወለድ ምጣኔና ከእፎይታ ጊዜ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር ከመፍጠር፣ ከምርት ማቀነባበር፣ ከመስሪያ ቦታ፣ ከቴክኖሎጂ ተደራሽነት ጋር እንዲሁም ከሌሎች ሥራዎቻቸው የሚስተጓጉላቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ፡፡
እነዚህ ተግዳሮቶች ሴቶች የንግድ ሥራቸውን በፍጥነት እንዳያሳድጉና የልፋታቸውን ውጤት ማግኘት እንዳይችሉ ትልቅ ማነቆ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋር ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ ተሰማርተው ያሉ ሴቶች ተሰባስበውና ተደራጅተው ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ ከዓመት በፊት የሴቶች የኢኮኖሚ ማጎልበት ፎረም መስርቷል፡፡ ፎረሙ በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ፣ የሚገጥማቸውን ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ፣ መንግሥትም እንደ ድልድይ ሆኖ እንዲያግዝና ሌሎች ተቋማትም በጋራ ውጤታማ እንዲያደርጓቸው ያስችላል፡፡
ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግሥት ብቻ የሚሠራው ሥራ በቂ እንዳልሆነ ሚኒስትሯ ጠቅሰው፣ የልማት አጋሮች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። ይህም የሴቶችን የኑሮ ደረጃ እንዲሁም የቤተሰባቸው የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ኤክስፖው ነጋዴ ሴቶች አብረው የሚመካከሩበት፣ አንዷ ከሌላዋ የምትማርበት በመሆኑ ሴቶች በጋራ የጀመሩትን ይህ ጉዞ በስኬት ማስቀጠል እንደሚችሉ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡ ኤክስፖው ምርቶችን ከመሸጥና ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የሚኖረው መስተጋብር ሴቶችን በንግዱ ዘርፍ ለማብቃትና በሥራ ፈጠራ ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩል ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ነው ያስታወቁት፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች፣ አምራች ሴቶችና ሴት የንግድ ተቋም መሪዎች 35ሺ ለሚደርሱ ጎብኚዎች ምርትና አገልግሎታቸውን በማስተዋወቅ እንዲሁም በመሸጥ ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችሉበት አጋጣሚ መሆኑ ተጠቁሟል። ከ100 በላይ የሴቶች አምራች ድርጅቶች በኤክስፖው መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡
ኤክስፖው ሴት የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ላይ ያሉ ሴቶችን የሚያበረታታና ሴቶች ፍትሐዊና በጾታ እኩልነት ላይ የተመሰረተ እገዛ እንዲያገኙ በተለይም ለሴቶች ትልቅ ፈተና የሆነውን የገበያ ተወዳዳሪነትና ዘላቂነት የገበያ ትስስር ችግሮቻቸውን ከመፍጠር አንጻር ያለው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነው የተጠቀሰው፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015