እንባቆም እባላለሁ፤ በህይወት ያለሁ ታሪካዊ ሰው ነኝ፡፡ በእርግጥ አባቴ የብዙ አጋጣሚዎች ባለቤት እንደሆነ ነግሮኛል፡፡ እናቴን እንኳን የተዋወቃት ሰርግ ቤት ወጥ ጨላፊ ሆና ስታሳልፍ እንደነበር አጫውቶኛል። ታላቅ ወንድሜ ሳይቀር ከሚስቱ ጋር ለቁም ነገር የበቃው በተሳሳተ ስልክ እንደሆነ አውቃለው፡፡ አንዳንዴ ከአባቴ የወረስኩት ይሆን እንዴ እላለው፡፡ ግን አይመስለኝም፤ እየሱስ እንዲህ ጽፎኝ ነው፡፡ እየሱስ ባይጽፈኝ እንኳን እሱ በተወው ባዶ ገጽ ላይ ራሴን አበላሽቼ ጽፌው ይመስለኛል፡፡
ከመጀመሪያ ፍቅረኛዬ ከትርሲት ጋር የተዋወቅነው በካርታ ጨዋታ ነበር፡፡ ካርታ ውሃ አጣጭ ሲሰጥ አስባችሁታል?
ወደ ህይወቴ የመጣችው ሁለተኛዋ ሴት ማክዳ ትባላለች፡፡ ዛሬ ላይ እንዴት ተዋውቀን እንዴት እንደተለያየን ሳስበው ይገርመኛል፡፡ የተዋወቅነው ሊፍት ውስጥ ነው፡፡ ለአባቴ የተላከ ዶክመንት ላደርስ ስድስተኛ ፎቅ ወደሚገኘው ቢሮው እየሄድኩ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ሴት ስቀርብ ቀድሞ አፌ ላይ የሚመጣው ውሸት ነው፡፡ በእውነት መንገድ ተጉዤ የራሴ ያደረኳት ሴት የለችም፡፡ ማክዳንም ዋሸኋት፡፡ በካኪ ፖስታ የተሸፈነውን የአባቴን ዶክመንት እያሳየኋት ሲቪ ነው አልኳት፡፡ ስራ ልወዳደር እየሄድኩ እንደሆነ ዋሸኋት፡፡
በአዛኝ አይን አየችኝ፡፡ ይቅናህ የሚል በጎነት ከእሷ ወደእኔ ተላለፈ፡፡ አሁን ላይ ሳስበው እነዛ አይኖች ሊባርኩኝ ወደህይወቴ የመጡ መለኮታዊ አይኖች ነበሩ እላለሁ፡፡
ሊፍት ውስጥ እያለን ‹አንድ ነገር ብጠይቅሽ እሺ ትይኛለሽ› አልኳት፡፡
‹ምንድነው› አለችኝ በጠይም አይኖቿ ጠይም አይኔን እየቃኘች፡፡
‹እሺ የምትይኝ ከሆነ በአንቺ እሺታ ውስጥ የዛሬው ቅጥር ይሳካልኛል፡፡ እንቢ የምትይኝ ከሆነ ደግሞ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር ተመኝቼ የሚሳካልኝ አይመስለኝም› አልኳት፡፡ ወደ አባቴ ቢሮ እየሄድኩ እኮ ነው፡፡ ድርጅቱ የአባቴ እኮ ነው፡፡
‹እኮ ምንድነው ልወቀው› በቅድሙ ትህትና ደግማ ጠየቀችኝ፡፡
‹እሺ ስትይኝ ነው የምነግርሽ› አልኳት
‹እሺ› ምንድነው፡፡
ልነግራት አፌን ስከፍት ሊፍቱ ስድስተኛ ፎቅ ደርሶ ውረዱ ሲል ተከፈተ፡፡ እኔ ስወርድ እሷ ቀረች፡፡ አባቴ ቢሮ ደርሼ ዳግም ልገናኛት ብዙ ጠበኳት፡፡ ግን አላገኘኋትም፡፡ በግምት ከስድስት ወር በኋላ ይመስለኛል አንድ ካፌ ቁጭ ብዬ ማኪያቶ ስጠጣ ከርቀት አየኋት፡፡ ደስ እያለኝ ነበር ሄጄ ያናገርኳት፡፡
‹አስታወሽኝ? አልኳት፡፡
እርግጠኝነት በጎደለው አካኋን ‹ሊፍት ውስጥ? አለችኝ፡፡ የማስታወስ ብቃቷን እያደነኩ ራሴን በአዎንታ ነቀነኩላት፡፡
‹ያን ቀን ግን ምን ልትነግረኝ ነበር እንደዛ ልቤን የሰቀልከው?
