ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሹን የሚሸፍነው የሴቶች ቁጥር እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል:: ሆኖም የኅብረተሰቡን ግማሽ ያህል ያዙ ይባል እንጂ ተጠቃሚነታቸው እዚህ ግባ የሚባል ነው ለማለት አይቻልም:: በተለይም ከኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ነገሮች አሁንም መፍትሄን የሚፈልጉ እንደሆኑ ግልጽ ነው:: ምክንያቱም ዛሬም መብቶቻቸው ሳይቀር ከወንዶች ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ ያነሰ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ::
ለአብነት በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ያልተፈታ የመሬት ባለቤትነት መብት አለ:: ፍትሐዊ የሥራ ክፍፍል ጉዳይም በወንዶችና ሴቶች መካከል ልዩነቱ የጎላ ነው:: ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በብዙ መልኩ ይገድበዋል:: በአግባቡ እንዳይጠቀሙና ራሳቸውን እንዳያወጡ ያደርጋቸዋል:: በተለይም ይህ ነገር በስፋት የሚስተዋለው በኢትዮጵያ ገጠራማ ክፍሎች እንደሆነ እሙን ነው:: አሁን ድረስ አባት ለሴት ልጁ ሀብት የማውረስ ወይም እንድታስተዳድር እድል መስጠት ባህል አልሆነም::
በአንዳንድ ሥራዎችም ኃላፊነት ለመስጠት እጅጉን ይፈራል:: ምክንያቱም ብቃቷን እንኳን ቢረዱ ትወልድና ስራችንን ታስተጓጉለዋለች ትባላለች:: ይህ ደግሞ በተለይም ከሥራ ቅጥር ጋር በእጅጉ ይቆራኛል:: ከገጠሩ ይልቅ ከተማው ላይ ይሰፋልም:: ከተማው ላይም ቢሆን ከመንግስት ተቋማት ይልቅ ግሉላይ በስፋት የሚያጋጥም ነው:: ስለዚህም ነፍሰጡር የሆነች እናት እንዳትቀጠር ጭምር ትሆናለች:: እናም ይህን መሰል ችግሮች ሴትን ልጅ የፈለገችው ቦታ ላይ እንድትደርስ አላደረጋትም::
ታዲያ መፍትሄው ምንድነው? ከተባለ ሰሞኑን የተሰማው ነገር እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ይመስላል:: የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ፤ የሀሳቡ ጠንሳሽ ማሌሳ ኤቨንትና ፕሮዳክሽን ነው:: ሀሳቡን የሚያስፈጽመው ደግሞ ከዚህ ተቋም ጋር በመተባበር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆን፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በራስ አቅም ብቻ ሳይሆን ከአጋር አካላት ጋር በመስራት ነው ብሎ ያምናልⵆ በአይነቱ ልዩ የሆነና ብዙ ሴቶችን ወደ ሥራ ያስገባል የተባለለትን ኤክስፖ እውን እንዲሆንም ሰርቷል::
ይህ ኤክስፖ ‹‹Connect, Create, Accelerate›› በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የበላይነቱን ወስዶ ሌሎችን የመንግስት ተቋማት በማካተት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝበት ነው:: በርከት ያሉ አጋር አካላትም ገብተውበታል:: ለአብነት ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠቃሾች ናቸው::
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዚህ ኤክስፖ ሲሳተፍ አገልግሎት ሰጪ ሴቶች ይታሰባሉ:: ስለዚህም አምራቹን ዘርፍ ያሳትፋል:: ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሲታሰብ ደግሞ ሥራና ሰራተኛን ከማገናኘት አንጻር ያሉ ተግባራትን ያከናውናል:: ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ስናነሳ ደግሞ ፈጠራንና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በንግዱ ዘርፍ ሴቶች እንዲመለከቱ የሚያስችል ነው:: ስለዚህም በአጠቃላይ እነዚህ ተቋማት በንግዱ ሥራ ላይ ሴቶች እንዴት መጠቀም ይችላሉ በሚል የሚያግዙ ይሆናል::
ለመሆኑ ኤክስፖው ምን ለየት ያደርገዋል፤ ምንስ ጥቅም አለው? ከተባለ ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ እንደተገለጸው፤ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖው ምርታቸውን ከመሸጥ እና ከማስተዋወቅ ባለፈ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እንደ ማስፈንጠሪያ መድረክ ሆኖ ያገለግላል:: ማለትም መድረኩ ሴቶችን ያገናኛል፤ አዳዲስ ነገሮችን ፈጣሪ ያደርጋል:: በተጨማሪም የሚሰሩትን የሚያበረታታና ወደተሻለ መስመር የማስገባት እድል የሚፈጥር ነው::
የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖው ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በስካይላይት ሆቴል የሚከናወን ሲሆን፤ ሴቶች በስራ ፈጠራ፣ በአምራችነት፣ በንግድ፣ በገበያ ትስስር፣ በኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት እና ተወዳዳሪነት ዙሪያ ያላቸውን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያሰፉበት ነው ተብሎለታል::
