እነሆ ዛሬም ከነበርኩበት ሰፊ ግቢ አልወጣሁም:: ብዙ የኑሮ ሚስጥሮች፣ አስገራሚ የማንነት ታሪኮች ፣ በርካታ የሕይወት ገፆች ከሚገለጡበት አጸድ መሀል በግርምት ቆሜያለሁ:: በዚህ ሥፍራ የመገኘቴ እውነት ደግሞ በምክንያት ነው ::
ይህ ቦታ ለዓመታት በኀዘን የታጀበ ሳቅ አልፎበታል:: በለቅሶ የተዋጠ ሳቅ ደምቆበታል:: በዚህ ግቢ አያልፉ ይመስሉ ችግሮች ታልፈው የጨለሙ ቀናት ነግተዋል:: ክፉ ታሪኮች ተሽረው በአዲስ ሕይወት ተሞልተዋል::
ዛሬም የስፍራው መልካም እጆች ለተከፉ ነፍሶች ይፈጥናሉ:: ያዘኑትን ዕንባ የሚያብሱ ፣ ቋጠሮ ሚስጥሮች የሚፈቱ ደጋግ ልቦች ሁሌም ስለ መልካምነት ድካምን አያወቁም:: አብዛኞቹ የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ቤተሰቦች የመጎዳት፣ የማዘን ስሜትን አሳምረው ያውቁታል:: ከሕይወት ስብራታቸው ጀርባ ያሉ ታሪኮች አሁን ቢያልፉም ፈጽሞ አይረሷቸውም:: እንዲያም ሆኖ ዛሬ ላይ ቆመው ስለ ትናንት አይቆዝሙም:: ይልቁኑስ ሌሎችን ለማገዝ ፣ ለመርዳት መልካም ልባቸው በበጎነት ሲገለጥ ይውላል::
ዛሬም ከሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታደለ አየለ ጋር ጨዋታዬ ቀጥሏል:: አቶ ታደለ በግቢው ካሉ ነዋሪዎችና ካሳለፏቸው አስገራሚ ታሪኮች መሀል ጥቂት የሕይወት ገጸችን ገልጦ እያስነበበኝ ነው::
ከርታታዋ እናት …
የልጅነት ባሏን ሞት የነጠቃት ወይዘሮ ስለወደፊት ሕይወቷ እያሰበች ትጨነቃለች:: ትናንት ጎኗ የነበረው ግማሽ አካሏን ካጠች ወዲህ ግራ ይገባት ይዟል:: አሁን ቤት ጎጇዋ ያለእሱ መኖር ምንም ሆኗል:: ነፍስ ያላወቁ ሁለት ልጆቿ ከእሷ ሌላ ዓለም የላቸውም::
ወይዘሮዋ የገጠር ሕይወት ይከብዳት ይዟል:: ከአሁን በኋላ አርሶና ሸምቶ የሚያኖር አባወራ የላትም:: በትካዜ ስትውል የሁለት ልጆቿ ነገር አብዝቶ ያስጨንቃታል:: ለእነሱ መኖር የእሷ መቆም የግድ ነው:: ይህን ስታስብ የእጇ ጥሪት፣ የጎጇዋ ባዶነት ትውስ ይላታል:: ባለችበት የኑሮ አቅም ሁለት ልጆች የማሳደግ ብርታቷን ትፈትነዋለች:: አሁን ላይ ይህ አይነቱ አቅም ከእሷ የለም::
ውላ አድራ ወይዘሮዋ ብዙ አሰበች:: ከራሷ መክራ፣ ተማክራም ከውሳኔ ደረሰች:: ካለችበት ርቃ ከተማ ብትገባ ይሻል፣ ይበጅ መሰላት:: ሃሳቧን አላጠፈችውም:: ቀን ቆርጣ ጓዟን ሸከፈች:: ልጆቿን ይዛ መንገድ ጀመረች::
አዲስአበባ ያደረሳት እግሯ ጥቂት ቀናት በእንግድነት አቆያት:: ከተማ እንደገጠር አይደለም:: ባህል ወጉ ይለያል፣ ቤት ከእንጀራ ማግኘት ይከብዳል:: የልጆቹ እናት እያደር ከሰው መግባባት መላመድ ያዘች:: የሙት ልጇቿን ለማኖር የአቅሟን እየሰራች ፣ የእጇን ታጎርሳለች:: በእሷ መኖር እነሱ እንዲቆሙ ጉልበት ከፍላ ፣ላብ አፍስሳ ታድራለች::
