ትናንት ከጎናችን የነበሩ ብዙ ሰዎች ዛሬ እንደዋዛ ተለይተውናል። ጠዋት በሰላም በጤና አብረውን ሲሰሩ፣ሲጫወቱ ወዘተ የነበሩ በርካቶችን ከሰአት በኋላ እንደ ጤዛ ያጣንበት አጋጣሚ ቤቱ ይቁጠረው። ማታ ደህና እደር ተባብለውና ነገ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው የተለያዩትን ወዳጅ ህይወት ማለፍ ጠዋት የተረዱ ጥቂት አይደሉም። ብዙዎቻችን እንዲህ አይነት አስደንጋጭ ነገሮች ሲገጥሙን የምንደርስበት ድምዳሜ ይለያያል። አንዳንዶቻችን እንደ ፈጣሪ ቁጣ ልንቆጥረው እንችላለን። ሌሎች ደግሞ ሌላም ሌላም ነገር ሊያስቡ ይችላሉ።
የህክምና ባለሙያዎች ብዙ ጊዜ የሚሉት ነገር አለ፣ ‹‹አለመታመም ጤነኛ መሆን ማለት አይደለም።›› እውነት ነው። ትናንት አንድም የጤና እክል ያላየንባቸው ሰዎች ዛሬ ህይወታቸው አልፎ ስናይ ጤነኞች ነበሩ ብለን መደምደም በራሱ ጤናማ አይደለም። ብዙዎቻችን አሁን ላይ ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሆንን ሊሰማን ይችላል፣ ነገር ግን ጤነኞች ነን ምንም የጤና እክል የለብንም ማለት አይደለም። ይህን ደግሞ ሳይንሱም ቢሆን እንደሚደግፈው አይጠፋንም።
ብዙዎቻችን ወደ ሕክምና ማእከላት የምንሄደው ሕመም ሲሰማን ወይም አንዳች የጤና እክል ሲገጥመን ነው። ይህም መሆኑ አንዳንድ ሕመሞች በጊዜ ሳይደረስባቸው ይቀራል። ከዛም በላይ በቶሎ መሻሻል እንዳይኖር ሊያደርግና ከፍተኛ ወጪንም ሊያስወጣ ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውና እጅግ አሳሳቢ የሆነው የኩላሊት ሕመም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ሃኪሞች እንደሚናገሩት የሰው ልጆች ኩላሊት ሁለቱም ተዳክሞ ሃያ አምስት በመቶ እስኪቀር ድረስ አንድም ምልክት ላይታይ ይችላል፡፡
ድንገት ግን እዚያ ደረጃ ላይ በደረሰ ሰዓት ህይወት ለመንጠቅ ጊዜ ላይፈጅበት ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎች የዚህ ህመም ተጠቂ መሆናቸውን ባወቁ በቀናት ልዩነት አይሆኑ ሆነው ከአልጋ ቁራኛነት እስከ ህይወት ማጣት የሚደርሱት፣ ህመሙ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ያለ የሌለ ሃብታቸውን አሟጠው ከፍተኛ የህክምና ወጪ በማውጣት ለመዳን ሲጥሩ የሚታዩት፡፡ እንዲህ አይነት የጤና ችግሮች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው አስቀድሞ በየጊዜው በሚደረግ የጤና ምርመራ መታወቅ ቢችሉ ህይወትን እስከ ማጣት የሚያደርሰውን አደጋ በብዙ እጥፍ መቀነስ ይቻል ነበር፡፡
ይህን ለመከላከል እንዲቻል የጤና ባለሙያ ዎች የሚመክሩት ዓመታዊ የሆነ የጤና ምርመራ ማድረግን ነው። ይህም ከስር ከስር ሰዎች የጤናቸውን ሁኔታ እንዲከታተሉና በቶሎ እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል። ይህ ተደጋግሞ የሚነገረንና የምናውቀው ጉዳይ ቢሆንም ግን ተግባር ላይ የለንበትም። ግንዛቤውና መረጃው ቢኖረንም ባህሉን አላዳበርነውም፡፡
መደበኛ የጤና ምርመራ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት መካሄድ አለበት ወይም ቢካሄድ ጥሩ ነው የሚለው ላይ የጤና ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ የተለያየ አስተያየት ሲሰጡ ይደመጣል። በትንሹ በዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚመከር ግን በርካቶቹ ይመክራሉ።
ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደ ካንሰር እና አንዳንድ በቅድመ ጥንቃቄ ልንከላከላቸው የምንችላቸውን ሕመሞች ለመቆጣጠር ያግዛል። ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደ ቅድመ መከላከል ይቆጠራልም ይባላል። በዚህም ተከታታይነት ያለው ምርመራ ስለሚደረግ፣ ብሎም የቤተሰብ የጤና ታሪክ፣ የግል የአኗኗር ሁኔታና የመሰለው ስለሚነሳ፣ ከጤና ጋር በተገናኘ ያሉ ስጋቶች አብረው ሊነሱ ይችላሉ።
ከዚህና ከሚደረጉ ምርመራዎች በመነሳትም የጤና ባለሙያዎች በቀላሉ ሊደርሱ ይችላሉ የሚባሉ የጤና እክሎችን ቀድመው መከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን ተግባራዊ ያደርጋሉ። ከዛም ባለፈ አንድ ሰው ተላላፊ ላልሆኑ (በዘር ሊተላለፉ ለሚችሉ) በሽታዎች ያለውን የተጋላጭት ስጋት ለመለየት ያስችላል። ይህም ምልክቶች በብዛትና በስፋት ሳይታዩ አስቀድሞ በሽታው በቶሎ እንዲለይ እና ሕክምና በቶሎ እንዲሰጥ ያስችላል። ይህም በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ ጉዳት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የሚያግዝ ነው።
ከዚሁ ሳይርቅ፤ የተገኘ ወይም ምልክት የታየበት በሽታ ላይ ፈጣንና ተከታታይ የሆነ የጤና ክብካቤ እርምጃና የሕክምና መፍትሔ ለመስጠት ይጠቅማል። በቶሎ መደበኛ ሕክምና ጀምሮ ወደ ቀደመ ጤንነት ለመመለስም በእጅጉ ይረዳል። ‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ› እንዲሉ፤ ወቅትን ጠብቆ የጤና ምርመራ ማድረግ የግል ለውጥን ለመከታተልና ጤናማ የሆነ የአኗኗር መንገድን ለመከተል ትልቅ ሚና አለው። ለምሳሌ ጤናማ አመጋገብን በተመለከተ ከጤና ባለሙያ ተገቢውን ምክር ለማግኘት ብሎም ቀድሞ በማንኛውም አጋጣሚ የተደረገ ምርመራንና የምርመራ ውጤት ያለበትን ሁኔታ ለመከታተል ያግዛል። መድኃኒት እየወሰደ ያለ ወይም ቀደም ብሎ መድኃኒት የወሰደ ሰውም ጤናው ያለበትን ደረጃና ለውጡን ለመከታተል ያስችለዋል።
ከዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ስጋትን ይቀንሳል። ራሴን፣ ወገቤን፣ ጎኔን ወዘተ ያመኛል የሚልና መሰል የተለያዩ ምልክቶችን የሚያይ ሰው፣ የሕመሙ ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት ከመጨነቅ፤ ጥርጣሬዎችን ለማጥፋት እንዲህ ያለው የጤና ምርመራ ክትትል ትክክለኛውን የጤናውን ሁኔታ እንዲረዳ ያስችለዋል።
ይህንን እና መሰል ዓመታዊ የጤና ምርመራ ለማድረግ የገንዘብ አቅም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ በትንሽ ገንዘብ ጤና ጣቢያ ሄዶ ሙሉ ምርመራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ገንዘብ ይጠይቃል ቢባል እንኳን በኋላ ሕመም ሰውነት ላይ ሲሠለጥን ለመታከምና ለመዳን ከሚያስፈልገው ወጪ አንጻር ግን አነስተኛ ነው። ስለዚህም ለቅድመ ጥንቃቄ የሚያግዝ በመሆኑ በቅናሽ ዋጋ ምርመራ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የጤና ጣቢያዎችና የሕክምና ማእከላት በተቻለ አቅም አገልግሎቱን ለማግኘት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነውና እናስብበት፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2015