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሙድ ኤክስፖውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ይህ ኤክስፖ የሚያሳየን አንድ ነገር አለ:: ይህም በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል:: ሆኖም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ስራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች፣ የንግድ ተቋም ባለቤቶች እና መሪዎች ከብድር አቅርቦት፣ ከወለድ ምጣኔና ከእፎይታ ጊዜ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር ከመፍጠር፣ ከምርት ማቀነባበሪያና ማሳያ፣ ከመስሪያ ቦታ፣ ከቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ስልጠናዎችን ጋር የተያያዙ ችግሮች ይገጥሟቸዋል:: ይህ ደግሞ ባሰቡት ልክ እና ፍጥነት ችግሮቻቸውን ተቋቁመው እንዳያድጉና በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማነቆ ሆኖባቸዋል:: በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየታየ ያለውን አበረታች ውጤትና የለውጥ ጅማሮ በሁሉም ዘርፎች ፍትሃዊነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል እና የሴቶችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንዲሰራ ሆኗል::
ሴቶች ያሉባቸው ችግሮች በርካታ እንደሆነ የጠቆሙት ወይዘሮ አለሚቱ፤ ከችግሩ ስፋት አኳያ በመንግስት ብቻ በሚደረግ ጥረት የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ አዳጋች ነው:: ስለሆነም የልማት አጋራት፣ የግል ባለሃብቶች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች በትብብር ሊሰሩ ይገባል:: ይህ ኤክስፖም የሚያሳየው ይህንን መተባበር ነውና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል:: የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ደግሞ አንዱ ለነጋዴ ሴቶች ገበያ ማፈላለግን ላይ ያተኮረ ነው:: እናም ይህ ኤክስፖ ስኬታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዲሰራ ሆኗል::
በነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ ከ100 በላይ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾች እና የንግድ ተቋም መሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ይደረጋል:: አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ናቸው:: ምክንያቱም እንደአገር ያለንበት በኢኮኖሚ ያለው ተጠቃሚነት እጅግ አናሳ ነው:: ስለዚህም ያንን ለመፍታት እንደነዚህ አይነት አማራጮች ሁነኛ መፍትሄ ናቸውም ሲሉ አብራርተዋል::
ወይዘሮ አለሚቱ ኤክስፖው ሴት አምራቾችን፣ ነጋዴዎችን፤ ሥራ ፈጣሪዎችን እና የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ሴቶችን የሚያበረታታ፤ ሴቶች ፍትሐዊ እና በፆታ እኩልነት ላይ የተመሠረተ እገዛ እንዲያገኙ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የገበያ ተወዳዳሪነትና ዘላቂ የገበያ ትስስር ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ታዳጊ ሴቶች የሚኖረው ሁለንተናዊ ፋይዳና አበርክቶ ከፍተኛ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አስረድተዋል::
በኤክስፖው የሚሳተፉት ሴቶች ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጎብኚዎች ምርታቸውን የሚሸጡና የሚያስተዋውቁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሴቶችን ማብቃት መሪ ስራአስፈጻሚ ወይዘሮ ወይንሸት ገሪሶ ሲሆኑ፤ የንግድ ስራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቀደምት እና የኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ የቆየ ቢሆንም እስከ አሁን የአገሪቱን የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ንግድ ስርዓትን በአግባቡ የሚመራ፣ አጠቃላይና ወጥ የሆነ የንግድ ፖሊሲ እንዳልነበረ ያነሳሉ::
