ለምን እንደሆነ አላውቅም አራት ሰዓት አለፍ ሲል ይደብተኛል። ድብርቴን የምሸሸው የሆረር ፊልም በማየትና በደረቴ በመተኛት ነው። የዛሬውም አራት ሰዐት እንደተለመደው ምርግ ነበር። አብሮኝ ከሚኖረው ፍታወቅ ጋር አዋተን በገዛናት ፍራሽ ላይ በደረቴ ተኝቼ የረፋድ ድብረቴን አጎንብሼ አሳልፋለው። በጣቴ መሬት እየጫርኩ የማላውቀውን ነገር ሜዳው ላይ እጽፋለው። በዚህ መሀል ስሜን ከውጪ ሲጠራ ሰማሁት..ሮቤል? አንተ ሮቤል?
ነፍሴ ሳቀች..ጀምበር ፈንጥቃ ስፍራዋን ለረፋድ ስትለቅ ማንም የማያስቀኝ ሰው ነበርኩ። ከሰዐት እስኪሆን ማለዳ በጉያው ውስጥ የሸሸገው የአራት ሰዐት አጋንት ከላዬ ላይ ጮሆ እስኪወጣ ድረስ ማንም የማያዝናናኝ ሰው ነበርኩ። ለዘመናት የተላመድኩት ድባቴዬ የት እንደገባ ሳላውቀው በሄመን ድምጽ ነቃሁ።
ከአልጋዬ ላይ እንዴት እንደተፈናጠርኩ አላውቅም ራሴን በሩ ላይ አገኘሁት። እኔ ስወጣ እሷ ስትገባ ተጋጨን። መቼም የማይደገም ግጭት። አይኖቼን የት ላድርጋቸው? አፈርኳት። ፊት ለፊቴ በግንባሬ የተገጨ ግንባሯን እያሻሸች ቆማለች። አይኖቿ የእፍረት ዝናር ታጥቀው ያዩኛል። ጡቶቿ በስስ የቤት ውስጥ ፒጃማ ተወድረው ደረቴ ላይ ተነጣጥረዋል። ከንፈሯ ሩብ ያህሉ በጥርሶቿ በቄንጥ ተነክሶ ተደቅኖብኛል። አይኖቼን የት ላድርጋቸው?
መደናበሬን አይታ ይሆን እንጃ ‹ቤት ማንም የለም ናና ተጫወት› ብላኝ ወደ ቤት ተመለሰች።
ከበሩ ላይ አልተንቀሳቀስኩም። ፊልም የሚመስለውን አጋጣሚ በአእምሮዬ እየመለስኩ ቆሜያለው። ቆይቼ ሳስበው ከመጋጨትም በላይ የሆነ ነገር ያስተናገድን ይመስለኛል። ደረቴ ላይ አሁንም ድረስ የሚሰማኝ ደስ የሚል የውጋት ህመም አለ..በጡቶቿ የተወጋሁት። ጉንጬ ላይ ጸጉሯ የገረፈኝ አንዳች የሚያክል ሰንበር አለ። ራሴን በመስተዋት ሳየው ቀይ የከንፈር ቀለም ከንፈሬ ላይ ተለጉዶ ነበር። ይሄ እንዴት ሆነ? ደስ የሚል የሚያሳፍር ሳቅ ሳኩኝ። ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ደስ የሚልና የሚያሳፍር ሳቅ ይስቃል? ሄመንን አፈርኳት። መንገድ ላይ ስንገናኝ ለመሳሳም የተቀጣጠርን እንጂ ለመጋጨት የተገናኘን አንመስልም ነበር።
አንዳንድ ቀኖች አሉ..የሰው ልጅ አስቦና ተዘጋጅቶ የማይደግማቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች አሉ እንዴት እንደመጡ፣ እንዴት እንደሆኑ ታስቦ የማይደረስባቸው። ከሄመን ጋር የተጋጨንበትን የዛሬውን ቀን ጻፍኩት። መቼም እንዳይረሳኝ ስለምፈልግ።
ተነስቼ ወደነሄመን ቤት ሄድኩ። እንደ እኔ አራት ሰዐት ይደብራት ይሆን አላውቅም ብዙ ቀን ደብቶኝ በተኛሁበት የአራት ሰዐት ማግስት ላይ ጠርታኝ ቤት ሄጄ አውቃለው። እነሄመን ቤት ከተከራየሁ ስምንተኛ ወሬን ይዣለሁ። በወር አንድ ጊዜ የሚመጣ ፍታወቅ የሚባል ጓደኛ ቢኖረኝም አብሮኝ እንዳለ አልቆጥረውም። እሷም ይሄን ብቸኝነቴን ስለምታውቅ ነው መሰለኝ ቤተሰቦቿ ወጣ ሲሉ መጥህ ተጫወት ብቻዬን ነኝ ትለኛለች።
ቤት ስገባ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ተቀበለኝ..ዛሬም ሚኪያ እየዘፈነች ነው። ሁሌ እዛ ቤት ጠርታኝ ስሄድ በሚኪያ በሀይሉ ሙዚቃ ነው የምትቀበለኝ። እዛ ቤት የሚኪያ በሀይሉ መብዛት አልገባህ እንዳለኝ ወደ ሳሎን አቀናሁ። ሄመን ከሙዚቃው ጋር አብራ እየሞዘቀች ቅድም በተላተምኩበት ፒጃማዋ አገኘኋት።
‹ምነው ብቻሽን..እነማዘር የት ሄደው ነው? አልኳት ድምጼን አጥፍቼ ከምገባ ብዬ።
‹ማዘር ክፍለ አገር ሄዳለች…
‹እና ብቻሽን ነሻ!..