‹በነገርሽ ላይ ሁሉም ነገር አሪፍ ሆኗል፡፡ ያን ቀን አንቺ እሺ ባትይኝ ኖሮ አይሳካልኝም ነበር› ስል የውሸት ዘላበድኩ፡፡ ቀጥዬም ‹በድጋሚ የተገናኘነው በምክንያት ነው፡፡ ያን ቀን ቀንቶኝ ስራ ከጀመርኩ በመጀመሪያ ደሞዜ ራት የምጋብዛት የመጀመሪያዋ ሴት እንድትሆኚ ፍቃድ እየጠየኩሽ ነበር› ስላት በደንብ ሳቀች፡፡
በሚቀጥለው ቀን አሪፍ ራት ጋበዝኳት፡፡ ለስድስት ወር አብረን በፍቅር ቆየን፡፡ እንዴት እንደተለያየን ሳስበው ዛሬም ድረስ ያመኛል፡፡
ማክዳ የህይወት ዘመኔ ምርጥ ታሪኬ ናት፡፡ ነፍሷ በነፍሴ ውስጥ ዛሬም ድረስ አለች፡፡ ከህይወቴ ተሟጦ ያልወጣ እስትንፋሷን የምተነፍስ ይመስለኛል፡፡ በህይወቴ መጥተው ካለፉ ትናንትናዎች ውስጥ ዳግም እንድኖረው እድል ቢሰጠኝ እሷ ያለችበትን ትናንት እደግመው ነበር፡፡ ስንለያይ ለመጨረሻ ጊዜ ያልኳት አይረሳኝም፡፡ እንዲህ ነበር ያልኳት ‹አንቺ የታላቅ ነገር መጀመሪያ ነሽ፡፡ አንቺ የሌለሽበት ታላቅ ፍጻሜ የለም፡፡ አንቺ የደጋግ ነፍሶች ህልም፣ የመልካም ልቦች ራዕይ ነሽ። ከዚህ እስከዛ ጥግ የሌለሽ እግዚአብሄራዊ ሀቅ፡፡ ትንሹን ሰው ትልቅ አድርገሽዋል፡፡ ከፊትሽ ሳልሸሽ እንኳን ይቅርታ እንዳደረግሽልኝ አውቃለሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን እንባቆም እንዳትይኝ የማረባ ነኝና ስምኦን ብለሽ ጥሪኝ፡፡
እንዴት ተለያያችሁ አትሉኝም? ከእለታት በአንዱ ቀን አራት ኪሎ ከሚገኝ ካፌ ውስጥ ቁጭ ብያለሁ፡፡ አባቴን በሞት ካጣሁ ወዲህ የመኖር ትርጉሙ ጠፍቶኝ ግራ የተጋባሁበት ሰሞን ነበር፡፡ በልጅነቴ ውስጥ በወጣትነቴም ውስጥ ሳይሞት ስለሚኖረው አባቴ እያሰብኩ ትካዜ ላይ ነበርኩ፡፡ ከፊት ለፊቴ ጠረጴዛው ላይ ሞባይሌ፣ የመኪና ቁልፌና ግማሽ ያደረኩት ማኪያቶ ይታየኛል፡፡ እና ደግሞ ማንም ያልተቀመጠበት ባዶ ወንበር፡፡ መኪናዬ መንገድ ዘግታ ኖሮ ፓርኪንግ የሚሰራ አንድ ወጣት መኪናዬን ከመንገድ ላይ ዘወር እንዳደርግለት ነግሮኝ ከሀሳቤ እስከመለሰኝ ጊዜ ድረስ ሁሉ ነገሬ ስለሆነው አባቴ እያሰብኩ ነበር፡፡ መንገድ የዘጋች መኪናዬን አንፏቅቄ ስመለስ ከፊት ለፊቴ ከነበረው ባዶ ወንበር ላይ የሴት ቦርሳ ተቀምጦ አየሁ፡፡
ቦታዬ ጋ እንደደረስኩ ማክዳ ደወለችልኝ፡፡ ስልኬ ሳይለንት ስለነበር ሲበራ ነው ያየሁት፡፡ ጥሩ ስሜት ላይ ስላልነበርኩ አላነሳሁትም፡፡ ጠዋት ከቤት ስወጣ ከክፍለ ሀገር የምትመጣ ጓደኛ አለችኝ አስተዋውቅሀለው እንዳለችኝ ትዝ አለኝ፡፡ ወዲያው ስልኬ በርቶ ሲጠፋ አየሁት፡፡ ‹የት ነክ? ሩቅ ካልሆንክ የሆነ ቦታ እንድታደርሰኝ ነበር› የሚል የማክዳን መልዕክት አየሁት፡፡ ሩቅ ቦታ ነኝ ብዬ ስላሰብኩ ሳልመልስላት ወደ ትካዜዬ ተመለስኩ፡፡ አፍታ ቆይቼ ቀና ስል ከፊት ለፊቴ ባዶው ወንበር ላይ መላዕክ ትሁን ሰው የማትለይ አሳሳች ሴት ተቀምጣ አስተዋልኩ፡፡ ትካዜዬ ድራሽ አባቱ ጠፋ። ከቁጥጥሬ ውጪ የሆነ ‹ዋው! የሚል የአድናቆት ድምጽ ከአንደበቴ ሲወጣ ትዝ ይለኛል፡፡ ቀይ ናት። ወደቢጫነት የሚያደላ፣ ታጥቦ የተሸለተ የሚመስል አንጸባራቂ ጸዐዳ ቆዳ አላት፡፡ እንደ ሰባት ሰዐት ጀምበር አትዩኝ የሚል ውበት፡፡
