እንደመነሻ …
ዛሬም በርካታ የማንነት ፈተናዎች ከታለፉበት፣ ብዙ የህይወት እጥፋቶች ከተዘረጉበት፣ አሰልቺ የኑሮ ውጣወረዶች ከሚተረኩበት ሰፊ ግቢ ውስጥ እገኛለሁ። አሁንም እንደዋዛ ያለፉ የማይመስሉ ፣ አስደናቂ ታሪኮችን እየሰማሁ ነው፡፡
በትናንቱ የህይወት መንገድ እንደጥላ እልፍ ብለው ከሄዱት እውነታዎች መሀል በርካቶቹን በአግርሞት አደመጥኩ፡፡ እነዚህ ታሪኮች የዕንባና ሳግ ስሜት ይዘዋል ፡፡ ለእያንዳንዱ ባለታሪክ ያልደበዘዙ ማህተሞች ሆነው ጊዚያትን ቆጥረዋል ፡፡ ከማንነታቸው ተዋህደው፣ ከሀዘን ደስታቸው ተቀድተው ዛሬን ደርሰዋልና በአይረሴ ትዝታዎች ሁሌም ይተረካሉ፡፡
እነዚህ ሀቆች ትናንትን አልፈው ለዛሬ መታወሳቸው በምክንያት ሆኗል ፡፡ ‹‹ነበር›› ሲሉ ለማውሳት፣ ‹‹አልፏል›› ብሎ ለመንገር የመልካም ሰዎች ጥረትና ስብዕና ታክሎበታል፡፡ በሰፊው የሚሰጡ እጆች ፣ ቸርነት አርፎበታል፡፡ ትናንትን አልፎ ዛሬን ለማንጋት፣ ትጋት ከቅንነት፣ ቅንነት፣ ከበጎፈቃድ ተሳስሮ ‹‹ሰው›› ይሉት ማንነት ተገንብቷል ፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ግን መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነው አልነበረም፡፡ ያለፈን ታሪክ ለመቀየር፣ ጨለማውን በጸሀይ ለመተካት ብዙ ጋሬጣዎች፣ በርካታ ሻካራማ መንገዶች ታልፈዋል፡፡
ዛሬ በሙዳይ በጎ አድራጎት ቅጥር ግቢ በርካቶች በሰላማዊ ዕንቅልፍ እፎይታን ተችረዋል፡፡ አሁን ያለፈ ህይወታቸው የማንነታቸው ታሪክ ሆኖ ተሰናብቷል፡፡ ዛሬን በአዲስ ትንፋሽ በተቀበሉት አዲስ ዓለም ስለነገ መንገዳቸው ይወጥናሉ ፡፡ ስለመጪው ህይወታቸው ያስባሉ፡፡ ትናንትና በራሱ
ታሪክ ሆኖ ቢሸኝም ፣ የማንነታቸው እውነታ ግን ‹‹ነበር›› ተብሎ እንዲህ ይተረካል፡፡
እንግዳዋ…
አንድ ማለዳ የሙዳይን ቅጥር ግቢ አልፋ የገባችው ሴት ከቢሮው ደርሳ በሩን በዝግታ አንኳኳች፡፡ ሴትዬዋ ብቻዋን አልነበረችም፡፡ በቅርብ የተወለደ ጨቅላ አዝላለች። የጀርባዋን ልጅ በአንድ እጇ እየመታች አጥብቃ የያዘቻትን ትንሽዬ ህጻን እየጎተተች ወደውስጥ አለፈች፡፡ ለወይዘሮ ሙዳይ እሷን መሰል እንግዶች ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ በየቀኑ በርካቶችን እየተቀበለች ማስተናገድ ልምዷ ነው፡፡
እንግዳዋና ሙዳይ ጭውውት ይዘዋል፡፡ ሙዳይ ጥያቄዋን አውቃ ፍላጎቷን ልትሞላ ቃል ገብታለች፡፡ ሴትዬዋ በትዳር አብሯት የቆየው ባሏ ትቷት ከጠፋ ቆይቷል፡፡ በአራስ ጎኗ ልጆቿን ማሳደግ፣ ራሷን መምራት ቢሳናት አገሯ ልትገባ ወስናለች፡፡
ውሳኔዋ ግን እንዳሰበችው አልሆነም፡፡ አቅም ቢያንሳት፣ እጅ ቢያጥራት መላ ዘዴውን ፈለገች ፡፡ ‹‹አያሳፍረኝም›› ካለችው ግቢ ደርሳ ማልዳ በሩን አንኳኳች፡፡ ወይዘሮ ሙዳይ በሰማችው ታሪክ ከልብ አዝና ለመንገዷ ይበቃል ያለችውን ገንዘብ ቆጥራ ሰጠቻት፡፡
እመጫቷ በተሰጣት ፣ በሆነላት ሁሉ ተደሰተች። ከታላቅ ምስጋና ጋርም ግቢውን ለቃ ወጣች፡፡ አሁን አገሯ የሚያደርሳትን በቂ መሳፈሪያ ይዛለች፡፡ የምትሄድበት ቦታ ተወልዳ ያደገችበት፣ ደግ ክፉ ያለፈችበት ቀዬ ነው፡፡ የእሷ መሄድ አሁን ካለችበት በተሻለ ነገን እንደሚያሻግራት ታምናለች ፡፡
ይህ በሆነ ማግስት እመጫቷ ልጇቿን ይዛ ወደ ትውልድ አገሯ አቀናች፡፡ አገር ቤት የረገጠው እግሯ ቀድሞ ያመራው ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ነበር፡፡ እንደገባች ዘመዶቿን በአካል አገኘች፡፡ በደስታ፣ በፈፈግታ የተቀበላት የለም፡፡ በትናንት ማንነቷ የሚያውቋት ሁሉ ፊት አዞሩባት ፡፡ ሰርታ ትለወጣለች ያሏት ወጣት ሁለት ልጆች ይዛባቸው መምጣቷ አልተመቻቸውም፡፡
ውሎ አድሮ የልጆቹ አባት ከጎኗ እንደሌለ ባወቁ ጊዜ ፊት እየነሱ አገለሏት ፡፡ እየደጋገሙም ልጆቿ ‹‹ዲቃላ›› መሆናቸውን ይነግሯት ያዙ፡፡ ይህን ስታይ ከፋት፣ ሆድ ባሳት። በዘመድ መሀል ባዕድ መሆኗ ተሰማት ፡፡ በድንገት የሰው አገር ሰው የሆነች አስኪመስላት ተከዘች፡፡ ተስፋ አልቆረጠችም። ነገሮች እንደሚቀየሩ ገምታ ቀናትን ቆጠረች፡፡ አዲስ ለውጥ አልመጣም፡፡
አባት አልባ ሁለት ህጻናት ያላት ሴት አሁን ተስፋ ቆርጣለች፡፡ ከእንግዲህ ማንም ከጎኗ የለምና መወሰን ፣ መቁረጥ አለባት፡፡ ከዚህ በኋላ በማይፈልጓት ሰዎች መሀል መኖር ህይወቷን ይፈትናል፡፡ ቆም ብላ አሰበች፡፡ መላልሳ ከራሷ መከረችና ከውሳኔ ደረሰች፡፡ ወደመጣችበት ከመመለስ ሌላ ምርጫ አልነበራትም፡፡
የመልስ ጉዞ …
እመጫቷ እንግዳ ዘመዶቿ ፊት ቢነሷት መኖር ተስኗታል፡፡ ውላ አድራም ከራሷ መክራ ከውሳኔ ደርሳለች፡፡ አሁን ያመጧት እግሮቿ መልሰው እየወሰዷት ነው፡፡ አዲስ በባ ስትደርስ የተቀበላት አልነበረም፡፡ ሁለት
ህጻናት ልጇቿን ይዛ መንከራተት ጀመረች፡፡ እነሱን እያሉ በሰራተኝነት የሚቀጥራት እንደማይኖር ታውቃለች። ጥቂት ቆይታ ግን በራሷ ወሰነች፡፡ ከነ ልጆቿ ያለምንም ደሞዝ ከሚያሰሯት ሰዎች ዘንድ ተቀጠረች፡፡ አሁን ለእመጫቷ ህይወት በመጠኑ የቀለለ መስሏል፡፡ ጉልበቷን እየከፈለች የዕለት ጉርስ ታገኛለች፡፡ ስራ መግባቷ ጎዳና ከመውደቅ. የሰው እጅ ከማየት አድኗታል፡፡
ዓመታት ያለ ደሞዝ ክፍያ ቀጠሉ፡፡ እናት ሁለት ልጆቿ እያደጉላት ነው፡፡ እሷ በምትከፍለው የላብ ዋጋ እነሱ በልተው ከቤት ውለው አድረዋል፡፡ ያለአባት ያለማንም እገዛ የሚኖሩት ህጻናት ከእናታቸው ውጭ ሌላ ዓለም አያውቁም፡፡ ህይወትና ተስፋቸው እሷና እሷ ብቻ ነች፡፡
