የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን <<ኢትዮጵያን እንገንባ>> በሚል መሪ ቃል የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን ያሳተፈ ለሶስት ቀናት የቆየ ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርዒት በቅርቡ ማካሄዱ ይታወቃል:: ኤግዚቢሽኑ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አምራቾችን ከአምራቾች እንዲሁም የዘርፉን አምራቾችን ከተጠቃሚዎች ጋር በማገናኘት ኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ለጀመረችው ብርቱ ተግባር አጋዥ አቅም እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበትም ነው::
ከ24 አገራት የተውጣጡ 130 የሚሆኑ ኩባንያዎች በተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርዒት ላይ በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የግንባታ ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎቱ ያላቸው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ነበሩ:: የሲምፖዚየሙ መካሄድ ለኮንስትራክሽን ስራዎች ስኬታማነት በሚያስፈልጉ የግንባታ ግብዓቶች ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ላለው ክፍተት የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ብሎም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚያስችል ትልቅ መድረክ መሆኑ ታምኖበታል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት በሚታወቀው ዲ.ኤም.ጂ ኢቨንትስና በአገር በቀሉ ኢ.ቲ.ኤል ኢቨንትስ ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን በትብብር የተዘጋጀውና ለሦስት ቀናት የተካሄደው የቢግ 5 ኤግዚቢሽን ፤ ሀገር በቀል እና የውጭ ሀገራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋናዮችን የማገናኘት ዓላማ አንግቦ የተዘጋጀ ነው:: ኤግዚቢሽኑ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ነው የተከፈተው::
በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው መድረክ ላይ ከ6 ሺህ በላይ በህንጻ ንድፍ እና ግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የህንጻ ጥገናና አስተዳደር ባለሙያዎችና እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የዘርፉ አካላት እና ልሂቃንን በአንድ መድረክ ተገናኝተዋል፤ መድረኩ በርካታ የውጭ የግንባታው ዘርፍ ኩባንያዎች የተሳተፉበትና በኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን መልካም እድል መገንዘብ እና በአገሪቱ የግንባታ ስራዎችና ግብአት አቅርቦት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገ ስለመሆኑም ባለፈው ሳምንት ጽሁፋችን አመላክተናል::
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩት አገር በቀል ኩባንያዎችም መድረኩ ልዩ እድል ፈጥሯል:: በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰማሩት አገር በቀል ኩባንያዎች ኃላፊዎች እንደሚሉት ፤ መድረኩ አዳዲስ ገበያ እና አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ያገኙበት፣ ትስስር የፈጠሩበት ከመሆኑም ባሻገር ለሀገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ እድል የከፈተ ነው::
ምርታቸውን ይዘው በዚህ መድረክ ላይ ከተሳተፉት ሀገር በቀል ኩባንያዎች መካከል ማይዊሽ ኢንተርፕራይዝ አንዱ ነው:: ማይዊሽ ኢንተርፕራይዝ በስሩ በርካታ ኩባንያዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ ለመሬት ቁፋሮ፣ ለማዕድን ፍለጋ እና ለፔትሮሊየም ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖች እና ሞተሮች እንዲሁም ለህንጻ ግንባታ እና ለመንገድ ግንባታ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ለእርሻ ስራ የሚውሉ ማሽነሪዎችን ከውጭ ሀገራት በማስገባት ለሀገራችን በሚስማማ መልኩ የማሻሻል ስራዎችን ሰርቶ ለገበያ የሚያቀርብ ድርጅት ነው:: ኤግዚቢሽኑ እድል ከፈጠረላቸው አገር በቀል ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው::
የማይዊሽ ኢንተርፕራይስ የኦፕሬሽን ዘርፍ ስራ አስኪያጅ መሃመድ ሰይድ ሱሌማን እንደሚሉት፤ ማይዊሽ ኢንተርናሽናል የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከውጭ ሀገራት አስገብቶ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አስተካክሎ ለኢትዮጵያ እንደሚስማማ አድርጎ ያቀርባል:: ማሽነሪዎቹን በተለይም አቀበት ቁልቁለት ለበዛበት የኢትዮጵያ መልክአ ምድር በሚያመች መልኩ አስተካክሎ ሲያቀርብ ቆይቷል:: የማስተካከል ስራውን የሚሰሩ ከ60 በላይ ወጣት ሜካኒካል ኢንጂነሮችም አሉት:: ኢንጂነሮቹ ለእያንዳንዷ ነገር ጥናት እና ማስረጃ ላይ የተደገፈ ስራ ይሰራሉ:: ማሽኑ ያለ እድሜው ከተበላሸ ለምን ተበላሸ የሚለውን ለይተው መፍትሄ ይሰጣሉ::
በተለያዩ ወቅቶች በሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኖች ሲካሄዱ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ መሃመድ፤ በቅርቡ የተካሄደው የቢግ 5 ኮንትራክት ኢትዮጵያ ኤግዚቢሽን ግን ከእነዚያ ኤግዚቢሽኖች ይለያል ይላሉ:: ኤግዚቢሽኑ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰማሩ በርካታ አምራቾች ፣ አቅራቢዎች፣ እንዲሁም በዘርፉ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሳተፉበት እንደመሆኑ ለሀገሪቱ በርካታ እድሎችን ይዞ መምጣቱንም ይናገራሉ:: ከእነዚህ እድሎች መካከል ገበያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል::
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ገና ያልተነካ በርካታ እድሎች ያሉት ነው የሚሉት አቶ መሃመድ፣ በዘርፉ ገና ብዙ መሰራት የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉም ይጠቁማሉ:: መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ግድቦች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች ገና በብዛት እንደሚሰሩም ጠቁመው፣ እነዚህን ስራዎች ለመስራት የአገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በስፋት መሳተፍ እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ:: ኤግዚቢሽኑ በዚህ ረገድ ሰፊ እድል መፍጠሩንም ያመላክታሉ::
እንደአቶ መሃመድ ማብራሪያ፤ ኤግዚቢሽኑ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታም ከፍ ያለ ፋይዳ አለው:: ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ነው የነበረችው:: በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ቀርቶ ሀገራት ዜጎችን ከኢትዮጵያ ሲያስወጡ ፣ የጉዞ እገዳዎችን ሲጥሉ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: ያ ሁሉ አስፈሪ ወቅት አልፎ በሀገሪቱ ይህን መሰል ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን መካሄዱ ለሀገር ገጽታም የራሱ የሆነ ትልቅ ፋይዳ አለው::
የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የግንኙነት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ፣ በዘርፉ ምን ምን አዳዲስ ምርቶች አሉ የሚለውን እንዲያውቁ፣ ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት አድርጎ ወደ አገር ውስጥ ማምጣት ይቻላል የሚለውን ለመረዳት ኢግዚቢሽኑ የሚረዳ ነውም ይላሉ::
የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተግዳሮቶች የበዛበት ነው የሚሉት አቶ መሃመድ፤ በተለይም የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ለማስገባት ሀገሪቱ ከሌላት የውጭ ምንዛሪ አውጥታ እንደምትጠቀም ይገልጻሉ:: በመሆኑም አገሪቱ ካላት አነስተኛ ሀብት ቀንሳ የምታስገባቸው ማሽነሪዎች በአግባቡ ስራ ላይ መዋል አለባቸው ሲሉ ያብራራሉ::
ከማሽነሪዎች ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን ስራ የሚሰሩት የውጭ ዜጎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ መሃመድ ፤ ይህ ግን ትክክል አይደለም ይላሉ:: የሀገር ውስጥ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ:: ‹‹አቅም ያላቸው በርካታ ወጣቶች አሉ:: በመሆኑም ወጣቶች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል::›› ሲሉም ይጠቁማሉ:: ኩባንያቸው በቀጣይ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ የመገጣጠም እቅድ እንዳለው አብራርተዋል::
በኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ምርቶችን ይዞ የቀረበው ሌላኛው ሀገር በቀል ድርጅት ጂኦሲንቴቲክስ ኢንዱስትሪያል ወርክስ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር ነው:: ከተመሰረተ 19 ዓመት ገደማ ያስቆጠረው ይህ ድርጅት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ በአገራችን የውሃ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ያለ ኩባንያ ነው::
ኩባንያው በተለምዶ ‹‹ጂኦሲንቴቲክ›› በመባል የሚታወቁት የፕላስቲክ ቱቦዎች፣ ጠንካራ ቱቦዎች፣ የፕላስቲክ ወረቀቶች እና ጋቢዮን መረብ እና የተለያዩ ምርቶችን ያቀርባል:: እነዚህ ምርቶች የውሃ ሀብቶችን ከሁኔታው ጋር ለመጠበቅ፣ ለመሰብሰብ፣ ለማድረስ እና ለመያዝ የሚያገለግሉ ናቸው። የጂኦሲንቴቲክ ምርቶች በአገሪቱ ውስጥ በመስኖ ፕሮጀክቶች፣ የተለያዩ የውሃ አቅርቦቶች፣ እና በቀለበት መንገዶች የፍሳሽ ማስወገጃ ላይ ጥቅም ላይ ውለዋል::
የኩባንያው የገበያ ጥናትና የፕሮሞሽን ኦፊሰር ወይዘሮ ያይኔአበባ በቀለ እንደሚሉት፤ የውሃው ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዘርፎች ያለው ፋይዳ የላቀ እንደመሆኑ ድርጅታቸው ለውሃ ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ማምረት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው:: ምርቶቹንም በተለያየ አካባቢዎች ተደራሽ ያደርጋል:: በድርጅታቸው የሚመረቱ ቧንቧዎች ያለኬሚካል የሚመረቱ መሆናቸውንም ይገልጻሉ::
