ማንም ሰው ቆሻሻን የሚፀየፍ ቢሆንም የእርሷ ግን የተለየ ነው፡፡ በፍፁም ቆሻሻ ማየት አትፈልግም። ቆሻሻ ካየች ጥላ ከመሄድ ይልቅ ታፀዳለች፡፡ የአካባቢ ጠበቃም ነች፡፡ ደግሞም ገጣሚ ናት፡፡ አካባቢ በተለያዩ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች እንዲጎዳ አትፈልግም፡፡ ለዚያም ነው የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከአካባቢ ጋር ቁርኝት ያለውን የትምህርት መስክ መርጣ ያጠናቸው፡፡
የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች የራሷን ገቢ ለማግኘት ተማሪዎችን አስጠንታለች፡፡ ድንገት በተፈጠረ ስህተት በወጣ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ አጋጣሚውን ተጠቅማ በተመረቀችበት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ሞያ አይደለም ለሴቶች ለወንዶች እንኳን ፈታኝ በሆነው የቆዳ ማምረት ሥራ መደብ ተቀጥራ ሠርታለች፡፡ የፋብሪካው ቁንጮ መደብ በሆነው የኮሜርሺያል ማናጀር ሥራ ላይ ተመድባም ኃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች፡፡
በአንድ አጋጣሚ የተመቻቸ የማነቃቂያ ንግግር መድረክ ከአንድ የሥራ ፈጠራ ባለቤት ጋር እንድትገናኝ ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ ይኸው ዕድል የራሷን እሴት በመጨመር አዲስ ምርት ይዛ ወደ ገበያ ብቅ እንድትል ረድቷታል፡፡ ይህንኑ አዲስ ምርት ይዛ ወደ ገበያ በስፋት ለመግባትም ቅድሚያ ኅብረተሰቡን የማገልገል መርህ ይዛ ብቅ ብላለች፡- የካባው ትሬዲንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሔም ደጁ፡፡
ወይዘሮ ቤተልሔም ውልድትና እድገቷ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ነው፡፡ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ ሆኖም አባቷ ልጆቻቸው የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ በመፈለጋቸው እርሷም ከቤተሰቡ ጋር አብራ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በእውቀት ለህብረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ትምህርት ቤት ተምራ አጠናቃለች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቋ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገብታ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ በ1998 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ በጊዜው ትምህርቱ በጣም ከባድ፣ ሥራ የማይገኝበትና ብዙ ተማሪዎችም የማይመርጡት የነበረ ቢሆንም እርሷ የምትወደው የትምህርት መስክ በመሆኑ በትጋት ተምራ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ በዩኒቨርሲቲው በነበራት ቆይታም የተማሪዎች መማክርት ፕሬዚዳንት ሆና አገልግላለች፡፡ ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘም በተለይ ሴቶች መብታቸው እንዲጠበቅ በርካታ ሥራዎችን ሠርታለች፡፡
ወይዘሮ ቤተልሔም ቀድሞውኑ ከአካባቢ ጋር በተያያዘ የመሥራት ፍላጎት ያላት በመሆኑ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስክን የመጀመሪያዋ ምርጫ አድርጋና ወዳው ነበር የተማረችው፡፡ በተለይ ደግሞ የፀዳ አካባቢን ከመፍጠር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥራዎችን የመሥራት ጉጉቷ ለትምህርቱ ልዩ ፍቅር እንዲኖራት አድርጓል።