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ፖሊሲው አለመኖሩ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አፈፃጸም እና በንግድ ዘርፉ ላይ ያሉ የንግድ እድሎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ስታንዳርዶች በተመለከተ የአሰራር ወጥነት ችግሮች ይስተዋላል:: በተለይም ሴቶችን በተመለከተ ብዙ ክፍተት ይታይበት ነበር:: እናም በዘንድሮው ዓመት ይህንን ከማስተካከል አኳያ ትልልቅ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ:: አንዱ ፖሊሲውን የማሻሻል ሥራ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም በቀጣይ የሚከናወኑ በርካታ ተግባራት እንደሚኖሩ አንስተዋል::
የንግድ ፖሊሲው መነሻ አገራችን ቅድሚያ ትኩረት በምትሰጥባቸው እና የዓለም አቀፍ ንግድ ትኩረት የሆኑትን ምርትና አገልግሎቶች እንዲሁም የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች እና በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ በሆነው የንግድ ሰንሰለቶች ላይ ይሆናል:: ይህ ደግሞ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም በእኩል ደረጃ የሚሳተፉበት መሆን ይገባዋል:: እናም ከንግድ አንጻርና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ሴቶች እንዲልቁ ማድረግ ላይ መስራት ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ የሴቶችን አቅም የሚገነቡ ተግባራት ላይ መሥራት ግድ ነውና እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን ኤክስፖው ከፖሊሲው ቀጥሎ የሚተገበር አዋጪ ሥራ መሆኑንም ጠቁመዋል::
በኤክስፖው ምርት እና አገልግሎታቸውን ከመሸጥና ከማስተዋወቅ ባለፈ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሠማሩ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ አምራቾችና የንግድ ተቋም መሪዎች እንዲሁም በየትኛውም የሥራ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ስለ ፋይናንስ ቴክኖሎጂ፣ ስለዲጂታል ማርኬቲንግ፣ ስለ ገበያ ጥናት በመሳሰሉት መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲረዱ የሚሆኑበትም ነው ያሉት ደግሞ የነጋዴ ሴቶች ኤክስፖ ክሬቲፍ ዳይሬክተር ሲሃም ፈይሰል ናቸው :: ምክንያቱም ይህ ኤክስፖ በሦስት ተከታታይ ቀናት ቆይታው በሺዎች ለሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች ይሰጥበታል።
ከምርት ሽያጩ እና ከሥልጠናው ጎን ለጎን በሥራ ፈጣሪነት፣ ጊዜውን በዋጀው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስለሚሳተፉ ሴቶች እንዲሁም በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይትም ይካሄዳል:: ይህ ደግሞ በየዘርፉ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል:: ለአብነት ስኬታማ የሆኑ ሴቶች ልምዳቸውን ያጋሩበታል:: በዚህም በርካታ ሴቶች ልምድ እንዲቀስሙ ይሆናሉ:: በተመሳሳይ ባለድርሻ አካላት ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች በሰፊው ያብራራሉ:: ይህም በሥራ ውስጥ ያለ አገልጋይነት ምን ይመስላል የሚለውን ሀሳብ ሴቶች እንዲቀስሙ ይሆኑበታል::
የኤክስፖው ዋና አስተባባሪና የማሌሳ ኢቨንት ስራ አስኪያጅ ሰላማዊት ደጀን በበኩላቸው፤ በኤክስፖው ታዳጊ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የበለጠ ይበረታታሉ፤ ድርጅቶች ተቋማቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው ይማራሉ:: ገና ወደ ንግድ ለመግባት ያሰቡ ብቻ ሳይሆኑ በየትኛውም የሥራ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ጊዜውን የዋጀ ሥልጠና ያገኛሉና ቀጣይ ጉዟቸውን ያስተካከልሉ ይላሉ::
ኤክስፖው በተለይም ከ18 ዓመት እስከ 65 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የሚጠቀሙበት እንደሆነ የሚገልጹት አስተባባሪዋ፤ ለሥራ ቅጥር የሚመጡትን ለማስተናገድ የሚችሉ 14 ፈቃደኛ የሆኑ ሥራ ፈጣሪ ተቋማት መዘጋጀታቸውንም በመግለጫው ወቅት አንስተዋል:: ኤክስፖው በተመሳሳይ ሥራ እንዴት መጀመር እችላለሁ፤ ማን ጋር የምፈልገውን አገኛለሁና ምን አይነት ሥራ ለእኔ ተመራጭ ነው የሚለውን ለመረዳት የሚችሉበት ነው:: ምክንያቱም በየዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ አካላት አሉ:: በተለይም ሴቶች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው የሥራ መስኮች ላይ አቅማቸውን እንዲገነቡ የሚሆኑበት ነው:: እናም ተሳታፊዎች ወደኤክስፖው ሲመጡ የተለየ አቅም ለማግኘት፣ የስራ አጋር ለመተዋወቅ፣ ሥራቸውን የተሻለ ለማድረግና ሥራ ለማግኘት በመሆኑ እድሉ ባያልፋቸው መልካም እንደሆነ ያስረዳሉ:: እኛም ኑና የተሰጣችሁን እድል ተጠቀሙ በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2015