‹አዎ ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ…› አለችኝ በሚያሳዝን ድምጽ። ድምጽዋ ውስጥ ከብቸኝነት የገዘፈ ሌላ ብቸኝነትን አደመጥኩ። እኔ ሆኜ እንጂ ፍታወቅ ቢሆን ከዚህ ንግግሯ ውስጥ ብዙ እውነቶችን መዞ ያወጣ ነበር። ብዙ ጊዜ ነገር አይገባህም ይለኛል። እሱ ብቻ አይደለም እስከዛሬ የተዋወኳቸው ሴቶች ነገር አይገባህም ሲሉኝ አድምጫለው። የሄመን ‹ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ› ማለቷ ከወሬ ባለፈ ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባኝ ዝም አልኩ። ወር ሙሉ ከአጠገቤ ሲርቅ ያልናፈቀኝ ጓደኛዬ በአይኔ ላይ አንጃበበ።
‹አባዬም እንደምታውቀው በስራ ምክንያት አምሽቶ ነው የሚገባው..› ሳልጠይቃት ነገረችኝ። ይሄን ብላ ትታኝ ወደሚቀጥለው ክፍል አመራች። ምሳ እየሰራች እንደሆነ ከሚሰነፍጠኝ የወጥ ሽታ ተረዳሁ። ማዕድ ቤቱ ከሳሎኑ ፊት ለፊት ስለሆነ እንቅስቃሴዋ ሁሉ ይታየኛል። እኔ ሳሎን ሶፋ ላይ ሆኜ እሷ ማዕድ ቤት ሆና እስኪበቃኝ ቀላወጥኳት።
ማዕድ ቤት በስስ ፒጃማዋ ውስጥ የማይታየኝ ነገር የለም። እንደ ጣዝማ ማር የጠየመ ገላዋ የጠለለ የምንጭ ውሀ ይመስል ነበር። ቀይ ፓንት፣ ጥቁር ጡት ማስያዣ ደረቷንና ወገቧን ዞረው ሳይ ሀጢዐት ተሰማኝ። እዛ ቤት ስገባ የማያቸው የሁልጊዜም ትዕይንቶቼ ነበሩ። ብዙ ጊዜ አትገባኝም..የማልረዳት ሴት ናት። ለምንና እንዴት እንደምታስበኝ ሳላውቅ በምትሆነው መሆን እጨነቃለው። ቆይ አንድ ሴት ለአንድ ወንድ እህት ብቻ መሆን አትችልም? እኛ ወንዶች ሴት ልጅ ለፍቅር ብቻ ነው የቀረበችን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ የተሳሳተ ሶፍት ዌር የጫነብን ማነው?
በእጇ ምሳ ይዛ ወደሳሎን ተመለሰች።
እጄን አስታጥባኝ የመጀመሪያውን ጉርሻ ወደ እኔ ስትሰነዝር የሆንኩትን አረሳውም። ጉርሻዋ ብርቅ ሆኖብኝ ለረጅም ጊዜ አላመጥኩት። ያን ጉርሻ ወደ ሆዴ ሳልሰድ ቀን ሙሉ እያላመጥኩት ብውል በወደድኩ ነበር። ከዛ በኋላ ያልቆጠርኳቸውን ብዙ ጉርሻዎች አጎረሰችኝ። ሳላጎርሳት ዝም ብዬ መብላት ጀመርኩ። ባልተቀየመ ልብ ማጉረሷን ተያያዘችው።
እፎይ አልኩ..