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላም በገቢ ራሷን ለመቻል ወዲያው ነበር ሥራ መፈለግ የጀመረችው፡፡ ሆኖም በተማረችበት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስክ በቀላሉ ሥራ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ሥራ እስክታገኝ ድረስ ሌላ ሥራ መፍጠር ነበረባትና ‹‹ልጆች እናስጠናለን›› የሚል ጽሑፍ በትንሽ ወረቀት ላይ አሳትማ በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች አሰራጨች፡፡ በጊዜው አስር ልጆችን በማስጠናት በወር እስከ ሁለት ሺ ብር ድረስ ታገኝ ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ በወቅቱ ትልቅ የነበረ ቢሆንም ታዲያ ቤተሰቧ በተለይ አባቷ የራሷን ሥራ ፈጥራ እንድተሠራ ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ የማስጠናቱ ሥራ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡
የኋላ ኋላ ግን በተማረችበት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ሞያ ሥራ ማግኘቷ አልቀረም፡፡ አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ የሚገኘው ባቱ ቆዳ ፋብሪካ የሥራ ቅጥር በጋዜጣ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ፋብሪካው ለወንዶች ብቻ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ያወጣ ቢሆንም ጋዜጣው በስህተት ሥራው ለሴቶችም ለወንዶችም መሆኑን ጠቅሶ በማውጣቱ ይህን አጋጣሚ መጠቀም እንዳለባት ተረዳች። እናም ለመወዳደር አመለከተች፡፡
ማመልከቻዋን ካስገባች በኋላ ግን ሴት የሚለው ነገር ፋብሪካውን ጥያቄ ውስጥ ከቶት ነበር፡፡ ስለዚህ የቃለ ምልልስ ፈተናውን ለማለፍና በቦታው ላይ ብቁ ሆና ለመታየት በሚገባ ራሷን ለመግለፅ በርካታ ጥረቶችን አደረገች፡፡ ጥረቶቿ ሁሉ ፍሬ አፍርተው ለቃለ ምልልስ ቀርባ ፈተናውን አለፈች፡፡ በዩኒቨርሲቲ በነበራት ቆይታ ስታደርጋቸው የነበሩ ሁለገብ እንቅስቃሴዎችም ፈተናውን አልፋ ቆዳ ፋብሪካውን እንድትቀላቀል ረድተዋታል፡፡
ቆዳ ፋብሪካውን እንደተቀላቀለች የትምህርት ማስረጃዎቿ በአብዛኛው የማኔጅመንት ሥራውን እንድትሠራ የሚያስችልና ለዚሁ የቀረበ በመሆኑ አለቃዋ አብራው እንድትሠራ ጥያቄ አቀረበላት፡፡ ነገር ግን የእርሷ ፍላጎት በተማረችበት የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት መስክ የቆዳ አመራረት ሂደትና ቴክኖሎጂው ምን እንደሚመስል ለማየት ነበር፡፡ ለሴት የሚመቸው የቆዳ ፋብሪካው የሥራ ክፍል የመጨረሻ የቆዳ ማጠናቀቂያ ክፍል ቢሆንም እርሷ በብዛት ወንዶች የሚያከናውኑትንና ፈታኝ የሆነውን የቆዳ የመጀመሪያ ማምረት ሥራ ክፍልን መረጠች፡፡
በዚህ የሥራ ክፍል ውስጥ እያለች ‹‹አትችለውም›› የሚል ቅሬታ ከፋብሪካው በኩል ነበርና በሳምንቱ ሥራውን በሚመለከት ሪፖርት እንድታቀርብ ተጠየቀች። ቀን ከሌት ሳትተኛ በሳምንቱ በሥራ ክፍሉ ያየቻቸውን እያንዳንዱን ሥራዎች ከትባና አርባ ሁለት ገፅ ሪፖርት ፅፋ ለአለቃዋ አቀረበች፡፡ አለቃዋም በሪፖርቱ ደስተኛ ነበር። እንዲያውም ሪፖርቱን በማየት በፋብሪካው የጥናትና ልማት ሥራ ክፍል ብዙ ሳትደክም እንድትሠራ ፍላጎት አሳደረ፡፡ እርሷም በዚህ የሥራ መደብ ላይ ለመሥራት ደስተኛ ነበረች፡፡
በዚሁ ሁኔታ ላይ እያለች ነበር ትዳር የያዘችውና የፀነሰችው፡፡ ስለዚህ ሥራው በእርሷ ላይም ሆነ በልጇ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በሃኪሞች ስለተነገራት በቆዳ ምርት ሂደት ጥቅም ላይ የሚውለውን ኬሚካል መራቅ ነበረባት፡፡ ከሌላው የፋብሪካ ሥራ ግን አልራቀችም፡፡ ወደ ቢሮ ሥራዎች መጥታ ሥራዋን ቀጠለች፡፡ አለቃዋም ገና ስትቀጠር ሊያስገባት የነበረውን የኮሜርሺያል ማናጀርነት የሥራ መደብ ሰጣት፡፡ ደመወዟም አደገ፡፡ ትራንስፖርትም ተመቻቸላት፡፡