እናት ወር ሙሉ ሰርታ ደሞዝ ይሉትን አትጠብቅም። እንደሌሎች ያማራትን መግዛት፣ ያሻትን ማድረግ አትሞክርም ፡፡ የእሷ ክፍያ የልጆቿ መኖር ፣ የወር ደሞዟም ከቤት ውሎ ማደር ነው፡፡
አጋጣሚው…
ከቀናት በአንዱ በአሰሪዎቿ ቤት እንዲህ ሆነ ፡፡ ትልቋ ልጅ በድንገት ቤት የነበረን መስታወት ሰበረች። ይህን ያዩ ባለቤቶች በእጅጉ ተቆጡ፡፡ ድርጊቱ የሆነው በአንዲት ትንሽ ልጅ እጅ ቢሆንም ‹‹ይቅር›› ማለትን አልወደዱም።ቁጣና ተግሳጽ ያልበቃቸው ሰዎች አስቸኳይ ርምጃ ወሰዱ። ዓመታትን ያለክፍያ አብራቸው የዘለቀችው ሰራተኛ ልጆቿን ይዛ እንድትወጣ ወሰኑባት፡፡
ይህ አይነቱ ድንገቴ ጉዳይ ለልጆቹ እናት አስደንጋጭ ነበር፡፡ በዓመታት ቆይታዋ የቋጠረችው ገንዘብ፣ ለእኔ የምትለው ጥሪት የለም፡፡ ቤቱን ለቃ ስትወጣ በእጇ የነበሩት ሁለት ልጆቿ ብቻ ናቸው፡፡ ዛሬም ትጠጋበት ትጠይቀው ወዳጅ ዘመድ አታገኝም፡፡
አሁንም እንደቀድሞው ምርጫ ይሉት የላትም ፡፡ እንዲያም ሆኖ በዝምታ አልቆየችም፡፡ ልጇቿን እንደያዘች በቤት ሰራተኝነት ያለደሞዝ ለመቀጠር ተማጸነች፡፡ ይህን ማሰቧ ብቻውን መፍትሄ አልሆነም፡፡ እሷን እንጂ ልጆቿን ያልፈለጉ ቀጣሪዎች ዕድል ነፈጓት፡፡ ‹‹እንቅጠራት›› ያሉ ጥቂቶች ደግሞ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ፡፡ ተያዥ የሚሆናት ዋስ እንድታመጣ አጥብቀው ጠየቁ ፡፡
ይህን ማድረግ ያልቻለችው እናት ዳግም በሀሳብ ተዋጠች፡፡ እንዳሰበችው ዕቅድ፣ ውጥኗ አልተሳካም፡፡ በተስፋ መቁረጥ ተመላለሰች፡፡ ያልሰመረው ሙከራዋ እንደጅምሩ አልቀጠለም፡፡ ውሎ አድሮ የመጀመሪያ ማረፊያዋ ከጎዳና ዳር ሆነ ፡፡
ሕይወት በጎዳና …
አሁን እናትና ልጆች ከቤት ወደ ጎዳና ወጥተዋል፡፡ ይህ ቦታ ለነዚህ ነፍሶች አዲስ ዓለም ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ኑሮ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ቀኑ በጭንቅ ያልፋል። ጨለማው ይዞት የሚመጣው ጣጣ ለሴት ልጅ ይከብዳል ፡፡ እናት ልጆቿን ታቅፋ ቀናትን በጎዳና ላይ ገፋች፡፡
ለዕለት ጉርስ እጇን መዘርጋት ስትጀምር ልጆቿን ያዩ የእጃቸውን ይጥሉላት ያዙ፡፡ በሌላ ወገን ጎዳና መምጣቷን ያስተዋሉ አንዳንዶች በትኩረት ዓይን ጣሉባት፡፡ ልጆች ብትይዝም ወንዶቹ ሊምሯት አልፈለጉም ፡፡ ሊተናኮሏት፣ ሊደፍሯት ቀን አስልተው ማድባት ያዙ፡፡
አንድ ሌሊት ሴትነቷን ያሰቡ ጥቂት ወንዶች ጨለማውን ተተግነው ወደእሷ ተጠጉ፡፡ ሁኔታቸው የገባት እናት ልጆቿን እንደያዘች ልትታገላቸው ሞከረች፡፡ ይህ ሙከራዋ ድርጊቱን አስቁሞ በአካሏ ጉዳት አስከተለ ።፡ አንድ እጇ ክፉኛ ተሰበረ፡፡