አይን የሚፈሩ የሚመስሉ አይኖች አሏት፡፡ ደም የመሰለ፣ በንጋትና በመምሸት መካከል ያለ ከንፈር። የተለያዩ ቀለማት ያወዙት ርጥብ ከንፈር ከሰልካካ አፍንጫዋ ግርጌ ይታየኛል፡፡ እና የሸሚዟን አዝራር ጥሰው ያጮለቁ ጡቶች፡፡ ያ ቀን ማክዳን ካየሁበት ቀጥሎ ባልመሸ ያልኩት ሌላኛው ቀን ሆነ፡፡ ሴት ስቀርብ መጀመሪያ የሚመጣልኝ ውሸት ነው ብያችሁ የለ፡፡ ለዚች ሴት የሚሆን ሁነኛ ውሸት ሳስብ የሆነ ነገር ትውስ አለኝ፡፡ ወንበሬን ይዤ ወደተቀመጠችበት ሄድኩ፡፡
ስታየኝ በትንሹ ደንገጥ ብላ ተረጋጋች፡፡
‹ጠባቂዎችሽ የሉም? አልኩ ዙሪያዬን እየቃኘሁ።
‹የምን ጠባቂ? ስትል ግራ ለመጋባት ሞከረች፡፡
‹መቼም ይሄ ውበት ያለጠባቂ ነው የሚንቀሳቀሰው ትይኝና አመት እንዳልስቅ› አልኳት፡፡
ሳቀች…የትም ያልተሰማ ውበታም ሳቅ፡፡
በሳቋ መግባት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ ዘፍጥረት ታወሰኝ በሄዋን ሳቅ ሞት እንደመጣ፡፡ ጊዜ አላጠፋሁም ‹ከዛሬ ጀምሮ ያለምንም ክፍያ ለውበትሽ ዘብ ልቆም ራሴን አዘጋጃለሁ› አልኳት፡፡
‹ደስ ይለኛል› አለችኝ፡፡
እሺታዋን ተንተርሼ ‹አንድ ነገር ብጠይቅሽ እሺ ትይኛለሽ? ስል ጠየኳት፡፡
‹ምንድነው? አለችኝ ምንም ቢሆን እንቢ አልልህም በሚመስል አኳኋን፡፡
‹እሺ የምትይኝ ከሆነ በአንቺ እሺታ ውስጥ የሚከናወኑልኝ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እንቢ የምትይኝ ከሆነ ደግሞ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር ብመኝ አይሳካልኝም›፡፡
‹እኮ ምንድነው ንገረኝ?
‹እሺ የምትይኝ ከሆነ ነው የምነግርሽ›
‹እሺ ምንድነው?
ልነግራት አፌን ስከፍት ስልኳ ጮኸ፡፡ በምልክት ይቅርታ ብላኝ ስልኩን አነሳችው፡፡ ከሆነች ሴት ጋር ስታወራ ሰማሁ፡፡ የቱጋ ነሽ? ያለቻት ይመስለኛል፡፡ ያለንበትን ካፌ ስም ስትነግራት ሰማሁ፡፡
ስልኩን ዘግታ ‹እሺ ምን ነበር ንገረኝ› አለችኝ፡፡
‹ዛሬ በህይወቴ የምፈልገውን ስራ የጀመርኩበት ቀን ነው፡፡ በመጀመሪያ ደሞዜ የምጋብዛት የመጀመሪያዋ ሴት እንድትሆኚ እፈልጋለው› አልኳት፡፡
መስማማቷን በሳቋ ገለጸችልኝ፡፡ ስልክ እንቀያየር እደውልልሻለሁ› ከማለቴ ጓደኛዋ መጣች መሰለኝ እጇን አንስታ ስትጠራት አየሁ፡፡ ሁሉም ነገር እዚያ ጋር ተበላሸ፡፡ ለካ የማክዳ ጓደኛ ነበረች፡፡ ለካ ማክዳን እየጠበቀች ነበር፡፡ ለካ ጠዋት ከቤት ስወጣ ከክፍለ ሀገር የምትመጣ ጓደኛ አለችኝ አስተዋውቅሀለሁ ያለችኝ እሷን ነበር፡፡ ለካ ቅድም ስትደውልልኝ የነበረው እሷ ጋ እንዳደርሳት ነበር፡፡ ከማክዳ ጋር እንዲህ ባለው አጋጣሚ ተለያየን፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2015