‹‹ውሰዷት…››
ከቀናት በአንዱ አንዲት ወይዘሮዋ አጠገቧ ቀረብ ብለው እናቲቱን አናገሯት:: ልጆች ለማሳደግ ሌት ተቀን የምትባትለው ሴት የወይዘሮዋን ንግግር አልናቀችም:: ከሁለት ልጇቿ ሴቷን ወስደው ማሳደግ እንደሚሹ ሲነግሯት አላንገራገረችም ::
አሁን ልጆቿ በልተው፣ ለብሰው ማደር አለባቸው:: ይህን ለመሙላት አቅሙ ለሌላት እናት የወይዘሮዋ ቃል ታላቅ የምስራች ሆኗል :: የኑሮ ሸክም ያቀለሉላትን ትልቅ ሴት በምስጋና አክብራ ስለልጇ ነገ ተስማማች:: ሳታወላውል ይሁንታዋን ሰጠቻቸው:: ይሁን፣ ‹‹፡ውሰዷት፣ አሳድጓት›› አለቻቸው::
አ ሁን እረፍት አልባዋ እ ናት ድ ካም ሸ ክሟ ቀሏል:: ሴት ልጇን በማደጎ ከሰጠች ወዲህ ሃሳብ ጭንቀቷ ለወንዱ ልጇ ነው:: ጤና ባይኖራትም እረፍትን አታውቅም:: ለእሷና ለቀሪው ልጇ ጉሮሮ ጠዋት ማታ ትሮጣለች::
ት ንሽዋ ል ጅ ወ ይዘሮዋ ቤ ት እ ንደገባች አዲስ ሕይወት ጀምራለች:: አሁን ከርታታ እናቷ በእሷ በልቶ ማደር እፎይታ እየተሰማት ነው :: ልጇ ከእንግዲህ አይርባትም፣ አይጠማትም:: በአሳዳጊዋ መልካም እጆች ላይ ማረፏ የእሷንም ልብ አሳርፏል::
ነገን ተምራ ቁምነገር ደርሳ ማየት የእናትነት ምኞቷ ነው:: ይህ እደሚሆን ቃል የገቡላት ሴት ለትምህርቷ በማሰባቸው ደስ ብሏታል:: የወይዘሮዋን ትልቅነት፣ ከመልካምነት አዳምራ የተቀበለችው እናት የልጇን እጅ ከወይዘሮዋ አጨባብጣ ወደ ሕይወቷ ስትመለስ አልዘገየችም:: ሃሳብ ተቃሎ ፣ ችግር ቢነሳላትም ከልምዷ አልታቀበችም:: ወንድ ልጇን ለማሳደግ በድካም ባተለች:: ኑሮን ፣ ልታሸንፍ በጥረቷ ቀጠለች::
የአሳዳጊዋ እጆች …
ትንሽዋ ልጅና ወይዘሮዋ በአንድ መኖር ከጀመሩ ጊዜያት ተቆጥረዋል:: ልጅቷ እየተማረች ነው:: ትልቋ ሴት በልጅቷ መኖር ደስተኛ ናቸው:: ታዳጊዋ እጃቸው ከገባች አንስቶ ይበጃል ካሉት ስራ አገናኝተዋታል:: ስለእሳቸው በቅርብ የሚያውቁ ሴትዬዋ አዋቂና ‹‹ባለውቃቢ›› መሆናቸውን ይናገራሉ:: በእሳቸው ቤት ዘወትር የቡና ልማድ አለ:: ቡናው የሚፈላው በተለየ ክብርና ሥርዓት ነው::
ሴትዬዋ ትንሸዋን ልጅ የፈለጓት ለዚሁ ዓላማ ነበር:: ልጅቷ ሁሌም በአጠገባቸው ተቀምጣ ቡና እንድታፈላ፣ እንድትታዘዝ ፣ ዕጣን እንድታጫጭስ ይፈልጋሉ:: በእሳቸው አባባል ‹‹እየከደመች›› ማገልገል፣ እንደ ውቃቤያቸው ስሜት መታዘዝ ግዴታዋ ነው::