ከዚህ ምሽት በኋላ የእናትና ልጆች የጎዳና ዓለም ስጋት ገባው ፡፡ የምሽቱን ችግር ለመከላከል ቀኑን በመኝታ የምታልፈው ሴት ሌሊቱን ያለዕንቅልፍ ማደር ልምዷ ሆነ፡፡ ለእሷ የቀንና ሌቱ መለዋወጥ ለምና እንዳታድር ምክንያት ፈጠረ፡፡ አሁን ልጆቿ ሊራቡ እሷም ልትቸገር ነው ፡፡
ይህ ሲገባት ዕቅዷን ቀየረች፡፡ ለሌቱን ከቤተክርስቲያን እያደረች ቀኑን ለዕለት እንጀራዋ አዋለች ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ አልቀጠለችም፡፡ ቤተክርስቲያን ማደሯ ሲታወቅ በግቢው ድርሽ እንዳትል ታገደች፡፡ አሁንም እናት ስለልጆቿ መኖር አርቃ አሰበች፡፡ ከእንግዲህ ተስፋ የምትለው ምርጫ ተሟጧል፡፡
‹‹እሰሩኝ…››
አስቸጋሪው እወነታ ከሌለው ጥግ አደረሳት፡፡ ለህይወቷ መላ ያጣችው ሴት ከፖሊስ ጣቢያ ደርሳ ‹‹በቃ ! እሰሩኝ›› ስትል እጇን ሰጠች፡፡ ሁኔታዋ ያሳዘናቸው ፖሊሶች አልጨከኑም ፡፡ ቀን ስትለምን ውላ ማታ ከእሰረኞች ጋር እንድታድር ፈቀዱላት፡፡
ይህ ዕድል ግን ብዙ አልቀጠለም፡፡ ለአዳር መመላለሷን ያልወደዱት ሌሎች ፖሊሶች ‹‹ሁለተኛ እንዳትመጪ›› ሲሉ ከለከሏት፡፡ መፍትሄ ያጣችው እናት ዳግመኛ ሀዘን ዋጣት ፡፡ ከእንግዲህ ደፍራ ጎዳና መመለስ አትችልም፡፡ ይህን ልሞክር ብትል በእሷና በልጆቿ ያለፈው ክፉ ታሪክ ይደገማል፡፡
ከጣቢያው በተባረረች ማግስት ከስፍራው አልራቀችም፡፡ ከእይታ ሳትወጣ ከፖሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት ከሚገኝ ስፍራ ማረፊያዋን አደረገች፡፡ እንዲህ መሆኑ ቢያንስ ከጥቃት እንደሚታደጋት አምናለች፡፡ እናት አሁንም ከነበረችበት ህይወት አልወጣችም፡፡ በቀን ውሎዋ ከልመና ተቀምጣ ለአዳር ልጆቿን ይዛ ትመጣለች፡፡
አሁንም እየተጨነቀች፣ እየተከዘች ብዙ አሰበች። መስራት የለመዱ እጇቿ ለልመና መዘርጋታቸው አብዝቶ ይቆጫታል፡፡ ይህ የሆነው ስለልጆቿ መሆኑን ታውቃለች። ለእነሱ መኖር ያልከፈለችው ዋጋ የለም፡፡ በዚህ ዕውነት የእናትነት ፍቅሯ አስገድዷት ብዙ ሆናለች፡፡
ይህን እያሰበች ዓይምሮዋ ርቆ ተጓዘ፡፡ ከዓመታት በፊት በሙዳይ በጎአድራጎት ግቢ የተዘረጉላትን ቸር እጆች አስታወሰቻቸው፡፡ ልቦናዋ መላልሶ ያለፈውን እውነት አስታወሳት፡፡ አንዳች ሀይል ስፍራው እንድትደርሰ ሹክ ሲል ተሰማት፡፡ ካለችበት ተነስታ በፍጥነት ወደስፍራው ተጓዘች፡፡
በሩ ሲከፈት…
የጎዳናዋ ሴት ግቢውን አልፋ የቢሮውን በር በዝግታ አንኳኳች፡፡ ከበሩ ጀርባ ያለ የሴት ድምጽ ‹‹ይግቡ›› ሲል ተሰማት፡፡ ይህን ድምጽ ከዚህ በፊት ታውቃዋለች። አላንገራገረችም በሩን በፍጥነት ከፍታ ፊት ለፊት ከምታያት ወ ይዘሮ ጋር ተፋጠጠች፡፡
