እንደሆነ እንጃ ቅዳሜ ሲሆን ደስ ይለኛል፡፡ ከቅዳሜ በፊት ያሉት ስድስቱ ቀናቶች ተጠቃለው የቅዳሜን ያክል ሰላምና ንቃት አይሰጡኝም፡፡ በዚህ ልክ ቅዳሜን መውደዴ ምን እንደሆነ አንድ ክፍለዘመን የሚያክል ጊዜ አስቤ መልሱ ላይ አልደረስኩም፡፡ የሆነው ሆኖ ቅዳሜ ሲመጣ፣ አርብ አመሻሽ ላይ አዲስ ፍጡር ነኝ፡፡ ሴሎቼ ታድሰው፣ ሀሳቤ ጎልሙቶ ሌላውን እኔን በራሴ ውስጥ እተዋወቀዋለሁ፡፡
ቅዳሜ ጠዋት ከመኝታዬ ስነቃ የማያት ጀምበር እንደ አርብና እሮብ ያለችውን አትመስለኝም፡ ከቅዳሜ ውጪ የትም ባልታየ ሰማይ ላይ አንዲት የቆነጀች ጀምበር በህብረቀለም ታጅባ ምስራቅ አድማስ ላይ ስትፈነጥቅ ለእኔ ብቻ ይታየኛል። ማታ ሆኖ ጀምበር ወደማደሪያዋ ስትሰገሰግ አዲስና ታይቶ በማይታወቅ የአድማስ መጥለቂያ ላይ ይቺኑ መልከልውጥ ጀምበር በእርጅና ሳይሆን በወጣትነት፣ በድብዛዜ ሳይሆን በሙቀት አለሙን ደህና ሰንብት ብላ ከቅዳሜ ውጪ ዳግም ላትታይ ወደቤቷ ስትሰምጥ አያለው፡፡
ጠዋት ወጥቶ ማታ የሚገባው የቀለሟ ህብር፣ ከእኔ ውጪ ለማንም ያልተገለጠለት ረቂቅ የውበትና የቁንጅና ሚስጢሯ ቅዳሜ ደርሶ ዳግም በሰማዩ እርቃን ላይ እስካያት ድረስ እናፍቃለሁ፡፡ ያን መናፈቅ ከምን ጋር እንደማጣምረው መሳይ አጥቼለት ብዙ ዘመን ዘልቄያለው፡፡ የእናቱን ጡት እንደሚሻ ህጻን፣ የሚወዱትን ሰው ቆሞ የመጠበቅ ያክል፣ በብዙ ክረምት ውስጥ ለአንድ ጊዜ ብልጭ ብላ እንደምትጠፋ ላመል ብራቅ፣ በሚወዱት ህብስት እንደሚላወስ አንጀት እንዲህ ይመስለኛል፡፡
ከቅዳሜ ውጪ ቀን ማጣቴ ያስተክዘኛል፡፡ ሁሉንም ቀናት የቅዳሜን ያክል አፍቅሬና ጓጉቼ መኖር እሻለው ግን ለዛ የሚሆን አቅም አጣሁ፡፡ አርብ ደርሶ ቅዳሜ ሊሆን ሰማዩ ሲያቅላላ ያኔ ሰርጌ ነው፡፡ ቅዳሜ መሽቶ እሁድ ሲወለድ ደስታየ አብሮ ይበናል፡፡ አንድ ራሴን አፍርሼ ልሰራ ተሰናዳሁ፡፡ እስከመች ቅዳሜን ብቻ አፍቅሬ፣ እስከመች ከሰባት ቀናት የአንድ ቀን ባሪያ ሆኜ እዘልቀዋለው ስል በራሴ ላይ አመጽኩ፡፡ አመጼ ቅዳሜን ብቻ አይደለም፣ ሰኞና ማክሰኞን ብቻ አይደለም ዘላለሜን የቀየረ አዲስ የለውጥ አብዮት ሆኖ ነበር ያገኘሁት፡፡ አነሳሴ በራሴ ላይ ላልመለስ፣ በማንነቴ ላይ ልጨክን ነበር፡፡ ሁለት ምርጫዎችን በልቤ ብራና ላይ ሰንቄ ወደማውቀውና ወደማላውቀው ፊትና ኋላ ዘመን ተንገዳገድኩ፡፡ ወይ ቅዳሜን ልጠላ አሊያም ደግሞ ሌሎቹን ቀናት እንደቅዳሜ ላፈቅር ራሴ ላይ ኒውክሌር ደቀንኩ። የሆነው ሌላ ነበር..እኔም እናተም መጪውም ትውልድ ከሚገምተው ሌላ፡፡
አንድ ማለዳ ገጠር ወደሚገኘው ቅድመ አያቴ ጋ ሄድኩ። በእናቴ ይሁን በአባቴ በማን እንደሚዛመደኝ አላውቅም፡፡ ብቻ ከወላጆቼ በአንዱ ስጋዬ እንደሆነ ደርሼበታለሁ፡፡ እናትና አባቴን ጨምሮ አያቶቼ በህይወት የሉም፡፡ በእርጅና ሳቢያ ይቺን አለም ሲሰናበቱ ይሄ ቅድመ አያቴ ግን አሁንም በመኖር ላይ ነው፡፡ ከአፈር ስለመሰራቱ ብዙ ጊዜ ተጠራጥሬ በዝምታ ራሴን ለጉሜያለሁ፡፡ አይደለም እኔ እሱ ራሱ እድሜውን በውል አያውቀውም፡፡ እድሜውን ሲጠይቁት ምልክት የሚያደርገው የመጀመሪያውን የጣሊያን ወረራ ነው፡፡
