በኢንዱስትሪ መናኸሪያነታቸው ከሚታወቁት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ድሬዳዋ፣ በማምረቻ ዘርፍ (Manufacturing Sector) የተሻለ የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ አላት። የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ተከትላ የተቆረቆረችውና ‹‹የኢንዱስትሪ ኮሪደር›› በመባል የምትታወቀው ድሬዳዋ፣ በንግድ ማሳለጫነቷ ተጠቃሽ ከተማ የነበረች ቢሆንም፣ ይህ የንግድ መናኸሪያነቷ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።
የድሬዳዋ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች እንደሚሳዩት፣ ከተማዋ ቀደም ሲል ወደምትታወቅበት የንግድ መናኸሪያነቷ ለመመለስ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። የዚህ ጥረቷ ማሳያ ከሆኑ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እያደረገችው ያለችው እንቅስቃሴ ነው። ይህ እንቅስቃሴዋም ሰምሮላት ውጤት እያገኘችበት ነው። የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮችን በመፍታት የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ዘርፉ በቦርድ እንዲመራ ተደርጓል። ይህም ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉዳዮች በቦርዱ እየታዩ የዘርፉ ችግሮችም ሆኑ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣንና የተደራጀ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ነው።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አቶ አበራ መንግሥቱ እንደሚናገሩት፣ በድሬዳዋ ከተማ ያለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንቅስቃሴ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡበት ይገኛል። ከተማዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ጥሩ አፈፃፀም አሳይታለች። የከተማ አስተዳደሩ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ377 አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ይዞ ነበር። ከዚህ ውስጥም ለ250 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት ችሏል። እነዚህ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ከ20 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው። የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ወደ ስራ ሲገቡ ከ21ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎም ይጠበቃል። ፈቃድ ከወሰዱ ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ (225) የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው።
በመሰረተ ልማት አቅርቦት እና በአገልግሎት ጥራት ረገድም የከተማ አስተዳደሩ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋትና የተሻለ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን እውን በማድረግ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አቶ አበራ ይገልፃሉ። ‹‹አንድ ባለሀብት የሚጠበቅበትን መስፈርት አሟልቶ ከቀረበ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ አገልግሎት ያገኛል። 202 ሄክታር ስፋት ያለው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ መንደር የራሱ የኃይል ማከፋፈያ ስላለው ከባድ የሚባል የኃይል መቆራራጥ ስጋት የለበትም። በመንገድ መሰረተ ልማት ረገድም የኢንዱስትሪ መንደሩ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድም አስፋልት ባይሆንም በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ ነው›› ይላሉ።
ድሬዳዋ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የላቀ አፈፃፀም እንድታስመዘግብ ከሚያስችሏት መልካም እድሎችና ግብዓቶች መካከል አንዱ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተመረቀው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ነው። የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት እንዲያስመዘግብ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።
አቶ አበራ እንደሚሉት፣ ነፃ የንግድ ቀጣናው ወደ ከተማዋ የሚገባውን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ‹‹ነፃ የንግድ ቀጣናው ብዙ ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ እያደረገ ነው። ‹‹ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተካሄደው ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› (Invest Ethiopia 2023) የኢንቨስትመንት ፎረም መጠናቀቅ ማግስት 27 የውጭ ባለሀብቶች ወደ ድሬዳዋ በመሄድ ነፃ የንግድ ቀጣናውን ጎብኝተዋል። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ባለሀብቶች የንግድ ቀጣናውን ጎብኝተው በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል›› በማለት ነፃ የንግድ ቀጣናው ብዙ ባለሀብቶችን ወደ ድሬዳዋ እየሳበ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም በበኩላቸው፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው በይፋ ከተመረቀ በኋላ ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በነፃ ንግድ ቀጠናው ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ በስራ ላይ የሚገኙ ስድስት ባለሀብቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ሦስቱ የሀገር ውስጥ ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ የውጭ ባለሀብቶች ናቸው። ባለሀብቶቹ ቆዳ ጫማ፣ ክር እና የሲሚንቶ ከረጢት በማምረት እንዲሁም የማቀዝቀዣ መሳሪያዎችንና መኪናዎችን በመገጣጠም ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል። በዚህ የድርጅቶቹ የምርት ተግባርም ለሦስት ሺ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት አራት አዳዲስ ተቋማት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን ሁለቱ በመኪና መገጣጠምና ሁለቱ ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርት ላይ ይሰማራሉ። ሁሉም አምራቾች የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች መሆናቸው የኢንቨስትመንት ስምሪቱን የበለጠ ጠቃሚ ያደርገዋል።
በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያዎቹ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ተኪ ምርቶችን አምርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ጫናን ለመቀነስ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ይሁን እንጂ ነፃ የንግድ ቀጣናው በነፃ የንግድ ቀጣና የአሰራር ስርዓት መሰረት ስራ አልጀመረም። በዚህም ምክንያት በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ በስራ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች ስራቸውን እያከናወኑ ያሉት በቀደመው የኢንዱስትሪ ፓርክ አሰራር ስርዓት መሰረት ነው። አቶ ካሚል እንደሚናገሩት፣ የነፃ ንግድ ቀጣና አዋጁ አለመጠናቀቅ ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው በገቡና መግባት በሚፈልጉ ባለሀብቶች ላይ ያሳደራቸው ተፅዕኖዎች አሉ። ‹‹የነፃ ንግድ ቀጣና አዋጁ ተጠናቆ መጽደቅ አለበት። የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሁንም የተሟላ አይደለም። ወደ ነፃ ንግድ ቀጣናው ገብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት ቢኖሩም ወደ ነፃ ንግድ ቀጣናው ገብተው አገልግሎት ያልጀመሩ ተቋማትም አሉ። ነፃ የንግድ ቀጣናው ከምርት ስራ በተጨማሪ የንግድና ሎጂስቲክስ ስራ ጭምር የሚሰራበት በመሆኑ እነዚህ ስራዎች የሚከናወኑባቸውን የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት ማጠናቀቅ ያስፈልጋል። አምራቾች አሁን ከሚያገኟቸው ማበረታቻዎችና ጥቅሞች በተጨማሪ ምርቶቻቸውን ያለምንም የኢንቨስትመንትና ጉምሩክ ውጣ ውረዶች ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ፤ የወደብ ቆይታ ጊዜን ይቀንስላቸዋል። ነፃ የንግድ ቀጣናው በነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር መሰረት ስራ እንዲጀምር ባለሀብቶች ጥያቄ አቅርበዋል›› ይላሉ። የዋጋ ተመን ደንብን ጨምሮ ሌሎች መመሪያዎችንና የውስጥ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም አቶ ካሚል አያይዘው ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ስኬታማ እንዲሆን ከብዙ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቁ በርካታ ኃላፊነቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ካሚል፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት ነፃ የንግድ ቀጣናው በራሱ ሕጋዊ መመሪያ መሰረት ስራውን እንዲያከናውን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ። ‹‹ እነዚህ አካላት ነፃ የንግድ ቀጣናው ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የሚኖረውን በጎ አስተዋጽኦ በሚገባ ተገንዝበው ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባቸዋል። ባለሀብቶች ችግሮቻቸው ሲፈቱላቸው የምርት መጠን፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር፤ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ፤ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ እንዲሁም ንግድ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲመራ በማድረግ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ እድል ይፈጠራል›› በማለት የንግድ ቀጣናውን በተገቢው የሕግ ማዕቀፍ ስራ ማስጀመር እንደሚገባ ይገልፃሉ።
በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ከሚገኙ አምራቾች መካከል አንዱ ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› (Elauto Engineering) የተሰኘው ኩባንያ ነው። ከዘጠኝ ወራት በፊት የመኪና መገጣጠም ስራውን የጀመረው ኩባንያው፣ ለቤትና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም ፋብሪካ አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። የኩባንያው ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሁንዳኦል ፍቃዱ፣ ፋብሪካው እስካሁን ድረስ ከ500 በላይ መኪናዎችን የገጣጠመ ሲሆን፣ ከ200 ለሚበልጡ የድሬዳዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም በአውቶሞቲቭ ዘርፍ ለሰለጠኑ ባለሙያዎች የስራ እድል እንደፈጠረ ይናገራሉ።
ነፃ የንግድ ቀጣናን ማቋቋም የንግድ ዘርፍ ችግሮችን ለመቀነስና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ አወንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የምርትና የሎጂስቲክስ ተግባራት ተቀናጅተው በቀልጣፋ አሰራር የሚከወኑባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ለኢንቨስትመንት ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። የነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ ነው። በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ አንፃራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ናቸው። የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ያስገኛል ተብሎ ተስፋ በተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የንግድ ቀጣናው ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አቶ ሁንዳኦል ፋብሪካው በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ መገኘቱ ቀጣናው በሚተገብራቸው አሰራሮች መሰረት የነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር እድሎችና መልካም አጋጣሚዎች ተቋዳሽ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ይገልፃሉ። ‹‹በነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ቀላል የሆኑ የባንክና የጉምሩክ እንዲሁም ከቀረጥ ነፃ አሰራሮች ይኖራሉ። እነዚህ አሰራሮች ምርቶችን በቀላሉና በፈጣን ሁኔታ ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ ያግዛሉ›› ይላሉ። ነፃ የንግድ ቀጣናው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንደሚገባ መነገሩን አስታውሰው፣ ነጻ የንግድ ቀጣናው በነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር መሰረት ወደ ስራ ቢገባ ከነፃ የንግድ ቀጣና አሰራር የሚገኙ ጥቅሞችን ለማግኘትና ስራን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበትን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል። የንግድ ቀጣናው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ረሺድ ባለፈው ሳምንት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ ለነፃ የንግድ ቀጣናው አሰራር ትግበራ መሰረታዊ የሆኑ የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቀው የነፃ ንግድ ቀጣናው አዋጅ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያዘጋጀው የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ህግ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ነፃ የንግድ ቀጣናውን በ2016 ዓ.ም የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው። ለነፃ የንግድ ቀጣናው ምቹ የሆነ የሎጂስቲክስ ስርዓት በመዘጋጀቱ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው ገብተው ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የጠቆሙት ምክትል ሥራ አስፈፃሚው፤ ነፃ የንግድ ቀጣናውን በታቀደው ጊዜ ወደ ስራ ለማስገባት ለባለሀብቶች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2015