የሁለተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ዘንድሮም በህዝብ የንቅናቄ ተሳትፎ ሊከናወን ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ሀሳብ ሰሞኑን በይፋ ተጀምሯል። በዚህ በዘንድሮው አምስተኛው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊየን የዛፍ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
በመጀመሪያው ዙር ለተከታታይ አራት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ ተከናውኗል፡፡ በመርሀ ግብሩ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በመርሀ ግብሩ 20 ሚሊየን የሚገመት ህዝብ እንደተሳተፈበትም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ የዛፍ ችግኝ ተከላ በተጠናከረ የህዝብ ተሳትፎ እየተካሄደ ይገኛል። የችግኝ ተከላው በህዝብ ንቅናቄ እየተካሄደ ያለበትን መንገድ አስመልክቶም የተለያዩ ሙያዊ ሀሳቦች እየተንጸባረቁም ይገኛሉ፡፡ አንደኛው ወገን የችግኝ ተከላው በህዝብ የንቅናቄ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል ሲሆን፣ ሌላው ወገን ደግሞ ዘመቻው ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻል በተደራጀ የተቋም አሰራር መመራት አለበት የሚል ሀሳብ በማንሳት ይሞግታል፡፡
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ በህዝብ የንቅናቄ ተሳትፎ መቀጠል እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ አቶ ከበደ መርሃግብሩ የዜጎች መሆኑን በመግለጽ፣ አካባቢን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነትም የትውልዱ፣ አልፎም የዜጎች ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ላይ የመንግሥት ኃላፊነት ልማቱ በቴክኖሎጂ እንዲከናወን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ባለሙያዎችን በማቅረብ እገዛ ማድረግ፣ የገንዘብ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ወቅትም በማቅረብ ድጋፍና ክትትሉን ማጠናከር ነው ይላሉ፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ በዚህ መልኩ መከናወኑ አግባብነት አለው ብለው የሚገልጹት አቶ ከበደ፣ የዛፍ ችግኝ ተከላ ሥራ ከፍተኛ መዋእለነዋይ ይጠይቃል፤ በአገር አቅም ደግሞ የሚቻል አይደለም፤ ይህንን መወጣት የሚቻለው በመተጋገዝ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ በደን መመናመንና በአፈር መሸርሸር በመሬት መራቆት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ይህንንም ችግር በርብርብ ካልሆነ ሥራውን ለአንድ አካል ብቻ በመተው ውጤታማ መሆን አይቻልም። ለአንድ ወገን የሚተው ሥራ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይቀረፍም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው የጉልበት አስተዋጽኦ በገንዘብ ቢተመን ብዙ ቢሊየን ብር ይገመታል፡፡
ህብረተሰቡ የሚያደርገው ተሳትፎ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ወጭ እንደሚያስቀርም ነው የሚናገሩት። በመሬት አቀማመጥ አስቸጋሪነትና በመሬት መራቆት ከፍተኛ ተግዳሮት የገጠማቸው እንደነ ኮሪያና ቻይና ያሉ አገሮች ችግሩን መቋቋም የቻሉት በዜጎች ተሳትፎ እንደሆነም አቶ ከበደ አብነት ጠቅሰው ያብራራሉ። የችግኝ ተከላ ስራው በዘመቻ መካሄድ የለበትም የሚሉ ወገኖች ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ ካለማየት፣ ያለውን ተግዳሮትና ዜጎችም ኃላፊነት እንዳለባቸው ካለማጤን የሚሰጡት ሀሳብ አድርገው ይወስዳሉ፡፡
‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሁለተኛው ዙር የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብርም ለም የሆነች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የዜጎች ኃላፊነት መሆኑን የሚያጠናክር መሆኑን ነው አቶ ከበደ ያመለከቱት። አሁን ላይ ያለውም ሆነ ተተኪው ትውልድ የሚጠቀመው ዛሬ በተሰራው ሥራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም አንጻር፤ አንድ ችግኝ ፀድቆ ለምርት እስኪደርስ ረጅም ዓመት የሚወስድባቸው አንዳንድ የዓለም አገራት መኖራቸውን አቶ ከበደ ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ግን ለእጽዋት መጽደቅ ምቹ የሆነ የአየርፀባይ እንዳላት ይናገራሉ፡፡ ይህም ችግኙ ረጅም ዓመት ሳይወስድበት