ኪነጥበብ
«የሰንበት ቀጠሮ» የግጥም በጃዝ ምሽት ዛሬ ይደረጋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ 75ኛ ዓመት ልደቱን ምክንያት በማድረግ ካዘጋጃቸው ክዋኔዎች መካከል ዛሬ «የሰንበት ቀጠሮ» የግጥም በጃዝ ምሽት ይካሄዳል።
በኤጀንሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ከቀኑ 10:00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ የግጥም በጃዝ ምሽት ላይ ገጣሚያን ነብይ መኮንን፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ትዕግስት ማሞ ግጥሞቻቸውን ያስደምጣሉ። እንዲሁም ደግሞ የኪነጥበብ ባለሙያዋ አስቴር በዳኔ ወግ፣ ዲስኩር ደግሞ በመጋቢ ሀዲስ ዓለማየሁ እሸቱ የሚቀርብ ሲሆን መድረኩን በፍቃዱ አባይ እየመራው ሻሎም ለኢትዮጵያ የባህል ቡድን ያደምቀዋል ተብሏል።
በተያያዘ ዜናም በእለቱ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ለአንድ ሳምንት በተለያዩ መርሐ ግብራት ሲያስብ የቆየው ሰባ አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓሉ የመዝጊያ ሥነሥርዓት ይደረጋል። ይህንንም የተመለከተ ዝግጅት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በዛው በቅጥር ግቢው ይኖራል። ከአሜሪካ በተጋበዙ ሙዚቀኞች ሙዚቃዎች ይቀርባሉ፤ የአርበኞች የድል በዓልን የሚያመለክቱ ክዋኔዎችም ይኖራሉ። በዚህም ላይ ሊታደም የወደደ ሁሉ እንዲገኝ ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል።
13ኛው አዲስ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ዛሬ ይጠናቀቃል
ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ መርሐ ግብራት የጀመረው 13ኛው አዲስ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ዛሬ ሚያዝያ 27 ቀን 2011ዓ.ም ይጠናቀቃል።
ማምሻውን ከ11፡00 ጀምሮ በቫምዳስ መዝናኛ ማዕከል በሚካሄደው በዚህ የመዝጊያ ክዋኔ የተለያዩ የፊልም ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል። ለእለቱ የተመረጠው «My name is Genet» (ስሜ ገነት ነው) ፊልም ለእይታ የሚቀርብ እንደሆነም አዘጋጆቹ ገልጸዋል። መሳተፍ ለሚፈልጉም ሁሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
«ማምሻ» የሥነጽሑፍ ምሽት
ማክሰኞ ይካሄዳል
የሚያዝያ ወር ማምሻ ወርሃዊ ጥበባዊ ምሽት «ስብሐት» በሚል ርዕስ ማክሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን 11፡30ሰዓት ጀምሮ ብሥራተ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ በሚገኘው በላፍቶ ማዕከል፤ እንይ ሲኒማ ቁ.1 አዳራሽ ይካሄዳል።
በዝግጅቱ ላይ ገጣምያን የግጥም ሥራዎ ቻቸውን ያቀርባሉ። ሙዚቃዎች ይደመጣሉ፤ ወጎች ይነበባሉ ተብሏል። ሥነ ሥዕልን የተመለ ከተም ሃሳብ በዚህኛውም ማምሻ እንደሚነሳ አዘጋጆቹ አሳውቀዋል።
«እንድቅትዮን» የሥነ ጽሑፍ ምሽት ከነገ በስቲያ ይካሄዳል
«እንድቅትዮን» የሥነ ጽሑፍ ምሽት አራተኛ ዝግጅቱ ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡30 ጀምሮ በገነት መናፈሻና ሆቴል ይካሄዳል።
በዚህ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ላይ ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ፣ ገጣምያን ትዕግስት ማሞ፣ ምግባረ ሲራጅ፣ ልዑል ኃይሌ፣ ሀብታሙ ያለው፣ ሄለን ፋንታሁን እንዲሁም በትዝብትን ከእንዳልክ ጋር የቴሌቪዥን ዝግጅት የሚታወቀው እንዳልካቸው ዘነበ ይገኛሉ።
«ኢትዮ– ኤርትራ» የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ነው
«ኢትዮ ኤርትራ» የተሰኘ በኢትዮጵያዊቷ ሠዓሊት ብርሃን በየነ እና በኤርትራዊው ሠዓሊ ነባይ አብርሃ የተዘጋጀ የስዕል ዓውደ ርዕይ ካሳለፍነው ሳምንት ሚያዝያ 24 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ለእይታ ክፍት ሆኗል።
በፈንድቃ የሥነጥበብ ማዕከል የቀረበው ይህ የስዕል አውደ ርዕይ በቁጥር ከ30 በላይ የሠዓሊያኑን ሥራዎች ያካተተ ሲሆን ከእሁድ በቀር ባሉት ቀናት ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ ለተመልካች ክፍት የሚሆን ነው። አውደ ርዕዩ እስከ ግንቦት 14 ቀን 2011ዓ.ም ይቀጥላልም ተብሏል።
አዳዲስ መጻሕፍት በገበያ ላይ
ባሳለፍነው ሳምንትና ከሰሞኑ የመጻሕፍቱን ገበያ ከተቀላቀሉ መጻሕፍት መካከል በደራሲ ተስፉላስኪ የተዘጋጀው «ጥለት እና የእሳት እራት» የተሰኘው ልብወለድ መጽሐፍ አንዱ ነው። በፍቅር፣ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ጉዳይና ላይ የሚያጠነጥኑ ታሪኮችን አካትቷል የተባለለት ይህ መጽሐፍ፤ በ103 ገፆች ተዘጋጅቶ በ94 ብር ከ99 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል።
ሌላው በተርጓሚ ካሳሁን ከበደ በላይ «ኢትዮጵያ፡ የአብዮቱ ማስታወሻና ያመለጣት እድል» በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለንባብ የበቃው መጽሐፍ ነው። ይህም በኢንግሊዘኛ ቋንቋ ብሌየር ቶምሰን እና ማይኬ ካርስተንሰን በተባሉ ሰዎች የተጻፈ ሲሆን፤ የመጽሐፉ አዘጋጆች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደቶች ውስጥ የታዘቡትን ለማስታወሻ በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጁት ነው። ይህም መጽሐፍ በ306 ገጾች ተቀንብቦ በ120 ብር የመጻሕፍት ገበያውን ተቀላቅሏል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም