
አዲስ አበባ ፡- በመጪው ክረምት በቡና አብቃይ አካባቢዎች አንድ ነጥብ 59 ቢሊዮን የቡና ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የቡና ፣ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከቡና የሚገኘውን ገቢ በዘላቂነት ለማሳደግ በመጪው ክረምት አንድ ነጥብ 59 ቢሊዮን የቡና ችግኞችን ለመትከል በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ለዚህም አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የችግኝ ጉድጓድ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ድረስም 971 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጎድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ በቡና ችግኝ ተከላውም አምስት ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ቀደም ብለው ተተክለው ያረጁ የቡና ዛፎችን በነቅሎ ተከላ ለመተካትም 55 ሺህ 338 ሄክታር መሬት ላይ 193 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኝ እንዲሁም ተተክለው ባልጸደቁ ችግኞች ምትክም 205 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል።
አዲስ የቡና ችግኝም በ266 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚተከል መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም በሄክታር ከ8 እስከ 10 ኩንታል የቡና ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
ለቡና ችግኝ ከተዘጋጀው ጉድጓድ ውስጥም እስካሁን አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ የቡና ተከላ መፈጸሙን አመልክተዋል።
የሚተከሉት ችግኞች ጸድቀው ምርት መስጠት ሲጀምሩም በቀጣይ ዓመታት አጠቃላይ የቡና ምርትን ወደ 860 ሺ ቶን እንደሚያሳድገው ይጠበቃል ነው ያሉት።
አቶ ፍቃዱ ዓምና ከቡና ምርት ለማግኘት ከታቀደው 810 ሺ ቶን የቡና ምርት ውስጥ አጠቃላይ በ2015 ዓ.ም በተካሄደው የምርት ትመና 761 ሺ ቶን የቡና ምርት ተገኝቷል ። ይህም ምርት ከአዲስ መሬት ላይ 232 ሺህ 142 ሄክታር በመሸፈን አንድ ነጥብ 25 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል የተገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ 65 በመቶ የጽድቅ መጠን እንዳለውና በዘንድሮ የተሻለ አፈፃፀም እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ አንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸው፤ ኦሮሚያ ክልል 59 በመቶ፣ ደቡብ ክልል 12 በመቶ ፣ ሲዳማ ክልል 7 በመቶ ፣ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል 15 በመቶ ሽፋን እንዳላቸው አመልክተዋል።
በቀጣይም አዲስ ተከላን በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በቀጣይ በአስር ዓመታት ውስጥም የቡና ምርታማነት በሄክታር እስከ 12 ኩንታል ለማድረስ ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ፍቃዱ በቡና ዘርፍ ላይ እንደ ተግዳሮት እያጋጠሙ ከሚገኙት ችግሮች መካከልም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተባይ መስፋፋት ፣ አፈር ለምነት ማነስ፣ የግብአት አቅርቦት እጥረት፣ ቡናን ወደ ጫት እና የመሳሰሉት ምርቶች የመለወጥ ስራ መበራከት፣የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ክፍተቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም ስራዎች እየተሰሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የዘንድሮ የዝናብ ሁኔታ ለቡና ምርታማነት ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ የቡና ችግኞችን በሰፊው በማልማት የቡና መሬት ሽፋን ለማስፋትና ሀገሪቱ ከቡና ልታገኝ የምትችለውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሰራት አለበት ብለዋል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም