የብዙ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሪ ቃል፤ የሕዝብ ልሳን፣ የሕዝብ ድምጽ፣ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ… በአጠቃላይ የሕዝብ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው:: ለመሆኑ ግን የሕዝብ ሲባል ምን ማለት ይሆን?
የሕዝብ የሚባለው ነገር ብዙ ጊዜ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር ነው የሚያያዘው:: በተቃውሞም ሆነ በድጋፍ በኩል ያሉት ሚዲያዎች የሕዝብ ነን የሚሉት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ነው:: መንግሥትን ከልክ በላይ ማወደስ ወይም 24 ሰዓት መንግሥትን ብቻ መውቀስ ማለት ነው:: በዚህ መሐል የሕዝብ ጉዳዮች ሽፋን ሳያገኙ ተዳፍነው ይቀራሉ::
የሕዝብ ሲባል፤ የሕዝቡ የዕለት ከዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ፣ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ትውፊታዊ ልማድ፣ የሚዝናናበትንና ብሶቱን የሚገልጽባቸውን ስሜቶች ማጋራት፣ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴዎቹን አጀንዳ ማድረግ የመሳሰሉት ብዙም ትኩረት አይሰጣቸውም:: ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍል አርሶና አርብቶ አደር ነው:: ከዚህ የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ የአገሪቱን መሪ እንኳን የማያውቅ ይኖራል:: በእርግጥ የማሳወቅ ሥራ ነው መሠራት ያለበት:: ዳሩ ግን አቅራቢያው ያለውን ነገር በመተው አይደለም::
ለምሳሌ፤ አሁን ወሩ የሰኔ ወር ነው:: የሰኔ ወር ማለት በአገራችን የወቅቶች ምደባ የክረምት ወር መጀመሪያ ነው:: ‹‹ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል›› የሚባል አባባል አለው ገበሬው:: ዋናው የኑሮው መሠረት የሆነው የግብርና ሥራ የሚሠራው በሰኔ ነው:: በሰኔ ያልተዘራ ዘር ወቅቱ ስለሚያልፍበት ምርታማ አይሆንም:: ስለዚህ በዚህ ወቅት ለገበሬው ከምንም በላይ አንገብጋቢው ጉዳይ ስለግብርና ሲወራለት ነው:: ጆሮውን ሰጥቶ፣ ልቡን ከፍቶ የሚያዳምጥ ስለግብርና ሲወራለት ነው::
የሚዝናናው እንኳን ስለግብርና ሲወራለት ነው::
እዚህ ላይ አንድ የራሴን ትዝታ ላንሳ:: የ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተፈትኜ ውጤት እየተጠባበቅኩ በነበረበት ወቅት የነሐሴ ወር ከገባ ጀምሮ የሬዲዮ ዜና የማዳምጥ በተመስጦ ነበር:: ልክ ‹‹የ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና…›› ሲል ሰውነቴ ሁሉ ጆሮ ይሆናል:: የፈተናውን ዜና ከሰማሁ በኋላ እንኳን ደጋግሞ እሱ ብቻ ቢወራ እወዳለሁ:: በወቅቱ ሌሎች ዜናዎች ምንም ስሜት አይሰጡኝም:: ይህ ልጅነት ነው እንበል፤ ዳሩ ግን በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንሆን ስለሚቀርበን ነገር ሲወራልን ነው የምንወድ::
ለመሆኑ ሚዲያዎቻችን ምን ያህል የሕዝብ ናቸው? ዜናዎቻቸውም ሆነ ፕሮግራሞቻቸው ለተወሰነው (የተማረ ለሚባለው) የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ አይደለም ወይ? ይህ የሚሆነው ደግሞ የግል (የንግድ) በሆኑት ብቻ ቢሆን ኖሮ ብዙም አይደንቅም ነበር:: የሕዝብ ናቸው በሚባሉት (ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል/ከተማ አስዳደር ምክር ቤት) የሆኑት ሁሉ ናቸው:: አርሶና አርብቶ አደሩን የሚመለከቱ ፕሮግራሞች አሉ ቢባል እንኳን በሚመለከተው ተቋም የተገዙ የአየር ሰዓቶች ናቸው:: ያ የአየር ሰዓት የዚያ ተቋም ነው::
ዜናዎች ወይም ፕሮግራሞች የሚሠሩት በብዛት ሁነት ተጠብቆ ነው:: ለምሳሌ፤ ገበሬዎች ተቃውሞ ካሰሙ፣ መንግሥት መልዕክት ካስተላለፈ፣ የድርቅ ወይም የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም ነው:: ከዚያ ውጭ በመደበኛነት የብዙ የኅብረተሰብ ክፍል ሕይወት ነው ተብሎ የሚሠራበት በጣም ጥቂት ነው:: ከፖለቲካዊ ጉዳዮች አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ አይባልም::
በሁሉም ደረጃ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል (የተማረ፣ ገበሬ፣ ነጋዴ…) እኩል የሚያስደስት ዜና ወይም ፕሮግራም ላይኖር ይችላል:: ግን የገበሬው ሕይወት የማይመለከተው አለ ወይ? ሐኪም ወይም
መሐንዲስ ወይም መምህር ወይም ነጋዴ ‹‹ኤጭ! የግብርና ወሬ አስጠላኝ!›› ብሎ ያውቃል? በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ውስጥ ያለ የተማረ የሚባል ሰው የገጠሩ ማኅበረሰብ ላይ የሚሠራ ፕሮግራም አስጠላኝ (ሰለቸኝ) ብሎ አያውቅም:: ችግሩ የሚዲያ ሰዎች ስንፍና ብቻ ነው::
ከሦስት ይሁን አራት ዓመት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ የግብርና ሚኒስቴር በአዳማ ከተማ የሰጠው አንድ ሥልጠና ላይ ተሳትፌ ነበር:: ብዙ ሰዎች የሰጡት አስተያየት ‹‹ለምንድነው ግብርና ላይ እንደ ሌላው ጉዳይ በሰፊው የማይሠራው?›› የሚል ነበር:: ከመድረክ የተሰጠው መልስ ጋዜጠኞች ላይ ስንፍና እንዳለ የሚጠቁም ነበር:: የገጠሩን ሕይወት ለማሳየት ድካም አለው:: ጭቃ ወይም ዝናብ አለ፤ አቧራ ወይም ፀሐይ አለ:: መንገዱ ምቹ አይደለም፤ ውጣ ውረድ አለው:: መኝታውም ሆነ ምግቡ ከተማ ቦታ እንደተለመደው አይደለም:: በእነዚህ ምክንያቶች የመሥራት ተነሳሽነቱ ብዙም የለም:: ይህ ችግር ግን ከጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን ከአመራር ጀምሮ የሚፈጠር ነው::
ይህ ሲባል ግን የሚመሰገኑ የሉም ማለት አይደለም:: ለምሳሌ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለዓመታት የዘለቀው (እኔ እንኳን ሳውቀው ከ6 ዓመት በላይ ሆኖታል) ‹‹ውሎ አዳር›› ፕሮግራም የገጠሩ ብቻ ሳይሆን ከተሜው እንኳን የወደደው ፕሮግራም ነው:: ፕሮግራሙ የሚተላለፈው የገጠሩ ማኅበረሰብ እረፍት በሚሆንበት እሁድ ቀን ነው::
ከግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ‹‹ባላገሩ›› ቴሌቪዥን ላይ የአርሶ አደሮች የጥያቄና መልስ ፕሮግራም አለ:: አዘጋጁ (ማሩ ባላገሩ) ልክ እነርሱን መስሎ ነው የሚያቀርበው:: አርሶ አደሮችን በማዝናናት ያስተምራል ማለት ነው::
አማራ ቴሌቪዥን ላይ ለዓመታት የዘለቀው የአርሶ አደሮች ወግ አለ:: ይህ ፕሮግራም የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን የገጠሩ ሕዝብ እንዲያየው ከሚያደርጉ ፕሮግራሞች ዋናው ሳይሆን አይቀርም::
እነዚህን ፕሮግራሞች እንደ ምሳሌ ያመጣኋቸው ለመተቸት ብቻ ሳይሆን የተወደዱ ፕሮግራሞች ሲኖሩ ማድነቅም እንዳለ ለማሳየት ነው:: ምክንያቱም የከተማው ነዋሪ ሁሉ ነው የወደደላቸው:: ስለዚህ ሀገረሰባዊ ፕሮግራሞችን መሥራት ምን ያህል ተወዳጅ እንደሚያስደርግ ከእነዚህ ማየት ይቻላል ማለት ነው::፡
ሥራው አድካሚ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም:: ብዙ አካላዊ ድካም አለበት:: ዳሩ ግን የሕዝብ ነን ከተባለ ደግሞ ሕዝቡን መምሰል የግድ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የከተሜው ብቻ አይደለም፤ ሲቀጥል ደግሞ የከተሜው ሕዝብ የገጠር ፕሮግራም አታሳዩኝ አላለም:: እንዲያውም ከገጠሩ ማኅበረሰብ ያላነሰ ነው የሚወደው:: ሌላውንማ ከየትኛውም አማራጭ ያገኘዋል:: የዓመቱን የግራሚ እና ኦስካር ሽልማቶች፣ የቢልቦርድ መረጃዎች በየትኛውም አማራጭ ያገኛል:: ማየት የሚፈልገው የበይነ መረቡ ዓለም የማያውቃቸውን የአገሩን ቱባ ባሕሎችና ሥርዓተ ክዋኔዎች ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የአገራችን ቱባ ባሕሎችና ሥርዓተ ክዋኔዎች፣ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች ወደ በይነ መረቡ ዓለም መግባት አለባቸው::
የመዝናኛ ፕሮግራሞቻችን የግድ የውጭ ሰርከስ ብቻ መሆን የለባቸውም:: የገጠር ልጆች ሐረግ ላይ የሚያደርጉት ዥዋዥዌም ጨዋታ ነው:: የፈረንጆች የመሸዋወድ (ፕራንክ ይሉታል) ጨዋታ ብቻ አይደለም የሚያዝናና፤ የአገር ቤት ሰዎች ወግ ያዝናናል:: የአገር ቤት የባህል ዘፈኖችም ያዝናናሉ:: የሳልሳ ዳንስ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች ጭፈራዎችም ያዝናናሉ:: የኦሮሞ ቆነጃጅት አንገታቸው የተቀጨ እስከሚመስለን ድረስ ያንን ፀጉራቸውን ሲያዞሩት ጭፈራ ብቻ ሳይሆን ሰርከስም ሆኖ ያዝናናል:: የትግራይ ቆነጃጅት ሲሽከረከሩ ማየት፣ የጎጃም እንቅጥቅጥ ማየት ከሳልሳ ያንሳል ወይ?
በአጠቃላይ ሚዲያዎቻችን የሕዝብ ነን ካሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይምሰሉ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2015