
አዲስ አበባ ፡- የአቅም ማሻሻያ (ሪሚዲያል ) የትምህርት መርሃ ግብር ፈተና ከሰኔ 26 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት ፤ በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስደው ከ50 በመቶ በታች ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለአራት ወራት ያክል ሲሰጥ የነበረው የሪሚዲያል የትምህርት መርሃ ግብርን በማጠናቀቅ ከሰኔ 26 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015ዓ.ም ፈተናው ይሰጣል፡፡
ተፈታኞቹ ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ከ30 በመቶ ፈተና የወሰዱ መሆናቸውን አውስተው፤ ቀሪው 70 በመቶ ፈተና ሰኔ 26 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በማዕከል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፊዚክስ፣ ሂሳብ፣ኬሚስትሪ፣ እንግሊዝኛ ፣ ባዮሎጂ የትምህርት አይነቶችን በተከታታይ ከሰኞ እስከ አርብ የሚፈተኑ ሲሆን የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ታሪክ፣ ሂሳብ፣ ጂኦግራፊና እንግሊዝኛ ፈተናዎችን በተከታታይ ከሰኞ እስከ ሀሙስ እንደሚፈተኑ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ኤባ በአቅም ማሻሻያ ፕሮግራሙ 105 ሺህ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተፈታኞች እንዲሁም 107 ሺህ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተፈታኞች በድምሩ 212ሺህ ተማሪዎች የትምህርት መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ፈተናውም በተመሳሳይ ቀን፣ ሰአትና እኩል የመፈተኛ ጊዜ ይሰጣል ብለዋል፡፡
ተፈታኞች ይህ ዳግመኛ የማይገኝ እድል መሆኑን በመረዳት በትኩረት መስራትና መዘጋጀት ብሎም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለመሆን መትጋት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ለማለፍም በአጠቃላይ ከ50 በመቶ እና ከዛ በላይ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአቅም ማሻሻያ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪ መሰረት ወርቁ እና መቅደስ አለማየሁ እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት የሆኑ አምስት የትምህርት አይነቶችን እየተማሩ ሲሆን በመምህራን የሚቀርቡ የተለያዩ ሞጁሎችን ከማንበብ በተጨማሪ አጋዥ መጽሀፍትን በማጥናት ጭምር ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
ሌላው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ አቅም ማሻሻያ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ተማሪ ሰመረ አባተ በበኩሉ የተሰጣቸው የትምህርት እድል መልሶ የማይገኝ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ትምህርቱን እየተከታተለ እንዳለ ገልጾ፤ ትምህርታቸውን ለማማር በሚያመች መልኩ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መከታተላቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግሯል። ጥሩ ውጤት ለማምጣትና ወደ ቀጣይ ትምህርት ደረጃ ለመሸጋገርም የተሰጠውን እድል በአግባቡ እየተጠቀመበት እንደሆነ ነግሮናል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2015