![](https://press.et/wp-content/uploads/2023/06/EPA-3photo-15.jpg)
. በሕገወጥ ጫኝና አውራጆች ላይ ርምጃ ተወስዷል
አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ የሸራ ቤት ንግድ ከፈረሰባቸው መካከል አካል ጉዳተኞችና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን በጥናት በመለየት በተለያዩ የንግድ ስራዎች ለማሳተፍና የንግድ ሥርዓቱን ለማስተካከል የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በከተማዋ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ተደራጅተው ሲሰሩ የነበሩ ጫኝና አውራጆች ላይ ርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ከንግድ ቢሮ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ ከሸራ ንግድ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞችና የተለያየ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን በጥናት በመለየት በተለያዩ የንግድ ስራዎች እንዲሰማሩ ይደረጋል።
ምክትል ከንቲባው እንዳስታወቁት ፤ የኢኮኖሚ አቅማቸው ያደጉ ኢንተርፕራይዞችና ግለሰቦች ቀድሞ የያዟቸውን ቦታዎች እንዲለቁ ተደርጓል። የከተማ አስተዳደሩ አዳዲስና የተለቀቁ መስሪያ ቦታዎችን አቅም ላነሳቸውና፣ ስራ ለሌላቸው እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች እንዲተላለፉ ያደርጋል።
በከተማው የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፤ የስራ አጥነት ችግር ሊቀረፍ አልቻለም ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ በሌላ በኩል ከተማዋ የዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ መዳረሻ እና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ሞዴል እንድትሆን ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ ጃንጥራር እንዳሉት፤ እነዚህን ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦች አስታርቆ መሄድ ይጠይቃል፡፡ በአንድ በኩል የከተማዋን ውበት መጠበቅ እና በሌላ በኩል ሕጋዊ የሆነ የስራ ስምሪት ውስጥ ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት መደበኛ ያልሆኑትን በመደበኛ ስራ በማሰማራት የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ ይገባል፡፡
በመደበኛው የንግድ አሰራር ለመሰማራት ከፍተኛ መሰረተ ልማት የሚጠይቅ በመሆኑና ይህን ማድረግ ባለመቻሉ በርካታ አካላት መገበኛ ባልሆነ ሁኔታ እየሰሩ ቆይተዋል ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ በመሆኑም እነዚህ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ እየሰሩ እውነተኛ እና ተጨባጭ ችግር ያሉባቸውን አካላት ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ መስራት የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታን ማበላሽት ብቻ ሳይሆን እንደዚህ አይነት ንግዶች እየተስፋፉ የሚመጡ ከሆነ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያመጡት ቀዉስ ቀላል አይደለም። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ ጥናቶችን በማድረግ እነዚህን አካላት ወደመደበኛ እና ዘላቂ በሆነ ሥርዓት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዚህም ስራ አጦችን ለመርዳት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ አንድ ትልቅ ክላስተር ተቀርጾ እየተገነባ ነው። ይህ ክላስተር በአነስተኛ ደረጃ ያሉትን ወደመካከለኛ ለማሸጋገር እድል ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በሕገወጥ መንገድ ተደራጅተው፤ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ታቅፈው ህብረተሰቡን ለእንግልት ሲዳርጉ የነበሩ ጫኝና አውራጆች በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡
ከከተማዋ ማህበረሰቦች ለከተማ አስተዳደሩ ከሚደርሱ ቅሬታዎች አንዱ በሕገ ወጥ መንገድ በመደራጀት ከመናኸሪያ እስከ መኖሪያ ሰፈሮች ድረስ ህብረተሰቡን ለእንግለት ሲዳርጉት የነበሩ ጫኝና አውራጆች ጉዳይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ በሚደርሱት ቅሬታዎች እና ባደረገው ጥናት ሊደርስበት ችሏል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ሲሰራ ቢቆይም፤ ችግሩ ሊቀረፍ ባለመቻሉ ህብረተሰቡ ለእንግልት ተዳርጓል ብለዋል፡፡
ሃላፊዋ እንደተናገሩት የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ህገወጥ ማህበራትን በማገድ በማህበሩ የሚሰሩ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015