ዶክተር ሩት ምትኩ ትባላለች፡፡ ጠቅላለ ሀኪም እና የህብረታሰብ ጤና መምህርት ነች፡፡ ዶክተር ሩት ምትኩ የቃልኪዳን በጎ አድራጎት እና ጨቅላ ህፃናት እንክብከቤ ማዕከል መስራች እና ዳይሬክተር ነት፡፡ ወደዚህ ሥራ እንዴት እንደገበባች የምትናገረው ዶክተር ሩት፤ የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪ በነበረችበት ወቅት እናት እና አባቷ በህይወት የሌሉት ቃልኪዳን የሚባል አንድ ህፃን ልጅ ለአንድ ወር ያህል የህክምና ክትትል በምታደርግበት ወቅት እንደነበረ ትናገራለች። ይህ ታካሚ ከህመሙ አገግሞ ሲወጣ ሄዶ እንደጎበኛች የምትናገረው ዶክተር ሩት፤ በዚህ አጋጠሚ ነበር በዛ ለሚኖሩ ለሌሎች መሳል ህፃናት ተቋሙን በማስፈቀድ ነፃ የህክምና እርዳታ በመስጠት ስራውን እንደጀመረች የምትናገረው ፡፡
ዶክተር ሩት እንደምትለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የህክምና ችግር አለ፡፡ ይህንን ዘርፈ ብዙ ችግር ደግሞ በመንግስትና በተወሰኑ ጤና ተቋማት ጥረት ብቻ መቅረፍ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ይህን ችግር ለመቅረፍ በምን መልኩ መስራት እንችላለን በሚል እንደ ማህበር ጎደኞቿ ጭምር በማስተባበር ቃልኪዳን በሚል የህፃናት እንክብከቤ ተቋም መመስረት እንደቻለች ትገልፃለች፡፡
ስለ ማህበሩ አጀማመር ዶክተር ሩት ስትናገር፤ አሁን ያለው የህክምና ሂደት ለታካሚም ሆነ ለአካሚ የማይመች ስለሆነ ያንን ችግር መፍታት የሚቻለው ህክምና ሊደርስ የማይችልባቸውን ቦታዎች በማድረስ መሆኑን እምነት ስላደረባት ያንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ስትጥር ቆይታለች፡፡
የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪ በነበረችበት ወቅት ይህን ስራ ስትጀምር ምንም ገንዘብ አልነበራትም፡፡ሆኖም ይህ ሁኔታ ከአላማዋ ወደ ኋላ ሊያስቀራት አልቻለም። ገንዘብ ባይኖራትም ዕውቀት አላት፡፡ ስለዚህም ባላት ዕውቀት ማህበረሰቡን ማገዝ እንደምትችል አመነች፡፡ ጓደኞቿንም በማስተባበር ወደ ስራው ገባች፡፡
ነገር ግን ስራው ብዙ ተግዳሮት እንደነበረው ትናገራለች፤ የጊዜ፣የገንዘብ እና የአመለካከት ችግር ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ዘጠኝ ሀኪም እና አንድ ነርስ በአንድነት በመሆን ነበር ሥራውን የጀመርነው›› የምትለው ዶክተር ሩት፤በ50 እና በ100 ሰው አገልግሎት ተጀምሮ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ እስከ አንድ ሺህ ሰው የህክምና አገልግሎት መስጠት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ትገልጻለች፡፡ ይህን አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ ብዙ ቁጥር ያለው የጤና ባለሙያ ስለሚያስፈልግ ለማህበሩ በነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማፈላለግ የግድ ይል እንደነበረ ትናገራለች፡፡
ኢትዮጵያውያን ለበጎ ስራ ቅን ናቸውና በተደረገው ጥረትም ለማህበሩ በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር ከ450 በላይ ማድረስ መቻሉን ዶክተር ሩት ተናግራለች፡፡ ‹‹የጤና ባለሙያዎች ፕሮግራማቸውን በማስተካከል አመቺ በሆነ ቀን እየመጡ የነፃ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡አሁን ያለው ሁኔታ አበረታች ቢሆንም ካለው ችግር አንጻር ብዙ ሰዎችን ለመድረስ እና የተለያዩ ቦታዎች በመሄድ የህክምና ድጋፍ ለማድረግ ከዚህ በላይ የበጎ ፍቃድ ስራው እንዲሰፋ እንፈልጋለን ስትል›› ዶክተር ሩት ተናግረለች፡፡
የአንድ ጤና ባለሙያ ዋነኛ አላማ ህክምናን ለታካሚ ማድረስ ነው፡፡ ነገር ግን ከህክምና በፊት የመድሀኒት አቅርቦት፣የላብራቶሪ አገልግሎት እና መሰል አገልግሎቶችና ግብዓቶችን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ውድ የሆኑ የህክምና አገልገሎት መስጫ ማሽኖች ለስራዋ ፈታኝ እንደሆኑባት ዶክተር ሩት ትናገራለች፡፡ ሆኖም አንዳንድ በጎ አድራጊ ተቋማት በሚያደርጉላቸው ድጋፍ ስራቸውን ሳያቋርጡ እንዲሰሩ አስችሏቸዋል፡፡
‹‹ከዚህ በተረፈ ቤት አልባ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች እና በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ሰዎች ጋር ስንሄድ የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች፣የምግብ አገልግሎት መስጠት፣የአልበሳት ድጋፍ ማድረግ፣ የሻወር በመስጠት በጎዳና ላሉ ልጆች አገልግሎት እንሰጣለን›› ትላለች፡፡
ህክምና ሲባል መድሀኒት እና መርፌ ሰጥቶ ማከም ብቻ እንደልሆነ የምትናገረው ዶክተር ሩት፤ የግል ንፅህና ፣ምግብ አለመገኘት፤ ኩበት እና ሌሎች ቁሳቁሶችም ጭምር ለበሽታ እንደሚያጋልጡ ታስረዳለች፡፡በተለይም በዚህ ረገድ ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ትናገራለች።
በፋይናንስ የሚደግፋቸው አንድም ተቋም እንደሌለ የምትናገረው ዶክተር ሩት፤ይህንን ችግር ለመወጣትም ከግለሰቦች መዋጮ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ መድረኮችን እንደምታዘጋጅ ታስረዳለች፡፡ ‹‹ ሁለት መቶ ብር በወር፣ አምስት መቶ ብር በወር፣ አንድ ሺህ ብር በወር የሚሠጡን ሰዎች አሉ፡፡ አባል የሆኑ እና በየወሩ የገንዘብ ድጋት የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡ ከእነርሱ ላይ በማሰባሰብ መድሃኒት እንገዛለን፡፡ በሌላ በኩል አንድ ጊዜም ሆነ ሁለት ጊዜ ብቻ የገንዘብ ዕርዳታ የሚሰጡ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ልባቸው በፈቀደው መጠን ይህንን መድሃኒት እኔ እገዛለሁ ብለው የሚሰጡበት ሁኔታም አሉ፡፡›› ትላለች፡፡
ዶክተር ሩት እንደምትለው የትምህርት መሳሪያዎችን፣ ልብሶችን ወይም ጫማዎችን የሚለግሱ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ፋርማሲዎች ደግሞ ሲነገራቸው መድሃኒቶችን በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡ አሉ፡፡ በተጨማሪም አንዳንዴም መድሃኒቱን በነፃ የሚሰጡ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንጂ በቋሚነት እርዳታ የሚያደርግ የመንግስትም ሆነ የግል አካል የለም፡፡
ነገር ግን በተደጋጋሚ ከመንግስት ተቋም ጋር በጋራ ለመስራት ብዙ መሞከሩንና በተለይም በየክፍለ ከተማዎች የወጣት እና በጎ አድራጎት ቢሮዎች ቦሌ፣ የካ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች አካባቢ በተደጋጋሚ በመስራታቸው ነገሮችን በማቀናጀት በኩል እያገዟቸው መሆናቸውንም ዶክተር ሩት ትናገራለች፡፡