በእንግድነት ከበሩ የቆመችው ሴት ከወይዘሮ ሙዳይ ጋር ማውራት ይዛለች፡፡ እዚህ ስፍራ የመጣችው ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት አራስ ልጇን አዝላ ትልቋን ልጅ እየጎተተች ነበር ፡፡ የዛኔ የተቀበላት መልካም ፊት ዛሬም አልተለወጠም። አሁንም የሚያደምጡ ጆሮዎች ፣ በጥልቅ የሚያስተውሉ ዓይኖች ከእሷ ጋር ሆነዋል፡፡
የልጆቹ እናት የነበረውን አስታውሳ ከእሷ ከተለየች የሆነባትን ታሪክ ሁሉ አወጋች፡፡ ሙዳይ በሰማችው አሳዛኝ ጉዳይ ሁሉ አዝና ሊደረግላት የምትሻውን ጠየቀቻት ፡፡ ሁለቱ ሴቶች ልብ ለልብ ተግባቡ፡፡ ይሻላል ካሉት ውሳኔ ለመድረስ ጊዜ አልባከነም፡፡
እናት ከልጆቿ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ጎዳናውን ተሰናበተች፡ ፡ የመጀመረያው ለውጥም ሴት ልጇን ትምህርትቤት በማስገባት ተጀመረ ፡፡ ትንሹ ልጅ በማዕከሉ እያደገ ህይወት በመልካም መስመር ቀጠለ፡፡
እናት ልጆቿ ቦታ ሲይዙ ሙያዊ ስልጠና አገኘች። በማዕከሉ የሸክላ ስራን ተምራ በብቃት አጠናቀቀች፡፡ ስልጠናው ምርጥ ባለሙያ አድርጎ ለምርጫ አቀረባት ።፡ ትናንት ለልመና የተዘረጉ እጆች አሁን ለስራ ሰልተው ተጉ። ቀድሞ በሀፍረት የተሰበረ አንገት ዛሬን በኩራት ተቃና፡፡
ከሸክላው ስራ ጎን ለማዕከሉ እንጀራ የምትጋግረው ሴት በእጇቿ ሙያ የተመረጠች ተደናቂ ሆነች፡፡ ውሎ አድሮ በራስ መተማመኗ ዳበረ ፡፡ ይህኔ ለህይወቷ ይበጃል ያለችውን ስራ ለየች፡፡ ወደፊት ያዋጣል ባለችው የእንጀራ መጋገር ስራም አተኮረች፡፡
በዚህ ፍላጎቷ ሁሉ የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ከጎኗ አልራቀም፡፡ የጎደለውን እየሞላ ፣የጠየቀችውን እየሰጠ በእርምጃዋ ልክ ተከተላት፡፡ ልጆቿን በትምህርት አልቃ ራሷን የቻለችው ሴት የትናንት ታሪኳን ለውጣ የደሞዝ ተከፋይ ሆነች።
ውሎ አድሮ ጠንካራዋ ሴት ቤት ተከራይታ ያጣችውን ህይወት መለሰች፡፡ በተሟላ የቤት ዕቃ፣ የጎዳናን ታሪክ ‹‹በነበር›› የተካችው ወይዘሮ ዛሬ ስለሆነላት እንጂ ስለሆነባት ክፉ ታሪክ ብቻ አታስብም ፡፡ ለእሷ የትናንት ታሪኳ በዛሬው ስኬት ተክሷል፡፡ የፈሰሰ ዕንባዋ በጥንካሬዋ ታብሷል፡፡ ያለፈ ፈተናዋ ለዛሬ ማንነቷ ድንቅ አሻራ ነው ፡፡ አዎ! ትናንት በራሱ ታሪክ እንዲህ ሆኖ ታልፏል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ሙዳይን መሰል በጎ አድራጊ ልቦና እስትንፋስን ለማስቀጠል እውነተኛ አጋር ሆኗል፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015