አሁን እንግዳዋ ልጅ ወይዘሮዋ የሚሏትን ሁሉ ማድረግ አለባት:: እንዲህ ካልሆነ በላያቸው ያለ ውቃቢ ይቆጣል:: ውቃቢው ሲቆጣ ደግሞ ወይዘሮዋ የህጻኗን ጀርባ በጥርሳቸው እየነከሱ ፣ በጥርፍራቸው ይቧጥጧታል::
ዘወትር ብስጭት የማያጣቸው ሴት የንዴት ማብረጃቸው በአደራ የተቀበሏት ልጅ ሆናለች:: ልጅቷ ትምህርት ስትሄድ በትካዜ ትውላለች:: ጨዋታዋ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ አይደለም:: በድብርት፣ በዝምታ ፣ በብቸኝነት ትታያለች::
ከትምህርት ውላ ወደቤት ስትገባ የወይዘሮዋ መንፈስ በንክሻ ይቀበላታል:: የሰሉ ጥፍሮች ከጀርባዋ ያርፋሉ:: ስድብና ጩኸት፣ ቁጣና ተግሳጽ ታስተናግዳለች:: የልጅነት ገላዋ ደም እየተፋ ፣ ዓእምሮዋ ይጨነቃል:: ማልቀስ የለመዱ ዓይኖቿ ደጋግመው ያነባሉ:: ትኩስ ዕንባ በጉንጮቿ፣ በአንገቷ ሲወርድ ያመሻል::
ትምህርቷን በወግ የማትማረው ታዳጊ የብዙዎችን ትኩረት ስባለች:: ትካዜና ጭንቀት መገለጫዋ ሆኗል:: በኀዘንና አንገት መድፋት ትታወቃለች:: አንዳንዶች ሁኔታዋ ቢያሳስባቸው ቀርበው ተግባቧት:: ስለምን? ሲሉም ጠየቋት:: ገለልተኛዋ ልጅ ሰሚ ስታገኝ እውነቱን ተናገረች:: በሰላ ጥፍር የተቧጠጠ፣ በሾሉ ጥርሶች በንክሻ የተጎዳ ጀርባዋን ገልጣ አሳየች:: ገላዋን ያዩ ሁሉ የልጅቷን የስቃይ ኑሮ ተረዱት:: በመከራ የምትገፋው መሪር ሕይወት አሳሰባቸው::
ዕለቱን ወደቤት እንዳትሄድ ሲወሰን ለማረፊያዋ የሙዳይ በጎ አድራጎት ግቢ ተመረጠ:: በስቃይ ያሳለፈቻቸው ጊዜያት ታሪክ ሆኑ:: ኀዘንዋ ተረሳ:: ተረጋጋች:: ዕንባዋ ታበሰ :: ልጅቷ በግቢው ካሉ ልጆች ተቀላቅላ ትምህርቷን በትጋት ቀጠለች::
ጥቂት ቆይቶ አሳዛኝ ዜና ተሰማ:: ወላጅ እናታቸው በድንገት አረፈች:: ይህኔ የትንሽ ወንድሟ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ሆነ:: ለልጆቹ ከእናታቸው በቀር ዘመድ የላቸውም :: ይህ እውነት የወይዘሮ ሙዳይን ቀና ልቦና ጎበኘ:: ወይዘሮዋ ወንዱን ልጅ ጭምር ተረክባ የግቢው ቤተሰብ እንዲሆን ፈቀደች::
የአንድ እናት ልጆች- በሙዳይ
ከእናታቸው ሞት በኋላ እህትና ወንድም በአንድ ዋሉ:: ናፍቆት ትዝታቸውን፣ ሕይወት ዓላማቸውን ሊያወጉ ዕድል አገኙ:: አሁን እናት አባታቸው የሙዳይ ግቢ ሆኗል:: ነገን በድል ለማለፍ መበርታት፣ መጠንከር አለባቸው :: የእናታቸው ድካም ዋጋ የሚያገኘው በጽኑ ዓላማ ሲያልፉ ነው::
እህትና ወንድም መንገዳቸውን አልሳቱም:: ከግቢው የሚቸራቸው ፍቅርና ትኩረት ለውጤት አድርሷቸዋል:: ትናንትን በጥንካሬ አልፈው ዛሬ ላይ ሲቆሙ ከታላቅ ውጤት ጋር ሆኗል:: አሁን ሁለቱም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው::