ኤግዚቢሽኑ ለኩባንያቸው ብዙ እድሎችን እንደፈጠረ የሚናገሩት ወይዘሮ ያይኔአበባ ፤ በኤግዚቢሽኑ በርካታ ኮንትራክተሮች መጥተው የኩባንያውን ምርቶች መጎብኘታቸውን ጠቁመው፣ ተቋራጮቹ በቀጣይ ከኩባንያው ምርቶችን ወስደው ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል:: ከበርካቶች ጋር ትስስር መፍጠርም ችለዋል:: ይህም ለኩባንያው ትልቅ እድል ነውም ብለዋል::
ከኮንትራክተሮች ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን ኩባንያው የያዛቸው ምርቶች በአገር ውስጥ የተመረቱ ስለመሆናቸው እውቀቱ አልነበራቸውም የሚሉት ወይዘሮ ያየኔአበባ፤ በርካቶች በመገረም ስለምርቶቹ ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበርም አስታውሰዋል:: ኤግዚቢሽኑ ምርታቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲያስተዋውቁ እድል መፍጠሩንም ነው የተናገሩት::
ኤግዚቢሽኑ ሕዝቡ ስለ ድርጅቱ እንዲረዳ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በቀጣይ ምርቱን መንግሥት አይቶ ትኩረት እንዲሰጠው አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውንም የሚጠቁሙት የገበያ ጥናትና የፕሮሞሽን ኦፊሰሯ፣ ምርቱን በየአካባቢው ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የያዙትን እቅድ እንዲያሳኩም እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል::
ወይዘሮ ያየኔአበባ በቀደሙት ጊዜያት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ብቻውን የተሳተፈባቸው እንዲህ አይነት ትላልቅ ኤግዚቢሽኖች አልነበሩም ሲሉ ይገልጻሉ:: ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ተዳብሎ ሲካሄድ እንደነበር ጠቅሰው፣ በዘርፉ ባለሙያዎች በኩልም ብዙም ትኩረት ያገኘ እንዳልነበር አመላክተዋል:: የቢግ 5 ኤግዚቢሽን ግን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ብቻ የተሳተፈበት መሆኑ ሰፊና ለዘርፉ የበለጠ አጋዥ መሆኑን ነው የሚናገሩት::
እቃዎችና የማምረቻ ግብዓቶች ከውጭ ሀገራት እንደሚመጡ ይገልጻሉ፤ በአሁኑ ወቅት ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የግብዓት እጥረት መኖሩን ወይዘሮ ያይኔአበባ ጠቅሰው፣ መንግሥት የውሃው ዘርፍ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በመገንዘብ ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥና አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል::
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እንዳሉት፤ ኤግዚቢሽኑ ለአገር ውስጥና ለውጭ አልሚዎች ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል:: ዓላማውም ተቋማት ከተቋማት እንዲሁም ህብረተሰቡ ከተቋማት ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር እንዲሁም የእውቀት ሽግግር ማድረግ ነው:: ስኬት፣ ተግዳሮቶች እና እምርታዎችን ለመጋራት ነው:: በዚህ ረገድ እምርታ የተመዘገበበት ነው::
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዘርፎች ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች አማካሪዎች፣ ተቋራጮች፣ የሙያ ማህበራት የግንባታ እቃ አምራቾችና አቅራቢዎች፣ የፋይናንስ የግብዓት ተቋማት በአጠቃላይ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ዘርፍ መሆኑን በመጠቆም፤ ለግንባታ ፕሮጀክቶች ውጤታማነት የሁሉም አካላት ርብርብ እና ተሳትፎ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል::
የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ በአህጉራዊ፣ በክፍለ አህጉራዊ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የተወዳዳሪነት አቅምና ተግዳሮቶች የተነሳ ስትራቴጂክ እቅዳቸው የያዙዋቸውን ነገሮች በተሻለ ደረጃ ለማከናወን የሚረዳ የተለያዩ ዘዴዎችና አሰራሮችን በመፍጠር ለመተግበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: በእንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች፣ የልምድ ልውውጥ መድረኮችና የትውውቅ መድረኮች ላይ በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል::
ኢትዮጵያ በመንግሥትም በግሉ ዘርፍም ሰፊ የግንባታ ስራዎች የሚካሄዱባት አገር ናት:: ግንባታው በሀገሪቱ የግንባታ ግብዓት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት በአሁኑ ወቅት ሳይቀር በስፋት እየተካሄደ ይታያል:: ሀገሪቱ ገና ብዙ የመልማት ውጥኖች ያሏት ናት:: መሰል ኢግዚቢሽኖች ግንባታ እየተስፋፋባት ባለችው በዚህ አገር መካሄዳቸው የግንባታው ዘርፍ ተዋንያን ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የዘርፎቹን ችግሮች በጋራ ተወያይተው እንዲፈቱ፣ አማራጭ የግንባታ ግብዓቶችን፣ ተቋራጮችን እንዲያማትሩ ሰፊ እድል ይፈጥራል:: በቀጣይም ተመሳሳይ መድረኮች እንደ ሀገርም በክልሎችም እንዲካሄዱ ማድረግ ይገባል:: ይህም የዘርፉን ችግሮች በጋራ መፍታት፣ ቴክኖሎጂና እውቀት መጋራት፣ አማራጭ የግንባታ ቴክኖሎጂና እውቀትን፣ ተቋራጮችን ማማተር ያስችላል:: በተለይ ከዘርፉ ተዋንያኖች ጋር ትስስር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015