ጣሊያን ሀገራችንን ሊወር ሲመጣ ታሪክ እንደሌለው ግን ደግሞ ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ ከአድዋ ድል ላመል ዘግየት ብሎ በልጅነቱ እሱን ስትወልድ ከሞተችውና በመልክ ከማያውቃት እናቱ ይቺን አለም እንደተቀላቀለ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር አድምጫለው፡፡ እናም ያን የጊዜ ስሌት መሰረት አድርጌ እድሜውን ሳሰላው ከአንድ ክፍለዘመን በላይ፣ የስድስት ትውልድን እድሜ ቅርጥፍ አድርጎ እንደበላ ደርሼበታለው፡፡
በህይወትህ ከሚቆጭህ ነገር አንዱ ምንድነው ብዬ ለጠየኩት ጥያቄ ሲመልስልኝ ‹በአድዋ ጦርነት ጊዜ ተወልጄና ጎልምሼ ከምኒልክና ከአባ ሳፎ ጋር ለሀገሬ ክብር አለመዋደቄና ስለሀገሬ አለመሞቴን ሳስብ እቆጫለው እንዳለኝ አስታውሳለው፡፡ የተደሰትክበትስ ስለው ‹ለዳግም ወረራ ሊወጋን የመጣውን ጣሊያንን በእስተርጅና በእልህና በቆራጥነት መሰለፌን ሳስብ ለሀገሬ የዋልኩት ትልቁ ውለታ ያ ነው እላለው እንዳለኝ ይሄም የማይረሳኝ ንግግሩ ነበር፡፡
ከቅድመ አያቴ ጋር ተነጋግሮ መግባባት በህይወቴ ሁሌም ሞክሬው ያቃተኝ ነገር ነው፡፡
በተገናኘን ቁጥር..በተገናኘን ቁጥር አልኩ? እዚህ ጋ ሀሳብ ገድፌያለው..ከቅድመ አያቴ ጋር በአምስት አመት አንድ ጊዜ ካልሆነ የተገናኘንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ችግሩ ከእኔ እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነው፡፡ ቅድመ አያቴ አስቸጋሪ ሰው ቢሆን ኖሮ ተፈጥሮ መቶ ምናምን አመትን እንዲኖር አትፈቅድለትም ነበር ስል አንድ ቀን ተክዤ በተቀመጥኩበት የእሁድ ማለዳ ላይ ነው የተገለጠልኝ፡፡
ከዚህ መገለጥ በኋላ ነው እሱ ካለኝ ከየትኛውም ነገር ጋር ለመግባባትና ራሴን ለማሰናዳት የተዘጋጀሁት፡፡ ከአምስት አመት የዘለቀ ጊዜ በኋላ እሱ ብቻ ወዳለበት ገጠራማ መንደር ሄድኩ፡፡ እውነት እላለው የሆነ ሰይጣን ሰፍሮብኝ ያን አካባቢ፣ ያን ተፈጥሮ፣ ያን ገጠራማ ስፍራ፣ ያን አረንጓዴ ቦታ፣ ያን ለምለምና ቅዱስ፣ ያን በሁሉነገሩ የተስተካከለ አለም ጠላሁት እንጂ እግዜር ጌትነቱ መኖሪያቸውን በዛ ቦታ ስለማደርጋቸው ከአያቴ ቀጥሎ ቃሌን የምሰጠው እኔ እሆን ነበር፡፡
ከአያቴ ጋር ተገናኘን፡፡ ያው ነው ከዛሬ አምስት እና አስራ አምስት አመት በፊት እንደማቀውቀው፡፡ እኔ ወደ እሱ እሱ ወደእኔ የምናደርገው ጉዞ ባየሁት ቁጥር የሚያስገርመኝ ተፈጥሮአችን ነው፡፡ የአያቴ ሰውነት ከእርጅና ወደወጣትነት እንጂ ከእርጅና ወደሞት የሚንደረደር አይመስልም፡፡
እኔ የልጅ፣ ልጅ፣ ልጁ መኖር ታክቶኝ፣ እድሜ ተጭኖኝ ምርኩዝ በምሻበት እድሜዬ እሱ እንደጎረምሳ ሲያደርገው ሳይ እግዜር ዲሞክራት እንዳልሆነ እንዳምን ሆንኩ፡፡ ከእሱ ጋ መግባባት እሁድና ሰኞን ከምጠላው በላይ አዳጋች ሆኖ ያገያገኘሁት ቢሆንም ከእሱ ሌላ ህይወትንም ሆነ እውነትን እምነትንም ሆነ ብልሀትን እንደ መስተዋት አንጸባርቆ የሚሰጠኝ ሌላ ሰው እንደሌለ በማመን በሚገባው ቋንቋ ዝግ እያልኩና ለአንድ ቃል አስርና አስራ አምስት ጊዜ ቃላት እየደጋገምኩ ልግባባው ሞከርኩ፡፡ እንዲህ ስለው..እንዲህ ነበር ያለኝ፡፡
‹አበባ? አልኩት፡፡
ከሚቀምመው የእጽዋት መድሃኒት ላይ አፍታ ወስዶ አስተዋለኝ፡፡
‹እንዳንተ መሆን እፈልጋለሁ› ብዬ ዝም አልኩት፡፡
‹እንደእኔ ምን? አለኝ፡፡
በቃ እንዳንተ..