ለምርት እንዲደርስ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ምርቱን ለተለያየ የኢንዱስትሪ ግብአት ማዋል የሚቻልበት ዕድል መኖሩን አስረድተዋል። ከዛፍ ችግኝ ተከላው ጎን ለጎን በሚከናወነው የተለያየ ፍራፍሬ ልማትም እንዲሁ ምርቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርሶ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት እድል መኖሩን ገልጸዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ሀብት ማፍሪያና መበልፀጊያ እንደሆነ ሁሉም ዜጋ ተገንዝቦ የየድርሻውን መወጣት አለበት በሚል ሀሳብ በዛፍ ችግኝ ተከላው ላይ የህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲጠናከር መደረጉን ያስረዳሉ፡፡
በማህበረሰብ ንቅናቄ የሚከናወነው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ዘላቂነት፣ ችግኙን በእንክብካቤ እስከ መጨረሻው ውጤት ካለማድረስ እንዲሁም ከባለቤትነት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ሀሳብም አቶ ከበደ፤ አስተያየቱ ግምት እንጂ በጥናት የተደገፈ እንዳልሆነ ነው የሚገልጹት። የተተከሉትን ችግኞች መንግሥት ብቻ እንዲንከባከባቸው መጠበቅ የለበትም ይላሉ፡፡
አቶ ከበደ ክፍተቶች ያሏቸውንም አንስተዋል፡፡ በወል መሬት ላይ እንክብካቤ ማድረግ ላይ ጉድለት መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህም ቢሆን እንደትልቅ ችግር መታየት እንደሌለበት ነው የሚናገሩት፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን የሙያ ድጋፍ እና ቴክኖሎጂ ለይቶ በማሟላት ክፍተቱን ማረም እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
ህብረተሰቡ በወል መሬት ላይ የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችለው የምስክር ወረቀት የሚያገኝበት አሰራር በመኖሩ ሁሉም ባለቤት እንዳለው ያስረዳሉ። ከዚህ አንጻር በጋራ ለመጠቀም በሥራው ላይም በጋራ መሳተፍና መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በእስካሁኑ ተሞክሮም የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክበው ለውጤት ያደረሱ ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦችና ተቋማት መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በህዝብ ንቅናቄ ዘመቻ እየተከናወነ ያለው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ዘላቂነት እንዲኖረው በተቋማዊ አደረጃጀት መመራት አለበት ሲሉ የቀድሞው በአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የአፍሪካ የደንና የተፈጥሮ መፍትሄዎች አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር ገመዶ ዳሌ ‹‹አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በዘመቻ መጀመሩ አገራዊ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ለውጡም ቀላል ተደርጎ አይወሰድም›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብዝሐ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የቀድሞው የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ገመዶ፤ የዛፍ ችግኝ መትከል አስፈላጊነት ላይ በማህበረሰቡ ውስጥ የባህሪ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ትልቅ እመርታ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ ረገድ የተሰራው ሥራ ትልቅ ሀብት ነው ብዬ እወስዳለሁ ያሉት ዶክተር ገመዶ፣ ነገር ግን ማነቃቃት ለምን ተፈለገ? ዘመቻውስ ለምን? በዚህ ሁሉ ጥረት ምንድነው ማግኘት የተፈለገው? የሚለው መፈተሽ አንዳለበት ይናገራሉ፡፡
በሁሉም አቅጣጫ ርብርብ ሲደረግ የነበረው የተተከለው የዛፍ ችግኝ መጠን እና የህዝብ ተሳትፎ ብዛት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ህዝብን በንቅናቄና በዘመቻ የማሳተፉና የማነቃቃቱ ተግባር መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