ከአቶ ታደለ ጋር የነበረኝ ቆይታ ተቋጭቷል:: ከሙዳይ በጎ አድራጎት ግቢ አልወጣሁም :: አሁን ከማህበሩ መስራችና ስራ እኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ጋር ጨዋታ ቀጥያለሁ:: ወይዘሮ ሙዳይ ልበ ርህሩህና አዛኝ ሴት ናት:: የበርካቶቹን ታሪክ መለስ ብላ ስታወጋኝ ከዕንባዋ እየታገለች ከልቧ እያዘነች ነው:: በተፈጥሮዋ ተገርሜያለሁ:: የብዘዎችን ሕይወት የታደገችበት አንዱ ምክንያት ይህ እውነታ መሆኑ ገብቶኛል:: እኔም ከሙዳይ ዕንባ በስተጀርባ ከሚቀዱ ታሪኮች መሀል አንዱን ‹‹እነሆ!›› ብያለሁ::
የሙት ልጅ…
ይህ ታሪክ ዓመታትን ወደኋላ ይመልሰናል:: በወቅቱ በሙዳይ ግቢ ከሚታገዙ እናቶች መሀል አብዛኞቹ የኤችአይቪ ህሙማን ነበሩ:: እነዚህ እናቶች ጤናቸውን አሸንፈው ልጆች ለማሳደግ ሕይወታቸው የተፈተነ፣ የኑሮ ሸክማቸው የከበደ ነው:: የሙዳይ በጎአድራጎት ማህበር ለእነዚህ እናቶች የቅርብ ወዳጅና ቀኝ እጅ ነው:: በሕይወት እስካሉ ቀርቦ ያግዛቸዋል:: በሞራል፣ በተስፋ ያሳድራቸዋል::
ከእነዚህ እናቶች መሀል የስድስት ዓመት ልጅ ያላት ወይዘሮ በሙዳይ ቤተሰብነት ዓመታትን ዘልቃለች:: ይህች ሴት ጤናዋ እየታወከ አቅሟ እየደከመ ነው:: ይህን የተረዳው ማህበር የዕለት ምግቧን ችሎ የቤት ኪራይ ያግዛታል:: የአካባቢው ሰው እናትና ልጁን መቅረብና ማየት አይፈልግም:: በመገለል ዓመታትን እንዲገፉ፣ ምክንያት ሆኗል::
በግቢው የሴትዬዋ ትንሽ ልጅ ይማራል:: እናት ታማሚ ብትሆንም ከዛው ውላ የአቅሟን ሰርታ ትገባለች:: አንድቀን ግን ያልታሰበው ሆነ:: ወይዘሮዋ ልጇን ትታ ላትመለስ አሸለበች:: ጉዳዩን ቀድማ የሰማችው ወይዘሮ ሙዳይ ወደ ሴትዬዋ መኖሪያ ፈጥና አመራች:: ስፍራው ስትደርሰ ጎረቤቶቿ በመገለል ቆመው ሲንሾካሾኩ አየቻቸው::
በቤቷ ያረፈችው ወይዘሮ የተጠጋት የለምና አልተገነዘችም:: ወይዘሮዋ ሁሉንም በዓይኖቿ ቃኘች:: ማንም ሊገንዛት፣ ሊያሰተካክላት አልወደደም:: ነፍሰጡሯ ሙዳይ እስካሁን ይህ አይነቱ ልምድ የላትም:: የሞተ መገነዝ ቀርቶ አስከሬን ይሉት አይታ አታውቅም:: ጊዜ ወስዳ ጠበቀች:: ለውጥ የለም:: ምርጫ አልነበራትም:: ሃላፊነቱን ወስዳ የሴትዬዋን አስከሬን በድፍረት ገነዘች::
የዕጣ ፈንታ ነገር
የትንሹ ልጅ እናት በሞት ከተለየች በኋላ ወይዘሮ ሙዳይ ህጻኑን ለመውሰድ ተዘጋጀች:: ይህን ያወቁ ጎረቤቶች ግን እንዳትወስደው አከላከሏት:: ልጁ በግቢው ውሎ ሲመለስ ቤቱ ማደር እንደሚችልና በቅርብ እንደሚዳምጡት ሲነግሯት አመነቻቸው:: እንደተባለው ሆኖ ህጻኑ እናቱ በነበረችበት ትንሽዬና ጠባብ ቤት ማደር ጀመረ::