‹እኮ እንደ እኔ ምን?
‹ሰው እና ሌላም›፡፡ አልኩት፡፡
ፊቱ ላይ መልካቸውን በሚያሳይ በተለያየ ቀለም የተበጠበጡትን የእጽዋት መድሀኒቶች በአይኑ እየመረመረ፡፡ እጁን ወደአንዱ ሰደደ፡፡ ከእኔ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሊያነሳ ነው ብዬ ስጠብቅ ስራውን ጀመረ፡፡
‹አባባ? አልኩት በድጋሚ ፊት የነሳኝ ስለመሰለኝ፡፡ በቅድሙ አተያይ ቀና ብሎ አየኝ፡፡
‹እዚህ ምድር ላይ ልሆነው የምፈልገው አንድ ሰው አንተ ነህ፡፡ አንተን እንድታደርገኝ እሻለው፡፡ ራሴን ሆኜ የምኖርበት ዘመን እዚህ ጋ እንዲያበቃ እሻለው፡፡ ሞገስህን ስጠኝ፣ እምነትህን አውርሰኝ፡፡ ከቅዳሜ ውጪ የማፈቅራቸው አርብና እሮብ ሃሙስና ማክሰኞ እንዲኖሩ እፈልጋለው፡፡ እዚህ የመጣሁት አንተን ሆኜ፣ አንተን መስዬ ቀሪ ዘመኔን ለመኖር ነው› አልኩት፡፡ ከዚህ ንግግሬ በኋላ በእኔና በምኞቴ መካከል የሆነ የወርቅ ድልድይ ሲሰመር ታወቀኝ፡፡
አያቴ ተናገረ..
‹እኔን አልሰጥህም፡፡ እኔ እኔን ብቻ ነኝ፡፡ ምርጡን አንተን ግን ልሰጥህ እችላለው› ሲል ከወንበሩ ተነሳ፡፡ ና ተከተለኝ በሚመስል ሁናቴ በአይኔ ጥቁምታ ሰጥቶኝ ወደውጪ ይዞኝ ወጣ፡፡ ትንሽ እንደተራመድን እጅግ ከሚያስፈራ፣ ቅርንጫፉ ከማይታይ፣ በጨለማ ከተሞላ ጥቅጥቅ ካለ ደን ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ በፍርሀት እጁን ልይዘው እጄን ስሰድ አትያዘኝ ሲል ተቆጣኝ፡፡ ከዛ ቁጣ በኋላ ከቅድመ አያቴ ጋር አልተገናኘንም፡፡
እንዴት እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ ተለያየን፡፡ አስፈሪው ጫካ ውስጥ ራሴን ብቻዬን ሳገኘው አያቴ አኑረኝ ስለው ማንም ያልሞተውን ሞት ግደለኝ ያልኩት መስሎት ወደአንድ ማንም ወዳልሞተው ሞት ወስዶ የጣለኝ ነበር የመሰለኝ፡፡ በዛ ሁናቴ ውስጥ ሁለት ነገሮችን አስታውሳለው..ከዛ ጨለማና ጫካ ወጥቼ ዳግም ሰው መሆንን፡፡ ከተለያየን ከአንድ ሳምንት በኋላ አሁንም እንዴት እንደሆነ በማላውቀው ሁናቴ ቅድመ አያቴ በብዙ ብርሀን ወዳለሁበት መጥቶ ድምጹን ሲያሰማኝ አስታውሳለው፡፡
አንድ ቃል ብቻ መናገሩን አስታውሳለው..‹አሁን ምርጡን አንተን ሆነሃል፡፡ ወደየትም ብትሄድ አለም አገልጋይህ ናት› የሚል ቃል፡፡
እንዳለው ነበር..ሰው እና ሌላም ሆኜ፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2015