በኢትዮጵያ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውና ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎች ቁጥር በርካታ ነው። ስለዚህም የህክምና እርዳታውን የምታካሂዱት በምን መስፈርት ነው የሚለውን ጥያቄ እንድትመልስልን ጋብዘናት ነበር፡፡ ዶክተር ሩት እንደምትለው ብዙ ጊዜ ከሰዎች በሚደርሳቸው ጥቆማ በመመራት ለህክምና ፈላጊ ዜጎች ድጋፉን እንደሚያደርጉ ታስረዳለች፡፡
እንደሙዳይ ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚንከባከቧቸው ልጆች እንዲታከሙላቸው ጥሪ የሚቀርቡበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስ፤ ከክፍለ ከተማዎች እና ከክረምት የበጎ አድራጎት አገልግሎት ሰጪዎችም የነፃ የህክምና ዕርዳታ ጥያቄ የሚቀርብ መሆኑንም ትናገራለች፡፡ ከዛ ውጪ ራሳቸው የህክምና ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለው የሚገምቷቸውን ሰዎች ራሳቸው ጠይቀው የሚያክሙ መሆኑን ታስረዳለች፡፡
ዕርዳታውን ሲያደርጉ እና በሞያቸው ሕዝብን ሲያገለግሉ ከመንግስትም ሆነ ከማንኛውም ተቋም የተለየ እንክብካቤ የማይፈልጉ መሆኑን አመልክተው፤ ነገር ግን ሥራቸው በፋይናንስ ቢደገፍ ለበርካታ ዜጎች መድረስ እንደሚቻል ታስረዳለች፡፡ እንደወጣት ዶክተር ሩት ገለፃ፤… ብዙዎች ጥሩ በሚባል ደረጃ ትብብር ቢያሳዩም አንዳንድ የመንግስት ተቋማት ጋር እነርሱ ለሚሰጡት ነፃ አገልግሎት ከመተባበር ይልቅ ቢሮክራሲ የሚያበዙበት ሁኔታ መኖሩንም ትናገራለች፡ ፡ ይህ መስተካከል አለበት የምትለዋ ወጣት ዶክተር በተለይ ከጤና ጋር ተያይዞ የሚሠሩ የመንግስት ተቋማት እነርሱን እንዲደግፏቸው በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም ምላሹ አርኪ እንዳልሆነ ትገልጻለች፡፡በተለይ ከመድሃኒት አቅርቦት አኳያ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኩል ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ትላለች፡፡
በነፃ አገልግሎቱን ሲሰጡ አንዳንድ ጊዜ ሀኪሞችንና በሽተኞችን ለማንቀሳቀስ መኪና እንደሚቸገሩ ትናገራለች። ሐኪሞችም ሰዎችን በነፃ እያከሙ ሲቆዩ የሚራቡ በመሆናቸው ምግብ ሲያቀርቡ ከኪሳቸው እንደሚወጡ አመልክታ፤ ቢያንስ የትራንስፖርትም ሆነ የምግብ ወጪን የማገዝ ሁኔታ ቢኖር መልካም ነው ትላለች፡፡
ዶክተር ሩት እንደምትናገረው በዚህ የበጎ ፍቃድ ስራ ላይ ለአራት አመታት ቆይታለች፡፡ በእነዚህ ወቅቶች መልካም የሚባሉ ተግባራትን በማከናወን ዜጎችን ለመርዳት ችለዋል። ከፍለው መታከም የማይችሉ ወገኖች በነዶክተር ሩት ጥረት ተፈውሰዋል፡፡ በችግሮች ምክንያት ህፃናት እና ሴቶች ሳይታከሙ እንዳይቀሩ ገፍተው እስከ ማከም እንደሚደርሱም ነው ዶክተር ሩት የሚትናገረው፡፡
ወጣቶች በችግሮች መፈታት እንደሌለባቸው ዶክተር ሩት ትናገራለች፡፡ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ያንን ተስፋ ማጣት ከማሰብ ይልቅ እየሠሩ ተስፋ ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ትመክራለች፡፡