በሚቀጥለው ቀን ቤት ጠርታኝ ቁጭ ብያለው..ስልኳን አጠገቤ ትታው ወደ መኝታ ቤት ገባች።
አፍታ ቆይቶ ስልኳ አንድ የጽሁፍ መልዕክት መቀበሉን ተናገረ። ለምን እንደሆነ አላውቅም..የተላከው መልዕክት አየሁት። ቅስሜ ተሰበረ..ኪሩቤል በሚል ሴቭ በተደረገ ቁጥር ላይ ‹የኔ ፍቅር እንኳን ተወለድሽልኝ በጣም ነው የምወድሽ› ይላል። ቁጥሩን በአንድ ጊዜ እይታ ሸመደድኩት። ከመኝታ ቤት ስትመጣ ሌላ ሆኜ ነበር የጠበኳት። ቻው ሳልላት ትቻት ወደ ቤቴ ተመለስኩ።
ጓደኛዬን ፍታወቅ የሚመጣበት ቀን ስለነበር ስለሁሉም ነገር አወራሁት። ሳቀብኝ..እንዴት ማን እንደላከላት ሳታውቅ ትርቃታለህ? በስህተት የገባ ቴክስት ቢሆንስ? የማትወደው ልጅ የላከላት ቢሆንስ? ምን ታውቃለህ አለኝ። ልቤ ውስጥ የማላውቀው እውነት ተፈጠረ..ፍታወቅ ያለው ሁሉ እውነት ሆኖ አገኘሁት። ግን በምንም ተዐምር ሊሆን አይችልም። ፍታወቅ እያበደ መሰለኝ..አጉል ያውቃል ሲባል የዘባረቀው አለማወቅ ሆኖ ተገለጠልኝ። ሄመን ፍቅረኛ እዳላት አምኜ ተቀበልኩኝ። ከዛ በኋላ ብዙ ቀን ቤት ብቻዬን ነኝ ና ብላኝ ታውቃለች። ግን ሄጄ አላውቅም። ጭራሽ የማትኖርበትን ጊዜ እየጠበኩ ቤት መዋል ቤት ስትሆን ደግሞ ከቤት እየወጣሁ ከእሷ መሸሽ ጀመርኩ።
አንድ ቀን በሬን አንኳኩታ ስልክ አስደውላኝ ስልኬ ባላንስ የለውም ብላ መጣች። እንቢ ማለት ስለማልችል ስልኬን ሰጥቻት የሆረር ፊልሜን እያየሁ ቁጭ አልኩ። ስልኩ ሲጠራ ይሰማኛል..ለምን እንደሆነ አላውቅም ላውድ አድርጋዋለች።
ስልኩ ተነሳ..
‹ሄሎ ኪሩ..አለች።
‹አቤት! አለ አንድ ድምጽ።
ልቤ ጆሮ አብቅሎ ተከተላት። በተለይ ኪሩ የሚለውን ስም ስሰማ..
በቻልኩት ሁሉ ጸጥ ብዬ አደመጥኳት። ባለፈው ሳሎን ቁጭ ብዬ የኔ ፍቅር ብሎ ቴክስት የላከላት ወንድ እንደሆነ ደረስኩበት። ቤቴ ድረስ መጥታ ልታስቀናኝ መሞከሯ አናደደኝ። የእውነት ጠላኋት። እፎይ ብዬባት ነበር..
ስልኩን ዘግታ..‹ወንድሜ ነው ኪሩቤል ይባላል ሲመጣ አስተዋውቅሀለው አለችኝ›
ልቤ ቀጥ አለች..
እኛ ወንዶች ምንም እንደሆንን ደረስኩበት..ዓለም ላይ ምርጥ ስድብ ባገኝ ራሴን በዛ ስድብ እሰድበው ነበር። እንደ ወንድ ልጅ ደንቆሮ ዓለም ምን አላት ስል ራሴን አረከስኩት። አለማወቅን፣ ራስወዳድነትን በዚህ ልክ ማነው የጫነብን? ሄመን የሌላም ሆና እህቴ መሆን እንደምትችል እንዴት ማመን አቃተኝ እያልኩ ራሴን አሳነስኩት።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2015