በኮሜርሺያል ማናጀርነት የሥራ መደብ የቆዳ ፋብሪካውን ለአስራ አምስት አመታት አገልግላለች፡፡ መጀመሪያ በገባችበት የቆዳ ማምረት የሥራ ዘርፍ ደግሞ ለሁለት አመት ሠርታለች፡፡ ፋብሪካው እንዲያድግና ብቃቱ እንዲጨምር የበኩሏን አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡ በዚሁ የሥራ ሂደት ታዲያ አማራጮችን በማየት የማስተር ኦፍ ኮሜርስ ትምህርቷን ሕንድ አገር ከሚገኘው ኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በርቀት ተከታትላ በ2004 ዓ.ም አጠናቃለች፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለች ታዲያ ሁሌም በአእምሮዋ የሚመላለስ ጥያቄ ነበር፡፡ ይኸውም ‹‹በርግጥ ቤተልሔም የራሷን ህልም እየኖረች ነው?›› የሚል ነበር። ‹‹የራሴ የምትለውና ወደራሷ ብታቀርበው ልታደርገው የምትችለው ነገር ምንድን ነው?›› የሚል ቅርብ ነገር እንዳለም ፈለገች፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለች ነበር በአንድ የማነቃቂያ መድረክ ላይ ታድማ ህልማችሁን ግለፁ ስትባል ‹‹ኢትዮጵያን ንፁና አረንጓዴ በማድረግ አካባቢን ንፁህ ለማድረግ የሚተጋ ትውልድ መፈጠር አለበት›› ብላ የመለሰችው፡፡
‹‹የእኔ አስተዋፅኦ ቢሆንና ትንሽ ነገር መሥራት የምችልበትን አካባቢ መፍጠር ብችል›› ብላ እንቅስቃሴ እያደረገች ባለችበት ወቅት በዚሁ የማነቃቂያ መድረክ አቶ አስናቀ በፍቃዱ ከተባለና መጥፎ ሽታ የሚያጠፋና ከእፅዋት የሚሠራ የፈጠራ ሥራ ይዞ በመድረኩ ከታደመ ሰው ጋር ተገናኘች፡፡ ምርቱ የአገር ውስጥ መሆኑ ደግሞ ለማወቅ ይበልጥ አነሳሳት፡፡ ስልክ ቁጥር ተቀብላ በማግስቱ ደወለች፡፡ ተቀራርበው ተወያዩ፡፡
እናም እንደ ኬሚካል ኢንጂነር ባለሞያነቷ በቅድሚያ የፈጠራ ሃሳቡን በማድነቅ መጥፎ ሽታ ማፅጃ ምርቶቹ ወደገበያ ወጥተው ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ቀለማቸውን ሳይቀይሩና ሳይበላሹ ረጅም ጊዜ የሚቆዩበትን የእሴት ጭመራና የላብራቶሪ ፍተሻ ሥራዎች ሠራች፡፡ ምርቱ በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን በኩል ማረጋገጫ እንዲያገኝና ሕጋዊ እንዲሆንም አድርጋለች፡፡ የሥራ ፈጠራ ባለቤትነቱንም በ2015 ዓ.ም መግቢያ በአቶ አስናቀ በፍቃዱ ስም አስመዝግባዋለች፡፡ የምርት ናሙና ፍተሻም በተመሳሳይ አሠርታለች፡፡
ቀጥሎ ለአቶ አስናቀ የፈጠራ ሥራ የሚገባውን ክብር በመስጠትና ክፍያም በመፈፀም በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ካባው ጄኔራል ትሬዲንግን በጋራ በማቋቋም የመጥፎ ሽታ ማጥፊያ ምርቶችን ማምረት ጀመረች፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ በትምህርት ያገኘችውን ሳሙና የማምረት እውቀት በመጠቀም ከሽታ ማጥፊያው ጋር አቀናጅታ የሚያፀዳ ብቻ ሳይሆን ሽታም ጭምር የሚያጠፋ የራሷን የልብስ ፈሳሽ ሳሙና፣ የመስታወት ማፅጃ ሳሙናና የዕቃ ፈሳሽ ሳሙና መፍጠር ችላለች፡፡
በተለይ ደግሞ የመስታወት ማፅጃ ፈሳሽ ሳሙናው ከማፅዳትና ሽታ ከማጥፋት ባለፈ ጀርሞችንም የሚገድል መሆኑ እሴት የተጨመረበት የፈጠራ ሥራዋን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ምርቱ ለቁስል ማፅጃም እንዲሆን በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ፍቃድ እንዲያገኝ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ መጥፎ ሽታ ማጥፊያ ምርቶቹን ለማምረትም አገር በቀል ዛፎችና ቅጠላቅጠሎች ከገበሬዎች ተሰብስበው በግብአትነት ይውላሉ፡፡ ለልብስና ዕቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙናዎች ማምረቻ ደግሞ ከውጭ አገር የሚገቡ የኬሚካል ግብዓቶች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡
ሥራውን በ50 ሺ ብር መነሻ ካፒታል አዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ የጀመረው ካባው ትሬዲንግ በአሁኑ ጊዜ ካፒታሉ ወደ 800 ሺ ብር አድጓል፡፡ ለስድስት ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በቀጣይም ምርቶቹን በማሳደግ ካፒታሉን ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር የማሳደግ እቅድ ይዟል፡፡ ማሽኖችን ለመግዛትም በልማት ባንክ በኩል ብድር እንዲመቻች ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ የሥራ ፈጠራው በገንዘብ እንዲደገፍም ለልማት ባንክ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ኅብረተሰቡ ከአካባቢ ጋር በተገናኘ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት ብዙ መሠራት እንዳለበት የምትገልፀው ወይዘሮ ቤተልሔም፤ ከዚሁ በተጓዳኝ ደግሞ ኅብረተሰቡ በአገር ውስጥ ምርት ላይ ያለውን በጎ ያልሆነ አመለካከት ለመቀየርና በምርቶቹ ላይ እምነት እንዲኖረው በብዙ መሥራት እንደምትፈልግ ትገልፃለች፡፡ ለዚህም መጀመሪያ ኅብረተሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ትጠቅሳለች፡፡ በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ እንዲገዛና በምርቶቹ ላይ ያለውን እምነት እንዲገነባ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትጠቁማለች፡፡
ከዚህ አንፃር እርሷም ምርቶቹን ለጥቁር አንበሳና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች፣ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ ለሕፃናት ማቆያ፣ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችና ወረዳዎች በነፃ በማቅረብ ኅብረተሰቡ ምርቶቹን እንዲለማመድ ማህበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ምርቶቹ በአሁኑ ጊዜ በሸማቾች ዘንድ ተቀባይነትን እያገኙ መምጣታቸውን የምትጠቅሰው ወይዘሮ ቤተልሔም፤ በመጀመሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን ማቅረብና ኅብረተሰቡን ማገልገል እንጂ ትርፍ ማግኘት ተቀዳሚ ዓላማዋ እንዳልሆነ ትገልፃለች፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሰዎች የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታቸውን የሚያስተካክሉበት ሥርዓት እንዲዘረጋና ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት አሠራር እንዲፈጠር የማድረግ ውጥን እንዳላት ትጠቁማለች፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ወደቢዝነሱ ዓለም መቀላቀል ለሚፈልጉና የራሳቸውን ሀሳብ አመንጭተው ህልማቸውን እውን በማድረግ ራሳቸውን መለወጥ ለሚፈልጉ ሴቶች በቅድሚያ በራሳቸው ላይ እምነት ማሳደር እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡ ሴቶች በራሳቸው ልክ ማመን ሲጀምሩ ሀሳባቸውን አመንጭተው ህልማቸውን እውን ማድረግ እንደሚችሉም ታስረዳለች፡፡ ለዚህም ሁሉም ሴቶች የተሰጣቸውን ጥበብ አውርደው ማለፍ እንዳለባቸው ትመክራለች፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015