መሠረታዊ ትኩረት መሆን ያለበት በተቋማዊ አደረጃጀት እንዲመራ ማድረግ ላይ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ዘመቻውንና ተቋማዊ ሥራው ተቀናጅቶ መተግበር ይኖርበታል። ከፍተኛ መዋእለነዋይ ፈሶበት ለተከላ የሚዘጋጀው ችግኝ በአግባቡ ስለመተከሉ የሚጠይቅ፣ ድጋፍ ሲያስፈልግና የክትትል ሥራም ለመሥራት አቅዶ የሚተገብር ተቋም ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ገመዶ ገለጻ፤ በተቀናጀ ሁኔታ የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት ይኑር ሲባል ለችግኝ ተከላ ሥራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። አጠቃላይ የደንና የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በሀብት አጠባበቅና አጠቃቀም ላይ ግንዛቤው ያደገ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሆን አለበት። በተቀናጀ መልኩ መመራቱ ተሳታፊነቱም ዘላቂነት እንዲኖረው ለማስቻል ያግዛል።
እንዲህ ያለው አሰራር ሲጠናከር በጊዜያዊ ኩነቶች ላይ የሚደረግ ተሳትፎን ያስቀራል። ለእዚህም በተለይ ማህበረሰብ ላይ የማያቋርጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድም መገናኛ ብዙሃንን መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቋማዊ አደረጃጀቱ በበጀት እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የወል መሬትን ጨምሮ እየተከናወነ ያለው የዛፍ ችግኝ ተከላ ባለቤት አለው ሲሉ አቶ ከበደ የሰጡን ሀሳብ ዶክተር ገመዶ አይስማሙበትም፡፡ ዶክተር ገመዶ በወል መሬት ላይ እየተካሄደ ባለው የችግኝ ተከላ ላይ ክፍተት እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ በወል መሬት ላይ እንዲተከል የሚፈለገውን ያህል ችግኝ እንዲተከል ድጋፍ የሚያደርግ አካል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ዶክተር ገመዶ እንዳሉት፤ የዛፍ ችግኝ ተከላው የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ ካለው ጠቀሜታ ባሻገር ለማህበረሰቡ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን ይኖርበታል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የዛፍ ዝርያዎች እንዲተክሉም ሆነ ወደፊት እንዴት ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው በሚለው ላይ ለመስራት በባለሙያ እገዛ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በተቋማዊ አደረጃጀት ነው፡፡
የተፈጥሮ ሀብትን የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም ሊኖር እንደሚገባና እንደአገርም መታየት እንዳለበት ዶክተር ገመዶ ይጠቁማሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮም የዛምቢያን ለአብነት እንዲህ ሲሉ ይገልፃሉ። በዛምቢያ የአረንጓዴ ልማትና ዘላቂ እድገት፣ የደን ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር መሥሪያቤቶች እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በዚህ ደረጃ የተቋቋመ ተቋም የሌላት ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ የአካባቢ ደን የአየርንብረት ሚኒስቴር ቢኖራትም በመዋቅር መፍረሱን አስታውሰው፣ ተቋማዊ አደረጃጀትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ግንዛቤ ተይዞ አሰራሩ ጭምር መስተካከል አንዳለበትም ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን የሚቋቋሙ አገር በቀል ችግኞች እንደሚገኙበት ባለፈው ሐሙስ በአፋር ክልል ተገኝተው መርሃግብሩን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር አረንጓዴ አሻራ ለትውልድ የሚተረፍ ቅርስ እንደሆነ፣ የአየር ንብረት ለውጥንና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም እንደአገር የተወጠነ አገርበቀል አካሄዳችን ነው ሲሉ ገልጸዋል። ለምግብ የሚውሉ እጽዋትን መትከል የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበት አንዱ መንገድ እንደሆነም ተናግረው፣ መርሃግብሩ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በሚከናወነው የችግኝ ተከላም እንደ አፕል፣ መንደሪንና ሌሎች ፍራፍሬዎች ያሉትን ማስፋፋት ይገባልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ዜጎች በኃላፊነት ስሜት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የመጀመሪያውን ዙር ጨምሮ በአጠቃላይ በሚከናወነው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር 50 ቢሊየን የዛፍ ችግኞችን ማልማት ከተቻለ እንደአገር ትልቅ እመርታ እንደሚመዘገብና አሻራ ማሳረፍ እንደሚቻልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2015