
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያላቸው በርካታ ጀግኖችን አፍርታለች፡፡ ትላንት የተከበረው የጀግኖች አርበኞች ቀንም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው፡፡ ቀደምት አባቶቻችን በየጊዜው አገራችንን ለመውረር የመጡ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን በታላቅ ወኔና እልህ በመታገል የአገራችንን ነጻነት ጠብቀው ኖረዋል፡፡ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት ከሆነው አድዋ እስከ ካራማራ የተገኙ ድሎችም የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ በዚህ ብቻም አይደለም፤ በተለያዩ ዘርፎች ለአገራቸው ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጽመው ያለፉ ጀግኖቻችን በየዘመናቱ አፍርተናል፡፡ በአትሌቲክስ፣ በትምህርት፣ በህክምና፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በኪነጥበብ ወዘተ በአገራቸው ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር አንቱታን አትርፈው ያለፉ ዜጎቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ዛሬም ቢሆን ከድህነት ጋር ትግል የገጠሙ በርካታ ጀግኖች አሉን፡፡ በፖለቲካው መስክም ለአገራቸው ትልቅ ታሪክ ሰርተው ለማለፍ እድሜያቸውን ሙሉ የታገሉ ጀግኖች አሉን፡፡
ለምሳሌ ከአራት አስርት አመታት በፊት የነበረውን የፊውዳል ስርዓት ለመጣል ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ የታገሉ ጀግኖች በርካታ ናቸው፡፡ ከዚያም ወዲህ ከነበረው የደርግ ስርዓት ጋር ታግለው የወደቁና ለድል የበቁ ጀግኖቻችንም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ባለንበት ስርዓት ውስጥም ቢሆን በስርዓቱ ውስጥ ችግር ሲያጋጥም ከዝምታ ይልቅ መራራ ትግል በማድረግ ለውጥ ያመጡ ጀግኖች አሉን፡፡ ለነዚህ ሁሉ ጀግኖቻችን ታዲያ ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳም ለአገራቸው ታላቅ ቁምነገር ሰርተው ካለፉ ጀግኖቻችን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ዶክተር ነጋሶ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ “መሬት ላራሹ” ብሎ በፊውዳል ስርዓቱ ላይ አመፅ ከተጀመረበት የትግል ታሪክ ጀምሮ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ለህዝቦች ሉኣላዊነት የታገሉና መስዋዕትነት የከፈሉ የአገራችን አንጋፋ ባለውለታ ናቸው፡፡
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለነጻነት፣ ለእውነትና ለፍትህ ትልቅ ቦታ የሚሰጡ የእውነት ሰው እንደነበሩ በቅርበት የሚያውቋቸውና በእሳቸው ዙሪያ የተፃፉ የግል ታሪክ ድርሳናት የሚገልጹት እውነታ ነው፡፡ ወደፖለቲካው የገቡትም የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን ለሰው ልጅ እኩልነትና ፍትህ እንደሆነ የኋላ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡ ዶክተር ነጋሶ በወጣትነታቸው ዘመን የውጭ አገር የትምህርት እድል በማግኘታቸው የተሻለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል እድል አግኝተው ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ለእሳቸው ዋነኛው ጉዳይ እንዳልነበር በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ጀርመን አገር በኖሩበት የትምህርትና የስራ ዘመናቸውም ከፖለቲካው ሳይርቁ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለህዝባቸው ልዕልና ታግለዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በፖለቲካው መስክ ባደረጓቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች የአገራቸውን የፖለቲካዊ ሁኔታ ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል፡፡
ለምሳሌ በአገራችን ላለፉት 24 አመታት በስራ ላይ የቆየው ህገመንግስት እውን እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮም የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር በመሆን አገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግን ከራሳቸው ጥቅም በላይ የህዝባቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ታላቅ መሪ እንደነበሩ ያስመሰከሩት ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም በኢህአዴግ ውስጥ የተከሰተውን መከፋፈል ተከትሎ ለህዝብ ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትን አቋም በመያዝ ሃቀኝነታቸውን በገሃድ አስመስክረዋል፡፡ የሚመሩት መንግስታቸውም ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ከመሰረቱ መስተካከል አለበት በሚል በውስጥ ያካሄዱት ጠንካራ ትግል ስልጣናቸውን እንደሚያሳጣቸው ቢገምቱም ይህንን ከማድረግ ወደኋላ አላሉም፡፡ የእሳቸው ትግል በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡
ከዚያ በኋላ ቁጭ ብለው ተቀምጠው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ሳይበድሉ በጡረታ በሰላም መኖር እየቻሉ አሁንም ከኔ ጥቅም ይልቅ ህዝብ ይበልጣል በሚል ስሜት ጥቅማቸውን ሁሉ ትተው ዳግም ከስርዓቱ ጋር ለመታገል ወስነው በግላቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመወዳደር ፓርላማ ገብተዋል፡፡ በነዚህ ሁሉ የትግል አመታት ግን የግል ህይወታቸው እና አኗኗራቸው የተጎሳቆለ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የምድራዊ ኑሮ መጎሳቆል ትግላቸቸውን አላስቆመውም፡፡ እስከመጨረሻው የህይወት ፍጻሜያቸው ድረስም ለህዝባቸው ነጻነት፣ አንድነትና ፍትህ የታገሉና ያታገሉ ታላቅ የአገራችን ባለውለታ ነበሩ፡፡
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህይወታቸው ቢያልፍም ታሪክ የማይረሳው ትልቅ አሻራ ትተውልን አልፈዋል፡፡ በተለይ እያንዳንዱ ሰው በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ ከራሱ እና ከቤተሰቡም በላይ ለአገር አስተዋፅኦ ማበርከት ትልቅ ክብርና ሞገስ እንዳለው በተግባር አሳይተውናል፡፡ ለመጪው ትውልድም አገርን መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተጨባጭ ታሪክ አስቀምጠውልን አልፈዋል፡፡ የእሳቸው ታሪክ አንዴ ብቻ ተሰምቶ የሚያበቃ አይደለም፡፡ አሁን ያለውም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ ቀስ በቀስ እየገለጠ የሚያነበውና የሚማርበት ትልቅ መፅሃፍ ነው፡፡ በመሆኑም ስለከፈሉልን መስዋዕትነትና ስላኖሩልን ታሪክ ሁሉ እናመሰግናቸዋለን፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011