ለምሳሌ አንድ አብሯቸው ተምሮ የተመረቀ ወጣት ቤቱ ሆኖ ሥራ እየፈለገ ላፕቶፕ ላይ ከመዋል ይልቅ በነጻ ጤና ጣቢያ እየሔደ ያገለግል ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ተምረህ ዶክተር ሆነህ እንዴት በነፃ ታገለግላለህ የሚሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡለት የሚሰጠው ምላሽ ‹‹በመስራት የያዝኩትን ዕውቀት አሳድጋለሁ እንጂ አላሳንሰውም፤ ስለዚህ ሥራ አግኝቼ ክፍያ እስከማገኝ ድረስ ባገለግል ምንም አላጣምና ያለኝን ዕውቀት ሥራ ላይ አውለዋለሁ፡፡›› ብሎ ብዙ ሰው በነፃ ያክም እንደነበር ያስተዋለችውን ትናገራለች፡፡ ሥራ ለመያዝ የደረሱ ወጣቶች ትኩረታቸው ገንዘብ ማግኘት ብቻ መሆን የለበትም በሙያቸው ሕዝብን ማገልገል አለባቸው ትላለች፡፡
እንደወጣት ዶክተር ሩት ገለፃ፤ ተምረው የተመረቁ ሰዎች ሥራ ባያገኙም ሥራ እስከሚያገኙ ተስፋ ቆርጠው ከመቀመጥ ይልቅ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የበጎ አድራጎት ሥራን ቢያከናውኑ ከመጎዳት ይልቅ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል፡፡ እንደውም ዕውቀቱ እስካለ ድረስ በየትኛውም አጋጣሚ እውቀቱን አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋል የተሻለ ልምድ ለማግኘት እና ሥራ ሊሰጣቸው ለሚችል ሃይልም ስራ እንዲሰጣቸው ዕድል መፍጠር መሆኑን ትናገራለች፡፡
‹‹እዚህ አገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለመደ አይደለም ››የምትለው ዶክተር ሩት፤ የበጎ ፍቃድ ተግባር ያልተለመደ ስለሆነ ብዙዎችን ግር ቢያሰኝም እንደውም ከክፍያ ይልቅ እውቀትን በነፃ መስጠት በጣም አስደሳች መሆኑንም ታብራራለች፡፡ የነፃ የሙያ አገልግሎት ለነፍስም ለስጋም የሚሆን አስደሳች መሆኑን በማስታወስ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠትን መልመድ አለባቸው ትላለች፡፡
‹‹ሁሉም ሰው ራስ ወዳድ ሆኖ ለራሱ በማድላት ስለራሱ ብቻ የሚታገል ሆኗል፤ ጊዜው የሚያስገድድ ቢሆንም ለሰውም እልፍ ያለ ነገር የመስራት ልማድ መኖር አለበት›› ትላለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ የህፃናት ማሳደጊያ እንዳሉና ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎችም ከተሞች ብዙ የሕፃናት ማሳደጊያዎች መኖራቸውን በማስታወስ፤ የህክምና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ህፃናትን የማጠብ ፤የማፅዳት ቀላል አገልግሎቶች እንኳን በማንኛውም ወጣቶች መሰጠት የሚቻሉ በመሆናቸው ሁሉም ጉልበቱንም ዕውቀትንም በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል ብላለች፡፡ ማንኛውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ ካለ በእነርሱ በኩል የሚቻል መሆኑንም ነው የገለፀችው፡፡ በመጨረሻም በጎ ፍቃደኝነትን ሁሉም ሊያበረታታው እና በሁሉም ሊፈፀም የሚገባ መልካም ተግባር በመሆኑ በየመስኩ ሁሉም እንዲሳተፍ ወጣት ዶክተር ሩት ጥሪ አቅርባለች፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2015