በወቅቱ የጎረቤቶቹ ዓላማና ዕቅድ ሌላ ነበር:: በሟች ቤት የቀሩ ንብረቶችን በልጁ አሳበው መውሰድ ፈልገዋል:: ሰዎቹ ልጁን አልወደዱም:: የሚመገብበትን ሰሀንና ኩባያ ጭምር ለይተዋል፣ መጸዳጃ ነፍገው ከእኩዮቹ እንዳይጠጋ አግልለዋል:: እሱ የሚነካውን ዕቃ ጥለው የእናቱን ንብረት ሽተዋል::
የአንድ ቀን ቃል …
የሟቿ ልጅ አዳሩ እንጂ ውሎው በሙዳይ ግቢ ነው:: አሁን ወይዘሮዋ አራስ በመሆኗ ቤት ውላለች ‹‹እማ›› የሚላት ህጻን ሁሌም ከስሯ አይጠፋም:: እሷን ሲያገኝ ፈገግታው ይለያል፣ ፊቱ ይደምቃል፣ ነጻነት ይሰማዋል:: እንደልጅነቱ ያየውን እያነሳ፣ እየጣለ ይጫወታል:: አንድ ቀን ከሙዳይ አጠገብ የዋለው ልጅ ሳያስበው የአራስ ህጻኗን ኩባያ በእጁ ነካ:: ወዲያው በድርጊቱ አፍሮ ተሳቀቀ፤ አዘነ:: ልጁ ኩባያውን አንስቶ ለሙዳይ ሰጣት:: እንደነካው ተናግሮም እንድትጥለው አዘዛት::
ሁኔታው ያልገባት ወይዘሮ በግርምት እያስተዋለች ለምን ስትል ጠየቀችው:: ጎረቤቶቹ እሱ የነካውን ዕቃ በሙሉ እንደሚጥሉ አስታውሶ ህመሙ ለልጇ እንዳይጋባ እሷም ኩባያውን መጣል እንዳለባት አሳሰባት:: ሙዳይ ከልብ አዘነች:: ምክንያት ፈላጊ ዕንባዋ በፊቷ ተገለበጠ:: በዚህ ስሜት አልቆየችም:: ልጁን ከነበረበት አውጥታ በሙሉ ነጻነት ያድግ ዘንድ በሯን ከፈተችለት::
እነሆ! ይህ ታሪክ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል:: የዛኔ በጎረቤቶቹ ያልተገባ አመለካከት የተገለለው የስድስት ዓመት ህጻን ዛሬ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ይገኛል:: ያለፈው ታሪክ ለእሱ የሕይወቱ አንድ አካል ቢሆንም ስለሆነበት ሁሉ የሚያስታውሰው የለም:: ዛሬ ግን በሙዳይ ድጋፍና እገዛ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ በዘንድሮ ዓመት ይመረቃል::
እነዚህ ታሪኮች ከሙዳይ ሰፊ ግቢ ከሚመዘዙ አይረሴ እውነታዎች መሀል እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው:: ዛሬም ቢሆን በዚህ አጸድ አስገራሚ የሚባሉ የኑሮ ሚስጥራት ፣ ጠብቀው የታሰሩ የሕይወት ቋጠሮዎች በውል ይፈታሉ:: ያለፉ፣ ይረሱ የማይመስሉ ፣ ታሪኮችም መፍትሄና መላ ይበጅላቸዋል:: በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር:: ዕንባን በሚያብሰው፣ ሳቅን በሚመልሰው ሰፊ አጸድ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015